ዛሬ ወደ 2015 አዲስ አመት ተሸጋግረናል፡፡ እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁ! ፀሐፊ ገጣሚና መምህር ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ አዲስ አመትን ወይም የዘመን መለወጫን አስመልክቶ የሚከተለውን ብሏል፤ “ፍቅርና መተሳሰብን፣ ይቅርታንና መቻቻልን የነፈገንን የብሔረተኝነት ግድግዳ አፍርሰን፣ ከከረመ ደዌያችን ለመፈወስ ስንዳክር አምናን ሸኝተን፣ አዲስ ሃይማኖታዊ ከፋፋይ ግድግዳ ለማቆም ከንች ጠርበን ወደ አዲሱ አመት እየገባን፣ ስለምን ‹እንቁጣጣሽ!› እንባባላለን? የብሔርን ከፋፋይ አጥር፣ በብሔር የፍቅር ሰንሰለት ለመተካት፣ የዳከርንበትን አምና ፍሬ በማየት ተስፋ ሳይሆን፣ በአዲስ የሃይማኖት ከፋፋይ ግንብ ስጋት ከተቀበልነው፣ አዲስ አመት አለ? ‹እንቁጣጣሽ› መባባል አግባብ ነው? ሲል ጸሐፊው ይጠይቃል፡፡
ከልጃገረዶች ‹አበባ አየሽ ወይ – ለምለም› ቄጠማ፣ ከኮበሌዎች በቀለማት ያሸበረቀ አበባስ ስለምን እንቀበላለን! ሁሉስ ስለ አዲስ ተስፋ፣ በልባችን ስለ ሰነቅነው ብሩህ ቀን ተምሳሌት አይደለምን? ከሜዳው፣ ከሸንተረሩ፣ ከዥረቱ፣ ከአደዩና ከመስቀል ወፉ -ከተፈጥሮስ ይሁን እንጉደል፣ እንዴት ከልጆቻችን ተስፋና ምኞት እንጎድላለን? ሲልም ይጠይቃል፡፡
የዛሬውን የ2015 መስከረም አንድ የባህልና ቱሪዝም አምድ በፀሃፊ ገጣሚና መምህር ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ ጠንከር ያለ ሃሳብ መጀመር የፈለግነው በምክንያት ነው። ኢትዮጵያ ከውስጥ በባንዳ፣ ከውጪ ደግሞ በታሪካዊ ጠላቶቿ ተከባ፣ ዜጎቿ ያለፈውን ዓመት የዘመን መለወጫ በተስፋና ስጋት ውስጥ ሆነው አሳልፈዋል። በቅርቡ የሰላም ጭላንጭል የታየ ቢመስልም ቅሉ አሸባሪው ሕወሓት በለኮሰው ጦርነት፣ የሰላም አየር እንዳይነፍስ፣ በኑሮ ውድነት እንዲፈተኑ፣ አገርና ዜጎች ሙሉ አቅማቸውን ለልማት እንዳያውሉ ተደርገዋል፡፡ በዚህ አይነቱ ወቅት ነው እንግዲህ አዲሱን 2015 አመት በዛሬው እለት የተቀበልነው።
ዘመን ተለውጧል፤ ከዘመን ጋር መለወጥ ሲገባቸው፣ መለወጥ ቀርቶ ዝግጁነቱ የሌላቸው ጥቂት አይደሉም፤ ዛሬም በአምናው መንገድ የሚሄዱ ሞልተዋል፡፡ ይህ መታረም አለበት፤ ዘመን ብቻውም መለወጡ ትርጉም የለውም፤ ዘመን መለወጡን የሚያቀነቅኑ ሁሉ፣ በዘመን መለወጥ የሚያተርፉ ሁሉ የአመለካከት ለውጥም ማምጣት ይኖርባቸዋል፡፡ ወደቀደመው አመት መመለስ እንደማይቻል ሁሉ፣ ተመልሰው መያዝ የሌለባቸው ነገሮች ወደ አዲሱ አመት እንዳይሻገሩ ለማድረግ ብዙ መስራት ይገባል፡፡
ኢትዮጵያውያን ምንም ያህል በአስከፊ ችግር ውስጥ ቢሆኑም የዘመን መለወጫን ደግ ደጉን እየተመኙ፣ ፍቅርና ሰላም እንዲመጣ ለሚያምኑት አምላክ እየተማፀኑ፣ ልጆች በወግ ባህሉ ጨዋታ ደምቀው ነው፣ ሽማግሌዎች እየመረቁ የሚቀበሉት።
ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ፣ የታሪክ፣ የተፈጥሮና የባህል መናገሻ ነች። ህዝቦቿ በብዙ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች ውስጥ ሆነውና ተዋደው የሚኖሩ የፍቅርና የመከባበር ተምሳሌቶች ናቸው። አገሪቱ የራሷ የዘመን መቁጠሪያና ፊደል ያላት፤ በሌላው ዓለማት በማይገኙና ተወዳጅ በሆኑ በዓላት፣ አልባሳትና የአመጋገብ ስርዓት የምትታወቅም ነች።
ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ ብትሆንም፣ እነዚህ ብሔር ብሔረሰቦች እጅግ ብዙና ህብርን የተላበሱ እሴቶችና የጋራ ማንነቶችም ያሏቸው ናቸው። ዜጎች ከየሃይማኖታቸው ከሚቀዱ የበዓል ስርዓቶች የተገነባ ውብ ማንነት መላበሳቸው፣ በመቻቻል ለዘመናት አብሮ በመኖር ባዳበሩት እሴት የተነሳ ሁሉም የሚጋሩት ባህልና ኢትዮጵያዊ ቀለም ያላቸው መሆናቸውም እንዲሁ የማንነታቸው መገለጫ ነው።
የዘመን መለወጫ ከተበሰረበት ቀን አንስቶ “ከመስከረም እስከ መስከረም” አያሌ ተወዳጅና በጉጉት የሚጠበቁ ክብረ በዓላት፤ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ስነ ስርዓቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ይካሄዳሉ። ከዘመን መለወጫ “እንቁጣጣሽ” እስከ መስቀል፣ ኢሬቻ፣ ጨምበላላ፣ ጥምቀት፣ ጊፋታ እና ሌሎችም በርካታ የማህበረሰቡን ባህላዊና ሃይማኖታዊ ስርዓቶች የሚያሳዩ ተወዳጅ እሴቶች በድምቀት ይከበራሉ። አገሪቱ ከውጭ ሆኖ የሚመለከታቸውን በሚያስቀኑና “የኔ በሆኑ” በሚያሰኙ ኢትዮጵያዊ ህብር ማንነቶች የደመቀችና የተወደደች ነች።
የዘመን መለወጫ ደግሞ ለምን እንደተባለና ለምን “መስከረም” ወር ላይ እንደሆነ ሊቃውንት ያትታሉ፡፡ “ብርሃናት/ፀሐይ፣ጨረቃ፣ ከዋክብት/ የዓመት ዑደታቸውን በጳጉሜን ወር ጨርሰው በመስከረም ወር ስለሚጀምሩ ነው፡፡ ያን ጊዜ ሌሊቱም ከቀኑ ጋር ይተካከላል፡፡ በሌላ በኩልም በዘመነ ኖኅ ዓለምን ውኃ አጥለቅልቋት ከቆየ በኋላ ዳግመኛ ከነበረው ውኃ የተገለጠችበት ወር «በመጀመሪያም ወር በምድር ታየች፤ የንፍር ውኃው ከምድር ደረቀ» የሚለውን መሠረት አድርገው የአቡሻኽር ሊቃውንት የዘመን መለወጫን ታሪካዊ አመጣጥ ያስረዳሉ፡፡
እንደ ሊቃውንቱ ገለፃ፤ ዘመን ተለወጠ ሲባል የሚለወጡት ወራቱ ብቻ አይደሉም፡፡ በወቅቱ የሚከሰቱት (የተከሰቱት) መልካምም ሆኑ ክፉ ነገሮች “ገጠመኝ” ሲሆኑ፣ ወራቱ ግን ያው በየዓመቱ እየተፈራረቁ ይመጣሉ፡፡
ዘመን መለወጫ ላይ የሰው ልጆች ሕይወት ሊለወጥ ይገባል፡፡ ተማሪው ተምሮ ወደቀጣዩ ክፍል (ደረጃ) የሚገባበት፣ ገበሬው የክረምትን ወራት በሚገባ ተጠቅሞ የሚቀጥሉትን የበጋ ወራት በተስፋ የሚቀበልበት፣ ሠራተኛው የክረምቱን ዝናብ ታግሶ የፀሐይን ወራት የሚቀበልበት ሌላውም እንደዚያው ሆኖ ወራቱ በዚያ ዘመን ያላቸው የተፈጥሮ ክስተቶች የሚለወጡበት ሁኔታ ዘመን ተለወጠ እየተባለ ይነገራል፡፡
አዲስ አመት ባህላዊ ስርዓት
ጨለማው ሲጠፋ ዝናቡ ሲያቆም፤
ያ የለውጥ ወራት መጣ መስከረም።… እያሉ ወጣት አዛውንቱ፣ ህፃናት ልጃገረዶች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ያዜማሉ። ልክ እንደ ዛሬዋ ቀን (መስከረም አንድ) አዲስ ዓመት ሲመጣና “መስከረም ሲጠባ” በኢትዮጵያውያን ዘንድ ወግ ባህሉ፣ ጭፈራው ድምቀቱ እዚህም እዚያም ይታያል። በተለይ መላ ኢትዮጵያውያን በጋራ በየራሳቸው ሃይማኖታዊ ስርዓትና ባህላዊ ይዘት ይህን ቀን በድምቀት ያከብሩታል።
ከዋዜማው ጀምሮ በየቤቱ ጨፌና ቄጠማ ይጐዘጉዛል። አበባ በሥርዓት እየተዘጋጀ በየቦታው ይቀመጣል። ልጆች አዳዲስ አልባሳት ለብሰው በደስታ ይፈነድቃሉ። ቤተዘመድ ከሌላው ቀን በተለየ ይጠያየቃል። ወዳጅ ጓደኛ ስጦታ ይለዋወጣል። በዕንቁጣጣሽ መዓልት በተደመረው አድባር ሰፈርተኞች ከርቀትም ከቅርበትም ይሰበሰባሉ። አባቶች ይመርቃሉ። “ዝናቡን ዝናበ ምሕረት፣ እህሉን እህለ በረከት ያድርግልን፣ ሰላም ይስጠን፣ እህል ይታፈስ፣ ገበሬ ይረስ፣ አራሽ ገበሬውን፣ ሳቢ በሬውን ይባርክ፣ ቁንጫን፣ አንበጣን፣ ትልን… ያጥፋ፣ ምቀኛን ሸረኛን ያጥፋ፣ ወጡ ገቡ ሰቡ ረቡ የሚለውን ሁሉ እግሩን ቄጠማ ዓይኑን ጨለማ ያድርገው፣ ያርገው፣ ያረገው፣…” እያሉ ምርቃቱን ያዥጎደጉዱታል። ሁሉም ያለውን ተካፍሎ በህብረት ይበል፤ ይጠጣል። በእለቱ ጥጋብ፣ ፍቅር እና ደስታ በቀጣዮቹ ቀናት ይሆናሉ። ተስፋን ሰንቆ ፡፡
በዕለተ ዕንቁጣጣሽ በተለይ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የልጃገረዶች ጭፈራና ጨዋታ እየደራና እየሞቀ ይሄዳል። በኢትዮጵያ ውስጥ በርከት ያለ ቋንቋ እና ባህላዊ ስርዓት በመኖሩ ምክንያት የዘመን መለወጫ ግጥሞችና የጭፈራ አይነቶች ሊለያዩ ቢችሉም፣ አብዛኛዎቹ ተስፋን፣ ፍቅርን፣ አብሮ መብላትን፣ የልጃገረዶችና ጉብሎች መፈላለግና መተጫጨትን እና ሌሎች የደስታ መልክቶችን የሚይዙ ናቸው። ከእነዚህ መካከል ተቀባዮቹ “ያደይ” እያሉ “ዕንቁጣጣሽ ያደይ ዕንቁጣጣሽ” “በየት ገባና ቆነጠጠሽ” “ቆነጠጠኝ ልቤን ልቤን ኩላሊቴን ፤ እናቴን ጥሩ መድኃኒቴን፤ እሙ ካልመጣች መቸም አልድን፤ እርሷን ካጣችሁ መቀነቷን፤ አበባሽ አደይ አበባዬ…” ሲሉ ያዜማሉ፡፡
ዕንቁጣጣሽ- ባህላዊ አልባሳት
ኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው በርካታ ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶች መካከል የሕዝቦቿ ባህላዊ አልባሳት፤ ጌጣጌጥና መገልገያ ቁሳቁስ ይጠቀሳሉ። እነዚህ መድመቂያዎች ይበልጥ የሚታዩትና ተፈላጊነታቸው የሚጨምረው በዓላት በሚመጡበት ጊዜ ነው። በተለይ በዘመን መለወጫ የመስከረም ወር (በእንቁጣጣሽና በመስቀል) በዓላት ወቅት የብሔር ብሔረሰብ መገለጫ የሆኑ፣ ወቅቱን ያማከሉ ባህላዊ ዜማዎች ኢትዮጵያውያንን ያሸበርቃሉ።
ይህንን ፅሁፍ ለማሰናዳት እንዲረዳን ወደ አንድ የባህል አልባሳት ቤት ጎራ ብለን ነበር። የ“የቶቤል የአገር ባህል አልባሳት መሸጫ ሱቅ” ባለቤት አምሳል ባዬ ይህን ስራ ከጀመረች ሶስት ዓመታትን አስቆጥራለች። ወደዚህ ስራ ለመግባት ምክንያቱ “የአገሯን አልባሳት በእጅጉ መውደዷና አዘውትራ መልበሷ መሆኑን አምሳል ትገለጻለች፡፡ አልባሳቱን ለቀሪው ወገኗ በስፋት ለማስተዋወቅ፣ በውጭ አገራት ለሚገኙና በቀላሉ ምርቱን ለማግኘት ለሚቸገሩ ወገኖቿ እድሉን ለማመቻቸት ይረዳል ብላ በማሰብ ወደ ስራው መግባቷን ትናገራለች።
“በተለይ በአዲስ አመት ወይም ዘመን መለወጫ ወቅት ገበያው ይደራል፣ ትእዛዝ በብዛት እንቀበላለን” የምትለው አምሳል ባዬ፤ ኢትዮጵያውያን የአገር ባህል ልብሶቻቸውን በመስከረም ወር የዘመን መለወጫ፣ መስቀል ጥምቀትና ሌሎች መሰል ሃይማኖታዊና ባህላዊ ስነ ስርዓቶች ሲኖሩ እንደሚጠቀሙባቸው ትገልፃለች። የአደይ አበባን መፍካት፣ ልምላሜውን ለመግለፅና በብሩህ ተስፋ መሞላታቸውን ለማመልከት ቢጫ ቀለማትን የያዙ የአገር ልብሶችን እንደሚጠቀሙ ታስረዳለች።
በቶቤል የአገር ባህል ልብስ ቤት የወንድ፣ የሴት፣ የእናቶችና የወጣቶች የተለያዩ አገር ባህል አልባሳት ይገኛሉ። ቀሚስ ከነነጠላው፣ ስካርብ (የአንገት ላይ ልብሶች) ቲሸርቶች እና መሰል በርካታ ባህላዊ አልባሳት በተለያዩ ቀለማትና የጥበብ ክር ደምቀው መደርደሪያዎች ላይ ተሰቅለዋል።
አምሳል ሁሉም ሰው በሚፈልገው ዲዛይንና ቀለም አልባሳቶቹን በሸማኔዎች እንደምታዘጋጅ ተናግራ፣ እንደየጥራትና መጠናቸው ዋጋቸውም እንደሚለያይ ነው ያብራራችው። ከአራት ሺህ ብር አንስቶ እስከ ሃያ ሺ ብር ድረስ የባህል አልበሳት ለሽያጭ መቅረባቸውን ትገልጻለች፤ ከዚያም የሚያንሱና የሚበልጥ ዋጋ ያላቸው ባህላዊ አልባሳት መኖራቸውን አጫውታናለች።
እንደ መውጫ
የዘመን መለወጥን በማስመልከት በምሥራቅ ጎጃም ዞን በወርሃ ነሐሴና ጳጉሜ ከሚከወኑ በርካታ የማይዳሰሱ ባህላዊ ክዋኔዎች መካከል እንግጫ ነቀላ አንዱ ነው። እኛም እንደ መውጫ እንዲረዳ በልጃገረዶችና ጉብሎች በዚህ ወቅት የሚዜመውን ግጥም እንደሚከተለው አቀረብንላችሁ። ወጣት ሴቶች እንዲህ በማለት ሲያዜሙ…
‹‹እቴ አበባዬ ነሽ
አደይ ተክለሻል
አደይ ተቀምጠሻል
ባሶና ሊበን
አዋጋው ብለሻል
ቦሶና ሊበን
ምነው ማዋጋትሽ
አንዱ አይበቃም ወይ›› በዚህ ጊዜ ወንዶች ደግሞ ያዘጋጁትን ዳቦት (የችቦ ስም) በእሳት ለኩሰው እያበሩ በመምጣት እንግጫ ለሚጎነጉኑት ሴቶች ያበሩላቸዋል፡፡
ዳቦታቸውን እያበሩ ወደ ሴቶቹ በሚያመሩበት ጊዜ የሚያዜሙት አላቸው፡፡
‹‹ኢዮሃ ኢዮሃ
የቅዱስ ዮሐንስ
የመስቀል የመስቀል
አሰፉልኝ ሱሪ
ኢዮሃ›› በማለት ያዜማሉ፡፡ አዲስ ዘመንም በይፋ መምጣቱ ይበሰራል።
በመግቢያችን ላይ ለመጥቀስ እንደሞከርነው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚከናወኑ የማህበረሰቡ መገለጫ እሴቶች በሙሉ የጋራ ሃብቶች ናቸው። ከሃይማኖታዊ ፋይዳቸው በዘለለ ባህላዊ እሴቶች የሚጎላባቸው አያሌ ክብረ ባእላትም እንዲሁ ተዋደውና ተከባብረው በሚኖሩ ማህበረሰቦች መካከል ይገኛሉ። የዚህ ጥቅል ድምር ኢትዮጵያ የሚል አንድ የጋራ ማንነትን ይፈጥራል። በጥቅሉ ኢትዮጵያ ውስጥ በዓልና ባህል ልዩ መስተጋብር አላቸው። በተለይ ደግሞ “የዘመን መለወጫ” የሆነው የመስከረም ወር ሲመጣ።
ለዚያም ነው አገራችን ኢትዮጵያ የሺህ ዘመናት የአገረ መንግስት ታሪክ፣ ውብ ባህልና ማንነት ያላቸው ብሔረሰቦች በጋራ ተዋደውና በአንድነት ተጋምደው የሚኖሩባት አገር መሆኗ በገሃድ የሚታይ ሃቅ ነው ይምንለው። መልካም አዲስ ዓመት ለሁላችንም!!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 2015 ዓ.ም