መንግሥት መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግርን እውን ለማድረግ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል ብሎ ትኩረት ከሰጣቸው ተግባራት መካከል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት አንዱ ነው:: የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሦስት ዋና ዋና መሠረታዊ ተልዕኮዎች አሏቸው:: እነዚህ ተልዕኮዎቻቸውም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራን ማስፋት እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማከናወን ናቸው:: ፓርኮቹ በሚገነቡባቸው አካባቢዎች ለሚኖረው የኅብረተሰብ ክፍል ሥራ በመፍጠርና ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆነ የሥራ ከባቢ እውን በማድረግ ለሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል::
የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ተመራጭ ከሚያደርጓቸው መካከል በርካታ አገልግሎቶችን አንድ ሥፍራ ላይ ሰብሰብ አድርገው የሚያቀርቡ መሆናቸው፣ ተገቢ መሠረተ ልማት የሚገነባላቸው እንዲሁም ከሌሎች አምራቾች ጋርም የሚያገናኙ መሆናቸው ይጠቀሳሉ:: ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያም ብዙ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማቋቋም እንዲሁም ሰፊ የሰውና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን፣ ማሽኖችን ከቀረጥ ነፃ ማስገባትን፣ የብድር አቅርቦትን፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን እና የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን እንደማበረታቻ በማቅረብ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ፋብሪካዎቻቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲከፍቱ ጥረቶች ተደርገዋል::
በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ:: ፓርኮቹ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ለአገራዊ ምጣኔ ሀብት እድገት ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ:: በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የማምረቻ መናኸሪያ እንድትሆን የሚደረገውን ጥረት ለማቀላጠፍ ላቅ ያለ ሚና ይጫወታል ተብሎ የተጣለበት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ውጤቶች ተገኝተውበታል::
እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም በተጠናቀረ መረጃ መሠረት፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በቀጥታ በምርት ተግባራት ላይ 81ሺ ሠራተኞች ተሰማርተዋል:: ይህ አሀዝ ከፓርኮቹ ውጪ ያሉና ተዘዋዋሪ በሆነ መንገድ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸውን ሰዎች አይጨምርም:: በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ውስጥ የሚገኙ አምራቾች ከፓርኮቹ ውጪ ካሉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ጋር የሥራ ትስስር ስላላቸው በዚህ ሂደትም በርካታ የሥራ ዕድሎች ተፈጥረዋል::
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሥራ ከጀመሩበት ጊዜ ወዲህ ከ61 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ምርቶች ለአገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ ገበያ ቀርበዋል:: በሌላ በኩል ፓርኮቹ ሥራ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ፣ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ፣ ለውጭ ገበያ የቀረበውና በተኪ ምርቶች የተገኘው ዋጋ አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር ሆኗል:: ከዚህ ውስጥ፣ 930 ሚሊዮን ዶላር የሚሆነው ገንዘብ ለውጭ ገበያ ከቀረቡ ምርቶች የተገኘ ገቢ ነው:: ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ተኪ ምርቶችን የማምረት ተግባርም (Import Substitution) ጥሩ ውጤት እየተመዘገበበት እንደሆነ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን መረጃዎች ያሳያሉ::
የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማፋጠን ብዙ አስተዋፅኦዎችን እያበረከቱ ቢሆንም፣ በሙሉ አቅማቸው እንዳያመርቱ መሰናክል የሚሆኑ የተለያዩ ችግሮች ሲያጋጥሟቸው ይስተዋላል:: በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተፈጠረው የፀጥታ መደፍረስ በጦርነቱ ቀጣና ውስጥ በሚገኙ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩ ይታወቃል:: የዚህ ችግር ሰለባ ከሆኑት ኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ (Kombolcha Industrial Park) አንዱ ነው::
የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ90 ሚሊዮን ዶላር የተገነባና በ75 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ የኢንዱስትሪ ፓርክ ሲሆን፣ ዘጠኝ ሼዶችም አሉት:: ከአንድ ሺ ሁለት መቶ በላይ ሠራተኞችም አሉት:: የጨርቃ ጨርቅ ምርቶችን አምርተው ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ አራት የደቡብ ኮሪያ፣ የኢጣሊያ፣ የአሜሪካና የቻይና አምራች ኩባንያዎች የገቡበት ይህ ኢንዱስትሪ ፓርክ፤ በ2014 ዓ.ም አሸባሪው ሕወሓት በአማራ ክልል በፈጸመው ወረራ ውድመትና ዘረፋ እንደተፈጸመበት ይታወቃል::
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች ከዚህ ቀደም እንዳስታወቁት፣ በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ላይ የደረሰው ጉዳት በሁለት መልኮች የሚገለጽ ነው፤ የመጀመሪያው ዝርፊያ፤ ሁለተኛው ደግሞ ውድመት ነው። በዚህም የፓርኩ የቢሮ ዕቃዎችና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (IT) ሲስተሞች፣ የአምራች ኩባንያዎች ቢሮዎችና ቁሳቁስ፣ ለውጭ ገበያ የተዘጋጁ የጨርቃ ጨርቅ አልባሳትና የቆዳ ውጤቶች ተዘርፈዋል። ወደ ፓርኩ ገብተው በምርት ሥራ ላይ ያሉ ድርጅቶች አምርተዋቸው የነበሩና ወደ ውጭ ሊላኩ የተዘጋጁ የተለያዩ ምርቶች ተሰርቀዋል። ኩባንያዎቹ የሚያመርቷቸውን ምርቶች ለማምረት ጥቅም ላይ የሚውሉ ጥሬ ዕቃዎችም ተወስደዋል።
በድርጅቶቹ ቢሮዎች ውስጥ የነበሩ መገልገያዎች፣ በቀላሉ ሊተኩ የማይችሉ መሣሪያዎችና የምርት ሥርዓቶች፣ አገልግሎት መስጫዎች፣ የደኅንነት መጠበቂያ መሣሪያዎች፣ የኤሌክትሪክ እና ሌሎች ገመዶች፣ ለፓርኩ ተጨማሪ ግንባታ ለማድረግ እንደመጋዘን ሲያገለግሉ የነበሩ ኮንቴይነሮች፣ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ ያሉ ተሽከርካሪዎችና ሌሎች ቁሳቁስ ተዘርፈዋል፤ወድመዋል:: አምራች ኩባንያዎቹ ለሥራዎቻቸው ያስገቧቸው መለዋወጫ ዕቃዎችና ሌሎች ጥሬ ዕቃዎች ከፍተኛ ውድመትና ዝርፊያ ተፈፅሞባቸዋል። የፓርኩ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫዎች፣ የማምረቻ ቦታዎች፣ የኬሚካል ማጣሪያ እና ሌሎች በፓርኩ ውስጥ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ ክፍሎች ከፍተኛ ዝርፊያና ውድመት ደርሶባቸዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ፣ የኮርፖሬሽኑን የ2014 በጀት ዓመት አፈፃፀም አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ በሰጡበት ወቅት፣ ‹‹በሰሜን የአገሪቱ ክፍል የተከሰተው የሰላምና ፀጥታ መደፍረስ በኢንቨስትመንት ተግባራትና በኮርፖሬሽኑ ዓመታዊ እቅድ አፈፃፀም ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል፤ የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ በጦርነቱ ከፍተኛ ውድመት ደርሶበት ነበር:: በኢንዱስትሪ ፓርኩ ላይ የደረሰው ጉዳት በሁለት መልኮች የሚገለፅ ነው:: አንደኛው የኮርፖሬሽኑ ሀብት የገጠመው ውድመትና ዝርፊያ ሲሆን፤ በፓርኩ ውስጥ በሥራ ላይ የነበሩ አምራች ድርጅቶች የደረሰባቸው ዝርፊያ/ውድመት ደግሞ የጉዳቱ ሌላኛው መልክ ነው›› በማለት ገልጸው ነበር::
መንግሥት በባለሀብቶች ተመራጭ የሆነውን ይህን የኢንዱስትሪ ፓርክ ከደረሰበት ውድመት አገግሞ በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲመለስ የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል:: በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኮሚዩኒኬሽንና ማርኬቲንግ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሔኖክ አስራት፣ ኮርፖሬሽኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር ያከናወናቸው ተግባራት የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከደረሰበት ውድመት አገግሞ በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲመለስ ስለማስቻላቸው ይገልፃሉ::
እርሳቸው እንደሚሉት፣ ኢንዱስትሪ ፓርኩን በፍጥነት ወደ ሥራ ለመመለስ በኮርፖሬሽኑና ተባባሪ ባለድርሻ አካላት ከተከናወኑ ተግባራት መካከል ጉዳት የደረሰባቸውን መሠረተ ልማቶች የመጠገንና የሥነ ልቦና ጉዳት ለደረሰባቸው ሠራተኞች የሥነ ልቦና አቅም ግንባታ ድጋፍ የማድረግ ሥራዎች ይጠቀሳሉ::
‹‹የወደሙ መሠረተ ልማቶች ተጠግነው በድጋሜ አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል:: ጦርነቱ ያስከተለው ሥነ ልቦናዊ ጫናም ቀላል ባለመሆኑ በፋብሪካዎቹ ውስጥ የሚሠሩት ሠራተኞች በጥሩ መንፈስ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ የሚያግዙ የሥነ ልቦና ግንባታ ሥራዎች ተሠርተዋል::›› የሚሉት አቶ ሄኖክ፣ ‹‹ፋብሪካዎቹን ወደ ሥራቸው ለመመለስ የሚያግዙት የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ሥራዎች ካለቁ በኋላም ወደ ምርት ሥራቸው ተመልሰዋል፤ ሁሉም አምራቾች ማምረት በሚችሉበት አቅም እያመረቱ ነው:: ምርቶቻቸውንም ወደ ውጭ እየላኩ ይገኛሉ›› በማለት ይገልፃሉ::
እንደ አቶ ሄኖክ ማብራሪያ፤ የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ኩባንያዎችን ወደ ምርት ሥራቸው ለመመለስ ከተከናወኑ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት በተጨማሪ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ በምርት ሥራ ላይ ተሰማርተው ለሚገኙት ኩባንያዎች የተደረጉ ሌሎች ማበረታቻዎችም አሉ:: ከእነዚህም መካከል ለኩባንያዎቹ የተደረጉ የሼድ የኪራይ ጊዜ እፎይታና የኪራይ ምህረት ይጠቀሳሉ::
‹‹በፓርኩ መሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ደርሷል፤ ተመርተው ወደ ውጭ ሊላኩ የተዘጋጁ ምርቶችና የቢሮ መገልገያ ዕቃዎች ተዘርፈዋል›› በማለት በፓርኩ ላይ የተፈፀመውን ውድመትና ዘረፋ ያስታወሱት አቶ ሔኖክ፣ ኢንዱስትሪ ፓርኩ በገንዘብ ሲሰላ ምን ያህል ውድመትና ዘረፋ እንደተፈፀመበት ጥናት የሚያደርጉ ከተለያዩ የመንግሥት አካላት የተውጣጡ ኮሚቴዎች ውድመቱንና ዘረፋውን እያጠኑ እንደሚገኝና የጥናት ሥራው ሲጠናቀቅ እንደሚገለፅ ጠቁመዋል::
የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ወደ ሥራ እንዲመለስ ከሌሎች ኢንዱስትሪ ፓርኮች ድጋፍ እንደተደረገለት በፓርኩ የሥራ ኃላፊዎች ተገልጾ ነበር:: ፓርኩ እስከ መጋቢት 2014 ዓ.ም አጋማሽ ባሉት ወራት ወደ ውጭ ከላካቸው ምርቶች ከሰባት ነጥብ አራት ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት እንደቻለ የተገለፀ ሲሆን፤ ይህ አፈፃፀም ፓርኩ ከውድመትና ዘረፋው በኋላ ወደ ሥራ ተመልሶ ያከናወነውን ሥራም የሚጨምር ነው:: ከተገኘው ገቢ ውስጥ ሦስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ዶላሩ ፓርኩ ካጋጠመው ውድመትና ዘረፋ በኋላ ወደ ሥራ ተመልሶ ካከናወነው የምርት ሥራ የተገኘ ነው:: ከሴት የእጅ ቦርሳ፣ ካልሲ፣ የወንድ ሙሉ ሱፍ፣ የስፖርትና ሌሎች አልባሳት ሽያጭ የተገኘው ይህ የፓርኩ ገቢ፣ ውድመቱና ዝርፊያው ተፅዕኖ እንዳሳደረበት ግልጽ ነው::
በቅርቡ የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክን የጎበኙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ኢንዱስትሪ ፓርኩ በጦርነት ከደረሰበት ጉዳት በማገገም አሁን ያለበት ወቅታዊ የሥራ እንቅስቃሴ የሚደነቅ መሆኑን ገልፀዋል:: በኢንዱስትሪ ፓርኩ እና በአምራች ኩባንያዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት በአፋጣኝ በመጠገንና መልሶ በማቋቋም ወደ ምርት ሂደት ለማስገባት መስዋዕትነት የታከለበት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ያስታወሱት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ፤ ፓርኩን ወደ ሥራ ለመመለስ የተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ውጤት በማምጣታቸው በአሁኑ ወቅት ኢንዱስትሪ ፓርኩ በጥሩ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል:: አምራች ኩባንያዎች የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመቅረፍም ያልተቋረጠ ድጋፍ ለማድረግ ጥረት እንደሚደረግም ተናግረዋል::
ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ያላትን አቅም በመጠቀምና ከዚሁ ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የምታደርገውን መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግር ለማሳካት አምራች ዘርፉ አሁን ካለው አፈፃፀም በብዙ እጥፍ እንዲጨምርና እንዲሻሻል ማድረግ ያስፈልጋል:: የአምራች ዘርፉ እድገት ሊሻሻል የሚችለው ከኢንቨስትመንት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ነው:: የኢንዱስትሪ ፓርኮች ደግሞ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተግባራዊ በማድረግ ለኢንቨስትመንት መስፋፋት ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ ናቸው:: ስለሆነም የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በመፍታትና አፈፃፀማቸውን በማሻሻል መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግሩን ማሳካት ይገባል::
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 19 ቀን 2015 ዓ.ም