ከ1986 በፊት በነበረው የትምህርት ስርዓት የተማሪዎችን የወደፊት ጉዞ ሚቃኑና የዕለት ተዕለት ኑሯቸውን በቀላሉ መምራት የሚያስችሏቸው የትምህርት አይነቶች በስፋት ይሠጡ ነበር። በዛ ወቅት ከነበሩ ትምህርቶች ምን ታስታውሳለህ(ሽ) ቢባል ብዙው ሰው ደርሶ ካየው የእጅ ሥራንና እርሻን ሳይጠቁም ያልፋል ለማለት ያስቸግራል። ምክንያቱም እነዚህ ትምህርቶች ቤታችንን አስውበው ግቢያችን የደረሰ ውበትን ሰጥተውናል። የምንፈልገውን ተመግበንም ውስጣችን እንዲያምርም አድርገውናል። ከምንም በላይ ከጎረቤት የምንግባባበትንና የምንዋደድበትን እድል ሰጥተውናል። እንዴት ከተባለ ዳንቴልና የተለያዩ የጥልፍ ስራዎችን በመስራት ጉርብትናችንን አጥብቀናል። በእርሻ ትምህርትም ምድሪቱ ያበቀለችውን በመስጠትም እንዲሁ የእኔ ቤት የእናንተም ነው ብለናል፡፡ቀደም ባለው ጊዜ ደግሞ የግብረ ገብነት ትምህርት የዜጎችን ማንነት በመቅረጽ ረገድ የማይተካ ሚና ነበረው።
ይህ ደግሞ ዛሬ ዳግም ወደ ትምህርት ስርዓቱ ቢገባ ምን ያህል ጠቀሜታ እንዳለው በግልጽ የሚያረጋግጥ ነው። የብዙዎች እይታ ያረፈበት የቀድሞ ትምህርት ስርዓትም ለዚህ ይሆናል። ተወዳጅ፣ ተናፋቂና አገር አሳዳጊ እንደሆነ በደንብ የሚያሳይም ነው። ያው ሁሉንም ትምህርቶች ላይሆን ይችላል። ጉድለቶችም ይኖሩታል። ምክንያቱም ዛሬ ያለነው 21ኛው ክፍለዘመን ላይ ነን። ያንን የሚመጥን ሥራና ተግባር ያስፈልገናል። እናም እንደትምህርት ሚኒስቴር ይህንን ሲያደርግ ቀደምቶቹንና ተወዳጆቹን ዳግም በማምጣት ከዘመኑ ጋር የሚራመዱና ተማሪን የሚገነቡ አድርጎ አዘጋጅቶታል፡፡
ተሻሻለ፤ ተከለሰ ሲባልም የቀደመውን ሙሉ ተግባር እርግፍ አድርጎ ተወ ማለት አይደለምና መሻሻልን ከዘመኑና ከነባር እውቀት ጋር አዛምዶታል። ለዚህም ማሳያው ቀደም ብለው በትምህርት ስርዓት ውስጥ ተካተው ሲሰራባቸው የቆዩት የትምህርት መስኮች ዳግመኛ በአዲሱ ስርዓትም ተካተው እንዲሰራባቸው መሆናቸው ነው። በጉዳዩ ላይ ሲሰሩ የነበሩትና በትምህርት ሚኒስቴር አሁንም እያገለገሉ ያሉት ኃላፊዎች ይህንን ያረጋግጣሉ።
የመጀመሪያው በትምህርት ሚኒስቴር የሥርዓተ ትምህርት ማበልፀጊያ መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ቴዎድሮስ ሸዋርገጥ ሲሆኑ፤ የፍኖተ ካርታ ተሰርቶ የትምህርት ስርዓት አተገባበሩ ተፈትሾ በአዲስ መልክ ለመሥራት ሲታቀድ ብዙ ስኬቶችን ለማምጣት እንደሆነ በሙከራ ትግበራ አጀማመር፣ በተዘጋጁት የማስተማሪያ መጽሀፍትና በትምህርት አሰጣጥ ዙሪያ የአሰልጣኞች ሥልጠና በደብረ ብርሀን ከተማ በተከናወነበት ወቅት ተናግረዋል።
የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሥርዓተ ትምህርት ሪፎርሙ ግድ መሆኑን የጠቀሱት መሪ ስራአስፈጻሚው፤ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ሥርዓተ ትምህርቱ ታስቦበት እንዲዘጋጅ ሆኗል። ሰነዶችም የሚያካትታቸው የተማሪ ባህሪያት፣ የይዘት ፍሰት መርሀ ትምህርትና ሌሎች ዝግጅቶች ናቸው። በዚህ ውስጥም ፍኖተ ካርታው የተሻሻለውና አዲሱ ስርዓተ ትምህርት የተዘጋጀው በትምህርት ሥርዓቱ የመማር ማስተማሩን የጥራት ደረጃ ለማሻሻል፣ እንዲሁም ሙያዊ ግዴታውን በብቃት የሚወጣ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የትምህርት ማኅበረሰብ ለመፍጠር ነው። ለዚህ ደግሞ ተወዳጅና ለውጥ አምጪ ትምህርቶችን በትምህር ስርዓቱ ውስጥ ማካተት ጠቃሚ እንደሆነ ያነሳሉ።
በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ግብረ ገብነት፣ አገር በቀል ዕውቀት፣ ሙያና የቀለም ትምህርት፣ ቴክኖሎጂ፣ ምርትና ተግባር፣ ጥናትና ምርምር ትኩረት የተደረገባቸውም ለዚህ እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ ደግሞ ተማሪዎች የሀገር በቀል እውቀት እንዲኖራቸው፤ የግብረ ገብና የሥነ- ምግባር ባለቤት እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። በተጨማሪም የሥራና ተግባር ትምህርት ተካቶ ስለሚሰጣቸው የራሳቸውን ሥራ በራሳቸው እንዲፈጥሩ እድል ይፈጥርላቸዋል። ከተቀጣሪነት ተላቀው የራሳቸውን ገቢ የሚያመነጩ ተማሪዎች ያደርጋቸዋልም ይላሉ።
በትምህርት ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶች ስርዓተ ትምህርት ዴስክ ኃላፊ ወይዘሮ ዛፉ አብርሃ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ስርዓተ ትምህርቱ በዚህ ዓመት ሙሉ እና የሙከራ ትግበራ ከተደረገበት በኋላ በ2016 ዓ.ም የሚኖሩ ችግሮችን በማስተካከል እና በማዳበር ሙሉ ለሙሉ ወደ ትግበራ የሚገባ ይሆናል። ለዚህ ደግሞ እንደ ትምህርት ሚኒስቴር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው። አንዱ የትምህርት አይነቶች አካታችነት ነው። ይህ ሲባልም ሥራና ተግባርን የሚያካትቱ፤ አገርን በቀላሉ የሚለውጡ የትምህርት አይነቶችን አስገብቶ ተማሪዎች እንዲጠቀሙባቸው ማድረግ ነው። ለአብነትም የእርሻ ትምህርት፤ ግብረገብና የስነጥበብና የአገር በቀል እውቀት ትምህርቶች ከፍተኛ ለውጥ ያመጣሉና ወደተግባር እንዲገባባቸው ተደርገዋል። ምን ምን ጥቅም ይሰጣሉ ከተባለ ብዙ መዘርዘር ይቻላል።
የእርሻ ትምህርት
በልቶ ከማደር ባሻገር ገቢያችንን ከፍ ለማድረግ ስናስብ ዘመናዊ የእርሻ ሥራን መጠቀምና በእውቀት የጎለበተ እርሻን መፍጠር ግዴታችን እንደሆነ እናምናለን። ለዚህ ደግሞ እውቀት ግድ ነው። እናም እርሻን እንደ አንድ የትምህርት አይነት አድርጎ መጠቀሙ መፍትሄ እንደሚሆነን አጠያያቂ አይደለም። በእርግጥ ከዚህ ቀደም በነበረው ስርዓተ ትምህርት ውስጥ እርሻ ብቻ ሳይሆን ኑሮዘዴ የሚባልም የትምህርት አይነት ነበር። ይህ ደግሞ ስንቶችን እንደለወጠ የነበሩበት ይናገሩታል። በተለይም ለአካባቢ ስነምህዳር የሚሰጡት ትኩረት ምንም መተኪያ የሌለው እንደነበረ ታሪክ ያስረዳናል።
ለምግብነት የሚሆኑ ነገሮችን ከመግዛት ይልቅ ከጓሯቸው፤ አለፍ ሲልም ከትምህርትቤት ቅጥር ግቢ እየወሰዱ መጠቀም የተለመደ እንደነበርም እስከቅርብ ጊዜ እየታየ ያለ ነው። ለዚህም ብዙዎቻችን ዛሬ ድረስ ምስክር የምንሆንላቸው በአካባቢያችን ያሉ የእርሻ ልማት ጣቢያዎችን ልናነሳ እንችላለን።
ለምሳሌ፡- ደብረብረሃን ከተማ ላይ ያለው ረጅሙን ዓመታት ያስቆጠረው የመምህራን ኮሌጅ ለግቢው ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው ማህበረሰብ ጭምር ብዙ አትክልትና ፍራፍሬን በዘመናዊ የእርሻ ጥበብ በቅናሽ ዋጋ ጥራት ያለው ምርት ዛሬ ድረስ ያቀርባል። ሻገር ስንል የሸዋሮቢት ማረሚያ ቤትም እንዲሁ ምርቶቹ የተለዩና በአገር ጭምር የሚታወቁ አድርጓቸው ቀጥሏል። ወደ ሁሉም አቅጣጫና ክልል ብንሄድ ብዙዎችን ዘርዝረን የማንጨርሳቸውን ማሰልጠኛዎች፣ የማህበረሰቡ መጋቢዎችን ማንሳት እንችላለን። ለዚህ ደግሞ መሰረቱ ምንም ሳይሆን የእርሻ ትምህርት ነው።
ትናንት ችግኝ ማፍላት አንዱ የትምህርት አካል ነበር፤ ችግኞችን መንከባከብም እንዲሁ። ይህ ሲሆን ደግሞ መደብ ጭምር ተሰጥቶ ነው። እናም ውጤቱ የሚለካው በአለው ውጤታማነት ልክ ነበር። በተጨማሪም የእንሰሳት ባህሪን መለየት፤ የቻሉትን ህክምና መስጠት፤ ቤተሰብን በግብርናው ዘርፍ ማገዝ የመሳሰሉ ነገሮችንም የእርሻ ትምህርት ካበረከታቸው ነገሮች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። ከዚህ አኳያ ትምህርቱ ዳግመኛ እንደ አንድ የትምህርት አይነት ተደርጎ ለተማሪዎች መሰጠት መጀመሩ ይበል የሚያሰኝ ነው። በእርግጥ የእርሻ ትምህርትና ተግባሩ በነበረበት ቀጥሎ ቢሆን ኖሮ ለአገራችን ብቻ ሳይሆን ለአለምም ጭምር እንተርፍ እንደነበር ማንም ይረደዋል። ከእነዚህ ዘመን ተሸጋሪ አምራቾች አንጻር አይተንም መገመት የምንችለው ይህንኑ ነው፡፡ዛሬም ይህው በጎ ተግባር እንዲቀጥል ትምህርት ሚኒስቴር በአዲሱ የትምህርት ስርዓት አካቶት ይዞት ብቅ ብሏል።
ግብረገብነት
ይህ ትምህርት የተጀመረው ገና ዘመናዊ ትምህርት ወደአገራችን ከመግባቱ በፊት በቄስ ትምህርትቤት እንደሆነ ታሪክ ያስረዳል። እንደውም ዘመናዊው ትምህርት እንኳን ሲጀመር መምህራኑ ከዚያው የተውጣጡ እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ። እናም ያ ዘመን መምህራን የሚከበሩበት፤ ጎረቤት እንደ አባትና እናት የሚታይበት፤ ልጅ ከልጅ የማይለይበት፤ ታላቅ ለታናሹ የሚያዝንበት፤ታናሽ ታላቁን የሚያከብርበት ሁሉም ለሁሉም ሰው የሆነበት ነበር። መተሳሰብ የበረታበት፤ አብሮ መብላትና መጠጣት ልምድ የሆነበትም ነበር። ሽማግሌ የሚከበርበት፣ ወጣቱ ጎንበስ ብሎ የሚታዘዝበትና በሱስ ያልተጠመደበትም ነበር። ያ ዘመን ትምህርትም ቢሆን ተፋልሞ የሚገኝበት ነው። ማለትም ስነምግባር የሌለው ልጅ መቼም ውጤታማ የማይሆንበት ነበርና።
ያ ዘመን ለንባብም ሆነ ለትምህርት ልዩ ትኩረት ይሰጥበታል። ዛሬስ ካልን ነገሩ ተቃራኒ ሆኖ እናገኘዋለን። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ተቆጪ ያጣና በስነምግባር የተሞረደ ትውልድ የሚያፈራ የትምህርት ስርዓት አለመኖሩ ነው። በተጨማሪም ዘመን አመጣሽ በርካታ ነገሮች መኖራቸው ነው።
ወሬው ከቴክኖሎጂው ጋር ብቻ በመሆኑ ማህበራዊ ትስስሮች ሳይቀሩ እየቀሩ መጥተዋል። አሁን አሁንማ ጎን ለጎን ማውራትም እየቀረ ነው፡፡እና ግብረ ገብነት ርቆናል። ሆኖም በአዲሱ የትምህርት ስርዓት አንዱ ሆኖ መካተቱ ነባር ባህላችንን ከማቆየቱም በላይ ራስን፣ ቤተሰብንና አገር ወዳድ ትውልድን ለማፍራት ያስችላል። ምክንያቱም የስነምግባር መኖር የመጀመሪያው ጥቅም መዋደድን ማጎልበት ነው።
አገር በቀል እውቀት
አገር በቀል እውቀትን መጀመሪያ ስናነሳ ብዙዎቻችን ትዝ የሚለን ነገር ባህላዊ መድሃኒቶቻችን ናቸው። ብዙዎችን ፈውሰው ለዛሬ አድርሰዋቸዋል። ዛሬም ቢሆን እየተጠቀምንላቸው ከበሽታችን የምንድንበት አጋጣሚ ቀላል እንዳልሆነ ሁላችንም የምንረዳው ጉዳይ ነው። ከፈዋሽነታቸው አኳያም ብዙ ጥናቶች እንደተደረጉባቸውና በህክምና ሰጪ ተቋማት ጭምር እንዲከፈቱ የሆኑበት አጋጣሚ ቀላል አይደለም። በተጨማሪም አውሮፓውያን ጭምር በኢትዮጵያ ባህላዊ ዕውቀቶች ዙሪያ ትኩረት አድረገው ምርምር ሲያደርጉም ይታያሉ።
አገር በቀል እውቀት አንድ ትርጓሜ የለውም። ግን ብዙ ነገሩ ገንዘብም ሕይወትም የሚሆን ነው። ለአብነት መድሃኒቱን አነሳን እንጂ ባህሉ፣ ወጉ፣ አኗኗኑ፣ የአሰራር ጥበቡ ወዘተ ዘርዝረን የማንጨርሰው ነገር ነው። እናም ከትምህርት አንጻር መሰጠቱ በርካታ ጠቀሜታዎችን ከግለሰብ እስከ አገር ድረስ ያስገኛል። እንዴት ከተባለ እውቀቶችን በማውጣትና በመጠቀም ነው። ሁሉም በአካባቢው ያለውን ነባር እውቀት በማጋራት፣ እንዲተገበር በመስራትም ነው። የተለያዩ ዕሴቶችንም በማስተዋወቅ አንድትንና አብሮነትን ያጎለብታል፡፡
ሥነ ጥበብ
ሥነ ጥበብ ብዙ አይነት የሰው ልጅ ድርጊቶችን የሚያጠቃልል ዘርፍ ነው። እንዲታዩ ወይም እንዲሰሙ፣ እንዲወደዱ ወይም እንዲተገበሩ የምንፈልጋቸውን ነገሮች በጥበብ ኃይል በሙያው እንዲፈጸሙ የምናደርግበት ድርጊት ነው። እናም ይህ ዘርፍ በአይነት ጭምር ተከፍሎ እናገኘዋለን። ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያህል ስዕል ፤ የሐውልት ሥራ፤ ስነ ሕንጻን የመሳሰሉ ነገሮች አቅፎ የምናገኘው ነው። ሌላውና ከዚህ ዘርፍ የሚመደበው ኪነት የምንለው ሲሆን፤ ብዙዎቻችን ከኪነጥበብ ጋር አገናኝተን የምንጠቀምበት ነገር ግን በባህሪው የተለየ የሆነው የስነጥበብ አይነት ነው። ማለትም ኪነት ማለት እንደ ጭፈራ፣ ሙዚቃ፣ ቴአትር፣ ፊልም፣ ስነጽሑፍን የሚይዘው ክፍል ነው።
ይህ የትምህርት አይነት በጥበብ ተመርቶ ራስን ማነጽ የሚያስችል ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። ይህ የትምህርት አይነት ሁሉም ትርጉም ያላቸው የጥበብ ሥራዎችን በመያዝ የሚያስፈልጉትን ፅንሰ-ሀሳቦችን ፣ የፈጠራ ችሎታን ፣ የእጅ ጥበብና የመሳሰሉትን በቀላሉ ለመተግበር የሚያስችልም ነው። ለሁሉም ተማሪዎች የሚያዳብሩበት ደህንነቱ የተጠበቀ ፣ የበለፀገ እና የተከበረ አካባቢን ይሰጣቸዋልም። በተጨማሪም በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ሕዝቦች መካከል የመተማመንና የመግባባት ድልድይ ይገነባል፤ ከግለሰብ እስከ አገር ድረስ ያለውን ማንነትም ያጎላል፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ትምህርቱ ውበት እና መንፈሳዊ ፍላጎቶችን ያረካል።
የእውቀትን ፍላጎት ያሰፋል። ራስን ለመግለጽ ያለን ዝግጁነት ያዳብራል፤ ባህላችንን የምናስተዋውቅበትን እድል ይሰጣል። እናም በአዲሱ ትምህርት ሥርዓት ውስጥ ተካቶ መምጣቱ ይበል የሚያሰኝ ነውና ከፖሊሲው ባሻገር አይተን እንጠቀምበት በማለት ተሰናበትን። ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን መስከረም 23/2015