ባለፈው ዓመት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከተካሄደው ጦርነት ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ክስተቶች ለኢንቨስትመቱ ዘርፍ መሰናክል እንደነበሩ በተደጋጋሚ ተገልጿል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንም በ2014 በጀት ዓመት የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትንና የተገኙ ውጤቶችን አስመልክቶ ይፋ ባደረገው መረጃ፣ ከጦርነቱ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የኢትዮጵያ ከአጎዋ መታገድ እና የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጫና በበጀት ዓመቱ ካጋጠሙ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ተግዳሮቶች መካከል እንደሚጠቀሱ አመልክቷል። በበጀት ዓመቱ እነዚህ ተግዳሮች የነበሩ ቢሆንም፣ የተሻለ አፈፃፀም የተመዘገበበት እንደሆነም ኮሚሽኑ አያይዞ አስታውቋል።
እንደ ኮሚሽኑ መረጃ፣ ኮሚሽኑ በበጀት ዓመቱ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን (Foreign Direct Investment – FDI) ለመሳብ የተለያዩ የፕሮሞሽን ስራዎችን ሰርቷል፤ በተለያዩ የዓለም ሀገራት በሰራቸው የሀገሪቱን የኢንቨስትመንት አማራጮችና ዕድሎች የማስተዋወቅ ስራ ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ኤጀንሲዎች ማኅበር (World Association of Investment Promotion Agencies – WAIPA) እና የዓለም ባንክ ግሩፕ (World Bank Group) በጥምረት የሚያዘጋጁትን ዓለም አቀፉን የ ‹‹Strengthening IPA Advocacy Services’ Gold Award 2021›› ሽልማት አግኝቷል።
በበጀት አመቱ ከሦስት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በመሳብ የዕቅዱን 64 ነጥብ አራት በመቶ ማሳካት የተቻለ ሲሆን፣ በሀገሪቱ በነበረው አለመረጋጋት፣ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን እና የኮቪድ-19 ስርጭት በአፈፃፀሙ ላይ ተፅዕኖ ማሳደራቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያሳያል።
በ2014 በጀት ዓመት በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ለመሰማራት ፍላጎት አሳይተው መስፈርቶቹን ላሟሉ 168 ባለሀብቶች አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ እንዲወስዱ ተደርጓል፤ ከእነዚህም መካከል 100 በማኑፋክቸሪንግ (77 የውጭ እና 23 የሀገር ውስጥ)፣ 62 በአገልግሎት (59 የውጭ እና 3 የሀገር ውስጥ) እና ስድስት በግብርና (የውጭ) ዘርፎች ለመሰማራት ያቀዱ ናቸው።
እንደ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ፣ በ2014 በጀት ዓመቱ ለፕሮጀክቶች በተደረገው ድጋፍ ከኢንዱስትሪ ፓርክ ውጪ እና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ባሉ የኢንቨስትመንት ተግባራት ለ77 ሺ122 ዜጎች የሥራ እድል ተፈጥሯል። 374 ፕሮጀክቶችን (304 ከፓርክ ውጪ እና 70 በፓርክ ውስጥ) ወደ ትግበራ (ማምረት እና አገልግሎት) ለማሸጋገር ታቅዶ 284 ፕሮጀክቶችን (234 ከፓርክ ውጪ እና 50 በፓርክ ውስጥ) ወደ ትግበራ (ማምረት እና አገልግሎት) ማሸጋገር ተችሏል።
በበጀት ዓመቱ አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከወሰዱ የባለሀብቶች ስብጥር መመልከት እንደሚቻለው ፈቃድ ከወሰዱት ባለሀብቶች መካከል የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች 26 ብቻ ናቸው። ይህም የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚኖራቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ አመላካች ነው።
በአሁኑ ወቅት በምጣኔ ሀብታቸውና በፖለቲካ ተፅዕኗቸው የዓለም ኃያላን የሆኑት ሀገራት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶቻቸውን በመደገፍ ረገድ በርካታ ተግባራትን አከናውነዋል። እነዚህ ሀገራት ባለሀብቶቻቸውን በማገዝና በመጠበቅ የሰሩት ስራ የአምራችነት አቅማቸውን አሳድጎ የምጣኔ ሀብት እድገታቸው ዘላቂ እንዲሆን አስችሏቸዋል። ለአሁኑ የምጣኔ ሀብት ኃያልነታቸው መሰረት የሆናቸው ከውጭ ጥገኛነት ያላቀቃቸው የውስጥ አምራችነት አቅማቸው እንደሆነ ይታወቃል።
የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን የመደገፍ ጥረት በብዙ መልኮች ሊገለፅ ይችላል። የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን የሚያበረታቱ ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲዎችን በመቅረፅ፣ ፋይናንስን ጨምሮ ግብዓቶችን በማቅረብ፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦትን በማሟላት እንዲሁም ቢሮክራሲያዊ የአሰራር ውጣ ውረዶችን በማቃለል ለባለሀብቶቹ ድጋፍ ማድረግ ይቻላል።
የምጣኔ ሀብት ሳይንስና የፐብሊክ ፖሊሲ ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ፣ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ያላቸው ተሳትፎ እንዲያድግ መንግሥት ፋይናንስን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎችን ማድረግ እንዳለበት ይናገራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፣ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን አቅም ለማሳደግ የሚያስችል የተደራጀ የመንግሥት መዋቅር መገንባት ያስፈልጋል።
‹‹የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች አቅማቸው ሊያድግ የሚችለው ካፒታል ይዘው ከሚመጡ የውጭ ባለሀብቶች ጋር ሲሰሩ ነው። የሀገር ውስጥ ባንኮች፣ በተለይም የግል ባንኮች፣ ለባለአክሲዮኖቻቸው ጥቅም ከመደራረብና ለሰራተኞቻቸው በየዓመቱ ደመወዝ እየጨመሩ ከመዝለቅ ተሻግረው አሰራራቸውን ማዘመንና ለልማት ፕሮጀክቶች የሚያቀርቡትን ብድር ማሳደግ አለባቸው›› ይላሉ።
በበጀት ዓመቱ በግብርና ዘርፍ ፈቃድ የወሰዱት ሁሉም ባለሀብቶች የውጭ ባለሀብቶች ናቸው። ግብርና የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ዋነኛ መሰረት ሆኖ ሳለ በዘርፉ የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱት ሁሉም ባለሀብቶች የውጭ ባለሀብቶች መሆናቸው ዘርፉንና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን በማስተሳሰር ረገድ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባል።
‹‹የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን በስፋት ማሳተፍ የሚችለው ትልቁ ሀብታችን እርሻ ነው›› የሚሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፣ በእርሻ ኢንቨስትመንት ላይ ለመሰማራት ያሉት መሰናክሎች ብዙ እንደሆኑ ይገልፃሉ። ባለሀብቶቹ መሬት ተረክበው ስራ ከጀመሩ በኋላ ከወሰን ማስከበርና ከመሬት ባለቤትነት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎች በኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ ብዙ እንቅፋቶችን ሲፈጥሩ እንደሚስተዋሉ ያስረዳሉ።
‹‹በእርሻ ኢንቨስትመንት ለመሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶች በየመስሪያ ቤቱ ብዙ መጉላላትና ውጣ ውረድ ያጋጥማቸዋል። ስለዚህ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በግብርናው ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ለእነዚህ ችግሮች መፍትሄ መስጠት ይገባል›› ይላሉ። ከዚህ በተጨማሪም ‹‹በግብርና ዘርፍ ላይ ለመሰማራት የግብርና እውቀት ያስፈልጋል። የግብርና ኢንቨስትመንት የባለቤቱን እውቀትና ክትትል ይፈልጋል›› በማለት የግብርና እውቀት ለዘርፉ ኢንቨስትመንት ውጤታማነት ወሳኝ እንደሆነ ያስረዳሉ።
በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህርና በ‹‹ፍሮንቲየርአይ (Frontieri)›› ጥናትና አማካሪ ድርጅት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሞላ አለማየሁ ከዚህ ቀደም ለ ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ በሰጡት ማብራሪያ፤ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍ ጥያቄ ሊነሳበት የማይገባ ጉዳይ እንደሆነና ተጨባጭ ምጣኔ ሀብታዊ ለውጥ እንደሚያመጣ ተናግረዋል። ባለሀብቶቹ ምርቶችንና አገልግሎቶችን በማቅረብ ከሚኖራቸው ሚና ባሻገር ለዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር፣ ገቢ ምርቶችን በመተካት እና የወጪ ንግድን በመጨመር ትልቅ አስተዋፅኦ ስለሚኖራቸው ይህን ሚናቸውን የበለጠ እንዲያሳድጉ በመንግሥት ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ገልጸዋል።
እንደ ክተር ሞላ ገለፃ፣ በተለይ ኢትዮጵያ በስራ አጥነትና በዋጋ ንረት እየተፈተነች ባለችበት በአሁኑ ወቅት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍ እጅግ አስፈላጊ ተግባር ነው። የመንግሥት ድጋፍ ምጣኔ ሀብቱን በማነቃቃት፣ የሥራ እድል በመፍጠር፣ የገቢ ንግድ እቃዎችን በመተካት፣ የወጪ ንግድን በማሳደግ ጥቅል ሀገራዊ ምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴው ዘርፈ ብዙ ለውጥ እንዲኖረው ያደርጋል።
የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ከሚጋጥሟቸው ችግሮች መካከል የግብዓቶች (መሰረተ ልማቶች) አለመሟላት፣ የፋይናንስ አቅርቦት ችግር እና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ዋናዎቹ እንደሆኑ ጠቁመው፤ መንግሥት የአጭር ጊዜ መፍትሄዎችን ጨምሮ የባለሀብቶቹን ችግሮች ለማቃለል የሚረዱ የፖሊሲና የመዋቅር እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚኖርበትና ለባለሀብቶቹ የሚያደርገውን ድጋፍ በየጊዜው መገምገምና ማሻሻል እንዳለበትም ገልጸዋል።
የሀር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍ ሀገር በራሷ አምራቾች ላይ እንድትተማመን ያስችላል። ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም ፖለቲካ ምክንያት በሚፈጠሩ ችግሮች ከሚከሰት አደጋ ለመዳንም ይረዳል። በዚህ ረገድ ዶክተር ሞላ ‹‹የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በፋይናንስና በቴክኖሎጂ አቅም ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማድረግ ምጣኔ ሀብታዊ ስብራትና ክፍተት እንዳይፈጠር ለማድረግ ያግዛል።›› ሲሉ ይጠቁማሉ።
ዶክተር ሞላ ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉት የውጭ ኩባንያዎች በሀገር ውስጥ የሚቆዩት የሀገር ውስጥ ፖለቲካው እስከተመቻቸው ድረስ ነው ሲሉም ይገልጻሉ። እንደ አሳቸው ገለጻ፤ ፖለቲካው ሳይመቻቸው ቀርቶ ኩባንያዎቹ ከሀገር ቢወጡ ሀገሪቱ በርካታ ዓመታት እንደገና ወደኋላ እንድትመለስ የሚያደርግ አደጋ ይከሰታል። ስለሆነም ይህን ስጋት ለማስወገድ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን በመደገፍ አቅማቸውን እንዲጎለብቱ ማድረግ ያስፈልጋል።
‹‹በምጣኔ ሀብታቸው የበለፀጉት የዓለም ሀገራት የሀገር ውስጥ ለባለሀብቶቻቸው ቀደም ባሉት ጊዜያት ብቻም ሳይሆን አሁንም ከፍተኛ ድጋፍና ጥበቃ ያደርጉላቸዋል። ሀገራቱ በፋይናንስ አቅርቦትም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ለባለሀብቶቻቸው የተለየ የድጋፍ መርሃ ግብር አላቸው። የበለጸጉት ሀገራት ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶቻቸው የሚያደርጉት ድጋፍ፣ ገና በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ከሚያደርጉት ድጋፍ ቢበልጥ እንጂ አያንስም›› ሲሉ ያብራራሉ።
የኢትዮጵያ ከአፍሪካ የእድገትና የንግድ ተጠቃሚነት መርሃ ግብር (አጎዋ) መታገድ፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የነበረው ጦርነት፣ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ጫና እና የመሰረተ ልማት አቅርቦት በሚፈለገው ደረጃ አለመሟላት በበጀት ዓመቱ ያጋጠሙ የኢንቨስትመንት ተግዳሮቶች እንደሆኑ ኮሚሽኑ ገልጿል።
‹‹አጎዋ›› አሜሪካ ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ ሀገራት የሰጠችው ነፃ የንግድ እድል ሲሆን፤ ኢትዮጵያም የዚህ እድል ተጠቃሚ ሆና ቆይታለች። ይሁን እንጂ ባለፈው ዓመት የአሜሪካ መንግሥት ባሳደረው ፖለቲካዊ ጫና ምክንያት ኢትዮጵያ ከዚህ ነፃ የንግድ እድል ተጠቃሚነቷ ታግዳለች። ከ2014 ዓ.ም የኢንቨስትመንት ዘርፍ ተግዳሮቶች መካከል አንዱ ሆኖ የተጠቀሰውም ይኸው የኢትዮጵያ ከ‹‹አጎዋ›› ተጠቃሚነቷ የመታገዷ ጉዳይ ነው።
‹‹ኢትዮጵያ ከ‹አጎዋ› መታገዷ ትልቅ በደል አድርሶብናል›› የሚሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ ‹‹መርሃ ግብሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን የሥራ እድል እንዲሁም ሙያዊ ልምድና እውቀት ያገኙበት እድል ነበር። እነዚህ ኢትዮጵያውያን የሚሰሩባቸው ድርጅቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ገብተው የተሰማሩ ኩባንያዎች ናቸው። እንደ ቻይናና ቬትናም ያሉ ሀገራት ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት እድገት ያስመዘገቡት ደግሞ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ስራ ምክንያት ነው›› በማለት ‹‹አጎዋ›› ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ጠቃሚ መርሃ ግብር እንደነበር ማሳያዎችን በመጥቀስ ያስረዳሉ።
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በ ‹አጎዋ› እድል ከቀረጥ ነፃ ወደ አሜሪካ የሚገቡ ምርቶች ብዙ ቢሆኑም ኢትዮጵያ በይበልጥ ያተኮረችው በጨርቃ ጨርቅ ውጤቶች መሆኑንና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ግን የተሻለ እየተጠቀሙበት እንደሆነ አስታውሰው፤ የ‹‹አጎዋን›› ተጠቃሚነት እድል መልሶ ለማግኘት ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ ሌሎች አማራጮችን መመልከትም እንደሚያስፈልግም ይናገራሉ።
‹‹አማራጭ መፍትሄዎችንና እድሎችን መፈለግ እንጂ አሜሪካ ላይ ተጣብቀን መኖር አይገባንም። የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠናን (African Continental Free Trade Area – AfCFTA) ስለመጠቀም ማሰብ ይገባል። ምጣኔ ሀብቱን ለማሻሻል እየተወሰዱ ያሉ፣ እንደካፒታል ገበያ እና የባንኩን ዘርፍ ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት የማድረግ፣ እርምጃዎችን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ይላሉ።
ባለፈው የበጀት ዓመት የኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ብዙ ፈተናዎች አጋጥመውታል። ሀገሪቱ በእነዚህ ፈተናዎች ውስጥ ሆናም ፈተናን እንደ መውጫ በመጠቀም ውጤት ያስገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በመቀመር መስራት ያስፈልጋል። በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በባህሪው ለግጭት፣ ለጦርነትና ለመሳሰሉት ስስ በሆነው የኢንቨስትመንት ዘርፍ ይህን ያህል መራመድ መቻሉ ሁኔታዎች በሚቻቹ ብዙ ርቀት መጓዝ እንደሚቻል ያመለክታል። አሁን የተያዘውን የኢትዮጵያ ታምርት እንቅስቃሴና ሌሎች ከዓለም አቀፍና የመሳሰሉት ጫናዎች የመውጫ መንገዶች በመጠቀም የኢንቨስትመንት ዘርፉን ችግሮች በመፍታት ሀገራዊ የማምረት አቅምን ማሳደግና ምጣኔ ሀብታዊ እድገትን ዘላቂና አስተማማኝ ማድረግ ይገባል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን መስከረም 26/2015