ከ48 ዓመታት በፊት፤ መስከረም 3 ቀን 1967 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ በፊት ለፊት ገጹ እንዲህ አለ። ‹‹እንኳን ከ፲፱፻፷፮ ዓ.ም ወደ ፲፱፻፷፯ ዓ.ም አዲሱ ዓመት ከሰላማዊ የአስተዳደር ለውጥ ጋር በደህና ያሸጋገራችሁ፤ ይህ ያለምንም ደም መፋሰስ የተጀመረው ‹ኢትዮጵያ ትቅደም› ዓላማ መሰላል ሆኖ የመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ኑሮ የሚቀራረብበት፣ አንድነታችንን የሚያጠናክርበት ዘመን እንዲሆን እንመኛለን። ‹ኢትዮጵያ ትቅደም!› መጪው ዘመን የሰላም የለውጥ ጊዜ ይሁንልን!››
መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም የኢትዮጵያን የታሪክ ማርሽ የቀየረ ነው። ለሺህ ዘመናት የኖረ ንጉሣዊ ሥርዓት የተገረሰሰበት ነው። ኢህአዴግ ግንቦት 20ን ብልጽግና መጋቢት 24ን ቢያቆለጳጵሱም የመስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ማርሽ ቀያሪነት ግን ገናና ነው። በኢትዮጵያ የመንግሥታት ታሪክ ውስጥ መሰረታዊ የሚባል የሥርዓት ለውጥ ያመጣ ነው። ኢህአዴግ የ17 ዓመት ታሪክ ያለውን ደርግን ነው ያስገወደ፣ ብልጽግናም የ27 ዓመት ታሪክ ያለውን ኢህአዴግን ነው የለወጠው። ደርግ ግን ለሺህ ዘመናት የኖረውን ንጉሣዊ ሥርዓት ነው ያስወገደው።
ከእነዚህ ጋር ሲነጻጸር መስከረም 2 በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ልዩ ነው። ምናልባት ግንቦት 20 እና መጋቢት 24 በመጥፎውም በደግም ስማቸው ሲደጋገም እንሰማ ይሆናል። ይህ የሆነው ግን ከታሪክነት ይልቅ ገና በዜናነት ደረጃ ስላሉ ነው። መስከረም 2 ግን ታሪክ ሆኗል። አሁን እንደ ታሪክ ነው የምናስታውሰው።
በዛሬው የሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን ከ48 ዓመታት በፊት የተከሰተውን የመስከረም 2 1967 ዓ.ም የንጉሡን መወገድና የደርግን ወደ መንበረ ሥልጣኑ መምጣት እናስታውሳለን። የፍስሃ ግዜ ‹‹የኢትዮጵያ የአምስት ሺህ ዓመት ታሪክ››፣ የፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983›› መጽሐፎችን፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣን እና የተለያዩ ድረ ገጾችን ይህን ጽሁፍ ስናዘጋጅ በዋቢነት ተጠቅመናል።
መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ምን ተፈጠረ?
ከዛሬ 48 ዓመታት በፊት መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም የደርግ አባላት 13 ሆነው ወደ ቤተ መንግሥት ሄዱ። ቤተ መንግስት እንደደረሱም ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴን አስጠሯቸው። ንጉሱም በዝግታ ከፎቅ ላይ ወርደው በዙፋናቸው ላይ ሲቀመጡ የደርግ አባላት ደነገጡ። ንጉሡ የአገዛዝ ዘመናቸው ማብቃቱንም አረዷቸው። ሻምበል ደበላ ዲንሳ ደርግ የወሰነውን የውሳኔ ሃሳብ እንዲህ አነበቡ።
‹‹ … ለሀገርና ለህዝብ ደህንነት ሲባል በዛሬው ዕለት ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ከስልጣን ወርደዋል፤ ለደህንነትዎ ሲባልም አስተባባሪው ኮሚቴ ወዳዘጋጀልዎ ቦታ እንዲሄዱ ተወስኗል …›› የሚል ይዘት ያለው ደብዳቤ ተነበበ። ሻምበል ደበላ ውሳኔውን አንብበው ሲጨርሱ ንባባቸውን ሲጀምሩ የሰጡትን ወታደራዊ ሰላምታ ደገሙ።
ንጉሱም ዝም ብለው ቆዩና መናገር ጀመሩ። እንዲህም አሉ።
‹‹ያነበባችሁትን ሰምተናል፤ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት ስንሆን ስም ብቻ አይደለም። ቢሆንም በየጊዜው የሚለዋወጠው ነገር ደግሞ ላገር የሚጠቅም ነገር እስካለበት … የኢትዮጵያን ታሪክ ጠብቃችሁ ማልማት ከቻላችሁ የእኛ ታሪክ እዚህ ላይ ያበቃል፤ ካልቻላችሁ የእናንተ ታሪክ ያበቃና የእኛ ይቀጥላል፤ አገራችንንና ሕዝባችንን በምንችለው አገልግለናል፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ እድል የእኛን መወገድ የሚጠይቅ ከሆነ ስራችንን አቁመን ማንኛውንም ነገር ለመቀበል ዝግጁ ነን፤ ‹አሁን ተራው የእኛ ነው› ካላችሁ ኢትዮጵያን ጠብቁ›› በማለት ተናገሩ።
ራሳቸው ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ‹‹ትግላችን›› በሚለው መጽሐፋቸው እንደገለጹት፤ ንጉሡ ‹‹ምን ይደረግላችሁ›› ሲባሉ ‹‹ምንም አያስፈልገንም፣ እግዜር እንደፈቀደልን እንኖራለን›› ብለው ነበር። ከዚህ የምንረዳው ‹‹ያዙኝ ልቀቁኝ!›› የሚል እልህ ውስጥ አልገቡም ነበር ማለት ነው። በእርግጥ ቢገቡስ ምን ያመጣሉ! የተያዙት በወታደር እጅ ነው።
ከታሪክ ድርሳናት እንደምንረዳው፤ ንጉሡ በደርግ እጅ ለመውደቅ ከመዳረጋቸው በፊት በራሳቸው ሰዎች ተደጋጋሚ ምክር ተነግሯቸዋል። ከቃላዊ ምክር እስከ ጦራዊ ማስጠንቀቂያ ዕድሎችን አሳልፈዋል። እነ ፀሐፈ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ‹‹ንጉሥ ሆይ! እያደረጉት ያለው ነገር ከዘመኑ ጋር የዘመነ አይደለም›› ብለዋቸዋል። እነ አቤ ጉበኛ እና ሀዲስ አለማየሁ በልቦለድም በእውነተኛ ታሪክም እየጻፉ ነግረዋቸዋል። እነ ጄኔራል አብይ አበበ ‹‹አውቀን እንታረም›› በሚል ግልጽ መልዕክት ባለው ጽሑፍ ነግረዋቸዋል። አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ ግልጽ ደብዳቤ ጽፈውላቸው እንደነበርም ይነገራል። የአምባሳደር ብርሃኑ መልዕክት ንጉሡ ከወረዱ በኋላ በደርግ ዘመነ መንግሥት ‹‹አብዮታዊ መድረክ›› በሚለው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዓምድ ላይ በሰፊው ተብራርቷል።
ንጉሡ የሚባሉትን ባለመስማታቸው ነገሮች እየከረሩ ሄዱ። በንጉሡ ላይ መጀመሪያ አካባቢ የነበረው ተቃውሞ ‹‹የተማረ›› በሚባለው ወገን በኩል ነው። የነ ገርማሜ ንዋይ መፈንቅለ መንግስት ሙከራም የመጀመሪያ ጥንስሱ ወታደራዊ ሳይሆን ምሁራዊ ነበር። ጄኔራል መንግስቱ ንዋይ ወታደር ቢሆኑም ገርማሜ ንዋይ ግን የተማረ ከሚባለው ወገን ነበሩ። ንጉሡ በምሁራዊ ውይይት አልሰማ ሲሉ ነው ወደ ወታደራዊ ኃይል (የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ) የሄደው።
ንጉሡ ይሄን ሁሉ ማስጠንቀቂያ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው የተጠየቀው ለውጥ ሳይመጣ 13 ዓመታት ተቆጠሩ። አሁን ሴራው እየቀረበና እየረቀቀ መጣ።
የዚህ ሴራ ጠንሳሽ ራሱ የንጉሡ ጠባቂ የነበረው ክቡር ዘመኛ መሆኑ ደግሞ የነገሩን ፍጥነት እውን አደረገው።
ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም ከጦር ሠራዊት፣ ከክቡር ዘበኛ፣ ከብሄራዊ ጦር፣ ከፖሊስ አባላት የተወከሉ መለዮ ለባሾች፣ የጦር ኃይሎች፣ የፖሊስ ሠራዊትና የብሔራዊ ጦር አስተባባሪ፤ በአራተኛ ክፍለ ጦር ግቢ ተሰብስበው ኮሚቴ አቋቋሙ። ይሄው ኮሚቴ ነው ሐምሌ 1 ቀን 1967 ዓ.ም ‹‹ደርግ›› ተብሎ የተሰየመው። በኮሚቴውም ሻለቃ መንግስቱ ኃይለማርያም ሊቀ መንበር፣ ሻለቃ አጥናፉ አባተ ምክትል ሊቀመንበር ተደርገው ተመረጡ።
ይህ ስብስብ ነው እንግዲህ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ለሺህ ዘመናት የኖረውን ንጉሣዊ ሥርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የገረሰሰው። የሰለሞናዊ ሥርወ መንግስት የመጨረሻው ነጋሲ የሆኑት ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ከዙፋናቸው ወርደው ወደ ቮልስ ዋገን መኪናቸው ገቡ። ወታደራዊው ደርግ መንበረ ሥልጣኑን ተቆናጠጠ።
‹‹አዝጋሚው መፈንቅለ መንግስት›› የሚባለው የደርግ አብዮት ንጉሣዊ ሥርዓቱን ያስወገደው በቅጽበታዊ መፈንቅለ መንግስት ሳይሆን በረጅም ጊዜ ስልታዊ ዝግጅት ነው። መጨረሻ ላይ አብዮት ልጆቿን ብትበላም ለዚህ ሴራ ተደጋጋሚ ስውር ስብሰባዎችን አድርገዋል። በእርግጥ ንጉሡን ከማስወገዳቸው በፊትም አንዳንድ አለመግባባቶችና ንትርኮች ነበሩ።
ደርግ በነበረው የአገዛዝ ጨቋኝነትና ጨካኝ እርምጃዎች ታሪኩን ጭቃ ቀባው እንጂ ንጉሣዊ ሥርዓቱን በማስወገድ ተመስግኖ ነበር። ለሺህ ዘመናት የኖረ ሥርዓትን ያለምንም ደም ማስወገድ ትልቅ ስልት ነው። በየትኛውም የዓለም አገር ነባር ሥርዓት በስምምነት አልተለወጠም። እንኳን ነባር ሥርዓት ተመሳሳይ ሥርዓት ለመቀየር እንኳን ደም መፋሰስ ይታያል። ደርግ ግን የኢትዮጵያን ንጉሣዊ ሥርዓት በስልታዊ ለዘብተኛ መፈንቅለ መንግስት አስወገደው።
ዳሩ ግን ንጉሣዊ ሥርዓቱ ከተወገደ በኋላ ደርግ ደም በደም ሆነ። ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም ያለምንም ደም›› የሚለው መፈክር የምፀት መሰለ። ከጦር ጄኔራል እስከ ምሁር የአብዮት ሰይፍ አረፈበት። ቀይ ሽብር፣ ነጭ ሽብር እየተባለ አገሪቱ ሽብር በሽብር ሆነች።
የታሪክ ድርሳናት፣ የጋዜጣና መጽሔት ሰነዶች እና በወቅቱም የነበሩ ሰዎች እንደሚሉት፤ ከመስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ማግስት ጀምሮ ደርግ ለዘብተኛ አካሄድ ነበር የሄደው። እንዲያውም የታሰሩ ሰዎችን እየፈታም ነበር። የንጉሡን ልደትም አክብሮላቸዋል። እንዲህ እንዲህ እያለ ነው በኋላ ነገሮች ከድጡ ወደ ማጡ የሆኑት። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ደርግ የሚመሰገንባቸው ነገሮች አሉ። የአገር ፍቅር ጀግንነቱን የሥርዓቱ ተቀናቃኝ የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ሳይቀር መስክረውለታል።
‹‹ባላባት›› በሚል ኋላቀር ልማድ የኖረውን የመሬት ከበርቴነት አስወግዶ ድሃውን ተጠቃሚ አድርጓል። ማንበብና መጻፍ የማይችለውን ህዝብ ‹‹ዕድገት በህብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ›› ብሎ አስተምሯል። የተማረውን ክፍል እስከ ገጠር መንደሮች ድረስ በማዝመት የ60 እና የ70 ዓመት አዛውንቶች ሳይቀሩ እንዲማሩ አድርጓል። በዘመነ ኢህአዴግ የቀበሌ ሊቀመንበር የነበረው ሁሉ በደርግ የጎልማሶች ትምህርት የተማረ ነው። ቀይ ሽብር ብቻ ሳይሆን ይህም የደርግ ታሪክ ሆኖ ይመዘገባል።
ሌሎች የዚህ ሳምንት ክስተቶች በዚህ ሳምንት ከተከሰቱ ታሪካዊ ክስተቶች ጥቂቶችን በአጭር በአጭሩ እናስተዋውቃችሁ። አንጋፋው የኢትዮጵያ ሬዲዮ የተመሰረተው ከ87 ዓመታት በፊት መስከረም 2 ቀን 1928 ዓ.ም ነበር። ሬዲዮ ጣቢያውን መርቀው የከፈቱትና ስራ ያስጀመሩት ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ነበሩ።
አንጋፋው የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የተመሰረተው ከ101 ዓመታት በፊት መስከረም 3 ቀን 1914 ዓ.ም ነበር። ማተሚያ ቤቱ ሥራ የጀመረው በንጉስ ተፈሪ መኮንን መኖሪያ ግቢ በምትገኝ ‹‹ጨው ቤት›› በምትባል ሁለት ክፍል ቤት ውስጥ ሲሆን፣ የበኩር ስራው ደግሞ ‹‹ዮሐንስ አፈወርቅ›› የተሰኘው ቅዱስ መጽሐፍ ነበር። የድርጅቱ የመጀመሪያው ስራ አስኪያጅ አቶ ገብረክርስቶስ ተክለሃይማኖት ነበሩ።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን መስከረም 8/2015