የመኖሪያ ቤት ችግር በተለይም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ትልቁ ፈተና መሆኑን ቀጥሏል። በርካታ የከተማዋ ነዋሪ በክራይ ቤት እና በደባልነት ነው የሚኖረው። በከተማው ባለው የኪራይ ቤት እጥረት ምክንያትተከራይ የሚፈልገውን አይነት የኪራይ ቤት ማግኘት ይከብዳል። በዚህ ላይ የኪራዩ ዋጋ አይቀመስም።
በዚህ ላይ ያረጀውን መኖሪያ ቤት ማደስም ሆነ አዲስ ቤት መገንባት ባለመቻላቸው የተነሳ ሊወድቁ በተቃረቡ እና ለኑሮ በማይመቹ ቤቶች የሚኖሩ የከተማዋ ነዋሪዎችም በርካታ ናቸው።
የከተማዋን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት መንግስት የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም መፍትሄ ለመስጠት ርብርብ ሲያደርግ ቆይቷል። በአሁኑ ወቅትም የተለያዩ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አስቀምጦ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ሆኖም የከተማው የቤት ችግር የነዋሪዎችን አቅም መፈታተኑን ተያይዞታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ደግሞ ከከተማዋ መኖሪያ ቤቶች ጥቂት የማይባሉት በእርጅና በመሳሰለው ሳቢያ የሚያኖሩ አይነት አይደሉም፤ ነዋሪዎቹ በእቅመ ደካማነትና በመሳሰሉት ሳቢያ ቤቶቹን መልሶ መገንባት የሚችሉ ባለመኖናቸው የተነሳ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለመኖር ተገደው ቆይተዋል።
መንግስት ይህን ችግር ህብረተሰቡን በማስተባበር ለመፍታት በቤቶች እድሳት ላይ በትኩረት እየሰራ ይገኛል። በእዚህ በኩል እያደረገ ካለው ጥረት መካከል በህብረተሰብ ተሳትፎ እና በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተገነቡ እና እየታደሱ ያሉ የአቅመ ደካማ ቤቶች ይጠቀሳሉ። በበጎ ፈቃድ እና በህብረተሰብ ተሳትፎ ቤቶችን ማደስ እና አዳዲስ ቤቶችን ገንብቶ አቅም ለሌላቸው ማቅረብ በተለይም ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ እየተለመደ መጥቷል። በዚህም በተለይም የአቅም ደካሞች ህይወት እየተቀየረ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳዊት ከበደ እንደተናገሩት፤ በተጠናቀቀው 2014 አም የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት እና ግንባታ ስራዎች ተከናውነዋል።
በ2014 በጀት ዓመት በአጠቃላይ ስምንት ሺህ አካባቢ ቤቶች ባሉበት በከፊል እና ሙሉ በሙሉ ታድሰው ለህብረተሰቡ ተላልፈዋል። ከዚህ ውስጥ 3ሺህ 645 ቤቶች ደግሞ ከግንቦት እስከ መስከረም ባሉት የክረምት ወራት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተገነቡና የታደሱ ናቸው።
በተለይም ከግንቦት እስከ መስከረም ወር ባሉት አምስት ወራት አመርቂ ስራዎች መሰራታቸውን አቶ ዳዊት ይጠቅሳሉ። ‘’በጎነት ለዘላቂ አብሮነት’’ በሚል መርሃ ግብር ከግንቦት አንድ 2014 ዓ.ም እስከ መስከረም 2015 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ለአምስት ወራት የዘለቁ ሰባት መርሃ ግብሮች ተቀርጸው ርብርብ መደረጉን ጠቅሰው፣ ከነዚህ መርሃ ግብሮች አንደኛው የሰብዓዊና ማህበራዊ አገልግሎት መርሃ ግብር መሆኑን ይጠቁማሉ። በሰብዓዊና ማህበራዊ መርሃ ግብር ውስጥ ከሚካተቱ ተግባራት መካከል የአቅመ ደካማ እና የሀገር ባለውለታ የሆኑ ዜጎች የቤት እድሳት አንዱ እንደነበር ነው ያነሱት።
በነዚህ አምስት ወራት ውስጥ 3 ሺህ 400 ቤቶች ለማደስ ታቅዶ እንደነበር የጠቆሙት አቶ ዳዊት፤ ባለሃብቶችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተሳተፉበት የቤት እድሳት ከእቅድ በላይ ማሳካት መቻሉን ጠቁመዋል። 3 ሺህ 645 አዳዲስ ቤቶችን መገንባት እና ማደስ ተችሏል። ከነዚህ ውስጥ 1 ሺህ 300 የሚሆኑት ሙሉ በሙሉ ፈርሰው እንደገና የተገነቡ ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ ባሉበት ቦታ ግድግዳቸው ወይም ጣሪያቸው ፈርሶ የታደሰ መሆኑን ተናግረዋል።
እነዚህ ቤቶች ጳጉሜ 1 በጎ ፈቃድ ቀን ተብሎ በተሰየመው መሰረት ለነዋሪዎቹ ተላልፈዋል። በአማካይ በነዚህ ቤቶች ውስጥ እስከ አምስት ሰው የሚኖርባቸው መሆናቸውን አቶ ዳዊት ጠቅሰው፣ የታደሱት እና እድሳት የተደረገላቸው 3 ሺህ 645 ቤቶች ውስጥ 18 ሺህ 222 የሚጠጉ ነዋሪዎች የሚኖሩባቸው መሆናቸውን ነው ያብራሩት።
እንደ አቶ ዳዊት ማብራሪያ፤ በህብረተሰብ ተሳትፎ እና በጎ ፈቃድ እድሳት ከተደረገላቸው እና እንደ አዲስ ከተገነቡ ቤቶች በተጨማሪም ዘጠና በስልሳ በተሰኘ ሰው ተኮር ፕሮጀክት በከተማ አስተዳደሩ አነሳሽነት 747 ቤቶችን በአዲስ መልክ በመገንባት ለነዋሪዎች ማስተላለፍ ተችሏል። ይህም በርካታ ማህበራዊ ችግሮችን መቅረፍ ያስቻለ ነው።
እድሳትና ግንባታው ቅድሚያ ተሰጥቷቸው መታደስ ያለባቸው እና እንደ አዲስ መገንባት ያለባቸው ቤቶችን በመለየት ረገድ ከፍተኛ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ እንደሚከናወን የተናገሩት አቶ ዳዊት፤ በልየታ ሂደት ውስጥ የተለያዩ አካላት የድርሻቸውን እንደሚወጡም ጠቁመዋል። ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ በመሆን ግንባታ እና እድሳት የሚያስፈልጋቸው ቤቶች ልየታ የሚያካሂድ ኮሚቴ በወረዳዎች እንዳለም ተናግረው፣ የድሃ ድሃ እነማን ናቸው የሚለው በጥንቃቄ እንደሚለይም ነው ያመለከቱት።
መገንባት ወይም መታደስ ያለባቸው የነማን ቤቶች ናቸው፤ በአካባቢው ከሚገኙ የግለሰብ ቤቶች እና የቀበሌ ቤቶች ውስጥ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ቤቶች የእነማን ናቸው በሚል ቤቶች መስፈርት ወጥቶላቸው እንደሚታደሱና እንደሚገነቡ ተናግረዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ አቅማ ደካማ የሆኑ፣ አጋዥ የሌላቸው፣ መስራት የማይችሉ በወረዳ ደረጃ ይለያል። በነዚህ ክፍለ ከተሞች እነዚህ እነዚህ ቤቶች ቢታደሱ ተገቢ ነው የሚለውን መረጃ ለሚፈልጉ አካላት ይተላለፋል። ግለሰቦች ባለሃብቶች፣ ተቋማት እና ድርጅቶች ማደስም ሆነ የግንባታ ስራዎችን እንዲሰሩ ይደረጋል።
አንዳንዶቹ ነዋሪዎች ለእድሳት ወይም ለመልሶ ግንባታ በሚወጡበት ወቅት ተመልሰው ወደ ቦታው የሚገቡም አይመስላቸውም ያሉት አቶ ዳዊት፣ ይህም ከዚህ ቀደም በመሃል ከተማ የሚኖሩት በመልሶ ግንባታ ምክንያት ወደ ዳር እየተወሰዱ ስለነበር የተከሰተ መሆኑን ያስታውሳሉ። አሁንም ተመሳሳይ ነገር ይፈጠራል በሚል ስጋት ከቤታቸው ለመውጣት ፍርሃት የነበራቸው እንደነበሩም ይገልጻሉ።
እንደ አቶ ዳዊት ማብራሪያ፤ በህብረተሰብ ተሳትፎ እና በበጎ ፈቃድ እየተሰሩ ባሉ ስራዎች የከተማዋን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ማቃለል እየተቻለ ነው። በርካቶችን ከአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ማላቀቅ ተችሏል። ይህም እውን ሊሆን የቻለው በህብረተሰቡ ተሳትፎ ነው። ባለሃብቱ እና ሌላው በጎ ፈቃደኛ ድጋፉ በትክክል ለሚያስፈልጋቸው አካላት እየደረሰ መሆኑን በአይናቸው በማየታቸው በርካቶች ተመሳሳይ የበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ የመሳተፍ ፍላጎት እያሳዩ ናቸው።
አምራች ያልሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን መርዳት ያስፈልጋል የሚለው እሳቤ ተቀባይነት እየጨመረ ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ አምራች ያልሆነውን የህብረተሰብ ክፍል የሚደግፉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ይጠቅሳሉ። ቤት ገንብተው እንዲሁም አድሰው ከመስጠት ባሻገር አንዳንዶቹ ሌሎች ወጪዎችንም እየሸፈኑ መሆናቸውንም አመልክተው፣ ሙሉ የቤት ውስጥ እቃ አሟልተው የሚሰጡም መኖራቸውን ነው የጠቆሙት።
እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ ማብራሪያ፤ የእነዚህ ቤቶች መገንባት እና እድሳት አንድምታው ብዙ ነው። ባለሃብቱን ጨምሮ ሌሎች ማገዝ የሚችሉ አካላት በበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ እንዲሳተፉ አስችሏል። በርካቶች ድጋፍ የሚፈልጉ ዜጎችን መደገፍ ቢፈልጉም የተደራጀ እና ተቋማዊ አሰራር ባለመኖሩ ለመደገፍ ሲቸገሩ ነበር። ይህ ኮሚሽን ተቋቁሞ የማስተባበር ስራ መጀመሩ መደገፍ የሚፈልጉት ድጋፋቸውን በተደራጀ መልኩ እንዲያቀርቡ አስችሏቸዋል።
አብዛኞቹ የቤት እድሳት የተደረገላቸው እና አዲስ ቤት የተገነባላቸው ነዋሪዎች በአንድ ወቅት ለኢትዮጵያ ትልቅ የዋሉ እና ራሳቸውንና ሀገራቸውን ያገለገሉ፣ በአንድም በሌላም መንገድ ይህችን ሀገር ለዚህ ትውልድ ያስረከቡ ናቸው። እድሜያቸው በመግፋቱና ረጂ በማጣታቸው ለችግር የተጋለጡ ናቸው። እድሳትና ግንባታው እነዚህን ሰዎች ከነበሩበት ሁኔታ መታደግና አለኝታነትን መግለጽ የተቻለበት ነው።
ትናንት ለሀገራቸው የዋሉ ሰዎች በዚህ መልኩ ድጋፍ ማግኘታቸው ዛሬም ለሀገራቸው ጠንክረው ለሚሰሩት መልካም መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው ያሉት አቶ ዳዊት፣ ውለታቸውን ሀገራቸው እንደማትረሳቸው እና በከባድ ሁኔታ ውስጥ ቢወድቁ እንኳ አስተዋሽ እንዳላቸው እንዲያስቡ የሚያደርግ ነው ይላሉ።
በተለይም ውድ ህይወታቸውንና የተለያዩ አካላቸውን ለሀገራቸው ሉአላዊነት ሲዋደቁ ላጡት ጀግኖች እና የጀግኖች ቤተሰቦች የቤት ግንባታ እና እድሳት መከናወኑ አገሪቷም ባላት ሃብት ለነዚህ አካላት ቅድሚያ በመስጠት የምትደግፈውና የምታበረታታው መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
እንደ አቶ ዳዊት ገለጻ፤ ኢትዮጵያዊያን ከበፊትም ጀምሮ የመረዳዳት እና የመተጋገዝ ባህል ያላቸው ህዝቦች ናቸው። ለእዚህም እድር እና እቁብ መሰል መረዳጃዎች ማሳያ ናቸው። ደቦን የመሳሰሉ በጋራ የመስራት ባህልም ኢትዮጵያዊያን የቆየ የመረዳዳት ባህል ባለቤቶች መሆናቸውን ያመለክታሉ። አሁን በአዲስ አበባ እና በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ እና በተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች እየታየ ያለው መልካም ተግባር የመረዳዳት ባህልን ያነቃቀ ነው። የመተጋገዝ እና የመረዳዳት ባህል እየጨመረ መምጣቱንም አመላካች ነው።
የቤት ግንባታና እድሳቱ አቅም አልባ ዜጎች ዘንድ እፎይታን የፈጠረ ነው። እነዚህ ነዋሪዎች ቤታቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ታድሶላቸው ተመልሰው የሚገቡ አይመስላቸውም ነበር። መንግስት በበጎ ፈቃድ የቤት ግንባታና እድሳት ሰበብ ከመሃል ከተማ ሊያስወጣቸው በማሰብ የሚሰራ ደባ የሚመስላቸውም ነበሩ ሲሉ ያብራሩት አቶ ዳዊት፣ ከዚህም የተነሳ የቤቶች እድሳት እና ወይም ግንባታ ተጠናቆ ተመልሰው ወደ ቤታቸው ሲገቡ ደስታቸው ከፍ ያለ እንደነበር ተናግረዋል።
እንደ አቶ ዳዊት ገለጻ፤ መሰል ጥርጣሬ ሲፈጠርባቸው የነበረው ከለውጡ በፊት በነበሩ ዓመታት በመሃል ከተማ ለዘመናት ይኖሩ ከነበሩበት ቀዬያቸው ለልማት የተነሱ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ወደ ዳር ሄደው እንዲሰፍሩ በመደረጉ ነው። በዚህም ምክንያት የብዙዎች ማህበራዊ ትስስር ተናግቷል። ከለውጡ በፊት የነበረው አካሄድ አሁንም ሊቀጥል ይችላል የሚል ስጋት በብዙዎች ዘንድ ነበር። ቤቶቹ ተገንብቶ አልቀው ከገቡ በኋላ ግን ጥርጣሬያቸው ትክክል እንዳልነበር መረዳት ችለዋል።
አዲስ አበባ ጉራማይሌ ነች። ውብ ሰወፈሮች እና ቦታዎች አሏት። በዚያው ልክ ደግሞ ለመኖር አስቸጋሪ የሆኑ ሊፈርሱ የተቃረቡ እና በሸራ የተወጠሩ ቤቶች የሚገኙባቸው አካባቢዎችም አሏት ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ አብዛኛው የቤቶች ግንባታና እድሳት እየተካሄደባቸው ያሉ አካባቢዎች የአጠቃላይ የመንደሩን ዉበት በመጨመር ገጽታው እየተቀየረ እንዲመጣ እያደረጉ መሆናቸውንም ነው የገለጹት።
እድሳትና ግንባታው ከተማን የማስዋብ እና የመቀየር ሚናም አለው ይላሉ። ሊወድቁ የተቃረቡ እና በሸራ የተሰሩ ቤቶች በህንጻ ሲተኩ በአካባቢው ላይ የሚኖረው ውበት ግልጽ ነው። ይህን በበጎ ፈቃድ እየተገነቡ ያሉ ቤቶች ለከተማዋ ዉበት የራሳቸውን ሚና እየተጨወቱ ስለመሆኑ አመላካች ነው ይላሉ አቶ ዳዊት።
እድሳት እየተደረገላቸው እና እንደ አዲስ እየተገነቡ ባሉ ቤቶች ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ቀደም ባሉ ጊዜያት ይኖሩ የነበረው አኗኗር እና ቤታቸው ከታደሰ እና እንደ አዲስ ከተገነባ በኋላ ያለው የአኗኗር ዘይቤያቸውም እየተቀየረ መሆኑን አቶ ዳዊት ይገልጻሉ። ሁኔታው ማገዶ ከመጠቀም ሌሎች ታዳሽ የሀይል ምንጮችን እንዲጠቀሙ እያደረጋቸው ነው፤፤ ይህም የደን መጨፍጨፍን በመቀነስ እየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው ሲሉ ያብራራሉ።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአንድ ወቅት ብቻ አገልግሎት አይደለም የሚሉት አቶ ዳዊት፤ በበጋ ወቅትም የቤት እድሳት እና ግንባታን ጨምሮ የተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማከናወን ታቅዷል ሲሉ ይጠቁማሉ። የክረምት በጎ ፈቃድ ማጠቃለያ መስከረም 30 እንደሚጠቃለል ጠቅሰው፣ለእዚህም ፕሮግራም ሊደረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አቶ ዳዊት ይጠቁማሉ። የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ ከተጠቃለለ በኋላ የበጋ እንደሚጀመርም አመልክተዋል። በዚህም የቤቶች እድሳት እና ግንባታን ጨምሮ በርካታ የበጎ አድራጎት ስራዎችን ለማከናወን እቅድ መያዙን ነው የተናገሩት።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን መስከረም 7/2015 ዓ.ም