ከሁለት ዓመት በፊት የዞኑ አስተዳደር፣ ምክር ቤት፣ ህዝብና ምሁራን በአካባቢው ያለውን እምቅ ሀብት አሟጦ መጠቀምና በራስ አቅም የመቆም እልህ አደረባቸው።ከክልሉ መንግስት በሚመደብ በጀት ብቻ የመንቀሳቀስ ጉዳይ፣ ተጨማሪ የኢኮኖሚ ምንጭ አለማማተር፣ የስራ አጥ ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መምጣት በእጅጉ አሳሰባቸው።
እነዚህ የደቡብ ብሄሮች ብሄረተሰቦችና ህዝቦች ክልል የከንባታና ጠንባሮ ዞን አስተዳደር፣ ምክር ቤት፣ ህዝብና ምሁራን ኢኮኖሚው ከለመደው መንገድ ውጪ ገቢ በሌላ መንገድም መምጣት አለበት የሚል ሀሳብ ማመንጨት ጀመሩ።ለእዚህም በዞኑ የሚገኘውን እንድ ትልቅ ታሪካዊ ተራራ ማልማት አሰቡ፤ ይህን 18ሺ ሄክታር የሚሸፍን ተራራ አልምተን የተሟላ የቱሪስት መዳረሻ ብናደርግ በውስጡ ሊፈጠር የሚችለው የቢዝነስ ሰንሰለት ትልቅ ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አደረባቸው። ለልማቱ የታጨው ተራራም ከከንባታና ጠንባሮ ዞን መቀመጫ ዱራሜ ከተማ ስምንት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው አምበርቾ ተራራ ሆነ፡፡
ይህ ልማት የተወጠነበት ወቅት 2012 ዓ.ም የኮረና ወረርሽኝ በዓለም አቀፍና በአገር ደረጃ ትልቅ ስጋት የሆነበት ነበር፤ ኮረና ስጋት ቢሆንም ዞኑ ለያዘው እቅድ ግን መልካም አጋጣሚ ሆኖ መገኘቱን በከንባታ ጠንባሮ ዞን አስተዳደር፣ ባህልና ቱሪዝም ትብብር የሚለማው የአምበርቾ ተራራ ኤኮቱሪዝም ስፍራና አረንጓዴ ልማት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ዘመዴ ሄራሞ ይገልጻሉ።
አቶ ዘመዴ እንደተናገሩት፤ ዞኑ እጅግ በርካታ ምሁራን የወጡበት ነው፤ ኮሮናውን ተከትሎ በርካታ የዞኑ ምሁራን ወደ ዞኑ ይመጡ ነበር፤ 42 ዶክተሮችና ፕሮፌሰሮች ወዶ በዞኑ ተገኝተው የዞኑን እምቅ አቅም ለማጥናት በአካባቢው ለሶስት ወራት ቆይተዋል፤ በወቅቱም ወደ 200 ገጽ ያለው አንድ እናት ሰነድ ተዘጋጀ።
ሀሳቡ ሲጠነሰስ በመጀመሪያውም አምበርቾን ወደ ቀደመው ማንነቱ መመለስ አለብን የሚል አቋም ተይዞ፤ ተራራው የምንጮች፣ የወንዞች፣ የፏፏቴዎች ተራራ መሆን አለበት፤ ስለዚህ ባህር ዛፎችንና ሌሎች ጎጂ ነገሮችን እያስወገድን ውሃ የሚያፈልቁትን ማበረታት አለብን የሚል ሀሳብ መጣ። ሁለተኛው ደግሞ ተራራው የቀደምት የከምባታ ህዝቦች መጥተው የኖሩበት የመጀመሪያው ተራራ እንደመሆኑ መጠን ይህን ታሪኩንና ባህሉን፣ ቅርሱን በዚህ ላይ በመጨመር ጎብኚዎችን ይበልጥ መሳብ ይቻላል በሚል ታሳቢም ወደ ማልማቱ መገባቱን አቶ ዘመዴ ያብራራሉ፡፡
የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ገበያ ባለሙያ አቶ ኢያሱ ሰለሞን በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ለ18 ዓመታት ሰርተዋል።የአምበርቾ ተራራ ደረጃ ሲሰራ ጀምሮ ያውቁታል፤ የዞኑ አስተዳደርና ምክር ቤት እንዲሁም የዞኑ ባሀልና ቱሪዝም መምሪያ በመጀመሪያ ደረጃ ይህን ጉዳይ ለማሰራትና አጠቃላይ የዚህን አካባቢ የኢኮኖሚ ትስስር ከመፍጠር አንጻር ቱሪዝም አንዱ የመልማት እድል እንደሆነ ሲያስቡ ምን እናድርግ የሚል አጠቃላይ የምክክር መድረክ ማድረጋቸውን ያስታውሳሉ።እሳቸውም በምክክር መድረኩም ተሳትፈዋል።ከዚያም በአገር ውስጥም በውጪም ያሉ የዞኑ ምሁራን ተሰባስበው ይህ ጅምር ካለ እንዴት አርገን አስተሳስረን የሕዝቡን የኢኮኖሚ የመልማት የዞኑን ማህበራዊ ችግር የምንፈታው የሚል ትልቅ ፕሮፋይል ሰነድ አዘጋጅተዋል፤ ይህን ሰነድ መነሻ በማድረግ ነው ወደ ስራ የተገባው።
ይህን ሁሉ ተከትሎ በተከናወኑ ተግባሮች በዚህ ተራራ ላይ 777 ደረጃዎች ተገንብተዋል።እንደ አቶ ዘመዴ ገለጻ፤ ተራራውም የ777 ደረጃዎች ተራራ በመባልም መጠራት ጀምሯል፤ የደረጃዎቹ ብዛት ሲሰላም ከዓለም ሁለተኛ ከአፍሪካ አንደኛት በመባልም እየተጠራ ነው፡፡
እነዚህን 777 ደረጃዎች ለመገንባት አራት ነጥብ ሁለት ሚሊየን ብር ወጪ ተደርጓል።ይህን ስራ የግል ተቀቋራጭ በ50 ሚሊየን ብር አይሰራውም ያሉት አቶ ዘመዴ፣ አንድ ሺ ወጣቶች፣ የዞኑ ምሁራን ኢንጂነሮች፣ አስተባባሪዎች ተሳትፈውበት መገንባቱን ተናግረዋል።
አቶ ኢያሱም ወደ ስራ ሲገባ የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቴክኒክ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው፣ በገንዘብ ደረጃ የዞኑ አስተዳደር የዞኑን ህዝብ አስተባብሮ ሰራተኞች ከደሞዛቸው ቀንሰው፣ ማህበረሰቡ በጉልበቱ በገንዘቡ ማቴሪያል በማቅረብ በማህበረሰቡ የደቦ ስርአት በመቀባበል የአምበርቾ ተራራ ፕሮጀክት መገንባቱን አረጋግጠዋል።
ፕሮጀክቱ የፌዴራል መንግስትም ይሁን የሌሎች ለጋሽ ድርጅቶች ፋይናንስ ድጋፍ አልተደረገለትም ይላሉ፤ አሁን የህግ ማእቀፍ ተዘጋጅቶለታል፤ የዞኑ አስተዳደር በጀት ይመድባል፤ ከዚህ በተጨማሪ ከህዝብ የሚሰበሰብ ገንዘብ ይኖራል፤ ከቱሪዝም የሚሰበሰብ ገንዘብ ይኖራል ሲሉ ስራ አስኪያጁ ይገልጻሉ።
ስራ አስኪያጁ እንዳሉት፤ ከተራራው ግርጌ ያለው ሜዳማ ስፍራ ከባህር ወለል በላይ 2ሺ 600 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የተራራው አናት ደግሞ ከባህር ወለል በላይ ሶስት ሺ 58 ላይ ይገኛል።በዚህ ከፍታ ላይ መሆኑ እጅግ ቀዝቃዛ ያደርገዋል ተብሎ ቢታሰብም የሚቀዘቅዝ አይደለም፤ ጉም ይመጣል ይሄዳል እንጂ ያን ያህል ቀዝቀዛ የሚባል ቦታ አይደለም።ኢትዮጵያውያን በእዚህ አይነቱ ውብ ስፍራ ላይ ሆነው የሚደሰቱበት ስፍራ ነው።የአካባቢው ማህበረሰብም እንግዳን የማክበር ባህል ያለው ሲሆን፣ ጎብኚዎችም በፈረስ፣ በመኪና፣ ወዘተ. ሆነው ሊጎበኙት የሚችሉበት ስፍራ ነው፡፡
ቦታው ማራኪ እና በተፈጥሮ ሀብቱ የታደለ ነው፤ ተራራው ላይ 777 ደረጃዎች ሲገነቡለትም በርካታ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ መልእክቶችን ታሳቢ ተደርገዋል።ጥንት በዚህ ቦታ ላይ የከንባታ ህዝብ ሲመጣ ሰባት ጎሳዎች ነበሩት፤ የተራራው ላይ ደረጃ አንዱ ሰባት የእነሱን ውክልና ይይዛል፤ ደረጃዎቹ በአምበርቾ ተራራ ላይ ቢገነቡም ተራራው አናት ላይ ሲደርስ ሌሎች ስድስት ተራራዎች ይታያሉ።አምበሪቾን ጨምሮ አካባቢው ላይ ሰባት የተለያዩ ተራራዎች ይገኛሉ።ሁለተኛው ሰባት እነዚህን ሰባት ተራራዎች ይወክላል።ሶስተኛው ሰባት ደግሞ ከተራራው ላይ ፈልቀው ቁልቁል የሚወርዱ በከንባትኛ ‹‹ለመለ ለጋ›› ተብለው የሚጠሩትን ወይም ሰባት ምንጮችን እንዲወክል ተደርጓል።
ስራ አስኪያጁ እንዳሉት፤ ‹‹አምበርቾ›› የሚለው ቃል የሁለት ቃላት ውህድ ነው።አንደኛው ‹‹አምባ›› የሚለው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ‹‹አሪቾ›› የሚለው ነው።በከንባትኛ ‹‹አሪቾ›› ማለት ጸሀይ ማለት ነው፤ አምባ ደግሞ መገኛ ወይም ቦታ ማለት ነው።ስለዚህ አንድ ሰው ተራራው አናት ላይ ከወጣ በምስራቅም ይሁን በምእራብ ጸሀይን ማየት ይችላል።አምበሪቾ ላይ የተገኘ ሰው ጸሀይ ስትወጣም ስትጠልቅም ማግኘት ይችላል፤ በከንባትኛ አምበሪቾ ማለት ‹‹አሪቾ አምባ›› ወይም ‹‹የጸሀይ መገኛ›› ማለት ነው ሲሉ አቶ ዘመዴ ያብራራሉ።
ቀደምት የከንባታ ህዝቦች መጀመሪያ የመጡትና የኖሩት እዚህ ተራራ ላይ እንደመሆኑ ባህላዊ፣ ሃይማኖታና ታሪካዊ ቅርሶችና ኩነቶች ነበሯቸው፤ ንጉሶቻቸውን ሾመውበታል፤ ለንጉሶቻቸው ተገዝተው ኖረዋል፤ የሚያስፈልጋቸውን ግብር ከፍለዋል፤ ጥሩ የሰራ ተሸልሞበታል፤ ወንጀለኛ ተቀጥቶበታል፤ ንጉስ ተቀያይሮበታል፤ ስለዚህ አካባቢው የንጉስ ሹመት ስርዓት አለበት።ከዚህም ታሪካዊ ፋይዳዎች እንዳሉት መረዳት ይቻላል፡፡
ተራራው ሌሎች በርካታ ሀብቶችም አሉት፤ ሰው ያልተከለው 200 ሄክታር የሚጠጋ ጥብቅ የተጥሮ የቀርከሃ ደን፣ በውስጡም አቦ ሸማኔና ሌሎች የዱር እንስሳት አሉት፤ ከ350 የሚበልጡ ለመዳህኒትነት ሊውሉ የሚችሉ እጽዋት ያለበትም ነው፤ ዋሻዎች፣ ሜዳዎች፣ ወዘተ እንዳሉት ያብራራሉ።
በአምበርቾ ተራራ ላይ እስከ አሁን የተከናወነው ልማት የተራራው ልማት የመጀመሪያ ምእራፍ ነው።ተራራው ሰባት ዋና ዋና ተራሮችን የያዘም ነው።ሌሎቹን ተራራዎች መመልከት የሚቻለው ተራራው አናት ላይ ሲደረስ መሆኑን ስራ አስኪያጁ ይጠቁማሉ።
በቀጣይ ሌሎች በርካታ ፕሮጀክቶች መቀረጻ ቸውንም አቶ ዘመዴ ይጠቁማሉ። እያንዳንዳ ቸው ከ10 እስከ 20 ሚሊየን ብር በላይ የሚያንቀሳቅሱ ከሶስት በላይ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በዚህ ዓመት በአካባቢው ስራቸውን እንደሚጀምሩም ጠቅሰው፣ ለአብነትም የቼክ ሪፐብሊክ በአረንጓዴ ልማት፤ አይአርአር የተባለ ድርጅትም እንዲሁ ፕሮፖዛል ማቅረባቸውን ይገልጻሉ፡፡
በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ የከንባታ ምሁራን እንዳሉ ጠቅሰው፣ በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ፕሮፖዛል ማቅረብ የሚያስችል አቅም እንዳለም አመልክተዋል።ይህን ሁሉ ተከትሎም የአምበሪቾ ተራራ የተሟላ አስፈላጊ ነገሮችን የያዘ የቱሪስት መስህብ ይሆናል ብለን እንጠብቃለን ይላሉ።
በመስህብ ስፍራው መንገድ፣ መብራት፣ ሻይ ቡና የሚጠጣባቸውና ሰዎች የሚዝናኑባቸው ቦታዎች እንደሚያስፈልጉም ተናግረው፣ ከእነዚህ መካከልም በዚህ ዓመት የተወሰኑትን እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።ሰዎች እዚህ አካባቢ ማደር ሊፈልጉ ይችላሉ፤ ድንኳን የሚያድሩ አሉ፤ ቤት ማደር እፈልጋለሁ የሚል ሊመጣ ይችላል፤ ለእዚህም የጎጆ ቤት ቅርጽ ያላቸው ቤቶችን እንሰራለን ሲሉ ገልጸዋል።
ማህበረሰብ ተኮር የቱሪዝም ስራ ነው የምንሰራው፤ እዚህ ቦታ ላይ አብዛኛውን ግንባታ አናደርግም፤ ፈረስ አናረባም፤ ይህን ማቅረብ የሚችሉትንና የሚፈልጉትን ግን ለማገናኘት እንሰራለን ሲሉ ይገልጻሉ።ማህበረሰብ ተኮር ቱሪዝም ጎብኚው አርሶ አደሩ የሚኖረውን እየኖረ ጉብኝት የሚያደርግበት መሆኑን ጠቅሰው፣ አካባቢው የእንሰት ነው፤ ቆጮ እየፋቀ፣ እያረደ፣ እየበላ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ እንዲጎበኝ ማድረግ ያስፈልጋል፤ ይህን ሁሉ በሰነዱ በሚገባ ተቀምጧል፤ ስለዚህ ማህበረሰቡ ዋና ተሳታፊ ሆኖ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡
የፌዴራል መንግስት የቱሪዝምን ጉዳይ እንደ ትልቅ ጉዳይ መያዙ የኛ ዞን በቱሪዝም ጉዳይ ላይ ይበልጥ እንዲሰራ አድርጎታል፤ የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ እያለ ሌላ ቱሪዝም የሚያለማ ተቋም አቋቁሞ እየሰራ ያለውም ከዚሁ አኳያ እንደሚታይ ይገልጻሉ።‹‹ከመንግስት እቅድ ጋር ተቀራርበናል፤ ለምሳሌ እኔ ስራ አስኪያጅ ሆኜ የምመራው ፕሮግራም አብዛኞቹ ስራዎች በባህልና ተሪዝም መምሪያ ላይ የሚሰሩ ናቸው።ዞኑ ይህን ጉዳይ ለብቻ የሚሰራ ተቋም እስከ ማቋቋም የደረሰበት ዋናው ምክንያት የመንግስት አገራዊ አቅድ ነው ይላሉ፡፡
አረንጓዴ ልማትን በሚመለከት በአምበርቾ ተራራ ልማት እናት ሰነድ ላይ በግልጽ ሰፍሯል ያሉት አቶ ዘመዴ፣ 18 ሺ ሄክታር የሚሆነውን የአምበርቾ ተራራ ሙሉ በሙሉ በአገር በቀል ዛፍ የመሸፈን ዓላማ እንዳለም ይናገራሉ፤ አገር በቀል ዛፎች ብለን ለአኮኖሚው የሚጠቅሙትን ወደ ጎን አንተውም ያሉት ስራ አስኪያጁ፣ ለምሳሌ ቀርከሃ በብዛት እንዲለማ እንደሚደረግ ይጠቁማሉ።ለአፈር ይጠቅማል ብለን ኮርች ብቻ አንተክልም፤ ቀርከሃ ካልተከልን ስራ አጥነትን አንቀንስም ነው የሚሉት፤ ስለዚህ አረንጓዴ አሻራን በሚመለከት አንዱ ትልቁ ክንፍ/ ሀምሳ በመቶ በሚባል ደረጃ/ የአረንጓዴ ልማት ስራችን ይሆናል ያሉት ስራ አስኪያጁ፣ ለእዚህም ችግኝ ጣቢያዎችን እያቋቋምን እየሰራን ነው ይላሉ።መንግስታዊ ድርጅቶችን ከዚህ ጋር እያስተሳሰርን ነው።አብዛኛዎቹ ስራዎቻችን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ጋር የሚገናኙ ናቸው ይባላል፡፡
ቦታው ለኢትዮጵያ አዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ይሆናል ሲሉም ጠቅሰው፣ በእዚህ ተራራ ላይ የተገኘ ሰው 3ሺ 58 ሜትር ከፍታ ላይ ሲወጣ በጣም እንደሚቀዘቅዘው ይጠብቃል፤ ይሁንና ግን ተራራው አይቀዘቅዝም፤ በዚህ ክረምት እንኳ ጉም ከመምጣቱና ከመሄዱ ውጪ ያን ያህል ቅዝቃዜ ያለበት ስፍራ አይደለም ሲሉ ያብራራሉ።
ተራራው በበርካታ ኢትዮጵያውያንና የውጪ ዜጎች እየተጎበኘ እንደሚገኝም አቶ ዘመዴ ይጠቁማሉ፤ እሳቸው እንዳሉት፤ ከ2013 ጀምሮ እስከ አሁን ከ300ሺ በላይ ሰዎች ጎብኝተውታል፤ እጅግ በርካታ ሰዎች ተራራው አናትም ሜዳውም ላይ ድንኳን እየተከሉ ጭምር አድረዋል፤ ካምፕፋይር አርገዋል፤ ተደስተዋል፤ የተለያዩ ጎዞዎች ተደርገዋል፤ ከእነዚህ ጎብኚዎች መካከል 570 የሚሆኑት ደግሞ ዳያስፓራዎች ናቸው፤ ከ90 በላይ ደግሞ የውጭ አገር ቱሪስቶችም ጎብኝተውታል ሲሉ ይገልጻሉ።ጎብኚዎቹ ተራራውን የጎበኙት ተራራውን በዩቲዩቦች፣ በመገናኛ ብዙሃን ማስተዋወቅ በመቻሉ መሆኑን ይናገራሉ።የጎብኚዎች ምርጫ እየሆነ መምጣቱንም ጠቁመዋል። ጎብኚዎች ይህን ቦታ ሲጎበኙም ሆነ ለጉብኝት ሲመጡ ደህንነታቸው የተጠበቀ መሆኑንም አቶ ዘመዴ በመጥቀስ መላ ኢትዮጵያውያን መስህቡን እንዲጎበኙት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በከንባታና ጠምባሮ ዞን አስተዳደር፣ በዞኑ ምክር ቤት፣ ህዝብና ምሁራን ርብርብ እንዲለማ የተደረገው የአምበርቾ ተራራ ምእራፍ አንድ ፕሮጀክት ሌሎች ክልሎችና ዞኖቻቸውም ተሞክሮ መቅሰም የሚችሉበት አርአያነት ያለው ተግባር ነው።ዞኑ የዞኑ ብሄረሰቦች የመኖሪያ ቤቶች አሰራር፣ የባህላዊ ምግብ አዘጋጃጀት፣ ባህላዊ ዘፈኖችና ውዝዋዜዎች ፣ ዋሻዎች፣ ፏፏቴዎች፣ ፍል ውሃዎች፣ ወዘተ. ያሉበት ስለመሆኑ በቅርቡ በዞኑ ባደረግነው ጉብኝት የበለጠ መገንዘብ ችለናል።ዞኑ በጀመረው መንገድ አሁንም ህዝቡን ሌሎች የልማት ሀይሎችን ማስተባበሩን አጠናክሮ በመቀጠል ለቱሪዝም መስህብ ሊውሉ የሚችሉ የተፈጥሮ፣ የባህልና የታሪክ ሀብቶቹን በማልማት የተነሳበትን ዓላማ ለማሳካት መስራት ይኖርበታል፡፡
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13 ቀን 2015 ዓ.ም