ከተማዋ በነዋሪዎቿ፣ በስራ አጋጣሚ ወይም እግረ መንገዳቸውን በተመለከቷት ሁሉ አእምሮ ወይም ልብ ውስጥ የመቅረት ልዩ መስህብ አላት። ይሄ ደግሞ የሚመነጨው ከሀይቋ፣ በፕላን የተከተመችና የውብ መንገዶች ባለቤት ከመሆኗና በየጊዜው እያደገች ካለችበት ሁኔታ ብቻ አይደለም፤ ከሰፋፊ ውብ መንገዶቿ በተጓዳኝ ለእግረኞች ከምትገነባቸው ውብ መንገዶች፣ በዛፎች፣ በሳር፣ በአበቦችና በመሳሰሉት ተክሎች ከተዋቡት አረንጓዴ ስፍራዎቿም ነው።
አረንጓዴ ስፍራዎቿ በሞቃታማነቷ የምትታወቀውን ሀዋሳ ነፋሻ፣ ከጸሀይ ሀሩር መሸሻ ጥላ በመሆን ያገለግሏታል፤ የአይን ማረፊያ አርገዋታል፤ የሀገራችን ከተሞች በህንጻና በመሳሰሉት ግንባታዎች እየተጠባቡ ባለበት በዚህ ዘመን፣ ሀዋሳ ለክፍት ቦታዎች ፊትም አሁንም እየሰጠች ያለችው ትኩረት በእጅጉ በአርአያነት ሊያስጠቅሳት የሚችል ነው። ከተማዋ አረንጓዴ ስፍራዎቿን በማልማት በኩል ሁሌም ባተሌ ናት፤ ከከተማ ለጥቂት ጊዜያት ወጣ ብሎ የተመለሰም ሳይቀር በእነዚህ ስፍራዎች ላይ የተጨመረ እንጂ የተቀነሰ አይመለከትም። ይህን ልማቷን የሁሌም አርጋው ኖራለች።
የከተማዋ ማዘጋጃ ቤትም እነዚህን የከተማዋን ክፍት ቦታዎች ወይም አረንጓዴ ስፍራዎች አሁንም በራሱም በማህብረሰቡና በተለያዩ ተቋማት ማልማቱን እንደቀጠለበት በቅርቡ በስራ አጋጣሚ በከተማዋ በተገኘሁበት ወቅት ከማዘጋጃ ቤቱ ምክትል ሃላፊው አቶ ታሪኩ ታመነ መግለጫ ተረድቻለሁ።
በአንድ ወቅት የሀዋሳ ማዘጋጃ ቤት የከተማዋን የአረንጓዴ ስፍራዎችን ማልማቱን አጠናክሮ ለመቀጠል ሲነሳ ክፍለ ከተሞች ለማልማት ፈልገው የቦታ ጥበት አጋጠማቸው ሲሉ ያስታወሱት የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ ታሪኩ፣ ምን ይሻላል ተብሎ ሲታሰብ ክፍት ቦታዎች/ ፐብሊክ ስፔሶች አሉ፤ ለምን እነሱን አናጣራም /ቼክ አናደርገም/ ብለን ተነሳን ይላሉ። ቦታዎቹ በተለያዩ ሼዶች መያዛቸውን አረጋግጠው ማጽዳት ሲጀመር ሌሎች ፐብሊክ ስፔሶች በግለሰቦች መያዛቸው ተደረሰበት የሚሉት አቶ ታሪኩ፣ በዚህ መነሻነት ሌላ መድረክ ተፈጥሮ ከህብረተሰቡ ጋር መግባባት ላይ ተደርሶ ወደ እርምጃ ተገባ ሲሉ ያሰታውሳሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ የሀዋሳ ማዘጋጃ ቤት በ2014 በጀት አመት በህብረተሰብ ተሳትፎ በሚሰሩ ሃያ አራት አጀንዳዎች ነበሩት። በበጀት አመቱ መስከረም አራት ቀን በእዚህ አጀንዳዎች ላይ የንቅናቁ መድረክ ከፈተ። ከተማዋ ጽዱ ውብ አረንጓዴ በሚል የምትታወቅበትን ገጽታዋን አጠናክሮ ለማስቀጠል ሁሉም ባለቤት ሆኖ በብሎክ በመንደር በቀበሌ እቅድ ወጥቶ ወደ ትግበራ እንዲገባ ተደረገ።
የሀዋሳ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ ታሪኩ ታመነ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሀዋሳ በተካሄደ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አንድ መድረክ ላይ የተገኙ የሚኒስቴሩ የስራ ሃላፊዎችና ከተለያየ ተቋማት የተውጣጡ የመገናኛ ብዙሃንና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት የመሰረተ ልማት ስራዎችን ባስጎበኙበት ወቅት እንዳሉት፤ በዚህ በተፈጠረው መነቃቃት ማዘጋጃ ቤቱ መጀመሪያ 12 ሺ ካሬ ሜትር በተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች በህገወጥ መንገድ ተይዞ የነበረ ፕብሊክ ስፔስ ለማጽዳት አቅድ ተያዘ፤ እቅዱ እየተሳካ ሲመጣ አሀዙን ወደ 25 ሺ ማሳደግ ውስጥ ተገባ። በተሰራው የተጠናከረ ተግባር 79 ሺ ካሬሜትር ክፍት ቦታዎች /ፕብሊክ ስፔስ/ ከህገወጦች ማስለቀቅ ተችሏል ።
እንደ ምክትል ሃላፊው ማብራሪያ፤ ንቅናቄውን ተከትሎ ክፍት ቦታዎችን /ፐብሊክ ስፔሶችን/ና የእግረኛ መንገዶችን /ዎክ ዌይዎችን/ የማጽዳቱ ስራዎችን የተለያዩ ከተሞች ሃላፊዎች እየጎበኙ ልምድ እየቀሰሙበት ይገኛሉ። እናንተም ሳትሰሙ አትቀሩም ብዬ አስባለሁ፤ በከተማዋ ስትዘዋወሩ የምትመለከቱትም ይሆናል ሲሉ ምክትል ሃላፊው አብራሩ።
ሀዋሳን ከሌሎች ከተሞች የሚለዩዋት ስትመሰረትም በፕላን የተመሰረተች ከተማ መሆኗ ነው፤ አስፓልቶቿ ከአሁኑም በተሻለ እስከ 30 እና 40 ሜትር ስፋት ያላቸው ፣ ብዙ ላንድስኬፕች፣ የእግረኛ መንገዶች /ዎክ ዌይዎች/ አላቸው። የተለያየ የፓለቲካ አለመረጋጋት በተፈጠረ ቁጥር ግለሰቦች እነዚህን ቦታዎች እየወረሩ ሼዶች እየገነቡ ይሰሩ የነበረበት ሁኔታ ነው ክፍት ቦታዎቹ በአግባቡ እንዳይለሙ አርጓቸው ቆይተዋል።
እነዚህን ህገወጥ ግንባታዎች ወደ ማፍረስ ከመግባታችን በፊት መጀመሪያ ላይ ከህብረተሰቡ ጋር ተግባቦት ፈጥረናል የሚሉት አቶ ታሪኩ፣ ከክፍለ ከተማና ቀበሌ አመራሮችና መዋቅሮች እንዲሁም ከህብረተሰቡ የተለያዩ አደረጃጀቶች ጋር በማእክል ውይይት ተደርጎ የጋራ መግባባት ላይ ከተደረሰ በኃላ ህብረተሰቡ ራሱ አምኖ እርምጃ እንዲወሰድ ነው የተደረገው ሲሉ ያብራራሉ። በአንዳንድ አካባቢዎች ህንጻዎችን ለሌላ ተግባር በማዋል በመንግስት ከፍት ቦታዎች ላይ የንግድ ስራ ይሰራ አንደነበር ጠቅሰው፣ የማጽዳቱ ስራ ሲከናወን ወደ ህንጻቸው ተመልሰው ስራቸውን እንደቀጠሉ ጠቁመዋል። ሼዶችን ተከራይተው ይሰሩ የነበሩትም ሌላ አማራጭ እንዲፈልጉ ሁለት ወር እድል ተሰጥቷቸው እንዲነሱ መደረጉን ገልጸዋል።
የማጽዳቱ ስራ አይቀጥልም ብለው በማሰብ ሌላው ሲያፈርስ ያላፈረሱ አንደነበሩም አስታውሰው፣ እርምጃው እየተጠናከረ ሲመጣና ሌሎች ማፍረሳቸውን ሲመለከቱ እነዚህም ያለምንም የጸጥታ ሀይል ጫና ወደ ሼዶቹን ማፈረሳቸውን ነው አቶ ታሪኩ የጠቀሱት።
አሁን መልሶ ማልማቱ ተጀምሯል፤ አቶ ታሪኩ አሮጌው መናኸሪያ አካባቢ ከዋርካ ሆቴል አደባባይ አንስቶ በአሮጌው መነሃሪያ ፊት ለፊት ወይም በሌዊ፣ በሹ ሆቴል ፊት ለፊት ባለው ከፍት ቦታ ላይ እየተካሄደ ያለውን ውብ የእግረኞች መንገድና የተለያዩ የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን በአብነት ይጠቀሳሉ። ይህ ፕሮጀክት በስተቀኝ በኩል ከዋንዛ ሰርክል ተነስቶ ሼል በመባል እስከሚታወቀው ማደያ ድረስ ይዘልቃል። እነዚህ ቦታዎች ለአመታት በአቅራቢያቸው በሚገኙ ድርጅቶችና በተለያዩ አካላት ሼዶች ተገንብተውባቸው ለተለያየ አገልግሎት ሲውሉ ኖረዋል።
እሳቸው እንደሚሉት፤ ይህ ስፍራ ወደ ልማቱ ከመገባቱ በፊት ከህብረተሰቡ ጋር መግባባት ተፈጥሮ ሙሉ ለሙሉ እንዲጸዳ ተደርጓል። አካባቢው በምስራቅ ክፍለ ከተማ ስር ይገኛል። በዚህ ከፍለ ከተማ ብቻ 12 ሺ 500 ካሬ ሜትር ቦታ ማጽዳት ተችሏል።
ይህን መልሶ ለማልማት ብዙ ካፒታል ይጠይቃል ሲሉ ምክትል ሃላፊው ይገልጻሉ። የአሮጌው መነኸሪያ አካባቢ ፕሮጀክት ብቻ እስከ 52 ሚሊየን ብር ድረስ ይፈልጋል። በመንግስት እቅም ብቻ ሊለማ አይችልም። እዚህ አካባቢ/ አሮጌው መነኸሪያ አካባቢ/ አንድን ቦታ በመንግስት በጀት አልምተን ካሳየን በኃላ ሌላውን ዲዛይን ሰጥተን በባለሀብቱ እንዲለማ ለማድረግ አንደ ከተማ ታስቧል ሲሉ ይጠቁማሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ለእግረኛ መንገድ ግንባታው የሚያስፈልጉ ታይሎቹን ተቋራጩ ራሱ እዚሁ እንዲያመርት ተደርጓል፤ ስታንዳርድ ወጥቶለት የጥራት ደረጃው እየተረጋገጠ የሚሰረም ነው፤ ማህበራት ደግሞ የማንጠፉን ስራ እንዲሰሩ ነው የተደረገው። በፕሮጀክቱ ብዙ ወጣቶች ከላይ እስከታች የስራ አድል አግኝተዋል።
ግንባታው ብዙ ነገሮችን ይይዛል። በእግር ተጓዦች /ዎክ የሚያደርጉ/፣ እናቶች አረጋውያን፣ ወዘተ. ይኖራሉ፡ ግንባታዎቹ ደረጃቸውን የጠበቁ መቀመጫዎች ይኖራቸዋል፤ ሰው ቁጭ ብሎ መዝናናት እንዲያስችሉ ተደርገው ነው የሚገነቡት። ሳር፣ ዛፎች፣ ብዙ አይነት አበባዎችም ይተከላሉ፤ የእግረኛ መንገዱ የራሱ መብራት ይኖረዋል።
ሁሉም የከተማዋ አካባቢ በዚህ መልኩ ይገነባል፤ ስለዚህ እዚህ ጀመርን እንጂ እየተስፋፋ ይሄዳል፤ ገና ፒያሳ አልሄድንም፤ አጸዳን እንጂ ስራ አልጀመርንም። ስለዚህ እዚህ ሰርተን ካሳየን በኃላ ባለሀብቱ ራሱ አንዲያለማ ለማድረግ ዝግጅት እያደረግን ነው። ሁሉም መንገዶቻችንን እንደዚህ ማልማት ከቻልን የጎብኚዎች ፍሰት ይጨምራል፤ ዜጎች በነጸነት ለአደጋ በማያጋልጥ መልኩ ዎክ እያረጉ መንቀሳቀስ ይችላሉ።
የመኪና የሞተር ሳይክል ማቆሚያ ስፍራ ይኖረዋል፤ ዘመናዊ ሼዶች ይሰራሉ፤ ይህ አካባቢ የንግድ አካባቢ ስለሆነ ለብስክሊት የሚሆን መንገድ አልተዘጋጀለትም፤ ለሎች አካባቢዎች ላይ ለብስክሌት መንቀሳቀሻና ማቆሚያ ይዘጋጃል። ስለዚህ ብዙ ነገሮችን የያዘ ፕሮጀክት ነው፤ የከተማዋንም ገጽታ ይቀይራል ፤ በቀጣይ አመት ስትመጡ እናንተም ዎክ እያረጋችሁ ትዝናናላችሁ የሚል ተስፋ አለኝ ሲሉም ለእኛ መልእክት አስተላለፉ።
አካባቢው በእርግጥም በተለያዩ መንገዶች ተከልሎ ለተለያዩ አገልግሎቶች ውሎ የነበረው ይዞታ ጸድቷል፤ ምንም አይነት ሼድ የለም፤ የሚታየው መንገዱ ለእግረኛ በሚመቹ ውብ ሸክላዎች እየተነጠፉ ናቸው፤ ዛፎች በተለየ መልኩ በዙሪያቸው ግንባታ እየተካሄደ ነው፤ ለመንገደኞች ማረፊያና ለአበባ ማልሚያ እየተዘጋጁ ናቸው፤ በመብራት ማሸብረቅ አንዲቻልም የመብራት መሰረተ ልማቶች አብረው እየተዘረጉ ናቸው። አበቦች ተተክለዋል።
ከታቦር ብቻ 25 ሺ ካሬ ሜትር ነው ያስመለስነው የሚሉት ምክትል ሃላፊው፣ ከሌምቦ ጀምሮ እስከ ሪፈራል ሰርክል ድረስ ብቻ 22ሜትር ስፋት ያለው ሙሉ በሙሉ በግለሰቦች የተያዘ መሬት እንዲጸዳ ተደርጓል፤ 22 ሜትር ስል ስፋቱን ነው። ስለዚህ እጅግ የሚየስደምም ስራ በዚህ አመት ተሰርቷል ሲሉ ያብራራሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ከሳውዝ ስፕሪንግ ወደ ውስጥ ስትገቡ በግለሰቦች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በተቋማት ሙሉ ለሙሉ ክፍት ስፍራዎቹ ፣ የእግረኛ መንገዶቹ በአረንጓዴ አንዲለሙ ተደርገዋል። ሀዋሳ ወደ ውስጥም ሲገባ ልማቱ ይህንኑ የሚመስለው። መንገዶች በአስፋልት በኮብል ስቶን ህብረተሰቡ ደግሞ ፊትለፊቱን በማልማት ሰፊ ተሳትፎ አድርጓል።
ጉብኝታችንን ቀጥለናል፤ የማዳረስ አይነት ጉብኝት ነው። ወደ ሌላው አረንጓዴ ስፍራዎች ልማት ተንቀሳቀስን። ወደ ፍቅር ሀይቅ ከሚወስደውና ከመዳህኒአለም ቤተክርስቲያን አካባቢ ከሚገኘው አደባባይ ወደ አሞራ ገደል በሚወስደው ውብ የአስፋልት መንገድ ጥቂት ተጉዘን ቆመን። ልክ እንደ ተሰባሰብን የከተማው ማዘጋጃ ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ ታሪኩ ማብራራታቸውን ቀጠሉ።
ይሄ የምትመለከቱት ደግሞ በህብረተሰብ ተሳትፎ የተሰራ ሲሉ ገለጹልን። የመንገዱ ዳርቻ በሳር እና በአበቦች ተውቧል፤ ለስፓርት መስሪያ የሚያገለግሉ መሰረተ ልማቶች ፣ የልጆች መጫዎቻዎችም አብረው ተገንብተዋል። እግረኞች ቢደክማቸው የሚያርፉባቸው መቀመጫዎች ተዘጋጅተዋል። ጧዋትና ከሰአት በኃላ ወደ አካባቢው የሚመጣ ህብረተሰቡ ሲዝናና ስፓርት ሲሰራ ታያላችሁ አሉን።
እንደ አቶ ታሪኩ ገለጻ፤ ለእዚህ ክፍት ቦታ ግንባታ የከተማና ኮንስትራክሽን መመሪያው የዲዛይንና አንዳንድ ድጋፎችን ከማውጣቱ በቀር ያወጣው ገንዘብ የለም። ሙሉ ወጪው በማህበረሰቡ ነው የተሸፈነው። ይህን ስራ በመንግስት በጀት ማኔጅ ማድረግ ያስቸግራል፤ በከተማ ደረጃ ብቻ ወደ 152 ሎቶች አሉ። አንድ ሎት በትንሹ 500 ካሬ ሜትር ስፋት ይኖረዋል፤ በትልቁ ሲታይ ደግሞ ከ800 እስከ 1000 ካሬ ሜትር ስፋት ይይዛል። 152 ሎቶቹን 152 ማህበራት ናቸው ማኔጅ የሚያደርጉት፤ አንድ ሎት በአንድ ማህበር ማኔጅ ይደረጋል።
ስራው ለወጣቶችም ሰፊ የስራ እድል የፈጠረ ነው። በአንዱ ማህበር አምስት ወጣቶች ይታቀፋሉ። ስለዚህ ስራው ምን ያህል ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚችል መረዳት ይቻላል።
ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅተን ስንሰራ፣ ለስራው ደግሞ እውቅና ስንሰጥ ይበልጥ እየተበረታታን ክፍት ቦታዎችን ማልማት ይቻላል ሲሉም ነው ምክትል ሃላፊው የተናገሩት።
ቅድም እንደጠቀስኩት 21ሺ ካሬ ሜትር ቦታዎች ተሰሩ ያልኩት እንዲህ አይነት ስራዎች ተደምረው ነው። ይህን ወደ ገንዘብ ስንቀይር 106 ሚሊየን ብር የሚያወጡ ስራዎች ናቸው የተነከናወኑት። የመንግስትን በጀት በእዚህ ስራ መሸፈን ተችሏል ሲሉ አብራሩልን።
ባስጎበኘናችሁ ስፍራዎች ብቻ አይደለም ልማቱ የተከናወነው፤ በከተማው የተለያዩ አካባቢዎች ተመሳሳይ ስራዎች በርካታ ናቸው ይላሉ። ሌሎች አካባቢዎች ብትሄዱ ተቋማት ያለሟቸውን አረንጓዴ ስፍራዎች ማየት ትችላላችሁ፤ ሞቢል አካባቢ ቢጂአይ ያለማው አለ፤ ሌሎች የግል ተቋማት ያለሟቸው ክፍት ቦታዎች የሚገራርሙ ስፍራዎች መሆን ችለዋል።
አቶ ታሪኩ በስራው ውጤታማ ለሆኑትም በቅርቡ ሽልማት እንደተበረከተላቸውም በተለይ ለጋዜጣው ሪፓርተር ሰሞኑን ተናግረዋል። በህብረተሰብ ተሳትፎ በተሰሩ በተለይ በአረንጓዴ ልማትና በ24ቱ አጀንዳዎች መነሻነት ሽልማቱ የተበረከተላቸው። በዚህም ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ከወጡ ክፍለ ከተሞች እንደኛው መኪና፣ ሁለተኛው ሞተር ሳይክል ሶስተኛው ኮምፒውተርና ፕሪንተር ተሸልመዋል። አንደኛ ብሎኮች፣ መንደሮች እና ቀበሌዎች ተሸልመዋል።
ሙሉ ለሙሉ አካባቢያቸውን አረንጓዴ ማድረግ የቻሉ፣ በሌሎች የህብረተሰብ ተሳትፎ አጀንዳዎችም የላቀ ውጤት በማምጣቸው መሸለማቸውን የጠቀሱት ምክትል ሃላፊው፣ የሽልማቱ ሌላው ፋይዳ እስከ አሁን የተከናወነው የአረንጓዴ ልማትና የህብረተሰብ ተሳትፎ ስራ በላቀ መልኩ አንዲቀጠል ለማድረግ ለእዚህም የውድድር መንፈስ ለመፍጠር ነው ይላሉ። ከሽልማቱም በኃላ በ2015 የሚሰሩ እቅዶች ቀርበው በየሩብ አመቱ አፈጻጸማቸው እየተገመገመ እውቅና ይሰጣል ሲሉ አቶ ታሪኩ ጠቁመዋል።
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን መስከረም 21/2015 ዓ.ም