ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ አንድ ቪዲዮ ሲዘዋወር አየሁና ልቤ ክፉኛ አዘነ። ቪዲዮው በሶስተኛው ዙር ጦርነት ወቅት በአሸባሪው ሕወሓት የተማረኩ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ሲንገላቱ የሚያሳይ ሲሆን የተገኘውም ከተማረከ የሕወሓት ወታደር ስልክ ላይ ነበር። ቪዲዮው ላይ እነዚህ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት በሰደፍ ሲደበደቡ፤ በድንጋይ ሲወገሩ፤ ጫማቸውን አስወልቀው በባዶ እግር ሲያስኬዷቸው፤ ሲሰድቧቸው፤ ሲረግሟቸው ያሳያል።
በቪዲዮው ላይ የሚታየው ሁለት ነገር ነው። አንደኛ የአሸባሪው ሕወሓት ወታደሮች በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ብሎም በኢትዮጵያ ላይ ያላቸው ጥላቻ ጽናት ይታያል። ይህ አስገራሚም ሆነ አዲስ ባይሆንም ነገር ግን በዚህ ቪዲዮ ላይ በማይደበቅ መልኩ ጎልቶ ይታያል።
የጥቅምት 24ቱ የጥላቻ ጥቃት በዚህ ቪዲዮ ላይ ተደግሞ ይታያል ቢባል ማጋነን አይሆንም። ያኔ በዚያ እለት በጥቃቱ ሰለባ የሆኑት ወታደሮች የደረሰባቸው ነገር ሲናገሩ ለማመን የሚከብድ ይመስል ነበር። ይህ ቪዲዮ ግን በእርግጥም የቡድኑ ሰዎች የተባለውን በደል ሁሉ የመፈጸም አቅም እንዳላቸው በግልጽ የሚያሳይ ነው።
ሌላኛው በዚህ ቪዲዮ የሚታየው የሰራዊቱን የመስዋእትነት ከፍታ ነው። ሰራዊቱ አጥንቱን ከስክሶ፤ ስጋውን ቆርሶ፤ ደሙን አፍስሶ አገራችንን ጠብቆልናል የሚለው ንግግር ከመደጋገሙ የተነሳ ዘልማዳዊ አባባል ቢመስልም በዚህ ቪዲዮ ግን በተግባር ታይቷል። በዚህ ቪዲዮ ላይ እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ወታደር ሲደበደብ እና ሲሰደብ የሚታየው ኢትዮጵያዊ ወታደር ስለሆነ እና አገራዊ ግዴታውን ስለፈጸመ ብቻ እንደሆነ በግልጽ ይታያል።
የሚሆንባቸው ነገር በሙሉ የሚሆነው ለግል ጉዳያቸው አይደለም። ለአገር ነው። የዛሬ ጽሁፋችን ማጠንጠኛም የታወቀውን የአሸባሪ ሕወሓት ለኢትዮጵያውያን ያለ ጥላቻ መዘከር ሳይሆን ለዚህ ሰራዊት የምንሰጠው እውቅና እና ክብር ያለ ቅደመ ሁኔታ መሆን እንዳለበት፤ ብሎም በቀጣይ ሰራዊቱ በትግራይ ክልል በሚያካሂዳቸው ዘመቻዎች በሙሉ አብረነው ልንቆም እንደሚገባ በድጋሚ ለማስታወስ ነው።
ዛሬ ላይ በወልቃይት በሚሊየን የሚቆጠር ሰው ተሰልፎ ምርት ሊሰበስብ ማሳ ላይ ውሏል። ባህር ዳር የጣና ፎረምን አዘጋጅታ የቀጠናው መሪዎችን አስተናግዳለች። ጎንደር የመንግስት የካቢኔ አባላት ግምገማን አካሂዳለች። ደሴ ወደ ቀድሞ ቅኝቷ ተመልሳለች። ደብረ ብርሀን የኢንዱስትሪ ከተማነቷን የሚያጠናክር ድግስ እያሰናዳች ነው። አዲስ አበባ አሁንም ሰላማዊ ኑሮዋን እየገፋች ነው። ይህ ሁሉ የሆነው ግን እንዲሁ በመላ አይደለም። ከላይ የጠቀስነውን መስዋእትነት የሚከፍሉ ጀግኖች ስላሉ ነው።
እኛ አንድ ቀን መንፈሳዊ ጉዞ ወይም ሀይኪንግ ተጉዘን በእግር የሁለት ሰዓት መንገድ ብንጓዝ በማግስቱ ስራ አንገባም። ወገቤን፤ እግሬን፤ ጀርባዬን አመመኝ እንላለን። ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ግን ይህ የእለት ተእለት ኑሮው ነው። እንደሚታወቀው ሰሜኑ የአገራችን ክፍል ተራራ ይበዛዋል። ሊያውም ረዣዥም እና ሰንሰለታማ።
ወታደር ደግሞ እንደ ሲቪል አስፋልት ተከትሎ አይሄድምና እነዚህን ተራሮች መሳሪያ ተሸክሞ መውጣት አለበት። ሊያውም ዝም ብሎ መውጣት አይደለም እየተዋጋ ከሰውም ከተፈጥሮም እየታገለ። ይህን የሚያደርገው ለግል ጉዳዩ አይደለም ለእኛው ነው…።
አንዳንዶቻችን የተለመደ የአመጋገብ ሂደት አለን። ምን ብንበላ እንጀራ ካልበላን እህል የበላን አይመስለንም። ሊያውም አይነቱን መርጠን። ወጡንም እንደዛው። ቁርጥ እና ቅቅል ካልበላ እህል የበላ የማይመስለውም አለ። በቀን አራቴ ካልበላ የከሳ የሚመስለውም ብዙ ነው።
ሰራዊቱ ግን ለቀናት ያለ ምግብ እና ያለ ውሀ ነፍስ ለማቆየት ያህል እየቀመሰ ነው የሚቆየው። ሱባኤ ይዞ አይደለም። ክብደት የመቀነስ ልምምድ ላይም ሆኖ አይደለም። ሌላው በልቶ እንዲያድር መስዋእትነት መክፈል ያለበት ኃይል ስለሚያስፈልግ ነው። ይህን የሚያደርገው ለግል ጉዳዩ አይደለም፤ ለእኛው ነው….።
ብዙዎቻችን ልብስ የምንለብሰው ለጥቂት ቀናት ነው። በቀን በቀን ልብስ የሚቀይርም አለ። ማታ ቤታችን ስንገባ ከሚያስደስቱን ነገሮች አንዱ ቀን አድርገነው የዋልነውን ጫማ ማውለቅ ነው። ይሄ ጫማ አልተመቸኝም፤ ያቃጥላል። ይሄ ልብስ አልተመቸኝም እንዲህ ወይም እንዲያ ሆኗል እንላለን።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለወራት ዩኒፎርም ሳያወልቅ ጫማውን በእግሩ እንዳለ ምሽግ ውስጥ ተቀምጦ አገር ይጠብቃል። ይህን የሚያደርገው እንደኛ የጤናው ጉዳይ ስለማያሳስበው ወይም ዘንጦ መታየት ስለሚጠላ አይደለም። ይህ የሚሆነው ሌሎች አምረው እንዲታዩ የተወሰነ ኃይል እየተጎሳቆለም ቢሆን መጠበቅ ስላለበት ነው። ይህም ለእኛው የተደረገ ነው..።
እንዲህ እንዲህ እያልን ብዙ ልንጽፍ እንችላለን። ዋናው ፍሬ ጉዳይ ግን ሰራዊቱ አሁንም በእያንዳንዷ ቀን እየከፈለ ያለው መስዋእትነት መረሳት የለበትም ነው። በተለይም በዚህ ወቅት ከምንጊዜውም በላይ ሰራዊቱን ማስታወስ እና ያለቅድመ ሁኔታ መደገፍ ግዴታ ነው። ሁላችንም አይናችንን በሰራዊቱ ላይ ልናደርግ ይገባል። ሁላችንም ከያለንበት ሆነን ለሰራዊቱ ማንኛውንም አይነት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆን አለብን።
ሕወሓት ሰሞኑን ሞቱ መቃረቡን ሲያውቅ የመሞቻውን ቀን ለማስረዘም ሌት ተቀን እየተጋ ነው። እነ ቴዎድሮስ አድሀኖም ጄኖሳይድ ሊፈጸምብን ነው እያሉ እየተፈራገጡ ነው። ለአይቀሬው ሽንፈት ሽፋን እያዘጋጁ ደግሞም ከተሳካ ዓለም ተረባርቦ ሽንፈታቸውን እንዲያስቀርላቸው እየሰሩ ነው። በዚህ ሁንታ መሀል ግን ያለመዘናጋት አይኖቻችን ሰራዊቱ ላይ ሊሆኑ ይገባል።
ሰራዊቱ እንደሚያሸነፍ እርግጥ ነው። ነገር ግን ድሉ ድላችን እንዲሆን በእያንዳንዷ የትግራይ ከተማም ሆነ የገጠር ቀበሌ ለሚኖረው ነጻ የማውጣት ዘመቻ ልንደግፈው አብረነው ልንቆም ብቻውን እንዳልሆነም ልናሳይ ይገባል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የትግራይ ህዝብ ነጻ ሊያወጣው ብዙ ዋጋ እየከፈለ ላለው የመከላከያ ሰራዊቱ ያለውን አጋርነት በተጨባጭ ማሳየት ይጠበቅበታል።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12 ቀን 2015 ዓ.ም