የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በ2015 በሁለቱ ምክር ቤቶች የመክፈቻ መርሀ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር እንዳሉት፤ መንግስት በ2015 በጀት አመት የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋትና ጤናማ የማክሮ ኢኮኖሚ እንዲፈጠር ጥረት ያደርጋል። የምግብ ምርትን በማሳደግና አቅርቦትን በመጨመር ውጤታማ የሆነ የፊሲካልና የገንዘብ ፖሊሲን መተግበር፣ የንግድ ሰንሰለትን በማዘመን ምርት ወደ ገበያ የሚመጣበትን መንገድ ማሳለጥ፣ የገቢ አቅማቸው አነስተኛ ለሆኑና አቅመ ደካሞች ድጎማ በማድረግ የዋጋ ንረትን አሉታዊ ተጽዕኖ መቀነስ ሌላው በበጀት አመቱ በመንግስት በትኩረት ከሚሰሩ ስራዎች ውስጥ መሆኑን አንስተዋል።
በአገራችን ባለፉት አመታት የዋጋ ንረት እየጨመረ የመጣ ክስተት ሆኗል። በ2014 ዓ.ም በርካታ ጫናዎች ቢከሰቱም በኢኮኖሚ ላይ ስኬት ተመዝግቧል። ባለፉት ተከታታይ ዓመታት የውጭ ምንዛሬ እድገት አሳይቷል። በአገሪቱ የተከሰተው የዋጋ ንረት በአብዛኛው ምግብ ነክ ምርቶች ላይ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ። ጫናው እንዲበረታ የሚያደርገውም በኢትዮጵያ አንድ ሰው ከወር ከሚያገኘው ከገቢው ወደ 54 በመቶ የሚሆነውን ለምግብ የሚያወጣ በመሆኑ ነው፡፡
ስለዚህ የምግቡ ዋጋ በተወደደ ቁጥር ለምግብ የሚያወጣው ወጪ ከ54 በመቶ በላይ እየሆነበት ሲሄድ የዋጋ ንረቱ እየከበደው እንዲሄድ ያደርገዋል፡፡ በምግብ የዋጋ ንረት ሳቢያ እየታየ ያለው የኑሮ ውድነትን ቢያንስ በተወሰነ ደረጃ ለመቀነስ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ነው፡፡ በተለይ የምግብ ምርቶችን መጨመር ወሳኝ ነገር ስለመሆኑም የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ።
ኢትዮጵያ ከምትፈልገው የምግብ ፍላጎት 75 በመቶውን ብቻ በአገር ውስጥ ምርት የሚሸፍን ሲሆን ቀሪው 25 በመቶ ከውጭ የሚገባ ምርት ነው፡፡ ይህን ለማስገባት ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ያስፈልጋል፡፡ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ማስገባት ቢቻል የዋጋ ንረቱ ላይኖር ይችል ነበር። ይህም ቢሆን ዘንድሮ ለምግብ ነክ ምርቶች ብቻ 3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ወጪ መደረጉንም መረጃው ያመለክተዋል፡፡
በያዝነው 2014 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት ለ2014 ዓ.ም. የተጨማሪ በጀትን ሳይጨምር 542 ቢሊዮን ብር የወጪ በጀት በማጽደቅ ከሐምሌ 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረ ሲሆን፣ ከዚህ የወጪ በጀት ውስጥ 436 ቢሊዮን ብሩ ከታክስና ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች እንዲሁም ከውጭ ዕርዳታ ለመሰብሰብ ታሳቢ ተደርጎ ነበር። የተቀረው ብር 106 ቢሊዮን ደግሞ በበጀት ጉድለትነት ተይዞ፣ ጉድለቱንም ከአገር ውስጥና ከውጭ ብድር ለመሸፈን ታቅዶ ነበር። በዚሁ መሠረት ከውጭ ብድር 38 ቢሊዮን ብርና 68 ቢሊዮን ብር ከአገር ውስጥ የተጣራ ብድር በመውሰድ የበጀት ጉድለቱ እንደሚሸፈን መታቀዱን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
የአገሪቱን ማክሮ ኢኮኖሚ ጤናማ ሆኖ እንዲቀጥል ምን መሰራት አለበት? ለኑሮ ውድነቱ፣ ከጥቁር ገበያው ችግር መፍትሄው ምንድነው? ስንል የኢኮኖሚ ባለሙያዎችን አነጋግረናል።
የኢኮኖሚ ባለሙያው የአፍሪካ ንግድ ምክር ቤቶች ዋና ጸሃፊ አቶ ክቡር ገና እንደሚሉት፤ የኑሮ ውድነትን ከዋጋ ንረት ጋር ስናያይዘው የቀን ከቀን የኑሮ ሂደት ጋር የሚነሳ ጉዳይ ሆኖ ነው የምናገኘው። ይህ ማለት የአንድ ዜጋ የትራንስፖርት፤ የምግብና የቤት ኪራይ ወጪን ያጠቃልላል። አንድ ሰው በአንድ ደመወዝ ብቻ ኑሮን መሸከም ሲከብደው የኑሮ ውድነት ተፈጠረ ማለት ነው።
ይህንን ችግር ለመቅረፍም በረጅም ጊዜ እቅድ ምርትን እንዴት መጨመር እንደሚቻል ማቀድ ነው። ይህም ሲባል የገዥውን ፍላጎት በሚያሟላ መልኩ ምርት እየጨመረ ዋጋ እየቀነሰ የሚመጣበት ሁኔታን ለመፍጠር አሁን የተጀማመሩ የኩታ ገጠም የስንዴ ልማት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። በዚህ ወቅት መፍትሄ ለሚሆኑ ስራዎች ተግባራዊ ምላሽ ለመስጠት አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ መሆናችንን የሚናገሩት አቶ ክቡር ገና እኛ ባለንበት ሁኔታ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ሰፋፊ ኢንቨስትመንቶችን ማምጣት አልተቻለም ይላሉ። በዚህም አዳዲስ የስራ እድሎችን የመክፈት ሁኔታ ተቀዛቅዟል። ሸማቹ ማህበረሰብ መግዣ ገንዘብ በማጣት የኑሮ ሁኔታው ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሆን ያደርገዋል ማለት መሆኑን ይናገራሉ።
ገበሬውንም በትልቅ ደረጃ እንዳያመረት ከማድረጉም በላይ፤ ወደ ኢንዱስትሪ ሊያድጉ የሚችሉ ምርቶችን የሚደግፉ እንደ ማዳበሪያ ያሉ ግብአቶችን ማምጣትም ምርታማነቱን አዳጋች ሊያደርገው የሚችልበት ሁኔታ መኖሩ ችግሩን አሳሳቢ ያደርገዋል ይላሉ።
ይህን ችግር ለመቅረፍ የአጭር ጊዜ እቅድ መሆን ያለበት ከቁጥጥር ጋር በተያያዘ መስራትና መንግስት ደግሞ መሰረታዊ ቁሳቁሶች ላይ ድጎማ ማድረግ፤ ይህም ነገሮች እስኪረጋጉ ድረስ ማስቀጠል የሚገባው መሆኑንም ጠቁመዋል። መንግስት ይህንን ለማድረግ አቅም እንዲኖረው ድሃ ህብረተሰብ ላይ ሳይሆን አቅም አለው የሚባለው የማህበረሰብ አካባቢ የታክስ ጭማሪ በማድረግ ገንዘብ መስብሰብ አንድ አማራጭ ነው ብለዋል።
ጤናማ ማይክሮ ኢኮኖሚ የመፍጠር ስራ ይሰራል ተብሎ የተጠቀሰው ጉዳይ አንደኛው የዋጋ ግሽበቱን ወደነበረበት መመልስ ወይም ካለበት በታች መቀነስ ሲቻል ነው። አሁን ያለው የዋጋ ግሽበት ምጣኔ ባለ ሁለት አሃዝ የሆነውን ከአምስት ከፍ ብሎ ከሰባት ባይበልጥ የማይክሮ አኮኖሚው የሚሻሻልበት ሁኔታ ሊፈጥር የሚችል መሆኑን ነው ያስረዱት።
ሁለተኛው የውጭ ምንዛሪውን በማስተካከል ምርትን ለማሳደግ የሚረዱ የውጭ ግብአቶችን ማምጣት፤ ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚውሉትን ለማምጣት መጣር ነው። የዶላር ፍላጎትን እና አቅርቦትን ማጣጣም የሚቻለው ለኤክስፖርት የሚሆን ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር በረጅም ጊዜ ማይክሮ ኢኮኖሚውን የሚያሻሽልበት ሁኔታ ይፈጥራል።
ሌላው ባንኮች የሚሰጡትን ወለድ ከኢንፍሌሽኑ ጋር የተጣጣመ መሆን ይኖርበታል። አንፍሌሽን ሰለሳ በመቶ ሆኖ የባንክ ወለድ አስር በመቶ ከሆነ ይሄ የሚስተካከልበት መንገድ እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል። መንግስት ከታክስም ሆነ ከተለያዩ ገቢዎች የሚያገኘው ገንዘብ ሲያጥር ከምንም ተነስቶ ገንዘብ ይፈጥራል፤ ይህም ግሽበቱን ለመቀነስ ስለሚያስችል ኑሮን ለማረጋጋት አንድ አማራጭ ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰዋል።
የኢኮኖሚ ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ በበኩላቸው፤ የኑሮ ውድነቱን ለመሻሻል መጀመሪያ ምክንያቶችን ማወቅ ያስፈልጋል ይላሉ። የኑሮ ውድነቱን ከፍ ያደረገው የብር ዋጋ ማሽቆልቆል ነው። ማህበረሰቡ የሚፈልጋቸው የምግብ አይነቶች በሚፈልጋቸው አልበሳት ከውጭ ስለሚመጡና ነጋዴው ከጥቁር ገበያ በሚያመጣው ዶላር ያስገባውን ልብስ በውድ ዋጋ ስለሚሸጥ የአገራችን ሁኔታ ልዩ እንዲሆን አድርጎታል ብለዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የኢኮኖሚ ሁኔታ የእኛን አገርም አጥቀቶታል። ከኮቪድ ወቅት ጀምሮ የትራንስፖርት ሰንሰለቱ ላይ ክፍተት መፈጠሩ በገቢ እቃዎች ላይ ጫናን ፈጥሯል። አገሪቱ የምታርሰው መሬት በቅርብ ጊዜ እየተሻሻለ ከመሆኑ በስተቀር 26 ሚሊየን ህዝብ በነበረበት ጊዜ የሚታረሰው እርሻና በ4 እጥፍ በጨመረበት ጊዜ ላይ ለውጥ አለመኖሩ በአገሪቱ ምርት ላይ ጫና እንዲፈጠር አድርጎታል።
ሌላው አገሪቱ የምታካሄደው ትላልቅ ፕሮጀክቶች መኖራቸው በርካታ ኢኮኖሚውን የሚደግፈው ገንዘብ ወደ ስራው መሄዱ አሳሳቢ ነው። ከላይ የጠቀስናቸው በሙሉ የኢኮኖሚ እድገት ቁስሎች በመሆናቸው የተነሳ እነሱን ከላከምን በስተቀር ችግሩ ስር መስደዱ የማይቀር ነው።
በአገሪቱ ውስጥ ያለው ከፍተኛ የሙስና ችግር በኢኮኖሚው ላይ ጫና ፈጥሯል። በተወካዮች ምክር ቤት ዋና ኦዲተሯ ሪፖርት በሚያቀረቡበት ጊዜ ከፍተኛ የመንግስት ገንዘብ እንደባከነ ስለመሆኑ ነው የገለፁት። ይሄን ያህል ገንዘብ ሲባክንስ መንግስት ምን እያደረገ ነው? የሚል ጥያቄ ያስነሳል። ይሄ የበጀት ገንዘብ ከግብር ከህዝቡ ተሰብስቦ በድጎማ ለስራ የቀረበ ገንዘብ በመሆኑ ይሄንን መቆጣጠርም የኢኮኖሚ ጫናውን ለመቀነስ ያግዛል።
ከመልካም አስተዳደር ችግሮች የሚመጡም ሁኔታዎች መኖራቸው ይታያል። ይህም ጥቂት ነጋዴዎች ህዝቡን እንዲበዘብዙ የሚፈቀድ ከሆነ፤ መንግስት ያንን መቆጣጠር ካልቻለ ህብረተሰቡ ችግር ውስጥ ይገባል። መንግስት ግን ይሄንን ለማስተካከል እሰራለሁ ማለቱ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
መንግስት ሁኔታዎችን ለማረጋጋት ከሌሎች አገራት የቀደመ ተሞክሮ መማር ይኖርበታል የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው በኮቪድ ወቅት ትላልቅ አገራት ለዜጎቻቸው እርዳታ ሲያደርጉ የነበረ መሆኑን አስታውሰዋል። መንግስትም ይሄንን ተሞክሮ በመውሰድ ማህበረሰቡ ከድህነት መረብ በታች እንዳይወርድ መስራት ይገባል።
በዋናነት አገሪቱ ውስጥ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ ማረጋጋት፣ በሙሉ አቅም ወደ ልማት የሚገባበትን አማራጭ መፍጠር ለኢኮኖሚው መረጋጋት ቁልፍ መፍትሄ ነው። አገሪቱ አይ ኤም አፍ እንደሚለው በ5 ነጥብ 3 የኢኮኖሚው ሁኔታ ያድጋል የሚል ትንበያ መኖሩን ተከትሎ ይህ እድል የማህበረሰቡን ሕይወት ያሻሽላል ብለው እንደሚጠብቁ ይናገራሉ። ህዝቡ እንዳይጎዳ፤ ህፃናት እንዳይራቡ፣ መድሃኒት እንዳይጠፋ የአጭር ጊዜን እቅድ በማቀድ ህዝቡን መታደግ ያስፈልጋል ብለዋል።
መንግስት በአገሪቱ ያለውን ከፍተኛ የመሬትና የውሃ ሀብት በመጠቀም ምርት መጀመሩ ተስፋ ሰጪ መሆኑን የተናገሩት የኢኮኖሚ ባለሙያው አሁን የተጀመረው ልማት ተጠናክሮ ከቀጠለ በቂ የምግብ አቅርቦት ይኖራል፤ ይሄ ደግሞ ህዝቡን ለማቆየት ያለው አስተዋፅኦ የማይናቅ መሆኑን ያብራራሉ።
ኢንዱስትሪ ፓርኮች ስራ እንዲጀምር በርካታ ኢንቨስተሮች እንዲመጡ የፋይናንስ ስርአቱን መቀየርና የውጭ ባለሃብቶችን እንዲጋብዝ ማድረግ የግድ ነው። ሌላው ችግር በአገሪቱ የካፒታል ገበያ አለመኖር ነው። ካፒታል ገበያ እንዲቋቋም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ሰጥቷል። የውጭ ባንኮችም እንዲገቡ ውሳኔ ተላልፏል። የውጭ ባንኮች ሲመጡ በአገር ውስጥ ያሉ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ይቀርፋል ብለዋል።
ከፍተኛ የመንግስት ወጪዎችን መቀነስ፣ ከብክነት የፀዳ አሰራር መስራት፤ በጠረጴዛ ስር የሚሄደውን ከፍተኛ የሙስና ሰንስለት መበጥስ አስፈላጊ መሆኑን ያስረዳሉ። ይህንን ለማፅዳትም የምርመራ ጋዜጠኝነትን አሳድጎ ችግሮችን ለመፍታት መነሳት ለቀጣይ አገሪቱ የተረጋጋ ኢኮኖሚ እንዲኖራት ለማድረግ ያስችላል።
የአፍሪካ ንግድ ምክር ቤቶች ዋና ጸሃፊ አቶ ክቡር ገና መፍትሄ ያሏቸውን ሀሳቦችን አስቀምጠዋል። ኢኮኖሚው ወደ ቦታው ተመልሶ ለኑሮ ወድነቱ መድሃኒት የሚሆነው ጦርነቱ የሚቆምበትን አማራጭ በመፍጠር ነው። አሁን ባለው ሁኔታ አገራችን ብቻ ሳትሆን በመላው ዓለም የተለያዩ ቦታዎች ጦርነቶች መኖራቸው የዓለም ኢኮኖሚ እንዲቀዛቀዝ ሆነዋል። የኛ አገርን ችግር ለመፍታት ለመነጋገር በጣም ተቸግረናል ግን ለህዝቡ ከታሰበ ጦርነቱን መቆም ነው ዋነኛው መፍትሄ። ለጦርነት የሚወጣ ገንዘብ፤ ወጣት፤ ሀሳብና ትጋት በሙሉ ለሰላም ቢሆን የተሻለ አማራጭ ነው።
ሁለተኛው ዋጋው እየናረ የሄደው የነዳጅ ዋጋ ነው። ይህ ከአገሪቱ ቁጥጥር ውጭ ነው። ምክንያቱም የነዳጅ ዋጋ በነዳጅ አቅራቢዎቹ አገራት ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ነው። ነገር ግን የተወሰነ ነገር በመደጎም ገበያውን ማረጋጋት ከአገሪቱ መንግስት የሚጠበቅ ነው። ለምሳሌ አቅም ያለው የሚጠቀመው ነዳጅና አቅም የሌለው በእግሩ የሚሄደው ግለስብ በነዳጅ ምክንያት ሕይወቱ ላይ የሚመጣ ጫና አስቸጋሪ ስለሆነ ለእንደዚህ አይነት ሰዎች ድጎማ ያስፈልጋል።
ሌላው ሰው ወደ ስራ ዓለም የሚገባበትና የውጭ ኢንቨስትመንቶች ወደ አገር የሚሳቡበት ሁኔታ ማመቻቸት የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ያግዛል። ይህም ከመሬት ጋር የተገናኙ፤ ከባንክ ጋር የተያያዘና የመንግስት ህግና መመሪያን በማስተካከል የውጭ ኢንቨስትመንት መሳብ የግድ ይላል ብለዋል።
በአጠቃላይ የሲቪል ማህበራትን ማጠናከር፤ ሙስናን መከላከል፤ ማህበረሰቡን ታሳቢ ያደረገ እንቅስቃሴ ማድረግና ለአገር እድገት በጋራ መረባረብ ለውጥ እንደሚያመጣ የዘረፉ ሙያተኞች አስረድተዋል። ካልሆነ ግን ውጭ ውጥተን ለልመና እጃችንን መዘርጋት የግድ ሊሆን እንደሚችል አሳስበዋል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ጥቅምት 8/ 2015 ዓ.ም