በኢትዮጵያ አዲስ ዘመን ተፈጥሮ በራሱ የተለየ ፍካት ይላበሳል፡፡ ሰማዩ ፈክቶ፣ ወንዙ ጠርቶ፣ ሜዳው በለምለም ሳር ተውቦ አዲስነት ይላበሳል፡፡ ተፈጥሮ እንደ አዲስ ተውቦ በሚገለጥበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያውያን ህይወትን በአዲስ ተስፋ ይጀምራሉ፡፡ በዛሬው ‹‹ሳምንቱን በታሪክ›› ዓምዳችን አዲስ ዓመት ሲቃረብ ተወልዶ በአዲስ አመት ዋዜማ ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ከፍ ያደረገን ጀግና እናስታውሳለን፡፡ ፅሁፉን ስናዘጋጅም ከተለያዩ ድረ ገፆችና ዘጋቢ ፊልሞች መረጃዎችን ወስደናል፡፡
የአዲስ ዘመን ስጦታ
እኤአ በ1960 የጣሊያና መዲና ሮም በኦሊምፒክ ውድድር ደምቃ ከርማለች፡፡ ኢትዮጵያ ከዚያ በፊት የኦሊምፒክ ተሳትፎ ታሪክ ቢኖራትም እስከዚያ ቀን ድረስ ምንም ሜዳሊያ ማግኘት አልተቻላትም፡፡ የውድድሩ መዝጊያ የሆነው የማራቶን ሩጫ ቀን ላይ ደርሷል፡፡ ለኢትዮጵያ ብሎም ለመላው ጥቁር ህዝብ አንድ ታላቅ ድል ሊበሰር፤ አንድ ቆፍጣና ኢትዮጵያዊ መድረኩ ላይ ይንጎማለላል፡፡
ተወዳዳሪዎች ተገርመው ያዩታል፡፡ ጥቁር ሆኖ በነጮች መሀል ቦታው ላይ መገኘቱ አልነበረም ያስገረማቸው፡፡ በእርግጥ ጥቁር ተወዳዳሪዎች በቁጥር ጥቂት ነበሩ፡፡ ነገር ግን ከዚያ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ በባዶ እግሩ ለመሮጥ ከመካከላቸው መገኘቱ ነበር የደነቃቸው፡፡ በባዶ እግሩ ለመሮጥ መዘጋጀቱን እያዩ መሳሳቅ፤ ሁኔታውን እየተመለከቱ መገረም ውስጥ ገቡ፡፡ በዚያ የውድድር መድረክ ላይ ከዚያ በፊት መሰል ተግባር የፈፀመ ማንም አልነበረም፡፡
ይህ አትሌት ግን አገሩ አደራ ብላ የሸኘችው ታላቅ ሃላፊነትም የሚሰማው ነበርና ለእግሩ ምቹ ጫማ በማጣቱ ምክንያት ከውድድሩ ራሱን ሊያገል ፈፅሞ አልፈቀደም ፡፡ ይህ ጥቁር ቆፍጣና ሰው ቆረጠ፡፡ በጫማ መሮጥ የሚከብደውን 42 ኪሎ ሜትር በባዶ እግሩ ከባለጫማዎች ጋር እወዳደራለሁ ማለቱ ብዙዎችን አስገረመ፡፡
የውድድሩ መነሻ ሰዓት ደረሰና የጅማሮው ድምፅ ተስተጋባ፡፡ ከአንድ ሰዓት በኋላ ብዙዎች ወደ ኋላ ቀሩ፡ ፡ የተቀሩት መሀል ላይ ሰብሰብ ብለው ይራወጣሉ፡ ፡ እርሱና እጅግ በጣም በቁጥር ያነሱት ደግሞ ከፊት መምራትን ይዘዋል፡፡ በወቅቱ በመገናኛ ብዙኃን ስለ ውድድሩ ለአድማጭ ተመልካች የሚያስተላልፉት ጋዜጠኞች ከእርሱ ውጭ ያሉትን ሯጮች ደጋግመው ይጠሩና “አንድ ጥቁር” አብሯቸው አለ፤ ብቻ ነበር የሚሉት፡፡ ልጁ ግን ኢትዮጵያዊ ጀግንነትን ታጥቆ በቆፍጣና ፊቱ እየገረመማቸው ሙያ በልብ ነው ያለ ይመስል ለድሉ ራሱን አዘጋጀ፡፡
አዎ! እነርሱ የመጨረሻው ሰዓት ደርሶ እውነታውን እስኪያዩ ትኩረት አልሰጡትም ነበር፡፡ ያ በባዶ እግሩ የተመለከቱት ጥቁር ሰው፤ የጥቁር ወርቅ እንደሆነ አልገባቸውም ነበር፡፡ ለአሸናፊነት የጠበቁት ሌሎችን ነበር፡፡ ነገር ግን አበበ ቢቂላ ልበ ብርቱ ነበርና ከፊቱ የነበሩትን ከኋላ አሰልፎ የአገሩን ስም ከፍ አደረገ፤ የኢትዮጵያን ባንዲራ ሮም ላይ አነገሰ፡፡ አበበ በኢትዮጵያ ብሎም በጥቁር ህዝብ ታሪክ፤ የመጀመሪያውን የማራቶን ወርቅ አሸናፊ ሆነ፡፡ ይህ የሆነው የዛሬ 62 ዓመት በዚህ ሳምንት ነበር፡፡ የአበባ ወርቅ ትርጓሜው ብዙ ነበር፡፡ ለአገሩም ያበረከተው የአዲስ ዘመን ስጦታ፤ ልደቱንም ያከበረበት ልዩ ገጠመኝ ነበር፡፡
“በጣም ደስ ብሎናል ምኞታችን ሞላ
አሸንፎ መጣ አበበ ቢቂላ … ”
የአትሌት አበበ ቢቂላ ልደት በዚህ ሳምንት ነሐሴ 30 ነበር፡፡ በእርግጥ አበበ ቢቂላ ለእናት ምድሩ የመጀመሪያው ድል የተቀዳጀውና የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘላትም ያኔ ሮም ላይ በዚሁ ወቅት ነበር፡፡
አበበን ለኦሊምፒክ ያበቃው አጋጣሚ
በውድድሩ ላይ ለመካፈል ወደ ጣሊያን ሊያመሩ ከተመረጡት አትሌቶች መካከል አልነበረም፡፡ በእርግጥም የአበበ እዚያ ውድድር ላይ መገኘት በአጋጣሚ ነበር፡፡ ለውድድር ሊሄዱ ከታሰቡት እና መጀመሪያ በተካሄደው ምርጫ ላይ የእርሱ ስም ፈፅሞ አልሰፈረም ነበር፡፡ ለጉዞ አየር ማረፊያ ከተገኙት አትሌቶች መካከል አትሌት ዋሚ ቢራቱ የተባለ ሯጭ አልተገኘም፡፡
የአትሌቲክስ ቡድን አሰልጣኙ የዋሚ እግር መጎዳቱንና ለሩጫው እንደማይደርስ ተነገራቸው፡፡ ዋሚ ኳስ ሲጫወት እግሩ በመሰበሩ መሄድ እንደማይችል ያረጋገጡት ስዊዲናዊው አሰልጣኝ ኦኒ ኒስካነን፤ አበበ ቢቂላ በዋሚ ቦታ እንዲሄድና እንዲጠራላቸው አድርገው ይዘውት ሄዱ፡፡
አበበ ቢቂላ በኦሊምፒክ ታሪክ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ እና በማራቶን የመጀመሪያው የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘ ጥቁር አትሌት ነው።
ወደ አትሌቲክስ ጉዞ
በያኔው ስያሜ ደብረ ብርሃን አውራጃ ቦና ወረዳ ጃቶ የተባለ ቀበሌ አበበ የተወለደበት መንደር ነው፡፡ ነሐሴ 30 ቀን 1932 ዓ.ም ደግሞ ወደዚህ ምድር የተቀላቀለበት ታሪካዊ ቀን ነው፡፡ አበበ ቀድሞ ሕይወቱን የጀመረው በሩጫ አልነበረም፡፡ ልጅ እያለ እግር ኳስና ልዩ ልዩ የስፖርት አይነቶች ላይ ተሳታፊ እንደነበር በእርሱ ዙሪያ የተፃፉ ድርሳናት ያትታሉ፡፡
ወደ ሩጫው ሜዳ ያመራው በአጋጣሚ በተመለከተው ሩጫ አሸናፊዎች ሽልማት ሲበረከትላቸው በፈጠረበት መነሳሳት መሆኑን ተናግሯል፡፡ ገና በወጣትነት እድሜው በውትድርና ሙያ አገሩን ማገልገል የጀመረው አበበ የንጉስ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የክቡር ዘበኛ አባልም በመሆን አገልግሏል፡፡ የክቡር ዘበኛ ወይም በወቅቱ ወታደር የነበረው አበበ በተቀጠረበት መስሪያ ቤት የክቡር ዘበኛ ውስጥ የሩጫ ውድድር መካፈል ጀመረ፡፡ ሩጫን ዘግይቶ ቢጀምርም በስፖርቱ ትኩረትን ለመሳብ ጊዜ አልፈጀበትም፡፡
በጦር ኃይሎች ውድድር በጊዜው ታዋቂ የነበሩትን ሯጭ ዋሚ ቢራቱን አሸንፎ ከንጉሱ እጅ የወርቅ ሜዳሊያና ዋንጫ ሽልማት አገኘ። በጦር ሰራዊቱ አሰልጣኝ የነበሩት ሲዊዲናዊው አሰልጣኝ ኦኒ ኒስካነን የአበበን ችሎታ በመገንዘባቸው ከሌሎቹ አትሌቶች ጋር ተቀላቅሎ ልምምድ እንዲሰራ አደረጉ፡፡
አሰልጣኙ ትጉህና ውጤታማ አትሌቶች ለማፍራት ይጥሩ ነበርና የሮም ኦሊምፒክ እስኪቃረብ ድረስ ከ2ሺህ ሜትር በላይ ከፍታ ባላቸው ተራራማ ቦታዎች ላይ የ1500 ሜ. ተደጋጋሚ የፍጥነት ሩጫ ልምምዶችን እንዲሰሩ ያደርጓቸው ነበር።
አትሌት አበበ ለመጀመሪያ ጊዜ በማራቶን ያሸነፈው አዲስ አበባ ላይ በተደረገ ውድድር ሐምሌ ወር 1960 ዓ.ም ሲሆን ርቀቱን ለማጠናቀቅ የወሰደበት ጊዜ 2 ሰዓት ከ21 ደቂቃ ከ23 ሰከንድ ነበር።
በነሐሴ ወር ሁለተኛ ውድድሩን ሲያደርግ የመጀመሪያ ሰዓቱን ከማሻሻሉም በተጨማሪ ከዓለም በከፍታዋ ሶስተኛ በሆነችው አዲስ አበባ ከተማ ላይ ሮጦ በእንደዚህ አይነት ሰዓት ማራቶንን ከጨረሰ በሌላ ዓለም በሚደረጉ ውድድሮች ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል አብረውት የሮጡት እና አሰልጣኞቹ ምንም ጥርጥር አልነበራቸውም።
አበበ የነገሰባቸው የሮም ጎዳናዎች
አበበ በአጋጣሚ ተሳታፊ የነበረበት የ1960 የሮም ኦሊምፒክ ከሌላው ኦሊምፒክ የማራቶን ውድድሮች ለየት ባለ መልኩ ነበር የተካሄደው። ማራቶኑ የሚካሄድባቸው ጎዳናዎች የከተማዋን ታላላቅና ታሪካዊ ህንጻዎች እና ቦታዎች ለዓለም እንዲታዩ ተደርገው የተዘጋጁ ነበሩ። በኦሊምፒክ ታሪክ በምሽት እንዲካሄድ የተደረገው የሮም ኦሊምፒኩ የማራቶን ውድድር በአውሮፓዊያኑ ሰዓት አቆጣጠር ማምሻውን 5:30 ላይ የማይክል አንጄሎ ንድፍ ውጤት ከሆነው ካምፒዶሊዮ አደባባይ ተጀመረ።
ውድድሩ ከተጀመረ ጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ሮም ጨለመች፡፡ የመሮጫ ጎዳናዎች ግን በግራና በቀኝ ዳር ላይ በተሰለፉት የሮማ ወታደሮች ባበሩት ችቦ በሚያምር ብርሃን አሸብርቀው ነበር። የመጨረሻው የማራቶኑ ሩጫ ክፍል የሚያልፈው ደግሞ ከሺዎች አመታት በፊት የጥንታዊቷ ሮም ወታደሮች ሰልፍ እንዲያካሂዱበት ተብሎ በተገነባው ዋንኛ መንገድ ላይ ነበር።
ከውድድሩ ባሻገር ሮም ታሪኳን ለዓለም ለማሳየትና ለኦሎምፒክ እና ለማራቶን ክብር ሲባል ነበር። በዚህ ውድድር 68 የማራቶን ሯጮች ሲሆኑ ከውድድሩ አዘጋጅ ጣሊያን ጋር በታሪክ ጠላትነት ካላት የጀግኖች አባቶች እና እናቶች አገር ኢትዮጵያ የመጣው አበበ ቢቂላ አንዱ ነው።
ታላቁ ውድድር በደመቀ ሁኔታ በምሽት በዚህ ሂደት ተጀመረ፡፡ አራት አትሌቶች የብሪታኒያው ኬሊ፣ የቤልጂየሙ ቫንዴንድሪኽ፣ የሞሮኮው ረሃዲን እና አበበ ቢቂላ ከሌላው ቡድን ተነጥለው ወደፊት ወጡ።
አበበ ከሲዊዲናዊው አሰልጣኝ ኒስካነን የተነገረው የመጀመሪያ ምክር ሞሮኳዊውን አትሌት ረሃዲን “እንዳትለቅ’’ የሚል ነበር። አስቀድሞ 12 ማይልን ሳያልፍ በመሪነት እንደማይሮጥ የተናገረው አበበ ከረሃዲ ጋር በመሆን 16ኛው ማይል ላይ ወደፊት ከሌሎቹ ተነጥለው ወጡ፡፡
ሁለቱ አፍሪካዊያን አትሌቶች አብረው እየሮጡ እንዳለ አበበ ከፊት ለፊቱ ያየው ነገር ፍጥነቱን እንዲጨምር እና ረሃዲንን ጥሎ እንዲሮጥ አደረገ፡፡ አበበ የተመለከተው ፋሺስት ኢጣሊያ አትዮጵያን ሲወር ሰርቆ ሮም ጎዳና ላይ አቁሞት የነበረውን የአክሱም ሀውልትን ነበር።
አበበ ስለ ሀውልቱ ቀድሞ አሰልጣኙ ነግሮት ነበርና ወኔ ቀሰቀሰበት፡፡ አበበ ከዚያ ሊያዝ አልቻለም። አበበ ረሃዲንን በ25 ሰከንዶች በመቅደም ርቀቱን 2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ16.2 ሰከንድ በማጠናቀቅ የዓለምን ክብረ ወሰን ሰበረ፡፡ ፈፅሞ ማንም ያልገመተውን የወርቅ ሜዳሊያ አጠለቀ፡፡ ለአገሩና ለመላው አፍሪካ ትልቅ ታሪክ ፃፈ።
ሮምን ለብቻው የወረረ ወታደር
ጋዜጠኞች ስለ አበበ አወሩ፤ ስለ ገድሉ ዘረዘሩ፡፡ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎቹ የኢትዮጵያና ያዘጋጅው አገር ጣሊያን ያለፈ ታሪክ በማስታወስ “ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመያዝ መላው ጦሯ ነበር ያሳተፈችው፤ ዛሬ ግን አበበ ቢቂላ የተባለ ኢትዮጵያዊ ወታደር ብቻውን በባዶ እግሩ ሮምን ወረረ፡፡” ብለው ዘግበውም ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መዝሙር ጣሊያን ላይ በክብር መዘመሩም ትልቅ ድል ነበር፡፡
አበበ ዳግም በኦሊምፒክ ድል
በባዶ እግሩ ሮም ላይ ሮጦ በማራቶን ዓለምን መቆጣጠሩ ሳያንስ እ.አ.አ በ1964 ቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ በማራቶን ውድድር በጫማው ሮጦ የወርቅ ሜዳሊያን አስገኘ፡፡ ነገር ግን ይህ ብቻ አልነበረም አስገራሚው ነገር፡፡ የኦሊምፒክ ውድድሩ ከመጀመሩ 40 ቀናት ቀደም ብሎ የትርፍ አንጀት ሕመም ገጥሞት ሆስፒታል ገብቶ የቀዶ ጥገና ተደርጎለት በደንብ ሳያገግም ማሸነፉ ነበር አጀብ ያስባለ ገድሉ፡፡
78 ሯጮች በተሳተፉበት በቶኪዮው ኦሊምፒክ የማራቶን ውድድር ላይ አንደኛ በመውጣት ውድድሩ ለመመልከት የታደመው 70 ሺህ ተመልካች ማመን በማይችልበት ሁኔታ ርቀቱን 2 ሰዓት ከ12 ደቂቃ ከ11.2 ሰከንድ በሆነ ጊዜ አጠናቆ የዓለምን ክብረወሰን በመስበር በሁለት ተከታታይ ኦሊምፒኮች በማራቶን አከታትሎ ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ያገኘ ብቸኛ አትሌት ለመሆን በቅቷል።
አሳዛኙ መጨረሻ
መጋቢት 15 ቀን 1961 ዓ.ም የተሰማው ዜና፤ ኢትዮጵያዊያንን ብቻ ሳይሆን መላውን የስፖርት አፍቃሪ ቤተሰብ ያሳዘነ ነበር። አበበ ከአዲስ አበባ 70 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ከባድ የመኪና አደጋ ደረሰበት። ለህክምና ወደ እንግሊዝ ተልኮ ለስምንት ወራት ያህል ሲታከም ቢቆይም እነዚያ ተአምር የሰሩ እግሮቹ ሊራመዱለት አልቻሉም፡፡ ታላቁ አትሌት ከወገቡ በታች አካል ጉዳተኛ ሆነ። ነገር ግን አትሌቱ ብርቱ ነበርና በሌሎች የውድድር ዘርፎች መሳተፉን ቀጠለ፡፡
አበበ እንግሊዝ አገር በተካሄደ የቀስት ውድድር አሸንፏል፡፡ ኖርዌ ላይ በተካሄደ የዊልቸር የ25ኪ.ሜ የአገር አቋራጭ ውድድር እንዲሁም ከሶስት ቀናት ቆይታ በኋላ በተካሄደው የ12 ኪ.ሜ ውድድር አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ ተሸልሟል፡፡ ታላቁ አትሌት አበበ ቢቂላ በጥቅምት ወር 1973 ዓ.ም በ41 አመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡ ተዓምረኛው ጀግና እትሌት አበበ ቢቂላ፤ የሰራቸው ገድሎች በወርቃማ ፅሁፍ ተከትቦ ዛሬ ድረስ ይወሳል፡፡
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 2015 ዓ.ም