
አዲስ አበባ፡- የብርጋዴር ጄኔራል ታደሰ ብሩ 100ኛ ዓመት የልደት በዓል እና “ከደናኔ እስከ ፊንፊኔ” የመጽሐፍ ምረቃ ሥነ ሥርዓት ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ ተካሄዷል።
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የጄኔራል ታደሰ ብሩ ፋውንዴሽን መሥራችና ልጃቸው ወይዘሮ ፀሐይ ታደሰ ብሩ፣ የኦሮሞ ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና፣ ማኅበራዊ የትግል ችግሮች መፍትሔ አግኝተው የማየት ሕልምና የጋለ ስሜት ስለነበራቸው እስከሕይወት መስዋዕትነት ድረስ መሥራታቸውን ተናግረዋል።
ወይዘሮ ፀሐይ ታደሰ ብሩ አባታቸው እስከ 17 ዓመታቸው እስከ 12ኛ ክፍል ካስተማሯቸው በኋላም “ካሁን በኋላ አንቺን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ማስተማር አለብኝ” ብለዋቸው የፊደል ሠራዊት የማቋቋም ሥራ መጀመራቸውንና “የተማረ ዜጋ መብቱን ይጠይቃል” የሚል ሀሳብ እንደነበራቸው ተናግረዋል።
ለትምህርት ብሩህ አዕምሮ ያላቸው ቢሆንም ከጣሊያን ወረራ ጋር ተያይዞ በለጋ እድሜያቸው እናትና አባታቸውን ማጣታቸው ፈተና ሆኖባቸው እንደነበር ጠቅሰዋል። በኢትዮ-ጣሊያን ጦርነት አባታቸው መገደላቸው፣ እናታቸውም በኃዘን ብዛት በወራት ልዩነት ሲሞቱባቸው በኃዘኑ ወደ ኋላ ሳይመለሱ በወኔ ዓላማቸውን ማስቀጠል ችለዋል ብለዋል።
ብርጋዴር ጄኔራል ታደሰ ብሩ ከራሱ አልፎ አገርን ጀግና አድርጓል ያሉት ወይዘሮ ፀሐይ የ100ኛ ዓመት የልደት በዓል ሲከበር የዛሬው ትውልድ ከእሱ የሕይወት አርአያነት እንዲማር ለማስቻል፤ እንዲሁም የአባታቸውን ሕልም ለማስቀጠል የተቋቋመው የብርጋዴር ጄኔራል ታደሰ ብሩ ፋውንዴሽን አስፈላጊውን ድጋፍ አግኝቶ እንዲንቀሳቀስ ለማስቻል መሆኑን አስታውቀዋል።
ብርጋዴር ጄኔራሉ ያጣውን የትምህርት ዕድል ልጆቹ እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን የኦሮሞ ልጆች እንዲማሩ ብዙ ጥረት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል። የፊደል ሠራዊት ኃላፊ በመሆንም “መማር ያስከብራል ሀገርን ያኮራል” በማለት በሰፊው ስለትምህርት ትኩረት እንዲሰጥ የለፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ ጄኔራል ታደሰ ብሩ የኦሮሞ ሕዝብ ትግል በትምህርት እና በትውልዱ እንዲጠበቅ በማሰብ ማኅበረሰቡ እንዲማር ትኩረት አድርጓል። ትምህርት የትውልድ ጉዳይ በመሆኑ በአንድ ዘመን እንደማያበቃ የዛሬም፣ የወደፊቱም ጉዳይ መሆኑ ለጄኔራል ታደሰ ግልጽ ነበር ብለዋል። ከዳለኔ እስከ ፊንፊኔ መጽሐፍ ደራሲ ወይዘሪት ዙፋን ኡርጋንም አመስግነዋል።
በአፋን ኦሮሞ እና በአማርኛ ቋንቋ የተዘጋጀውን መጽሐፉን 10 ሺህ ኮፒ ለትምህርት ቤቶች ለማከፋፈል እንዲሁም የብርጋዴር ጄኔራል ታደሰ ብሩ ፋውንዴሽንን ለመደገፍም ቃል ገብተዋል።
በመድረኩ የተገኙት የቀድሞ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት አቶ አባዱላ ገመዳ በበኩላቸው፣ “ብ/ጄኔራል ታደሰ ብሩ ከተወለደ መቶኛ ዓመቱ ቢሆንም ዛሬ ዳግም የተወለዱበት ቀን ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
መጽሐፉ ለሚቀጥሉት ብዙ መቶ ዓመታት የታሪክ ማጠቀሻ ሆኖ እንደሚያገለግልም ጠቅሰው መጽሐፉን በጽናት በመጻፍ ለደረሰችው ወይዘሪት ዙፋን ኡርጋ ምስጋና እና አድናቆት አቅርበዋል። ወጣቷ በብዙ ልፋት መጽሐፉን ለዚህ አብቅታለች ያሉት አቶ አባዱላ ገመዳ እንደ ዙፋን ያሉት ወጣቶች ሀገሪቷ የምትፈልጋቸው መሆኑን አመላክተዋል።
ለትውልድ የሚተላለፉ መሰል ተግባራትን በመሥራት በማኅበረሰቡ ሰፊ ድርሻ ያላቸው ሰዎችን ታሪክ አውጥቶ ማሳየት ያስፈልጋልም ብለዋል።
በሀይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15 ቀን 2015 ዓም