ቤዛ እሸቱ
ምቀኛ ሸረኛውን ያዝልን አቦ
ሀገር አማን ይሁን
ወሎ አማን ይሁን
ኢትዮጵያ አማን ትሁን
ወታደሩ ሁሉ ይጠበቅልን
ገበሬ ከምርቱ ፤ዳኛ ከፍርድ ቤት ይሁን
ሀገር አማን ይሁን
እመቤቶቹም ደህና ይሁኑ ሁሉም ይጠበቅ
ይሄ ከወሎ አባወራ የማይጠፋ የዘወትር ምርቃት ነው፤ ምርቃቱ በሚደረግበት የቡና ሥርዓት ላይ ታላቅ ሲመርቅ የተቀሩት ‹‹አሜን›› እያሉ ምርቃቱን ይቀበላሉ። ፈጣሪ ምርቃቱን እንዲያደርሰውም ይለማመናሉ ።
ሁሌ የታሰበው አይሆንምና አምና በወሎ የከተማና የገጠር አካባቢዎች ላይ በአሸባሪው ሕወሓት ወረራ ተፈጸመ ።በዚህ ወረራም ሕይወታቸው ካለፈው፣ የአካል ጉዳት ከደረሰባቸውና የመኖሪያ መንደራቸውን ለቀው ከተሰደዱት፣ ለስነ ልቦና ቀውስ ከተዳረጉት ነዋሪዎች በተጨማሪ በርካታ የመሠረተ ልማቶች በቡድኑ ወድመዋል፤ ተዘርፈዋል ።
በወረራው የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶና አሻሽሎ ለመገንባት ብዙ ቢሊየን ብር የሚጠይቅ መሆኑ በተለያዩ ወቅቶች የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ ።ለእዚህ መልሶ ግንባታም ሕዝቡ ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪዎች ሲተላለፉ ቆይተዋል ።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴርም በአማራ ክልል በወረራው ከፍተኛ ውድመት የደረሰባቸውን ሰባት ከተሞች በመምረጥ በ18 ፕሮጀክቶች የመልሶ ግንባታ በማድረግ ባሳለፍነው ሳምንት አስመርቋል ።በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በወረራው በእጅጉ ተፈትነው የነበሩ የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች የደስታ ምርቃት አድርሰዋል። መልካም ነገር ይጋባልና በከተሞች አካባቢ የተጀመረው ሌት ተቀን የልማት ሥራን የመሥራት ባህል በወረራው ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች የወደመውን መልሶ በመገንባትም ተደግሟል ።
በደሴ በኮምቦልቻና በከሚሴ ከተሞች በተካሄዱት የፕሮጀክት የምረቃ ሥነ-ሥርዓቶች ላይ የተገኙት የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ እንደገለጹት፤ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ከምንም በላይ ከተሞች ላይ ትኩረት አድርጎ ከፍተኛ ውድመት አድርሷል። ከተሞች ውስጥ ደግሞ የግል መኖሪያ ቤቶችን ሳይሆን ለሕዝቡ ነገ ትልቅ ጥቅም የሚሰጡ የሕዝብ ተቋማትን፣ በተለይ ትምህርት ቤት፣ የጤና ተቋማትና ከፍተኛ የሥራ እድል መፍጠር የሚችሉ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ተቋማትን አውድሟል ።
ሚኒስትሯ ከአራት ወራት በፊት አካባቢውን በተመለከቱበት ወቅት በማኅበረሰቡ ዘንድ የነበረውን ቁዘማ አስታወሱ፤ በእያንዳንዱ ተቋም ውስጥ አንድ ወንበር እንኳን የማይገኝበት ኮምፒውተርና ዶክመንቶች በሙሉ ተቃጥለውና ወድመው ሕጻናት የሚማሩበት ወንበር ሳይቀር ወድሞ መመልከት ልብ እንደሚሰብር ገልጸዋል ።በዛ ቁጭት የወደሙትን መልሶ መጠገን ሳይሆን ከነበረው ከፍ ባለ ደረጃ ለመገንባት በመግባባት ከክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ጋር የተሻለ መገንባት እንችላለን በሚል ወኔ የመሠረት ድንጋይ መቀመጡን አስታወሰዋል።
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ በቁጭት የበለጠ መነሳት ነባሩን ለመጠገን ወይም ለማደስ ሳይሆን አዳዲስ እንዲኖሩ ማድረግ ይጠበቃል ።ወራሪውንም ኃይል መበቀል የሚቻለው በውጤት የሚለካ ተጨባጭ ሥራን በመሥራት ነው ። ‹‹ማሸነፋችንን የምናረጋግጠውና መበቀል የምንችለው ይህን በማድረግ ነው›› በሚል ስሜት የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት 150 ሚሊዮን ብር በመመደብ ወደ እንቅስቃሴ መገባቱን ሚኒስትሯ ይገልጻሉ ። የመሠረት ድንጋዩ ከተቀመጠ በኋላ እውነት በተባለው ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ወይ? የሚል ፍራቻ እንደነበራቸውም ያስታውሳሉ ።ኢትዮጵያውያን ሲነኩ የበለጠ እንደሚበረቱ ጠቅሰው፣ በዚህ መልሶ ግንባታ በኮንስትራክሽን ዘርፉ ከሚታወቀው ከስምምነቱ ውጪ ውልን በማራዘም ጊዜ ከመግዛት ተላቆ ለመጀመሪያ ጊዜ ውሉ አራት ወር ሆኖ በሦስት ወር የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ማየት መቻሉን ነው ሚኒስትሯ የጠቀሱት ።ይህም የፕሮጀክቱን ሥራ ሲከታተሉ የነበሩ አመራሮችንና ባለሙያዎችን የሚያስመሰግን መሆኑን ጠቁመዋል ።
ሚኒስትሯ መሠረተ ልማቱን ያፈረሱ አካላት መሠረተ ልማቶቹ መልሰው መገንባታቸውን ሲመለከቱ ሕዝቡ ምን ያህል በወኔ የተሞላና በተስፋ ወደፊት መገስገስ የሚችል ወኔ ያለው መሆኑን እንደሚያዩበት ተናግረዋል ።ካሁን በኋላ እናጠፋለን ብለው ቢያስቡ ሕዝቡ ከዚህ የተሻለ መሥራት እንደሚችል እንዲገነዘቡ እንደሚያደርጋቸው ጠቅሰው፣ እንዲያውም እነሱን መነካካት ማሳደግ ነው ብለው እንዲያስቡና ተስፋ እንዲቆርጡ የሚያደርጋቸው ይመስለኛል፤ አሁንም ከዚህ የተሻለ መሥራት እንችላለን የሚል ፊት እያየሁ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ›› ብለዋል ።
የአማራ ክልል የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢያዝን እንኳሆነ በበኩላቸው የጠላት ኃይል በክልላችን በተለይ በምስራቁ አካባቢ ሁሉን አቀፍ ውድመት አድርሷል ይላሉ ።‹‹ጠላት ሞራልንም የመግደል ተልኮ ይዞ ነው ወረራ የፈጸመብን ።›› ያሉት ኃላፊው፣ ጠላትን መመከት ከተቻለ በኋላ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በከተሞች ሴፍቲኔት ፕሮግራም በኩል 150 ሚሊዮን ብር በመመደብ የወደመውን በሙሉ የመተካት ሳይሆን የተወሰኑ ተቋማትን መልሶ የመገንባት ሥራ መከናወኑን አስታውቀዋል ።በዚህም በሚኒስቴሩ ድጋፍ በሰባት ከተሞች ማለትም በሰቆጣ፣ ላሊበላ፣ ወልዲያ፣ ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ከሚሴና ሸዋሮቢት የ18 መሠረተ ልማቶች ፕሮጀክቶች መልሶ ግንባታ ሥራ መካሄዱን ገልጸዋል ።
እሳቸው እንዳሉት፤ ስምንት 12 ክፍሎች ያላቸው ትምህርት ቤቶች፣ ሦስት ጤና ጣቢያዎች፣ ሰባት የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ተቋማት ።በሰቆጣ፣ ላሊበላ፣ ወልዲያ፣ ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ከሚሴና ሸዋሮቢት ከተሞች ላይ ግንባታቸው ተካሂዷል ።ፕሮጀክቶቹ ትልቅ ትምህርት የተወሰደባቸውና ለወደፊት መልሶ ግንባታ ሥራም መሠረት የተጣለባቸው ናቸው ። ለወደፊቱም ከዚህ ልምድ በመቅሰም የወደሙ ተቋሞችን መመለስና ጠላትን ማሳፈር የሚቻልባቸውን ሥራዎች ለመሥራት እያሰብን እንገኛለን ሲሉ አቶ ቢያዝን ጠቁመዋል ።
በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የከተማ አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ፈንታ ደጀን እንዳሉት፤ የመልሶ ግንባታው መነሻ በወረራው መሠረተ ልማቶች የወደሙባቸው አካባቢዎች ናቸው ።ሌሎች አካባቢዎች በተሳለጠ መንገድ ሥራቸውን እየሠሩ በእነዚህ አካባቢዎች በወራሪው ቡድን የደረሰው ውድመት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ሚዛን የሚያሳጣ፣ የድሆችን ተስፋ የሚያጨልምና የታዳጊ ህጻናትን የትምህርት እድል የሚነሳ በመሆኑ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ከድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር ፕሮጀክቶቹ ተገንብተው ለምረቃ እንዲበቁ አርጓል ።ሚኒስቴሩ በቀጣይም የተመረቁትን ፕሮጀክቶች አገልግሎት የሚከታተልና የሚደግፍ ሲሆን፣ ከተሞች ከደረሱበት የእድገት ደረጃ የበለጠ እንዲያድጉና ከገጠር ወደ ከተማ ያለውን ፍልሰት የሚሸከም አቅም እንዲኖራቸው ድጋፍ ይደረጋል ።
በክልሉ ሰባት የአንድ ማዕከል የአገልግሎት መስጫ ማእዕከላት ተገንብተዋል፤ የአማራ ክልል ሥራና ሥልጠና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አወቀ ዘመነ እንደሚሉት፤ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫዎቹ ሁሉንም አገልግሎት በአንድ ማዕከል ለመስጠት በማሰብ የተገነቡ ናቸው፤ በማዕከሉ በተለይ ለሥራ እድል ፈጠራ ትልቅ ትኩረት ይሰጣል ።
የሥራ እድል ፈጠራ የክልላችን ትልቅ ችግር ነው ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፣ በወረራው የደረሰው ጉዳት የሥራ አጥነቱንም እያስፋፋው መሆኑን ይጠቁማሉ ።ሥራ አጥነትን ለመፍታት የማዕከላቱ ሚና ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል ።
እንደ አቶ አወቀ ገለጻ፤ በአንድ ማዕከል ሥራ ፈላጊዎችን በመመዝገብ የግንዛቤ ፈጠራና የሥራ ሥልጠና የሚካሄድ ሲሆን፣ በማዕከሉ ሥራ ፈላጊዎች እንዲደራጁ ይደረጋል። ሥራ ፈላጊዎችን ከቀጣሪዎች ጋር የማገናኘት፣ የገበያ ትስስር፣ የንግድ ፈቃድ፣ የግብር ከፋይ መለያ፣ የብድር አቅርቦት፣ የሼድ አቅርቦትን ጨምሮ ሥራ ፈላጊዎች የሚያስፈልጋቸው አገልግሎት በሙሉ በማዕከሉ ውስጥ የሚያገኙ ይሆናል ።
የቀድሞዎቹ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫዎች የታሰበውን በሙሉ ከመከወን አንጻር ውስንነት ነበረባቸው የሚሉት አቶ አወቀ፣ አዲስ የተገነቡትን የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ሞዴል ለማድረግ መታቀዱን ገልጸዋል ። ለዚህም ማዕከሎቹ የታሰበውን ሥራ እንዲሠሩ ግብዓት ለማሟላት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እንደሚሠራ ይጠቁማሉ ።
በደሴ ከተማ አቅራቢያ በሚገኙት የገራዶ አንደኛና መካከለኛ ደረጃና የደረቅ ወይራ አጠቃላይ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተገነቡ የተማሪዎች መማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ መጽሐፍት (ላይብራሪ) እና የላብራቶሪ ምርቃ ላይ የተገኙት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ እንደገለጹት፤ ትውልድን የሚያንጽና ሀገር የሚገነባ ትምህርት ቤት ምቹና ንጽሕናው የተጠበቀ፣ ልጆች እንዲወዱት ደረጃውን የጠበቀ መሆን አለበት ።ሆኖም በርካታ ትምህርት ቤቶች በዚህ ደረጃ አይገኙም ።ስለሆነም ትምህርት ቤቶችን የመቀየር ቀሪ ሥራ መሠራት ይኖርበታል ።
እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ማብራሪያ፤ አሸባሪው ሕወሓት በፈጸመው ወረራ ንጹሓን ዜጎችን ገድሏል፣ አቁስሏል፣ አፈናቅሏል፤ ንብረት አውድሟል፤ ዘርፏል። ሀብትና ንብረት ከተዘረፈበት አካባቢ አንዱና ትልቁ የሚገኘው የደሴ ከተማና አካባቢው ሲሆን፣ የወደመው ንብረት መልሶ እንዲተካ ከፌደራል መንግሥት ጀምሮ የሚገኙ የተለያዩ አካላት የሚችሉትን አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ ።የክልሉ መንግሥትም ለአምስት ዓመት የሚቆይ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በማቋቋም ወረራና ጥቃት በደረሰባቸው አካባቢዎች ሁሉ ቢቻል ከነበረው በተሻለ መልሶ ለመገንባት እንቅስቃሴ ጀምሯል ።
በ90 ቀናት ውስጥ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በደሴና በአካባቢው ከተጎዱ ትምህርት ቤቶች በመምረጥ መማሪያ ክፍሎችን በአዲስ መንገድ በመገንባት ለመማር ማስተማሩ ሥራ ዝግጁ አድርገዋል ።
በእኛ ሀገር መጀመር ነው እንጂ በፍጥነት መጨረስ ገና ባህል አላደረግነውም፤ ፕሮጀክቱ ጀምሮ በፍጥነት ሥራን የማጠናቀቅ ማሳያ ነው ሲሉ ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል ።ወደፊት የሚካሄዱትን ግንባታዎችንም በዚህ መንገድ በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን የማድረጉን ባህል አጠናክረን እንሄዳለን ሲሉ ገልጸዋል ።
በደረቅ ወይራ አጠቃላይ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ረሂማ ይመር በትምህርት ቤቱ ምረቃ ላይ ለተገኙት አመራሮች ትምህርት ቤቱ መታደሱ ጥሩ መሆኑን ጠቅሳ፣ የሰባተኛና ስምንተኛ ክፍል መማሪያ ክፍሎችም እንዲታደሱና፣ ውሃና መብራት እንዲገባላቸው፣ መጸዳጃ ቤት እንዲሠራና የመማሪያ መጽሐፍትና የላብራቶሪ እቃዎች እንዲሟላ ጠይቃለች።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ደረጃውን የጠበቀ መጸዳጃ ቤት ለመገንባት ቃል ገብተዋል፤ የአካባቢው መስተዳድር ሚኒስቴሩ ለሠራው ትምህርት ቤት አስፈላጊው ቁሳቁስና የመማሪያ መጽሐፍት እንዲያሟሉ ውሃ እና መብራት እንዲያስገቡ አደራ ብለዋል። የከተማው ከንቲባም ለትምህርት ቤቱ ውሃና መብራት ለማስገባት በሂደት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
ነዋሪነታቸው በደሴ ዙሪያ ገራዶ ቀበሌ የሆኑት አርሶ አደር ሽባባው አለማየሁ ፤ በሀገራችን በአንድ እጅ ክላሽ በሌላው እጅ ዶማና ማጭድ ተይዞ ልማቱ ሳይጓደል ጠላቶችን እየተከላከሉ በአጭር ጊዜ ይህን የመሰለ ሐውልት በመሠራቱ መደሰታቸውን አስታውቀዋል ።ይሄ ትምህርት ቤት ለልጅ ልጆቻችን የሚተርፍ ሐውልት ነው ሲሉ ገልጸው፣ የተሠራውን ትምህርት ቤት የሰው ልጅ ማደጊያ ነው በማለት ደስታቸውን አመልክተዋል ።
በከሚሴ ከተማ የሚገኘው የሰኔ 29 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ሌሊሳ አመንቲ በከተማው በአሸባሪዎቹ ሕወሓትና ሸኔ የሽብር ቡድኖች የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት እየተሠራ መሆኑን በመግለጽ፤ እርሳቸው የሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት ሦስት የመማሪያ ሕንጻዎች እንደተገነቡለት ይናገራሉ ።ትምህርት ቤቱ በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት በመገንባቱና ለምርቃት በመብቃቱም ተደስተዋል ።
በትምህርት ቤቱ ከአራት ሺ በላይ ተማሪዎች እንደሚማሩ በማንሳት በአጭር ጊዜ ግንባታው ተጠናቆ ለመማር ማስተማሩ ዝግጁ መሆኑን ጠቅሰው፣ ግንባታው የመማሪያ ክፍል ጥበትን እንደሚቀርፍና የተሻለ ትውልድ ለመፍጠር ሚናው የጎላ መሆኑን ያስረዳሉ ።
ሌላው በትምህርት ቤቱ ለረዥም ዓመታት ያስተማሩት መምህር መሐመድ ፋንታው በበኩላቸው አሸባሪው ሕወሓት ከሚሴን በያዘ ወቅት የትምህርት ቤቱን እንጨቶችና ወንበሮች ለማገዶ መጠቀሙን ገልጸው፣ ትምህርት ቤቱ በተደረገለት ጥገና የአካባቢውን ችግር መፈታቱን ይናገራሉ ።
የአማራ ክልል የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢያዝን በክልሉ የሚገኙ 228 ከተሞች በአሸባሪው ሕወሓት ወረራ ጉዳት ደርሶባቸዋል ።በሰባት ከተሞች የተሠራውን አድንቀው፣ በርካታ ከተሞች ተመሳሳይ ግንባታን እንደሚፈልጉም ይጠቁማሉ ።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ፕሮጀክቶቹ አድንቀው በተቋሞቹ የሚሰጠው አገልግሎትና በዚህም የሚገኘው የሕዝብ እርካታ የመጨረሻው ውጤት ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበው፣ ለዚህም አመራሩና ባለሙያዎች ኅብረተሰቡን ዝቅ ብሎ በማገልገል መጠናከር እንዳለበት አስታውቀዋል ።ፕሮጀክቶቹ የየአካባቢው ማኅበረሰብ መሆናቸውንም ተናግረው፣ኅብረተሰቡ ፕሮጀክቶቹን በቅርበት እንዲከታተልና እንዲደግፍም ጠይቀዋል ።
አመራር ከሕዝብ፤ ሕዝብ ከአመራር ጋር ከሆነ የማይፈታ ችግር የለም ።የሕዝብ ጥያቄዎች ይቀጥላሉ፤ ዛሬ ይሄን ስለሠራን ጥያቄዎችን በሙሉ መልሰናል ማለት አንችልም ያሉት ሚኒስትሯ፤ ይሄ ሥራ ግን እንደ ስፕሪንግ ወደፊት የሚያስፈነጥረን ነው ብለን መውሰድ እንችላለን ብለዋል ።በአንድ እጃችን የአካባቢውን ጸጥታና የኢትዮጵያን ሕልውና እያስጠበቅን በሌላ እጃችን የልማት ሥራን በመሥራት አዲስ ምዕራፍ የጀመርን መሆኑን በመገንዘብ መቀጠል ይገባናል ሲሉም አስገንዝበዋል ።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5/ 2015 ዓ.ም