ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት ሁሉም ሰላም ነበር ፤ ሰራተኛው በስራ ገበታው፣ ተማሪው በትምህርቱ፣ ነጋዴው በንግዱ፣ ገበሬው በእርሻው ሁሉም በተሰማራበት መስክ ውጤታማ ለመሆን ተፍ ተፍ ሲል ነበር። ሁሉም የእለት ጉርሱን ከማግኘት ባሻገርም ህልሜ፣ ግቤ ብሎ ያስቀመጠውን ዓላማ እውን ለማድረግ ይተጋ ነበር፤ ይህ እውነታ በተመሳሳይ በትግራይም ይስተዋል ነበር።
ይህ ሁሉ ሲሆን ግን በህዝባዊ እምቢተኛነት ከስልጣን የወረደው አሸባሪው ትህነግ ወደ ስልጣን ይመልሰኛል የሚለውን የመጨረሻ የጥፋት ተግባራትን፣ እኩይ ሴራዎችን ይጎነጉን ነበር፤ አገርን ከፍ ወዳለ ሁከትና ብጥብጥ በመክተት ከዚህ ለማትረፍ ቀን ከሌሊት ያለ እረፍት ይሰራ ነበር።
የጥፋቱና የሴራውን መጨረሻ ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በመሰንዘር በአደባባይ አረጋግጧል። በዚህ ፍጹም ከሆነ ከሀዲነት የመነጨው የቡድኑ ጥቃት፤ አገር እንደ አገር ከፍ ያለ የልብ ስብራት ውስጥ ገብታለች፡፡
እራሱን በነፃ አውጪ ስም ላለፉት አምስት አስርት አመታት ሲጠራ የነበረው ይህ አሸባሪ ቡድን፤ አገርና ህዝብ በአዲስ የታሪክ ምእራፍ ውስጥ፤ ከፍ ባለ ተስፋ ተነቃቅተው መንቀሳቀስ በጀመሩ ማግስት በአገር ላይ የከፈተው ጦርነት ከሁሉም በላይ የለውጡ ተስፈኛ ለነበረው የትግራይ ህዝብ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖበታል።
አሸባሪ ቡድን “አገር ለማፍረስ እስከ ሲኦል እንወርዳለን” በሚል የጥፋት ጥግ የጀመረው ጦርነት እነሆ ላለፉት ሁለት ዓመታት ያህል የትግራይን ወጣት ለእልቂት፤ የትግራይን ህዝብ ተነግሮ ለማልቅ ማህበራዊ ምስቅልቅል ዳርጎታል።
መቼም ቢሆን ከስህተቱ የማይማረውና ከራሱ በላይ ለማንም የማይጨነቀው አሸባሪው ትህነግ የኢትዮጵያ መንግስት ሆነ ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ለትግራይ ህዝብ የሚላከውን የእርዳታ እህል ሳይቀር በመንጠቅ ለቡድኑ ተዋጊዎች ቀለብ በማድረግ የራሱን ህልውና ለማስቀጠል የሄደበትም ኢሰብዓዊ መንገድና መንገዱ የትግራይን ህዝብ ያስከፈለው ዋጋ የቡድኑን የጭካኔ ጥግ ያመላከተ ነው።
የትግራይን ህዝብ በተደራጀ ጠንካራ መዋቅር የቡድኑ አስተሳሰብ ባሪያ በማድረግ ህዝቡ ምንም አይነት አማራጭ የፖለቲካ አማራጭ እንዳይኖረው አድርጓል። በዚህም ህዝቡ ፈርቶና ተገዶ አብሮት ለመቆየት ተገዷል። በዚህ ቆይታ ያተረፈው ነገር ቢኖር ልጆቹን ማጣት፣ በርሃብ ቸነፈር መገረፍን ብቻ ነው። ይህንን ደግሞ ከማንም ከምንም በላይ ራሱ ህዝቡ የሚያውቀው የሚመሰክረው ሃቅ ነው።
ቡድኑ እድሜውን ለማራዘም ብዙ ድንጋዮችን ፈንቅሏል። መንግስት የሰጠውን የሰላም እድል ጨምሮ በርካታ እድሎችንም አምክኗል። ከዛ ሁሉ በላይ ደግሞ ለህዝብና ለአገር ሲባል መንግስት ዝቅ ብሎ የሰላም ጥሪ አቅርቦ የእንደራደር መንገድን ከፍቶና ቢለውም አሁንም በእብሪት ያበጠው ልቡ አልረታ ብሎት እምቢታን መርጦ አገርን ለተደጋጋሚ እልቂት ዳርጓል።
በእውነት ሕዝቤ በሚለው ህዝብ ላይ እንደ አሸባሪው ትህነግ ግፍ የፈጸመና እየፈፀመ ያለ አረመኔያዊ ቡድን በዓለም ላይ ታይቶ ስለመታወቁ እኔ በግሌ እርግጠኛ አይደለሁም። የቡድኑን ያህል የስልጣን ጥማት ያለበትና አልጠግብ ባይ አለ ብዬ ለማሰብም እቸገራለሁ።
በእነዚህ ሁለት ዓመታት ህዝቡ ሕወሓትን በቃህ እንዲለው የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል ሰፊ ስራዎችም ተሰርተዋል። ሕዝቡ ካለበት አጣብቂኝ እና ከተሰራበት የከፋ ፕሮፓጋንዳ አንጻር ውጤታማነቱ የተጠበቀውን ያህል አልነበረም። ዛሬ ግን ነገሮች እየተቀየሩ ነው። ቡድኑ ከራሱ ጥቅም አልፎ ለሌሎች የሚተርፍ እንዳይደለ የመጣበት መንገድ ለትግራይ ህዝብ በግልጽ እያሳየው ነው።
የትግራይ ህዝብ እንደ ህዝብ አሁን ላይ ማድረግ ያለበት የሚመክረው የሚፈልግ አይደለም። በአሸ ባሪው ሕወሓት ላለፉት አምስት አስርት የደረሰበትን ግፍና በደል አስተዋሽ አይፈልግም። አሁን የሚፈ ልገው በቡድኑ ያጣውን ሰላምና ልማት ነው። አሸባሪው ትህነግና የትግራይ ህዝብ አንድ እንዳልሆኑ በገሃድ ማሳየት ነው። የትግራይ ህዝብ ትልቅ ማንነት ያለው፤ አገሩ እዚህ ለመድረሷ ከማንም በላይ ትልቅ ድርሻ የሚወስድና በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር መሆኑን ማስመስከር ነው።
የትግራይ ህዝብ ይህንን አሸባሪ ቡድን በቃህ ከላዬ ውረድ፣ የምሰጥህ ልጅም፣ ሃብትም መሬትም የለኝም፤ በሰላም ልኑርበት ከእህት ከወንድሞቼ አትነጥለኝ ማለት ያለበት ትክክለኛ ጊዜ አሁንና አሁን ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ አሁነኛ አገራዊ እውነታው አመቺ ነው።
አዎ! በተለይም የኢትዮጵያ መንግስት በተቆ ጣጠራቸው የክልሉ ከተሞች የሚኖሩ ህዝቦች ከዓመታት በኋላ ያገኙትን የነጻነት አየር በቀላሉ ከእጃቸው እንዲወጣ መፍቀድ የለባቸውም። ለዚህም ከመከላከያ ሰራዊቱ ጎን በመቆም እንደውም ሌሎች አጎራባቾቻቸው እነሱ ያዩትን የነጻነት ብርሃን ብልጭታ እንዲያዩ በሚችሉት ሁሉ መደገፍ እንዳለባቸው ይሰማኛል። በእርግጥ ይህንን አያደርጉም የሚል ግምት የለኝም።
መንግስትም እነዚህን የተጎዱ ህዝቦች ለማገዝ ለመደገፍ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል አለበት። ለትግራይ ወንድሞቻችን ከምንም በላይ አሁን ሰብዓዊ እርዳታው የሚያስፈልጋቸው ወቅት ነው፤ ይህ እንዲሆን የሚሹ ብዙ ለጋሽ አካላት ያሉ ቢሆንም የእኛ ትኩረት ሊሆን የሚገባው ግን ከልባቸው የትግራይን ህዝብ ለመርዳት ፍላጎት ካላቸው ጋር ብቻ መሆን አለበት።
በጠቅላላው የትግራይ ህዝብ ማመን ያለበት ነገር የተሻለው ሕይወትና መጻኢ ተስፋ ያለው ከአሸባሪው ትህነግ ውጭ ነው። ህዝቡ ለራሱና ለመጪው ትውልዶች ሲል ጀርባው ላይ የታዘለበትን የወንበዴ ቡድን ወዲያ ገፍትሮ ጥሎ ለአመታት ያጣውን ነጻነት ብሎም ሰላምና ልማት በራሱ መንገድ ሊያስመልስ ፤ዳግም ከእጁ እንዳይወጣ በጥንቃቄ ሊጠብቀው ይገባል። አበቃሁ።
በእምነት
አዲስ ዘመን ጥቅምት 11 ቀን 2015