የኢትዮጵያን የወጪና ገቢ ንግድ በማቀላጠፍና የኢንቨስትመንት ፍሰቱን በመጨመር ለአገራዊ ምጣኔ ሀብት እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ተስፋ የተጣለበት የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና (Dire Dawa Free Trade Zone)፣ ነሐሴ 8 ቀን 2014 ዓ.ም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ ስራ እንደጀመረ ይታወሳል።በድሬዳዋ የሚገኘውን የኢንዱስትሪ ፓርክና ደረቅ ወደብን ከዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት፣ ከባቡርና ከመንገድ ትራንስፖርት ጋር በማቀናጀት እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ የባንክና የጉምሩክ አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ ወደ አገልግሎት እንዲገባ ለማድረግ የሚያስችሉት ተግባራት ሲከናወኑ ከቆዩ በኋላ ስራ እንዲጀምር የተደረገው ነፃ የንግድ ቀጠናው፤ ለበርካታ ዓመታት ከነፃ የንግድ ቀጠና አሰራር ርቆ ለኖረው የኢትዮጵያ ንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ እድገት ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረው ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ነፃ የንግድ ቀጠናውን መርቀው ስራ ባስጀመሩበት ወቅት ‹‹ነፃ የንግድ ቀጠና ጥቅል አገራዊ ምርትን፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትንና የወጪ ንግድን ለማሳደግ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው።የበለፀጉት አገራት በንግድና ኢንቨስትመንት ስራቸው ትልቅ ለውጥ ያስመዘገቡት እንደነፃ የንግድ ቀጠና ያሉ አሰራሮችን በመዘርጋታቸው ነው።በድሬዳዋ የተቋቋመው ነፃ የንግድ ቀጠና የራሱ ሕግና አሰራር ያለው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረ ሌላ ትንሽ ኢትዮጵያ ነው።ነፃ የንግድ ቀጠናው እንዲቋቋም የተፈለገበት ምክንያት የተቀላጠፈ የሎጂስቲክስና የንግድ ስርዓት ለመዘርጋት ነው።ቀጠናውን በአግባቡ በመጠቀም በጥቅል አገራዊ ምርት፣ በወጪና ገቢ ንግድ እንዲሁም በኢንቨስትመንት ፍሰት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ ይገባል›› ሲሉ አብራርተው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ኢትዮጵያ 40 እና 50 ሚሊዮን ሕዝብ እያላት በነበረው አሰራር ልትቀጥል እንደማትችልና ቀልጣፋ አገልግሎት ለማቅረብ የሚያስችሉ አዳዲስ አሰራሮችን ማወቅና መተግበር እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ በተለይ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ነፃ የንግድ ቀጠናው የፈጠረውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በገቢና ወጪ ንግድ እንዲሁም በኢንቨስትመንት ላይ እመርታ እንዲመጣና ውጤት እንዲመዘገብ ከመንግሥት ጋር በመተባበር መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና የወጪና ገቢ ንግድን በማቀላጠፍ፣ የኢንቨስትመንት ፍሰትን በማሳደግና የስራ እድል በመፍጠር ለድሬዳዋ ብቻ ሳይሆን ጠቅላላ የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት እድገት እንዲያስመዘግብ አወንታዊ ሚና እንደሚኖረው ይጠበቃል። የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ካሚል ኢብራሂም ነፃ የንግድ ቀጠናው በይፋ ከተመረቀ በኋላ ብዙ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በነፃ ንግድ ቀጠናው ውስጥ ለመሰማራት ፍላጎት እያሳዩ እንደሆነ ይናገራሉ።
እንደ አቶ ካሚል ገለፃ፣ ነፃ የንግድ ቀጠናው በሌሎች አገራት ከሚገኙ ብዙ ነፃ የንግድ ቀጠናዎች ያላነሰ የመሰረተ ልማት አቅርቦት አለው። በዚህም ምክንያት በቀጠናው ውስጥ ገብተው በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ባለሀብቶች ቁጥር ጨምሯል።
እስካሁን ድረስ 48 ባለሀብቶች በነፃ የንግድ ቀጠናው ለመሰማራት ፍላጎት አሳይተው ተመዝግበዋል። ከዚህ በተጨማሪም በርካታ ባለሀብቶች ስለነፃ ንግድ ቀጠናው ገለፃ ስለተደረገላቸው፤ በቀጣይ ጊዜያት በነፃ የንግድ ቀጠናው ለመሰማራት ፍላጎት የሚያሳዩና የሚመዘገቡ ባለሀብቶች ቁጥር ከዚህም በእጅጉ የበለጠ እንደሚሆን ይጠበቃል።ምዝገባው በአዲስ አበባም እየተካሄደ ይገኛል።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፣ ወደ ነፃ የንግድ ቀጠናው ገብተው ለመሰማራት ፍላጎት ካሳዩት ባለሀብቶች መካከል በአምራች ዘርፎች የተሰማሩ ይገኙበታል። ከዚህ በተጨማሪም በአገልግሎትና በሎጂስቲክስ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሀብቶችም ወደ ነፃ የንግድ ቀጠናው እየገቡ ነው።
ቀልጣፋና ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ በመፍጠር በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ለመሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶችን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማስተናገድ ዘርፈ ብዙ ዝግጅቶች እንደሚያስፈልጉ አይካድም። በዚህ ረገድ የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ለባለሀብቶች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ የነፃ ንግድ ቀጠናው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ከማል ይገልፃሉ።እርሳቸው እንደሚሉት፤ የነፃ ንግድ ቀጠናውን መቋቋም ተከትሎ እየጨመረ የመጣውን የባለሀብቶች ፍሰት በብቃት በማስተናገድ ነፃ የንግድ ቀጠናውን ውጤታማ ለማድረግና አገራዊ ተጠቃሚነት እውን እንዲሆን የባለሀብቱን ፍሰት የሚመጥን አገልግሎት ለማቅረብ እየተሰራ ነው።
‹‹ነፃ የንግድ ቀጠናውን መቋቋም ተከትሎ የባለሀብቶች ፍሰት እየጨመረ በመምጣቱ እኛም ብዙ ዝግጅቶችን እያደረግን ነው።የሥራ መመሪያዎችንና ደንቦችን አዘጋጅተን ጨርሰናል።በነፃ የንግድ ቀጠናው ውስጥ የማምረቻ፣ የሎጂስቲክስና የመጋዘን (Warehouse) አገልግሎቶች ይሰጣሉ።የንግድ ቀጠናውን የአገልግሎት አቅም፣ እየጨመረ ከመጣው የባለሀብቶች ፍሰት ጋር ለማጣጣም መሬትን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶችን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ ነው›› ይላሉ።
በሌላ በኩል የአንድ ማዕከል አገልግሎት ይሰጣሉ ተብለው የሚጠበቁ ተቋማት ነፃ የንግድ ቀጠናው ስራውን እያከናወነ ባለበት ፍጥነት ስራቸውን የማከናወናቸው ጉዳይ እንደስጋት ሊነሳ እንደሚችል አቶ ካሚል ይጠቅሳሉ። ‹‹ለባለሀብቶች አገልግሎት የሚሰጡ የመንግሥት የንግድ፣ የኢንቨስትመንት፣ የኢምግሬሽን፣ የጥራትና ደረጃ፣ የሎጂስቲክስና ሌሎች ተቋማት ነፃ የንግድ ቀጠናው እየሄደበት ባለው ፍጥነት ልክ ላይሄዱ ይችላሉ የሚል ስጋት አለን›› ይላሉ። ይህን ስጋት ለማስወገድ በቅንጅት መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
‹‹ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ የነፃ የንግድ ቀጠና አሰራርን ተግባራዊ ባለማድረጓ ብዙ ጥቅሞችን አጥታለች›› የሚሉት አቶ ካሚል፣ ነፃ የንግድ ቀጠናው ንግድና ኢንቨስትመንትን በማነቃቃት ለድሬዳዋ ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ ያለው በመሆኑ ለውጤታማነቱ መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተጨባጭ ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባቸው ያስገነዝባሉ።
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ባለሀብቶችን በሚገባ ለማስተናገድ ተገቢውን ዝግጅት ማድረግ እንዳለበትና በባለሀብቶች ፍሰት የአካባቢው ማኅበረሰብ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ ስለሚሆን ኅብረተሰቡ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ለማቅረብ ተጠቃሚነቱን ማሳደግ እንደሚገባውም ይመክራሉ።
በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የኢንቨስትመንት ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ሐሰንም ነፃ የንግድ ቀጠናው መቋቋም ለከተማዋ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ማደግ አዎንታዊ ሚና እንዳለው ይናገራሉ።ከነፃ ንግድ ቀጠናው መቋቋም በኋላ ባለሀብቶች ከአገር ውስጥ ከውጭ አገራት በመምጣት የንግድ ቀጠናውንና ከተማዋን እየጎበኙና ብዙዎቹም በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍላጎት እያሳዩ እንደሆነም ይገልፃሉ።
በተለያዩ ምክንያቶች የተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች የከተማዋ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንዲዳከም አድርገውት እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ መሐመድ፣ በአሁኑ ወቅት የከተማዋ ሰላም የተረጋጋና አስተማማኝ በመሆኑ የኢንቨስትመንት ፍሰቱም እየተነቃቃ እንደሚገኝ ይገልፃሉ። ‹‹የከተማዋ ሰላም የተረጋጋ በመሆኑ ስራ ያቆሙት እየተከፈቱ ነው፤ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችም ወደ ስራ እየገቡ ይገኛሉ። የኢንዱስትሪውም ሆነ የአገልግሎት ዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃት እያሳዩ ነው›› በማለት የከተማዋ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ስላለበት ወቅታዊ ሁኔታ ያስረዳሉ።
እንደርሳቸው ገለፃ፣ የከተማዋ አስተዳደር ባለሀብቶችን ለመቀበልና ቀልጣፋ የኢንቨስትመንት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ አሰራሮችን አዘጋጅቷል። አስተዳደሩ አዋጭ የሆኑ 31 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን በመለየት ባለሀብቶች ግንዛቤ እንዲኖራቸው በተለያዩ ቋንቋዎች መረጃዎችን አደራጅቷል።ድሬዳዋ ከወደብ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝ የኢንዱስትሪ ከተማ በመሆኗ የከተማዋ ኢንቨስትመንት ለስራ እድል ፈጠራ ከሚኖረው አስተዋጽኦ አንፃር ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ዘርፎች እንዲሰማሩ አስተዳደሩ እንደሚያበረታታም ይናገራሉ።
አቶ መሐመድ እንደሚሉት፣ በአሁኑ ወቅት በድሬዳዋ ከአንድ ሺ 200 በላይ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ ይገኛሉ።ከእነዚህ መካከል 80ዎቹ ግዙፍ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ሲሆኑ አንዳንዶቹም በመጠናቀቅ ላይ ናቸው። ቀደም ሲል ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች መካከል አንዱ የነበረውን የመሬት ችግር ለመፍታት በተሰሩ ስራዎች፤ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርክ/ነፃ የንግድ ቀጠና መግባት ያለባቸውን ወደ ቀጠናው እንዲገቡ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ከተማ አስተዳደሩ ወዳዘጋጃቸው ስፍራዎች ገብተው እንዲሰሩ የሚያስችል የክላስተር አደረጃጀት ተግባራዊ ተደርጓል። ባለሀብቶች ለኢንቨስትመንት ማሟላት የሚጠበቅባቸውን መስፈርቶች አሟልተው በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገቡ ለማድረግ ለልማት የሚውሉ ቦታዎችን ቀድሞ በመለየትና የካሳ ክፍያዎችን በመፈፀም ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ ለመፍጠር እየተሰራ ነው።
በ2015 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ ለ490 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ፈቃድ ለመስጠት፣ 10 ትልልቅ ሆቴሎችን ለመገንባት፣ ለ17ሺ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር እቅድ የተያዘ ሲሆን፤ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ለኢንዱስትሪ ዘርፍ ነው። ከዚህ በተጨማሪም የመካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም በማሳደግና የስራ እድል ፈጠራ አቅማቸውን በመጨመር ወደ ከፍተኛ የአምራችነት ደረጃ እንዲሸጋገሩ ማድረግ የዓመቱ ትኩረት እንደሚሆን አቶ መሐመድ ገልፀዋል።
‹‹የኢንቨስትመንት ዘርፍ ችግሮችን በመፍታት የከተማዋን የኢንቨስትመንት ፍሰት ለመጨመር ዘርፉ በቦርድ እንዲመራ የተደረገ ሲሆን ሰብሳቢም የከተማዋ ከንቲባ ናቸው።ሁሉም የኢንቨስትመንት ዘርፍ ጉዳዮች በቦርዱ እየታዩ የዘርፉ ችግሮችም ሆኑ የባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች ፈጣንና የተደራጀ ምላሽ እንዲያገኙ ይደረጋል›› ይላሉ።
‹‹ነፃ የንግድ ቀጠናው ይፈጥራል ተብሎ የሚታሰበው የሥራ እድል ከድሬዳዋ አልፎ ለምስራቁና ለሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ጭምር የሚተርፍ ነው›› የሚሉት አቶ መሐመድ፤ ድሬዳዋ ከተማ ነፃ የንግድ ቀጠናው የፈጠረውን እድል በመጠቀም ጭምር በኢንዱስትሪ መናኸሪያነት የሚታወቀውን ስሟን (Industrial Brand) ለመመለስ ጥረት እያደረገች እንደምትገኝም ተናግረዋል።
የምጣኔ ሀብት ጥናት ምሁራን እንደሚያስረዱት፤ ነፃ የንግድ ቀጠናው የምጣኔ ሀብት ትስስርን ለማጎልበት ይረዳል።ኢንቨስትመንትን በማሳደግና ተጨማሪ የስራ እድሎችን በመፍጠር የሥራ አጥ ቁጥር እንዲቀንስ ያግዛል።የገበያ አማራጮች እንዲጨምሩ በማድረግ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲያድግም አስተዋፅኦ ያበረክታል።ይህም የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ ተጨማሪ አቅምና አማራጭ ይፈጥራል።አገር በቀል ባለሀብቶች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና አሰራሮችን እንዲለምዱ እድል ይፈጥርላቸዋል።ከዚህ በተጨማሪም የወጪና ገቢ ንግድን በማቀላጠፍ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በኢንቨስትመንት ላይ እንዲሰማሩ ያበረታታቸዋል።የንግዱ መፋጠን ደግሞ የምርት ፍላጎትን ለመጨመርና ደንበኞችን ለማፍራት ያስችላል።ይህም ነፃ የንግድ ቀጠና ከንግድ ልውውጥ በተጨማሪ የአገር ውስጥና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን የማሳደግም ድርብ አወንታዊ አስተዋፅኦ እንዳለው ያመለክታል፡፡
የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና፤ በንግድ ልውውጥና በኢንቨስትመንት ፍሰት ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማቃለል ከተተገበሩ የመፍትሄ አማራጮች መካከል አንዱ ተደርጎ ሊጠቀስ የሚችል ነው።ነፃ የንግድ ቀጠናው አዳዲስና ሰፊ የሆኑ የሥራ እድሎችን ለመፍጠር፣ ተኪ ምርቶችን ለማምረት፣ የእውቀት ሽግግርን ለማሳደግ እንዲሁም ለአገር ውስጥ የቀረቡ ምርቶችን ለማከማቸትና የሎጀስቲክስ ወጪን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።ይህም አገራዊ የሎጂስቲክስ ተወዳዳሪነትን ትርጉም ባለው መልኩ ሊለውጥ የሚችል በመሆኑ የአገሪቱን የገቢና ወጪ ንግድ ስርዓት ለማቀላጠፍ ያግዛል።አሰራሩ የሚያስገኛቸው ጥቅሞችና የሚፈጥራቸው እድሎች የምርት ወጪን በመቀነስ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋትም ትልቅ ሚና ይኖረዋል።እነዚህ ሁሉ ጥቅሞች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለጥቅል አገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት ዓይነተኛ ፋይዳ አላቸው።
በነፃ የንግድ ቀጠናዎች ውስጥ የሚተገበሩ ህጋዊ አሰራሮች ቀለል ያሉና ቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረዶችን የሚቀንሱ በመሆናቸው ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ለመሰማራት የሚያደርጉትን ጥረት በአንፃራዊነት ቀላል ያደርጉላቸዋል።በነፃ የንግድ ቀጠናው ውስጥ ገብተው የሚሠሩ ባለሀብቶች፣ አስመጪና ላኪዎችም ሆኑ ድርጅቶች የልዩ ልዩ ማበረታቻዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ።ይህ ደግሞ የአገር ውስጥ እና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ጉልህ ሚና ይኖረዋል።
ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ከሚሰጠው ከነፃ የንግድ ቀጠና ስርዓት ርቃ መቆየቷ ብዙ ጥቅሞችን እንዳሳጣት እየተገለጸ ነው።የእነዚህ ጥቅሞችና እድሎች መታጣት ደግሞ በአጠቃላይ እድገቷ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደረባት አይካድም።ድሬዳዋም ቀድሞ ትታወቅበት ከነበረው የኢንዱስትሪና የንግድ መናኸሪያነቷ ርቃ መቆየቷ ይታወቃል። በድሬዳዋ የተቋቋመውን ነፃ የንግድ ቀጠና ይህን ሁኔታ ለመቀየር ጥሩ እድል ይዞ መጥቷል።ስለሆነም በድሬዳዋ የተቋቋመውን ነፃ የንግድ ቀጠና በሚገባ በመጠቀም የድሬዳዋን የኢንቨስትመንት ፍሰት ማሳደግ ይገባል፤ ከድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና መልካም ተሞክሮዎችን በመቀመርና በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎችም ተጨማሪ ነፃ የንግድ ቀጠናዎችን በማቋቋም አገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገቱ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲያስመዘግብ ማድረግ ይገባል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን መስከረም 12 ቀን 2015 ዓ.ም