የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ኢትዮጵያን አስመልክቶ ያወጣው ‹‹ሪፖርት›› ለሕወሓት የሽብር ቡድን በግልጽ ያደላ መሆኑን በመግለጽ የኢትዮጵያ መንግስት በ‹‹ሪፖርቱ›› ከማዘኑም በተጨማሪ ለሰብዓዊ መብት መከበር በመቆርቆር የወጣ ባለመሆኑ ውድቅ ማድረጉን አስታውቋል።
በወቅቱ ኮሚሽኑ ይፋ ያደረገው ‹‹ሪፖርት›› ግዴለሽነቱን የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሶ ኢትዮጵያ ለሰላም ያላትን ቁርጠኝነት ከግምት ውስጥም ያላስገባ መሆኑን አመላክቷል። በተለይም ኮሚሽኑ በአሰራሩ በዋናነት ያነገበው የፖለቲካን ተልዕኮ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ላይ ፖለቲካዊ ጫና ለማሳደር ሲልም መንቀሳቀሱን በመግለጫው ጠቅሷል።
የመጀመሪያ ግኝት የሆነው የኮሚሽኑ ‹‹ሪፖርት ›› ይፋ የተደረገው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት፣ በኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት የተፈጸሙ ጥሰቶች አጣራለሁ በሚለው የሰብዓዊ መብቶች የባለሙያዎች ቡድን ነው።
የወጣው ‹‹ ሪፖርቱ›› በትክክል ለሰብዓዊ መብት በመቆርቆር የሰብዓዊ መብት ማስከበርን ያለመ ወይንስ መርዙን በማር ሸፍኖ የቀረበ ነው ሲል ያነጋገራቸው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ዶክተር ፍቃዱ መንግስቱ፣ በመጀመሪያውኑ ኮሚሽኑ ያወጣው ሪፖርት በትክክል የተሟላ ባለመሆኑ ትክክለኛ ሪፖርት ነው ብሎ መወሰድ የሚቸግር መሆኑን ይናገራሉ። እንዲህም ሲባል አንደኛ የሪፖርቱ የአሰራር ዘዴ ትክክለኛ አካሄድን የተከተለ አይደለም።
ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ እርሳቸው ይፋ የተደረገውን ጥናት እንዳዩት ከሆነ በመጀመሪያ ሪፖርቱ ሲዘጋጅ ችግሩ የተከሰተባቸውን አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ወይም ደግሞ በተቻለው መጠን ሸፍኗል ወይ የሚል ጥያቄ እንዲያነሱ እንዳስገደዳቸው ያመለክታሉ። ከዚህ አንጻር ችግሩ የተከሰተባቸውን አካባቢዎች በተለይ አማራ እና አፋር ሆነው ሳለ በአግባቡ አለመዳሰሳቸውን ያስረዳሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ለሰብዓዊ መብት በመቆርቆር የሚሰራው ስራ ለሁሉም እኩልነትን የሚያሳይ መሆን ይጠበቅበታል። ኮሚሽኑ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ላይ ግን ከዚህ አኳያ በተለይ በትግራይ ክልል ዳር እስከዳር የዳሰሰ ሲሆን፣ ችግሩ ገዝፏል ሲልም ያነሳል። በሪፖርቱ ላይ የታዘቡት እውነታ ግን ኮሚሽኑ የትግራይ ክልልን ያህል የሌሎቹንም አካባቢዎች ያልሸፈነ መሆኑን ነው።
ዶክተር ፍቃዱ፣ ኮሚሽኑ ያወጣውን ሪፖርቱ ካስተዋሉ በኋላ በሁለተኛ ደረጃ ጥያቄ የፈጠረባቸው ነገር ችግሩ የደረሰባቸውን ሰዎች አጥኚዎቹ ቡድኖች ያገኙት እንዴት ነው የሚለው ነው። ተጎጂዎቹን ያናገሯቸውስ በምን አይነት ሁኔታ ነው ሲሉም ያክላሉ። መረጃው የተገኘው በስልክ ብቻ ነው ወይ የሚለው ግልጽ መሆን እንዳለበትም ነው የሚናገሩት። እርሳቸው፣ ችግር የደረሰባቸውን ሰዎች በተቻለ መጠን በአካል ሊያገኟቸው ይገባል የሚል አስተያየት አላቸው። ከዚህ የተነሳ ሪፖርቱ ትክክለኛውን መረጃ ይዞ ተጠናቅሮ የቀረበ ነው ለማለት እንደሚቸገሩ ያስረዳሉ።
ሌላው ሪፖርቱ ለሰብዓዊ መብት በመቆርቆር የተሰራ አይደለም ሲሉ የጠቀሱት ደግሞ፤ ራሳቸው አጥኚዎቹ የችግሩ ተጋላጭ ናቸው ብለው የወሰዷቸውን ሰዎች 185 አካባቢ ነው ብለዋል። ነገር ግን አሁን ካለው የመሬት አቀማመጥ ከችግሩ ግዝፈት እና ስፋት አንጻር ወስደናል ባሉት ናሙና ብቻ ድምዳሜ ላይ መደረሱ ትክክል መስሎ አልታየኝም ብለዋል። ከዚህ አንጻር ሪፖርቱ በትክክል የተሰራ ነው አሊያም የችግሩን ሙሉ ስዕል የሚያሳይ ሪፖርት ነው ብሎ ለመቀበል አልደፈሩም።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አማካሪ አቶ ኢብሳ ነጋዎ በበኩላቸው፤ የዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የባለሙያዎች ቡድን በኢትዮጵያ ላይ አካሂጄዋለሁ ያለው ‹‹ሪፖርት›› አግባብነት የሌለው መሆኑን ይናገራሉ። በዚህ አካል ተጠንቶ የቀረበው ሪፖርት አነሳሱ ራሱ የፖለቲካ ቅኝት ያለው ነው። በመጀመሪያ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የሚያሳይ ጥናት ለመሆኑ ሕጋዊና ሙያዊ ሊሆን ይገባው ነበር፤ ነገር ግን ይህን ሳይንሳዊ አካሄድ የተከተለ አይደለም ይሞግታሉ።
በተለይ የሪፖርቱ ዓላማ በእርዳታ ብሎም በሰብአዊ መብት ስም የሚደረግ አካሄድና በመንግስት ላይ ጫና ለማሳደር የታሰበ ሴራ ነው። በቁጥር አነስተኛ የሆኑ አካላት በስልክ አነጋግሮ ብቻ ሪፖርት ይፋ ማድረግ በእርግጥም የሚያስገርም ነው ብለዋል። ሌላው በአፋር እና በአማራ ክልል የተገደሉ ንጹኃን ዜጎች፣ የተደፈሩ ሴቶች፣ የተቃጠሉ መሰረት ልማቶች ከግምት ውስጥ አልገቡም፤ ሌላው ቀርቶ በጋሊኮማ ብቻ የደረሰው አሰቃቂ የዘር ማጥፋት ግፍ በቂ ነበር። ሆኖም ግን በዚህ በኩል ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ማንሳት አልተፈለገም። ይህም ሆን ተብሎ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫና ለማሳደር ሲባል የተደረገ እንጂ በእርግጥ ኮሚሽኑ ለሰብዓዊ መብት ተቆርቁሮ ያጠናው እንዳልሆነ ነው የሚገባኝ። በመሆኑም ኮሚሽኑ አካሄድኩት ያለው ምርመራ ትክክለኛውን መንገድ የተከተለ ሳይሆን አድሏዊ ነው ለማለት ያስገድዳል።
በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አደረጃጀት አባላት ጥምረት፣ ለተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነርና ለተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ምክር ቤት አባል አገራት በጻፈው ደብዳቤ፤ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ጉዳይን እንዲመረምር የተሰየመው ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ቡድን የተቋቋመበት እሳቤ በተሳሳቱ መነሻዎች ላይ የተመሰረተ ነው ማለቱን ከጥምረቱ ድረገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። የተቋቋመውም ቡድን ሊፈርስ እንደሚገባም ነው ጥምረቱ በጻፈው ደብዳቤ የጠየቀው። ለዚህም በምክንያትነት ያስቀመጠው በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶችን ጉዳይ እንዲመረምር የተሰየመው ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ቡድን የፖለቲካ ዓላማ ያለውና ከደረጃ በታች የሆነ፣ የጉዳዩን አሳሳቢነት የማይመጥንና አንድን ወገን ብቻ ለይቶ ማጥቃትን ዓላማ ያደረገ አደገኛ ሪፖርት ይዞ መውጣቱ ነው። አባል አገራት ይህን የተሳሳተ ሰነድ በፊርማቸው ከማጽደቅ እንዲቆጠቡም ጥምረቱ ጠይቋል። ይልቁኑ አባል አገራቱ በኢትዮጵያ ለተጎጂዎች ዘላቂ ፍትሕ ለማስገኘትና ጥበቃ ለማድረግ የተጀመረውን ሂደት ሊደግፉ ይገባል ብሏል።
እንዲያውም አባል አገራቱ፣ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶችን ጉዳይ እንዲመረምር የተሰየመው የባለሙያዎች ቡድን ያቀረበው ሪፖርት ለአንድ ወገን ያደላና ፖለቲካዊ ዓላማን ያነገበ በመሆኑ ያቀረበውን ሪፖርት ውድቅ እንዲያደርጉና ኮሚሽኑንም እንዲያፈርሱ ጥምረቱ በጻፈው ደብዳቤ ጠይቋል። በተጨማሪም አባል አገራቱ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቅርበት በመስራትና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትን በማክበር የፍትሕ ስርዓቱ አቅም እንዲገነባ እንዲሁም በአማራ፣ አፋርና በትግራይ ክልሎች ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኝነት እንዲመረምሩ የኢትዮጵያን ፍትሕ አካላት እንዲያግዙ ጥያቄውን አቅርቧል።
የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ እንዳለ ንጉሴ በበኩላቸው፤ ሪፖርቱን ያዘጋጀው ኮሚቴው ከመጀመሪያው ጀምሮ በራሱ ሕገ ወጥ ነው ይላሉ። አካሄዳቸው በኢትዮጵያ ላይ ግልጽ የሆነ ጫና ለመፍጠር የተደረገ መሆኑን የሚያሳይ እንጂ ለሰብዓዊ መብት በመቆርቆር የተጠና አለመሆኑን ይናገራሉ። ሪፖርቱ በዚህ ልክ በሐሰት ድርሰት የተደራጀ ከመሆኑም በተጨማሪ እየተሰራ ያለውም በባለሙያዎች ሆን ተብሎ እንደሆነ ያመላክታሉ። ነገር ግን አሳዛኙ ነገር ሙያዊ አካሄድን የተከተለ አለመሆኑ ብሎም ግዴታውንም ያልተወጣ ጥናት መሆኑ ነው ሲሉ ያስረዳሉ።
ስለዚህ ይላሉ አቶ እንዳለ፣ ሪፖርቱ እንደሪፖርት ሊቆጠር አይችልም። ምክንያቱም አንደኛ ሳይንሳዊ ዘዴን አልተከተለም፤ ሁለተኛ ደግሞ መሳተፍ የሚገባቸውን ባለድርሻ አካላት አልተሳተፉበትም። ስለሆነም በሶስት ሰው የተሰራ ሪፖርት የ120 ሚሊዮን ሕዝብ አገር የሆነችውን ኢትዮጵያ አይመጥንም፤ በአፍሪካ ትልቋን ኢትዮጵያ፣ በጥቅል ነገሯ ስትወሰድ ደግሞ በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነችውን አገር እንዲሁም ጂኦፖለቲካዊው ድርሻዋ ከፍ ያለችውን አገር በእነዚህ ሶስት ሰዎች መወከል አይገባትም።
እርሳቸው እንዳሉት፤ የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩ.ኤስ.ኤ.አይ.ዲ) እርዳታን ለመላ ኢትዮጵያ ከመስጠት ይልቅ እየመረጠ የሚሰጠው ለአሸባሪው ቡድን ነው። ይህ ማለት ጥፋት ለሚፈጽም ቡድን መስጠት ማለት ነው። ለስንት ዓመታት የሚመጣለት እርዳታ እየሸጠ መሳሪያ ሲገዛበት የነበረው በተመቻቸለት መንገድ ነው። ይህ አሸባሪው ቡድን ሲዘርፍ አይናቸው ያያል። ነዳጁን፣ ዘይቱን፣ ስንዴውን ከነመኪናው ጭምር ሲዘርፍ አንዱ ላይ እንኳን ስለዘራፊነቱ አላነሱም። እንዲያውም ከምስረታው ጀምሮ እርዳታን፣ ረሃብን እንደጦርነት የተጠቀመው ቡድን ቢኖር ሕወሓት ነው ሲሉ ይናገራሉ።
ዶክተር ፍቃዱ በበኩላቸው፤ ሪፖርቱ ማካተት የተገባውን ሁሉ አካትቶ ካለመሰራቱ በተጨማሪ ዋና ዓላማው ችግርን ወደ አንድ ወገን እንዲያመዝን አድርጎ ለማሳየት መጣሩ ነው፤ ይህ ደግሞ ትክክል አይደለም። ምክያቱም የሪፖርቱ ዋና ዓላማ ለሰብዓዊ መብት መቆርቆርን የሚያሳይ ሳይሆን በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ፖለቲካዊ ተጽዕኖ ለማሳደር ነው ብለዋል።
የኮሚሽኑ ሪፖርት በአንድ ወገን ላይ ተጽዕኖ ከማሳደር ውጪ የችግሩን መሰረት በመዳሰስ እና መካተት የተገባቸው ተካትተው ባለመገኘታቸው የጥናቱን አካሄድ ሙሉ የሚያደርገው ሆኖ አላገኙትም። ጥናቱ የተሟላ ካለመሆኑም በተጨማሪ አንዱን የመደገፍ ሌላውን የማንኳሰስ አካሄድን የተከተለ ነው። ስለዚህም የሪፖርቱ አካሄድ በእርግጥም ለሰብዓዊ መብት በመቆርቆር የታሰበ አይደለም፤ እንደዛ ቢሆን ኖሮ ትክክለኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሳይንሳዊ አጠናን የተከተለ አካሄድ ይዞ ይነሳ ነበር። ነገር ግን ወደ ችግሩ ተጠግተው ግራና ቀኙን በእኩል ማየት እየተጠበቀባቸው ያንን ግን አላደረጉም። መልካም ይሆን የነበረው ችግሩ በተከሰተባቸው አካባቢዎች በመገኘት በአግባቡ መረዳት ቢችሉ ነበር። ዝም ብሎ ሪፖርት ነው በሚል ብቻ አንዱን አንስቶ ሌላውን ለመጣል የታለመ ከሆነ ግን አግባብ አይደለም። በመሆኑም ይህን ሪፖርት በንጽጽር የተሰራ ሪፖርት ነው ብለው አይወስዱም።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ አሸባሪው ሕወሓት ገና አንድ ብሎ ሲጀምር የሰሜን እዝን ከጀርባው በመውጋት እንደሆነ ይታወሳል። የመከላከያ ሰራዊትን በማጥቃት የጀመረው ጥቃት አንድ ሁለት እያለ መንግስት የዘረጋለትን የሰላም እጅ አልቀበልም በማለት ወደሶስተኛው ጦርነት አሻፈረኝ ብሎ መግባቱም ይታወቃል።በዚህም በአማራና በአፋር ክልል የፈጸማቸው ግፎች በርካታ ሲሆን፣ በተለይ ህጻናትንና በእድሜ የገፉትን እናቶችን ከመድፈር እስከማዋረድና መሸማቀቅ መድረሱ ይታወሳል። የመሰረተ ልማቶችን በተለይም የትምህርት እና የጤና ተቋማትን ከማፍረስ እስከማቃጠል የተሳተፈበት ተግባሩ እንደሆነም እሙን ነው። ይህ ሁሉ በአሸባሪው ሕወሓት አማካይነት በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ነው።
የሽብር ቡድኑ የኢትዮጵያ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት አደጋ ላይ ለመጣል ዳግም ጦርነት መክፈቱ፣ የሰብአዊ እርዳታ ተሽከርካሪዎችን ለጦርነት መጠቀሙ እና ለሰብአዊ እርዳታ የተዘጋጀ ነዳጅ ላይ ዝርፊያ መፈጸሙ በተደጋጋሚ መነገሩ ይታወሳል። ይሁንና ዓለም አቀፍ ተቋማት በሽብር ቡድኑ የተፈጸሙና ዓለም አቀፍ ህጎችን የጣሱ ወንጀሎችን ማጣራት ሲገባቸው ቸል መባሉ ሳያንስ ይባስ ብሎ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ለሕወሓት የሽብር ቡድን በግልጽ ያደላ ሪፖርት ይፋ ማድረጉ የኢትዮጵያን መንግስት ማሳዘኑ ይታወቃል።
እንደ አቶ እንዳለ አባባል፤ ኢትዮጵያውያን ለተሳሳተ ፕሮፓጋንዳ እጅ መስጠት የለባቸውም። ለእንዲህ አይነቱም ውዥንብር ቦታ መስጠት አያስፈልግም። ነገር ግን ሁሉም ዜጎች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የረከሰ ሪፖርት ስለመሆኑ መግለጽ ይጠበቅባቸዋል። ከወትሮ በተሻለ የበለጠ አንድነትን በማጠናከር እንዲህ አይነቱን ተራ ትርክትን መከላከል መቻል አስፈላጊ ነው። በውጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ተገቢነት የሌለው ሪፖርት ከመሆኑም በላይ የረከሰ ሪፖርት መሆኑን ሊያስገነዝቡ፤ ተገቢም አለመሆኑን ሊያሳውቁ ይገባቸዋል። በአሁኑ ወቅት በአማራው፣ በአፋሩ የደረሰውንና እየደረሰ ያለውን ጉዳት ማስረዳትም ይጠበቃል።
በኮሚሽኑ አማካይነት ይፋ የተደረገው የሰብአዊ መብት ‹‹ሪፖርት›› ለሰብአዊ መብት መከበር በመቆርቆር የተካሄደ ጥናት ሳይሆን በመንግስት ላይ ግልጽ የሆነ ፖለቲካዊ ጫና ለመፍጠር የታለመ መሆኑ እሙን ነው። በዚህም አካሄዱ በኢትዮጵያ ደካማ መንግስት በማስቀመጥ አገሪቱን ባሻቸው ልክ ለማሽከርከርም የታቀደ በመሆኑ ሕልማቸው እውን እንዳይሆን ከወዲሁ አንድነትንና መግባባትን ማጠናከሩ የግድ ይሆናል። የእርስ በእርስ አለመግባባት የሚኖር ከሆነ ግን በበሬ ወለደ ሪፖርታቸው አንዱን ብሔር ወይም ኃይማኖት በአንደኛው ላይ በማነሳሳት ምኞታቸውን እውን ሊያደርጉ ይችላሉና ሁሉም ዜጋ ንቁ ሊሆን ይገባል።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን መስከረም 24/2015