አንዳንድ የምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን ከሙያዊ ስነምግባር ውጪ የሆኑ ዘገባዎችን ማሰራጨት በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተለመደ መደበኛ ተግባራቸው ሆኗል። አሁን አሁን ደግሞ ይበልጥ በኢትዮጵያ ላይ ሀሰተኛ እና የተዛቡ ዘገባዎችን በማቅረብ ጭምር የዓለምን ማህበረሰብ በማሳሳት ተግባር ላይ ተጠምደዋል። ሀገሪቱ በሰላም ዙሪያ ያላትን ተነሳሽነትና ዝግጁነት ለዚህም እያደረገች ያለችው ስራ ለመዘገብ ደግሞ ብዕራቸው ይነጥፋል። ያዩና የሰሙትን እንዳላዩ ማለፍ በሌላ በኩል ደግሞ በሬ ወለደ ቅጥፈታቸውን ማራገብ የዘወትር ስራቸው ሆኗል።
ለምሳሌ ያህል በርካታ የእርዳታ እህል ወደ ትግራይ ክልል እየገባ ባለበት ሁኔታ፤ የኢትዮዽያ መንግስት ረሀብን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀመ ነው የሚል አንድምታ ያላቸው ዜናዎች ሲያስተላልፉ ነበር ። የእርዳታ እህል የጫኑ የአለም ምግብ ፕሮግራም መኪኖች ደግሞ የእርዳታውን እህል ይዘው ከገቡ በኋላ ህወሓት ለጦርነት መገልገያ ሲያውላቸው፤ ለሰብአዊ አገልገሎት የገባን የህጻናት አልሚ ምግብ ፣መድሀኒትና ሌላውን ከታለመለት አላማ ውጪ ሲውል አይቶ እንዳላዩ ከመሆን ያለፈ ዘገባ ሲሰሩ አልታዩም። በዝምታ ከመመልከት ያለፈ ምንም ሲሉ አልተደመጡም። እንዳውም ህወሓት በመሬት ላይ የተሸነፈ ሲመስላቸው የአድኑት፤ የድረሱለት ድምጻቸውን ቃላቀባይ በሚመስል መልኩ የህወሓትን መግለጫዎች ሲያራግቡና ሲያስተጋቡ ይታያሉ።
በተለይ ቢቢሲ አማርኛው፣ አልጀዚራ፣ሮይተርሰ፣ሲኤንኤን ፤ አልሀራም እና ሌሎችም ጋዜጦች ጭምር በተለይ የተዛባ እና ሀሰተኛ መረጃዎችን በማቅረብና በማውጣት ስራ ላይ ተጠምደው ዛሬ ለደረስንበት ደረጃ ደርሰዋል። በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብኣዊ መብቶች ምክር ቤት የሰብአዊ መብቶች የባለሙያ ቡድን ያቀረበውን ‹‹ሪፖርት›› የኢትዮጵያ መንግስት እንደማይቀበለው ቢያሳውቅም የመንግስትን አቋም ሳይሆን እነሱ በኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ ለማሳረፍና የኢትዮጵያን ስም ለማጠልሸት ያስችላል ብለው በሚፈልጉት መንገድ ሲዘግቡት ተስተውለዋል።
ለመሆኑ እነዚህ የምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን በዚህ ሙያዊ ባልሆነና ወደ አንድ ጎን ባደላና በተንሻፈፈ ዘገባ ላይ የተጠመዱት ለምን ይሆን? ከዚህስ ምን ያተርፋሉ ? ስንል የሙያው ባለቤት የሆኑ ምሁራንና ጋዜጠኞችን ጠይቀናል።
የአሀዱ ቲቪና ሬዲዮ ስራ አስኪያጀ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ በሰጡት አስተያየት ፤ አሸባሪው ህወሓት የቀደመ ታሪኩ ሀሰተኛ ነገሮችን በመፈብረክ መረጃ ማሰራጨት ነው።ከዛሬ 50 ዓመት በፊት ሲፈጠር ጀምሮ ማህበረሰቡን ያነሳሳበት መንገድ ሀሰተኛ መረጃን በማሰራጨት ነው፤ በደርግ ጊዜም የእርዳታ እህሎችን እየሸጠ የአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ትግራይ ላይ ረሃብ ገባ እያሉ የሚዘግቡበት ጊዜም ነበር። ሀሰተኛ የሆነ መረጃዎችን የሚያስተላልፍባቸው በዚህም ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ የሚያሳስተው አንዳንድ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም ነው። ይሄ አካሄዱ ደግሞ ቀደም ሲልም የሚታወቅ አሁንም የቀጠለበት ነው።
ጫካ በነበረበት ወቅትም በራሱ ልሳን የሚያስተላልፈውም የሀሰት ትርክቶችን ፤ በህዝቦች መካከል የታሪክ መጣረስን በመፍጠር የማጋጨት ስራን ነበር። የሚገርመው አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን በማጭበርበር ከዚህ ቀደም ከህዝብ በዘረፈው ገንዘብ ባለሙያዎችን እየገዛ በሀሰት መረጃ እንዲያሰራጭ የማድረግ ስራን ይሰራ ነበር።አሁንም የቀጠለው በነበረው በሚታወቅበት ታሪኩ ነው።
አሁንም አንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙሃን የሀሰት ወሬውን እንዲቀባበሉት የሚያደርጉለትን ሰዎች በተቋማት ውስጥ በአስፈላጊ ቦታዎች ላይ በማስቀመጥ ፤ለማጭበርበር በዝርፊያ ያከበቱትን ገንዘብ እየተጠቀሙበት ነው። ለምሳሌ የኢትዮዽያ መንግስት የሰላም ጥሪ አድርጎ ለድርድሩ ኮሚቴ መዋቀሩን እነማን እንደሆኑ ጭምር ሲያሳውቅ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን አልዘገቡም ነበር። ህወሓት ግን የሆነች ነገር ከተነፈሰ የአለም መነጋገሪያ ያደርጓታል ። ይሄ የሚያሳየው መገናኛ ብዙሃኑ ለሙያ ያደሩ ሳይሆን በጥቅም የተያዙ መሆናቸውን ነው።
እነዚህ ቡድኖች የእነሱ ጉዳይ አለም አቀፍ ወሬ እንዲሆን በየቦታው ያስቀመጧቸው፤ ተከፍሏቸው የሚሰሩ ተቋማትና ግለሰቦች በመኖራቸው ይህ ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረጉን ይናገራሉ። የቡድኑ አንዱ እስትራቴጂ ውሸትን ደጋግሞ በማሰራጨት እውነት ማስመሰል ነው። በዚህም የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃንን ብሎም አንዳንድ አለምአቀፍ ሚዲያዎችን በጥቅም በመግዛት ለመቆጣጠር የቻሉበት ሁኔታ መኖሩን ያብራራሉ።
ጋዜጠኛ ጥበቡ እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በአሸባሪው ህወሓት ውሸት ከአሁን በኋላ አይታለልም። የአለም ማህበረቡም ቢሆን ቡድኑ እንደልባቸው የሚጋልቡት ፈረስ ሆኖ ተመቻችቶ ስለተቀመጠላቸው አምነው የተቀበሉት ያስመስላሉ። ዋናው ዓላማቸው ግን ህወሓት የእነሱ መጠቀሚያ ስለሚሆን ይሄንን ቡድን ላለማጣት የፈጠራ ወሬዎችን በማሰራጨት ይተባበሩታል።
ወደትግራይ የሚላከው የሰብአዊ እርዳታ ለህዝቡ እንደማይደርሰው መንግስት እያወቀም ትርፍራፊውም ቢሆን ለትግራይ ህዝብ ይድረስ በማለት የእርዳታ እህል ወደ ክልሉ እንዲገባ ሲፈቅድ፤ እነሱ ለወታደሮቻቸው ቀለብ ብሎም ወታደራዊ ግብኣት መግዣ እያደረጉት ይገኛሉ። አለም አቀፍ ሰብአዊ እርዳታዎች በሙሉ ወደ ጦር ካምፕ ይገባሉ። እርዳታ የጫኑ መኪኖች አይመለሱም። ስለዚህ ግን አንድም አለም አቀፍ ማህበረሰቡ ሲጮህ አይሰማም።
የተለያዩ የአለም አቀፍ ተቋማት ልኡካን በእርዳታ ስም ወደ ክልሉ ሲገቡ አለምአቀፍ የቴሌፎን ጥሪዎችን በመስጠት በማስደወልና በማገናኘት ድጋፍ ሲሰጣቸውም ታይቷል። ይህንንም አይዘግቡትም። አማራ ክልል የተፈፀመውን ወንጀል፤ አፋር ክልል ውስጥ የተፈፀመውን ጥፋት ሰብኣዊና ቁሳዊ ውድመቶች አልተዘገቡም። በየክልሉ የተደፈሩ ሴቶች፤ ህፃናትና አረጋዊያንን ጥቃትም ሲናገሩ አይሰማም። ይህንን የሽብር ሀይል ትንፋሽ ለመስጠትና እድሜውን ለማራዘም የሀሰት ወሬውን መቀባበልን ልማዳቸው አድርገውታል ሲሉ ይናገራሉ።
ሌላው አስተያየታቸውን የሰጡን የወሎ ዩኒቨርሲት የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር አቶ እንግዳወርቅ ታደሰ አንዳሉት ፤ የመገናኛ ብዙሃን ሙያ የራሱ የስነ ምግባር መመሪያዎች አሉት። ጋዜጠኝነትም ራሱ የሚመራበት በርካታ መመሪያዎች ሊኖሩት ይገባል። በውጭ መገናኛ ብዙሃን ላይ የምንመለከተው የሀገራቸውን ርዕዮተ አለም ተከትለው ከመሄድ ያለፈ ነፃና ገለልተኛ ናቸው ለማለት የማያስደፍር ነው።
እነዚህ መገናኛ ብዙሃን የሀገራቸውን ጥቅም እስካከበረ ድረስ የሙያውን ስነ ምግባር ስለመከተል ሲያስቡ አይታይም። ለምሳሌ የፌስ ቡክ ካምፓኒ “ ሞት ለራሺያ” ተብሎ መፃፍ ይቻላል ብሎ እስከ መፍቀድ የደረሰ ከስነ ምግባር የወጡ አስተሳሰቦችን ሲያራምዱ ይታያሉ።
አንዳንድ የምእራባውያኑ መገናኛ ብዙሃንም በሀገራቸው የሙያውን ስነ ምግባር በተወሰነ መልኩ ተከትለው እንደሚሰሩ ይታወቃሉ ፤ ነገር ግን በውጭ ሀገራት ጉዳይ በተለይም በአፍሪካ ላይ የሚሰሩት ዘገባዎች ንቀት የተሞላበት፤ መሬት ላይ ያለው ነገር ሳይጣሩ፤ እነሱ የሚፈልጉት አካል ያቀረበላቸውን መረጃ አግንኖ የማቅረብ አዝማሚያ ይታይባቸዋል ብለዋል።
እነሱ የማይፈለጉትን ወገን ደግሞ ይመታልናል፤ ያንቋሽሽልናል ብለው የሚያስቡትን ትኩረት ሰጥቶ ሲሰሩ ይታያል። ይህ ግን የሙያውን ስነ ምግባር የተከተለ አለመሆኑን ያሳያል። መገናኛ ብዙሃኑ ነፃና ገለልተኛ ሆነው እውነተኛ መረጃዎችን እንዲያሰራጩ ቢፈጠሩም፤ በጊዜ ሂደት ያ አስተሳሰብ ጠፍቶ የሀገራትን ጥቅም ብቻ እያስከበሩ ቀጥለዋል።
በምስራቅ አፍሪካ ባለው ሁኔታ አንድ ጠንካራ ሀገር ሳይሆን በግጭት እየተቆራቆዙ የምእራቢያዊያን ፍላጎት የሚያስፈፅሙ የተለያዩ አገራት እንዲኖሩ ይፈለጋል። ይህንን ደግሞ በሚዲያዎቻቸው ሲያንጸባርቁ ይታያሉ። እነሱ ፍላጎታቸውን ለማስፈፀም ቢነሱ አይደንቅም ያሉት አቶ እንግዳወርቅ፤ ይልቁኑ አፍሪካውያን ሀሳባችን መሆን የሚገባው ይሄንን እንዴት መቅረፍ እንችላለን የሚለው ነው ብለዋል።
አቶ ጥበቡ በመፍትሄነት የጠቆሙት ደግሞ፤ሀሰተኛና የተዛቡ መረጃዎችን የሚያወጡና የሚያሰራጩ መገናኛ ብዙሃንን መቋቋም የሚቻለውና እውነታውን ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስገንዘብ የሚቻለው ሀሰቱን ከእውነት ለይተው የሚያወጡ ተቋማትን ማጠናከር ሲቻል ነው። በእነዚህ በኩል ዜናዎች እውነት ወይም ሀሰት መሆናቸው ይረጋገጣል። እነሱም ሀሰተኛ ዜናዎች ሲወጡ ወዲያው በሳተላይት ፎቶግራፎች በማሳየት በተለያየ መልኩ እውነታን ያረጋግጣሉ። ሀሰቱንም ያጋልጣሉ።
በመገናኛ ብዙሃን የወጡ ዜናዎችን በመመልክት ውሸት ሀሰት ከማለት የሚበልጥ ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል። ይህ ሲባል ስለ እያንዳንዱ ጉዳይ በቂ መረጃንና ማስረጃን ይዞ በሀቅ ላይ የተደገፈ ዘገባ ማሰራጨት ተገቢ ነው። በሌላ በኩል ሀሰተኛ ነገሮችን መንግስት እራሱ ብዙ ተከታይ ባላቸው ሚዲያዎች ሀሰተኛ ዜና ይዘው የወጡትን ተአማኒነታቸውን ማሳጣትና ማጋለጥ አለበት።
ሚዲያው የሚገኝበት ሀገር ያሉ የኢትዮዽያን ህዝብ የወከሉ አምባሳደሮች፤ ዲፕሎማቶች ይሄንን ሀሰተኛ መረጃ መታገል አለባቸው። ዲፕሎማቶች ከሀገራቸው ብዙ ገንዘብ እየተከፈላቸው ለሀገራቸው ሲቆረቆሩና ሲታገሉ አይታይም ይሄንን ማስቀርት ግዴታ መሆን አለበት ።
ዲፕሎማቶቻችን በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ይሄንን መታገል ይገባቸዋል። በተጨማሪም ሀሰተኛ ዜና ያሰራጨውን የሚዲያ ተቋም መጠየቅ አለባቸው። ልክ እንደ ባዶ ቤት ትቶ ዝም ከማለት ሉአላዊት ሀገር መሆኗን በሚያሳውቅ ልክ ሁሉም የሀገሪቱ ህዝብ ተናቦ መስራት ይኖርበታል። የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃንም በሀገር ጉዳይ በጋራ በመሆን ምርመራ በማድረግ ዘገባቸውን መስራትና ማጋለጥ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
አቶ እንግዳወርቅ በበኩላቸው፤ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን የሆነ ነገር ሲከሰት ለዛ ምላሽ የሚሰጡ ብቻ መሆናቸው ችግሩ እንዲበባስ አድርጎታል ይላሉ። ይህ ሲባል መገናኛ ብዙሃኑ ቀድመው አጥንተው በአካባቢው የሚገኘውን ተጨባጭ እውነታ ማሳየት አለባቸው። በዚህ ላይ በእቅድ ተይዞ የሀገሪቱን ሉአላዊነት ያስጠበቀ ዘገባ ቢሰራ በተሻለ መልኩ የሀገር ጥቅም ይከበራል።
በሀገራችን በተለይ በእንደዚህ አይነት በጦርነት ወቅት አንድ አይነትና የተናበበ መረጃ ማቅረብ የግድ ነው። የመንግስት የግል ጋዜጠኞች ተብለው በተዘበራረቀ መንገድ መሄዳቸው ቀርቶ እንደ ሀገር በአንድ አቋም የሀገርን ሉአላዊነት በሚያስከብር መልኩ መንቀሳቀስ የግድ የሚል መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመንግስት በኩል ፈጣንና ተገቢው መረጃ ባለመስጠቱ በሌሎች በኩል የሚወጡ መረጃዎች እውነት እንዲመስሉ እየተደረገ ይገኛል። ይሄንን ለመቅረፍ የሚመለከታቸው አካላት በየጊዜውና በአግባቡ መረጃ መስጠት የግድ መሆኑን በመረዳት የተሟላ መረጃ በጊዜው መስጠት ይገባል።
እውነተኛ መረጃዎችን በተቀናጀ መልኩ መስጠት የሀሰት መረጃዎች እንዳይበዙ ያደርጋል። ከዚህም በላይ የሀገሪቱ ዋና ዋና መገናኛ ብዙሃን ችግር አለበት የተባለው ቦታ ድረስ በመሄድ ዘገባ እንዲሰሩ ጥበቃ መስጠት፤ የሚድያ ሰዎች መረጃ ሰብስበው እንዲያሰራጩ መፍቀድ የሀሰት መረጃን ለማስቆም የተሻለ አማራጭ መሆኑን አስረድተዋል።
ባለሙያዎቹ እንዳሉት፤ አንዳንድ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የተዛባ መረጃ የሚያወጡትና ሀሰተኛ ዘገባ የሚያቀርቡት ከህወሓት ጋር ባላቸው የጥቅም ትስስር፤ በምስራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያ ጠንክራና ጎልታ እንዳትወጣ ባላቸው ፍላጎት ነው።ይሄንን መቋቋም የሚቻለውና የኢትዮጵያን እውነት ወደፊት ማምጣት የሚቻለው ሀሰተኛ ዘገባዎችንና የዘገቡትን መገናኛ ብዙሃን በመረጃና በማስረጃ ማጋለጥ ሲቻለ ብቻ ነው። ለዚህም ሀሰተኛውን ዘገባ የሚያጋልጡ ተቃማትን ማጠናከር ያስፈልጋል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን መስከረም 17/2015 ዓ.ም