አዲሱ ስርዓተ ትምህርት በርካታ ነገሮችን ይዞ እንደመጣና ተስፋ እንደተጣለበት ሁሉ በማህበረሰቡ ዘንድ በርካታ ጥያቄዎች እየቀረቡበት ይገኛል:: እናም ጥያቄዎቹን ግልጽ ለማድረግና ምን ይዞ እንደመጣ ለማሳየት በትምህርት ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶች ስርዓተ ትምህርት ዴስክ ኃላፊ ወይዘሮ ዛፉ አብርሃን አነጋገረናል:: እርሳቸው ያሉንንም እንደሚከተለው አቅርበነዋል::
አዲስ ዘመን፡- አዲስ ስርዓተ ትምህርት መተግበር ያስፈለገበት ዋነኛ ዓላማ ምንድ ነው?
ወይዘሮ ዛፉ፡- የአዲሱ ሥርአተ-ትምህርት አላማ ለህይወት ዘመን፣ ለቀጣይ ትምህርትና ለሥራ ዓለም እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆነ ብቃት ያላቸው ዜጎችን ማፍራት ነው። ከዚህም በላይ ዓላማው ከሌሎችም መሰል ባህርያት መካከል የሳይንስና ቴክኖሎጂ እውቀት ያላቸው፣ በፈጠራና በጥልቀት የማሰብ ችሎታ የተጎናጸፉ፣ ችግር ፈቺ የሆኑና ሞራላዊ ኃላፊነት በተሞላበት መልክ ሥራዎችን የሚያከናውኑ ዜጎችን መኮትኮትንም ያጠቃልላል። በዓላማዎቹ ውስጥም በአገር አቀፍ፣ በአህጉራዊ እነ በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ የሚሆኑ ዜጎችን መቅረጽ ነው።
በተጨማሪም እያንዳንዱ ዜጋ ከጾታ፣ ከችሎታ ወይም ከአካል ጉዳት፣ ከብሔር፣ ከሃይማኖት እና ከጂኦግራፊ አቀማመጥ የመነጨ ልዩነት ሳይደረግበት ግላዊ ማንነቱንና እምቅ ችሎታውን አውጥቶ ሁለንተናዊ እድገት እንዲጎናጸፍ ማድረግን ያካትታል።
አዲስ ዘመን፡- የአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ዋነኛ መዳረሻ ምንድን ነው?
ወይዘሮ ዛፉ፡- የአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ዋነኛ መዳረሻ በአገር በአፍሪካና በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ዜጎችን ማፍራት ነው:: በእውቀት ላይ በተመሠረተና በቴክኖሎጂ በሚመራ ኢኮኖሚ ውስጥ ገብተው ውጤታማ እንዲሆኑ ማስቻልም ነው:: የ21ኛው ምእተ-ዓመት ክህሎቶች የታጠቁ፣ በሁለንተናዊ መልክ የደረጁ፣ በሥነ-ምግባር የታነጹ፣ በራሳቸው የሚተማመኑ እና ኃላፊነት የሚሰማቸው የህይወት ዘመን ተማሪዎችን ኮትኮቶ ማብቃትም ነው። ስለሆነም አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ብዙ ነባር ችግሮችን ይፈታል::
አዲስ ዘመን፡- አዲሱ ስርዓተ ትምህርት የሚጠበቅበትን አላማ እንዲወጣ ምን ታስቧል ?
ወይዘሮ ዛፉ፡- አዲሱ ሥርዓተ-ትምህርት ከወረቀት ባሻገር ተግባራዊነቱን ለማረጋገጥ እና ጥራቱን እና ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ በዝግጅት ምዕራፉ የተዳሰሱ በአገሪቱ የተገኘውን አወንታዊ ተሞክሮና በከፍተኛና በተሻለ ደረጃ ለግብ ያበቁ አለምአቀፋዊ ተግባራትን ተጠቅሟል።ሥርዓተ-ትምህርትን ለማቀድ፣ ለመተግበር እና ለመገምገም የሚያስችል አቅጣጫን የሚያሳዩ መርሆዎችንና መመዘኛዎችንም አመላክቷል። በተጨማሪም የክልል መንግስታት መርሐ-ትምህርቶችን ለመገምገም፣ ለመንደፍና ከአካባቢያቸው ጋር ማዋደድ እንዲችሉ አቅጣጫ ተቀምጧል።
አዲሱ የሥርዓተ ትምህርት ማዕቀፍ፣ በነባሩ ሥርዓተ ትምህርት ላይ ለሚነሱ ውስንነቶች ምላሽ የሰጠ እንደሆነ ይታመናል:: በዚህ በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ከተደረጉት ለውጦች እጅግ ጠቃሚ የሆነው ሥርዓተ ትምህርቱ ከዓላማ ላይ ከተመሰረተ ሥርዓተ ትምህርት ወደ ብቃት ላይ የተመሰረተ ሥርዓተ ትምህርት (from objective-based to competency-based) የተደረገው ለውጥ ነው::
ይህ ለውጥ ሥርዓተ ትምህርቱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያከናውናቸው ዋናዋናዎቹ፤ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገት መሠረት የሆኑትን የሂሳብና የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶችን በማስተማር ላይ ያተኮረ፤ የሞራል እሴቶችን በማጎልበት ላይ ያተኮረ ሥርአተ-ትምህርት፤ ተለማጭነትን፣ ለአካባቢ፣ ብሄራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ምላሽ መስጠትን የሚያጠናክርና የህይወት ዘመን ትምህርትን የሚያበረታታ እና መምህራንን በተከታታይ የሙያ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ማሰማራትና ተከታታይ ድጋፍ በመስጠት ሥርአተ-ትምህርቱን እንዲተረጉሙና ከተማሪዎችና ከብሄራዊ እድገት ጋራ እንዲያጣጥሙ የሚያደርግም ነው::
ሁሉም ባለድርሻ አካላት በዚህ መሠረት የተዘጋጀውን ሥርአተ-ትምህርት በሚገባ ለመተግበር የሚያስችል አመራር ለመስጠት፣ ኃላፊነት ለመቀበል እና ሙያቸውን ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን ማረጋገጥ የሚያስችል ሥርዓት በመዘርጋት እንዲሁም የተሻለ የተማሪ ተኮር የመማር ማስተማር ሂደት እና ተከታታይ ግምገማን እውን በማድረግ የሚሰራም ነው:: በአጠቃላይ በትግበራው ሂደት የነበረውን ክፍተት ምላሽ በመስጠት ከወረቀት ባሻገር ተግባራዊነቱን የሚያረጋግጥ ሆኖ የተዘጋጀ ነው::
አዲስ ዘመን፡- ተቀናጅቶ የሚሰጡ ትምህርቶች የመፈጠራቸው መንስኤ ምንድነው ? ችግሮችስ አይፈጥሩም ተብሎ ይታሰባል?
ወይዘሮ ዛፉ፡- ሥርዓተ-ትምህርት ሲከለስም ሆነ ሲቀየር በሳይንሳዊ ጥናት እና ከማህበረሰቡ በሚገኝ ምክረሀሳብ መሰረት ነው:: መንስኤውም የፍኖተ ካርታው ጥናት ግኝት ሲሆን፤ ግኝቱ እንደሚያሳየው ሥርአተ-ትምህርቱ ከሁለተኛ ደረጃ በፊት በሚገኙት እርከኖች የትምህርት አይነቶችን በተናጠል ሳይሆን በተቀናጀ መልክ መስጠት እንዳለበት ያስገነዝባል:: የተለያዩ መንገዶችን በመፍጠር ተማሪዎች በትምህርት ቤቶችም ሆነ ከዚያ ባሻገር ላለው ህይወታቸው የሚያስፈልጉ እውቀት ክሀሎቶችንና ብቃት እንዲያዳብሩ ማድረግንም እንደሚያስፈልግ ይጠቁማል:: ምክንያቱም በየደረጃው የሚጠበቅባቸውን የባህሪይ መገለጫ በመላበስ ወደ ቀጣይ የትምህርት እርከን ሲደርሱ ወደ ስራ ዓለም ለመግባት ራሳቸውን እና ማህበረሰቡን ለማገልገል የሚያስችል ብቃት እውቀት እና ክህሎት ይላበሳሉ::
ይህ አሰራር እውነተኛ የህይወት ሁኔታዎችን የሚያንጸባርቅ፣ ዕውቀትና ክህሎትን ከአንድ የትምህርት መስክ ወደሌላ የትምህርት መስክ ማሸጋገርን የሚያበረታታና እውቀትን በተበታተነና በተናጠል መስጠትንና በትምህርት አይነት ላይ ብቻ የተገደበ የትምህርት አሰጣጥን የሚያስወግድ አቀራረብን ሥራ ላይ ማዋል የሚያስችል ነው:: ሰፋ ካለ መሠረት ከሚመጡ ተማሪዎች ፍላጎቶችና ችሎታዎች ጋር የተጣጣሙ የተለያዩና የተቀናጁ የትምህርት ልምዶችን መስጠት ደግሞ የተለያዩ የትምህርት ዘርፎችን ያቀፈና ለተማሪዎች ግላዊ እድገት፣ የህይወት ዘመን ትምህርት እና ቅጥር አማራጭ መንገድን የሚሰጥ ነው:: የሥራና የቴክኒክ ትምህርት በማስተዋወቅ ፈጠራን፤ ችግር ፈቺነትን የተላበሰ ዜጋን መቅረጽ ያስችላልም:: በዝግጅቱ ምዕራፍ እና በአተገባበሩ ሁኔታ አዲስ ከመሆኑ አንጻር ፍጹም ነው ማለት ባይቻልም ለውጡን ለመተግበር አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን ትኩረት በመስጠት እንዲተገበር ሆኗል::
አዲስ ዘመን፡- የአዲሱ የትምህርት ስርዓትን ተከትሎ ያጋጠሙ ችግሮች ይኖራሉ ? በተለይ ተንሳፋፊ የሚባሉ መምህራን እንደተፈጠሩ ከመምህራን አንደበት እየሰማን ነው:: እናም መፍትሄው ምንድነው ?
ወይዘሮ ዛፉ፡-እስካሁን ያጋጠመ ችግር የለም:: በአዲሱ ሥርአተ-ትምህርት ከሁለተኛ ደረጃ በፊት በሚገኙት እርከኖች የትምህርት አይነቶችን በተናጠል ሳይሆን በተቀናጀ መልክ መስጠት እንደ አገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በጥናት የተደገፈ ሲሆን፤ ዋናው ለውጡን የሚተገብሩት መምህራን ደግሞ ምንም አይነት ችግር እንዲገጥማቸው አያደርግም:: ይልቁንም በአጭር፤ በመካከለኛና በረጅም ሥልጠና አቅም መገነባት አስፈላጊ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራበታል:: የመምህራን ትምህርት ሥርዓተ-ትምህርትም ከአጠቃላይ ትምህርት ሥርዓተ ትምህርት ጋር ጎን ለጎን አቀናጅቶ ለማስኬድ ወደ ትግበራ ተገብቷል::
አዲስ ዘመን፡- ከቋንቋ ጉዳይ ጋር ተያይዞ የሚነሱ አስተያየቶች አሉ:: አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ከቋንቋ ትምህርት አሰጣጥ አንጻር ይዞት የመጣው አዲስ ነገር ምንድን ነው ?
ወይዘሮ ዛፉ፡- አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የተቀረጸው ከቅድመ አንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል ሲሆን፤ በቅድመ አንደኛ ደረጃ ሕጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋ ሲማሩ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ የእንግሊዘኛ ትምህርትን እንደ አንድ የትምህርት አይነት የሚማሩ ሆኖ ከ3ኛ ክፍል ጀምሮ የአጎራባች ቋንቋን ጨምሮ በአጠቃላይ ሦስት ቋንቋዎችን ይማራሉ:: ይህ ደግሞ ሳይንሱ የሚያስቀምጠው ነው:: እናም ሦስትና ተጨማሪ ቋንቋ ለምን ተማሩ የሚለው ከተነሳ ሳይንሱ ለምን ተተገበረ እንደማለት ይመስላል::
አዲስ ዘመን፡- በአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት መስጠቱ ከአለው የዘመኑ የትምህርት ስርዓት አኳያ ምን ያህል ውጤታማ ይሆናል፤ ማለትም የመርጃ መጸሃፍትና ሌሎች ዘመኑን የመጠነ ድጋፍ ሰጪ የትምህርት መሳሪያ ከማግኘት አንጻር?
ወይዘሮ ዛፉ፡- በአፍ መፍቻ ቋንቋ ማስተማር ሳይንሳዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሲሆን፤ በአዲሱሥዓተ-ትምህርት ሕጻናትን በራሳቸው ባህልና ወግ ከአካባቢያቸው ጋር የተዋሀደ እውቀትና ክህሎት በማስጨበጥ አካባቢያቸውንና ተፈጥሮን የሚያደነቁ እንዲሁም የሚንከባከቡ ዜጋን ለመቅረጽ ታሳቢ አድርጎ የሚሰራበት ሆኗል:: ሕጻናቱ በየደረጃው የሚጠበቅባቸውን የመገለጫ ባህሪይ በመላበሰ ወደ ሚቀጥለው እርከን በመሸጋገር የተግባቦት፣ አእሞራዊ እና አካላዊ ብቃታቸው የዳበረ እንዲሁም ወደ ቀጣይ እርከኖች ሲሸጋገሩ ዘመኑን ከአገራዊ እውቀት ጋር ለመዋጀት የሚያስችሉ ያደርጋቸዋልም በሚል እየተከወነ ያለ ነው::
አዲስ ዘመን፡- ሦስተኛ ክፍል ላይ በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ተጨማሪ የአጎራባች ቋንቋዎችን መስጠት ይጀመራል የሚል ነገር አለ ይህ ነገርስ የእርስ በእርስ ትስስርን ከማጠናከር አኳያ ያለው ውጤታማነት እንዴት ይለካል? ማለትም እንደ ደቡብ ያሉ ክልሎች ብዙ አጎራባች ቋንቋዎች ይኖሯቸዋል:: በምን መስፈርት ተነጥለው የመማር ማስተማር ስርዓት ውስጥ ይገባሉ ?
ወይዘሮ ዛፉ፡- የአጎራባች ቋንቋዎችን እንደ ክልሎች ተጨባጭ ሁኔታ የሚታይ ይሆናል:: የዚህን ሙሉ ኃላፊነትም የሚወስዱት ክልሎች ይሆናሉ:: ምክንያቱም የትኛው ቋንቋ የተሻለ ተግባቦትና ትስስር ይፈጥራል እንዲሁም የትኛው ለማስተማር ብቁ ነው የሚለውን ጠንቅቀው ያውቁታል:: ይህ ሲሆን ግን እንደ ትምህርት ሚኒስቴር ጥልቅ ክትትልና ግምገማ ይደረጋል::
አዲስ ዘመን፡- ስምንተኛ ክፍል ያጠናቀቁ ተማሪዎች ወደ ሚቀጥለው ክፍል መሸጋገር ካልቻሉ ወደ ሙያ መስክ እንዲሰማሩ ይደረጋል:: ይህ ከዕድሜ ለጋነት ጋር ተያይዞ ችግር አይፈጥርም ወይ ?
ወይዘሮ ዛፉ፡- የሙያ ትምህርት በአዲሱ ፖሊሲ ተቀርጾ እንዲሰጣቸው የሆነው ሙያ እንዲያገኙ ለማድረግ እንጂ ሌላ ነገር ታስቦ አይደለም:: በዚያ ላይ ትምህርቱ የሚሰጠው ለቀጣዩ ትምህርት እንዲያግዛቸውና አካባቢያቸውን በቻሉት ልክ እያገለገሉ እንዲሄዱ ለማስቻልም ነው:: ስለሆነም ስምንተኛ ክፍል ላይ የተማሪው ችግር ካልሆነ በስተቀር ማቋረጥም ሆነ ትምህርቱ እዚያ ላይ ያበቃል የሚባል ነገር የለም:: 12ኛ ክፍል ብቻ ነው ተመረቀ፤ አጠናቀቀ ሊባል የሚችለው:: ይህም ቢሆን ሁለት መሰረታዊ ነገሮችን ታሳቢ አድርጎ የተከናወነ ነው:: የመጀመሪያው ምርጫቸውን እንዲያስተካክሉ ለማድረግ ሲሆን፤ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ የሚወዱትን፣ ውጤታማ የሆኑበትን የትምህር መስክ እንዲመርጡ ያግዛቸዋል:: ሁለተኛው ደግሞ 12ኛ ክፍልን ሲያጠናቅቁ የአንድ ሙያ ባለቤት በመሆን በአካባቢያቸው ወደ ሥራ እንዲሰማሩ የሚያስችላቸው ነው:: ስለሆነም እንደማንኛውም የክፍል ደረጃ ተምሮና ሰርቶ የሚያልፍባቸው እንጂ የተለየ ነገር የሚገጥምበት አይደለም:: እናም እንደእነዚህ አይነት ስጋቶች ሊኖሩ አይገባም::
አዲስ ዘመን፡- ክልሎች በራሳቸው መጸሐፍ ያዘጋጃሉ:: ይህ ዝግጅት አድሏዊነት እንዳይኖረው ምን ያህል ይቃኛል፤ የተሳሳቱ ትርክቶች እንዳይኖሩበትስ ምን ያህል ጥበቃ ተደርጎበታል? በተለይም ከታሪክ አንጻር? የታሪክ ሽሚያና ጀግኖችን የማጠልሸት ልኬትን ማረም ላይ ምን አይንት ጽዱነት አለው?
ወይዘሮ ዛፉ፡- የስርዓተ ትምህርት ሰነዶች እንደ ትምህርት ሚኒስቴር በአገር አቀፍ ደረጃ ይዘጋጃሉ:: በተዘጋጁት ስታንዳርድ መሰረት ክልሎችም በራሳቸው አካባቢ ባህል እና ወግ የአንደኛ እና የመካከለኛ ደረጃ የመማሪያ እና ማስተማሪ መጽሀፍትን ያዘጋጃሉ:: ይህ ሲሆን ግን ደረጃውን እና ጥራቱን የጠበቀ ሥርዓተ ትምህርትን ተከትለው ነው:: በአጠቃላይ ትምህርት ሚኒስቴር ስታንዳርዱን ለማስጠበቅ ክትትል እንድናደርግ ያደርጋል::
አዲስ ዘመን፡- በአዲሱ የትምህርት ስርዓት የድሮ ትምህርቶች ዳግመኛ እንዲመጡ ሆነዋል:: ምክንያቱ ምንድነው ?
ወይዘሮ ዛፉ፡- እነዚህ ትምህርቶች ዳግም የመጡበት ዋነኛ ምክንያት የትምህርት ጥራቱ እና ብቁ ዜጋን ከመቅረጽ አንጻር የጎላ ድርሻ አላቸው፤ ለውስንነቶችም ምላሽ ይሰጣሉ:: ለአብነት በግብረገብ የታነጸ ዜጋ ከመቅረጽ አንጻር፤ ሥራና ትምህርትን ማስተሳሰር፤ ትምህርትን፤ በችሎታቸው እና በዝንባሌያቸው መርጠው መማር እና መስራት፤ እውቀትን ክህሎትን ማጎልበት ያስችላሉ:: በተለይም አገራዊ የሆኑ ማንነቶችን በሚገባ አውቀው የመጠቀምን ክህሎትን ያዳብራሉ:: የፈጠራ ሥራንም ያበረታታሉ::
አገርን ከፍ ከማድረግ አኳያም የማይተካ ሚና አላቸው:: በመድሃኒቱ፣ በባህሉ፣ በሥራ ፈጠራው የተሻሉ ነገሮችን ለማየትም ጉልህ ድርሻ አላቸው:: እነዚህ ትምህርቶች በአብዛኛው ከመጀመሪያ ደረጃ ጀምሮ ሊሰጡ የሚችሉ ናቸው:: ምክንያቱም መሰረት የሚጣለው እዚህ የትምህርት ደረጃ ላይ ስለሆነ:: ለምሳሌ የግብረገብ ትምህርትን ብናነሳ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ድረስ እንደ አንድ የትምህርት አይነት የሚሰጥ ይሆናል የእርሻ ትምህርትም ለ11ኛ እና 12ኛ ክፍል በሙያው መስክ እና እንደ አንድ የትምህርት አይነት ይሰጣል::
አዲስ ዘመን፡- የእንግሊዘኛ ቋንቋ በፊት በሳምንት ስድስት ጊዜ ይሰጥ ነበር:: በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ወደ ሶስት እንዲወርድ ተደርጓል:: ይህ የእንግሊዘኛ ቋንቋን የባሰ አያቆረቁዘውም ወይ?
ወይዘሮ ዛፉ፡- የተከለሱና ወደ ተግባር የተገባባቸው በርካታ ነገሮች አሉ:: ሙሉውን ሳያነቡና የተከለሰውን ሳያዩ አስተያየት መስጠት ተገቢነት የለውም:: የእንግሊዘኛ ቋንቋን በተመለከተ የተቀነሰ ነገር የለም:: ቀድሞ በነበረበት ሁኔታ ይቀጥላል::
አዲስ ዘመን፡- አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ሲቀረጽ የእንግሊዙ ኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ከሥርዓተ ትምህርት ጥናት እስከ መጻሕፍት ዝግጅት በገምጋሚነት መሳተፉ የነበረው ፋይዳ እንዴት ይገለጻል?
ወይዘሮ ዛፉ፡- ስርዓተ ትምህርት ሲዘጋጅ ጥናቶችም ሆኑ ዝግጅቶች እንዲሁም ግምገማዎች በገለልተኛ አካላት መታየት ይኖርባቸዋል:: ምክንያቱ ደግሞ ከአገራዊነት አልፎ አለማቀፋዊነትን የጥራት ደረጃውንም ለማምጣት ያስችላልና ነው:: ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ችግሮችን በሚገባ ለመመልከትም ያስችላል:: ስለሆነም በዓለም ደረጃ ተቀባይነት ያለውንና ብዙ ቡድንን ያቀፈውን ኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲን በጥራት አረጋጋጭነት የተሳተፈ ሲሆን 30 በመቶ በዓለም አቀፍ 70 በመቶ ቡድኑን ያዋቀረው በአገር ውስጥ ባሉ አማካሪዎቹ አማካኝነት ነው:: ይህ ደግሞ ለአገርኛው የተጠጋ ስራ እንዲሰራ አስችሎታል:: በተመሳሳይ ከኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ የሂሳብ ትምህርትን ከ9 እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን መጽሐፍት እንዲገመግም ተደርጓል:: በቀጣዮቹ ሥራዎች ላይም አብረው የሚዘልቁ ይሆናል::
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ማብራሪያ እናመሰግናለን::
ወይዘሮ ዛፉ፡- እኔም አመሰግናለሁ::
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 16 ቀን 2015 ዓ.ም