ሀገራችን ያለፉትን ዓመታት በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ አሳልፋለች:: ሉዓላዊነቷን የተፈታተኑ ሁለት ታላላቅ ጦርነቶች በአሸባሪው ሕወሓት ተከፍተውበታል፤ የአሸባሪው ተላላኪዎች በተለያዩ አካባቢዎች ያደረሷቸው ውድመቶች እና ጦርነቶቹን ተከትለው የመጡ ዓለም አቀፍ ጫናዎች፣ የኮቪድ ወረርሽኝና የኑሮ ውድነት ሌሎች ተግዳሮቶች ነበሩ:: ጦርነቶቹ የቱንም ያህል ፈታኝ ቢሆኑም፣ ኢትዮጵያውያን በመንግሥታቸው በሳል አመራር በመታገዝ በድል ተወጥተዋቸዋል::
በ2014 ዓመት አሸባሪው ሕወሓት የፈጸመውን ወረራ በመመከት፣ ጦርነቱን ተከትሎ በኢትዮጵያ ላይ የተደረጉ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጫናዎችን በመቋቋም፣ የሀገር ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ በተጨማሪ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በተለያዩ መስኮች ጣፋጭ ስኬቶች ተመዝግበዋል:: ከእነዚህ ስኬቶች መካከልም ዛሬ በሚጠናቀቀው የ2014 ዓ.ም በፈተናዎች ውስጥ በኢኮኖሚው መስክ ከተመዘገቡ ስኬቶች ዋና ዋና ያልናቸውን በዛሬው የስኬት አምዳችን ይዘን ቀርበናልን::
የዓባይ ግድብ
ግንባታው በ2003 ዓ.ም የተጀመረው የአባይ ግድብ እየተገነባ ያለው በኢትዮጵያውያን አንጡራ ሀብት ነው:: ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ግንባታው ከተጀመረ አንስቶ እስከ አሁንም ድረስ በተለያየ መልኩ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል:: የኢትዮጵያውያን የአንድነታቸው መገለጫ የሆነው ይህ ግድብ ዜጎች ድጋፎችን በማድረግ ብቻ አይደለም ግንባታው እንዲካሄድ እያደረጉ ያሉት:: ግንባታው ላይ ጫና ለማሳደር ግብጽን ጨምሮ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን በዲፕሎማሲው መስክ በመዋጋትም ጭምር ነው:: ግንባታው ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሆነው የሚገነቡት ግድብ እንደመሆኑም ግድቡን ዛሬ ከሚከበረው የአንድነት ቀን ጋር አስተሳስሮም ማየት ይቻላል::
ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ በአጠቃላይ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት የአሌክትሪክ ሃይል ያመነጫል:: 13 የሃይል ማመንጫ ዩኒቶች (ተርባይኖች) ይኖሩታል:: በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አባወራዎችን የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የሚጠበቀው የዚህ ግድብ ግንባታ፣ ባጋጠመው መጓተት የተነሳ መጠናቀቅ ከነበረበት ጊዜ መዘግየቱ ይታወቃል::
የለውጡ መንግሥት ከሞት የታደገው የዚህ ግድብ ግንባታ ታዲያ የዘገየውን ያህል፤ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ድሎች በአናት በአናቱ እየተመዘገበበት ይገኛል፤ በ2014 ዓ.ም በተለይ ከየካቲት ወር አንስቶ ግድቡ ሶስት ስኬቶች ተመዝግበውበታል::
ግድቡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ለሁለት ዙር የውሃ ሙሌት ተደርጎለታል፤ እነዚያ የውሃ ሙሌቱ መካሄዱ ይፋ የተደረገባቸው ቀናት ለኢትዮጵያውያን ታላቅ የተባሉ እንደነበሩ ይታወሳል:: ኢትዮጵያውያን በሙሉ በውሃ ሙሌቶቹ መጠናቀቅ የተሰማቸውን ደስታ አደባባይ ወጥተው ጭምር ነበር የገለጹት:: በዚህ ባጠናቀቅነው ዓመት ደግሞ ሦስተኛ ዙር ውሃ መሙላትና ሁለተኛውን ዩኒት ኃይል እንዲያመነጭ በማድረግ ደስታውን ከፍ ማድረግ ተችሏል:: በዚህም በዓመቱ በሁለት ዩኒቶች ማለትም ዩኒት አስር በየካቲት ወር ዩኒት ዘጠኝ ደግሞ በዚህ የክረምት ወቅት ሃይል ማመንጨት ተችሏል::
የዩኒቶቹ ወደ ስራ መግባትን ተከትሎ በሁለቱ ዩኒቶቹ ብቻ ግድቡን ከጊቤ ሶስት የሃይል ማመንጫ ቀጥሎ የሀገሪቱ ሁለተኛው ግዙፍ ኃይል ያመነጨ ግድብ እንዲሆን አድርገውታል:: እነዚህ እያንዳንዳቸው 375 ሜጋ ዋት ሃይል የሚያመነጩ ዩኒቶች፣ አሁን ባለው የግድቡ ከፍታ ከ550 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ሃይል እያመነጩ ናቸው:: በሙሉ አቅማቸው ሃይል ማመንጨት ሲጀምሩ ደግሞ 750 ሜጋ ዋት ማመንጨት ይችላሉ:: ግድቡ ገና እሸቱን ባቋደሰባቸው በእነዚሀ ሁለት ዩኒቶች ለሀገሪቱ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚችል ይገመታል::
ግድቡ በእነዚህ ዩኒቶቹ የኢትዮጵያውያንን በአባይ ወንዝ የመልማት ራእይ እውን መሆን እንዲሁም አባይ መብራትም ራትም መሆኑን መጀመሩን አብስሯል:: የአባይ ግድብ ሶስተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት ያደረገውም በእዚሁ ክረምት ነው:: ይህም ሌላው የዓመቱ ታላቅ ስኬት ተደርጎ ይወሰዳል:: ግድቡ በአሁኑ ወቅት ከ22 ቢሊዮን ሜትር ኩብ በላይ ውሃ መያዝ ችሏል:: ገና ከአሁኑ በጉባ አንድ ትልቅ ሃይቅ ተፈጥሯል::
የገቢ አሰባሰብ
ሀገሪቱ ወጪዋን በራሷ ገቢ ለመሸፈን የምታደርገውን ጥረት ተከትሎ የምትሰበስበው ገቢም እያደገ መጥቷል:: ለእዚህም ማሳያ ከሆኑት መካከል የገቢዎች ሚኒስቴር በተጠናቀቀው (በ2014) በጀት ዓመት 360 ቢሊየን ብር ሊሰብስብ አቅዶ ፣ 336 ቢሊዮን 710 ሚሊዮን 021 ሺ 930 ብር መሰብሰብ መቻሉ ይጠቀሳል፤ በዚህም የእቅዱን 93 ነጥብ 53 በመቶ ማሳካት ችሏል:: አፈጻጸሙ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የብር 57 ቢሊዮን 494 ሚሊየን 923 ሺ 697 ወይም የ20 ነጥብ 59 በመቶ እድገት አለው::
ገቢው በአገሪቱ በተፈጠረው ጦርነት ብዙ ገቢ ሰብሳቢ ተቋሞች ከስራ ውጪ በሆኑበት ፣ በጦርነቱ ምክንያት የንግዱ አንቅስቃሴ በተቀዛቀዘበት ፣ በተለያዩ አካባቢዎች በሚፈጠሩ ግጭቶች ገቢ ሰብሳቢ ተቋሞች በአግባቡ ስራቸውን እንዳይሰሩ በተቸገሩበት እንዲሁም የንግዱ ማሕበረሰብ ስራውን ተረጋግቶ ባልሰራበት ሁኔታ ውስጥ የተሰበሰበ በመሆኑ የተሻለ አፈጻጸም ሊያስበለው የሚችል መሆኑን ከገቢዎች ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል::
ተቋሙ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በገቢ አሰባሰብ ያስመዘገባቸው ውጤቶችም የሚሰበሰበው ገቢ እየጨመረ መምጣቱን ያስገነዝባሉ:: በ2010 በጀት ዓመት 152 ቢሊዮን ብር፣ በ2011 በጀት ዓመት 198 ቢሊዮን፣ በ2012 በጀት ዓመት 233 ቢሊዮን ብር፣ በ2013 በጀት 279 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም በ2014 በጀት ዓመት 336 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሏል፤ ይህም የገቢውን እድገት ቀጣይነት እንደሚጠቁም የሚኒስቴሩ መረጃ ይጠቁማል::
የወጪ ንግድ
ሀገሪቱ ከወጪ ንግድ ይበልጥ ተጠቃሚ እንድትሆን ከመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን አቅድ አንስቶ ብዙ ለመስራት ታቅዶ ነበር፤ ይሁንና ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ መጨመር ሲገባው በየዓመቱ ከእቅድ በታች ይሰበሰብ እንደነበርና ጉዳዩ አሳሳቢ መሆኑ በወቅቱ ሲገለጽ እንደነበርም ይታወቃል:: ሀገሪቱ በወጪ ንግድ ለማግኘት ያቀደችውን ገቢ ለማግኘት እንዲቻላት ብዙ ምርት የመላክ፣ የወጪ ምርት አይነቶችንና መዳረሻዎችን የማስፋት አቅጣጫዎችን በመከተል ብዙ ብትሰራም የሚፈለገውን ያህል ገቢ ማግኘት አልተቻለም ነበር::
ይህ ታሪክ ግን በ2014 በጀት ዓመት ተቀይሯል፤ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው 2014 በጀት ዓመት በወጪ ንግድ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ እንደቻለች አስታውቀዋል:: ለተገኘው ውጤትም የተጀመሩ ሁለንተናዊ የሪፎርም ሥራዎች ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ጠቁመዋል::
በ2014 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ ከ4 ነጥብ 12 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር መረጃዎች ያመለክታሉ። አፈጻጸሙም በወጪ ንግድ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመዘገበ ነው ተብሏል:: ይህ አፈፃፀም ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀርም የ 13 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተጠቁሟል:: በአጠቃላይ ለወጪ ንግዱ ገቢ የግብርናው ዘርፍ 72 በመቶ፣ የኢንዱስትሪው ዘርፍ 12 በመቶ እንዲሁም የማዕድን ዘርፉ 14 በመቶ አስተዋጽኦ ማበርከት ችለዋል:: ለተመዘገበው ውጤት ሁሉም ዘርፎች ከፍተኛ ርብርብ አድርገዋል::
የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ቀን “የኢትዮጵያን ባለ ልዩ ጣዕም ምርት ይግዙ” በሚል መሪ ሃሳብ በፓናል ውይይት፣ የእውቅናና ሽልማት መርሐ ግብር በተካሄደበት ወቅት የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ ለተመዘገበው ከፍተኛ የወጪ ንግድ ገቢ የመንግሥት ተቋማት እና የግሉ ዘርፍ የበኩላቸውን ሚና እንደተወጡ ጠቅሰው፣ በቀጣይም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በትብብር እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በ2014 በጀት ዓመት በወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ ችግሮች ውስጥ ሆነን ጠንካራ ኢኮኖሚ እየገነባን መሆናችንን ያሳየንበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የበጋ መስኖ የስንዴ ልማት
ዛሬ የሚሰናበተው የ2014 ዓ.ም ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ታምር የሰራችበት መሆን ችሏል:: ሀገሪቱ ከጥቂት ዓመታት በፊት በበጋ መስኖ የጀመረችው የስንዴ ልማት ፍሬያማ እየሆነ መጥቶ በ2014 ዓ.ም ስኬታማ መሆን ችሏል:: መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ በተጠናቀቀው የ2014 በጀት ዓመት በመጀመሪያው ዙር ስንዴ በበጋ መስኖ ለማልማት ከ405 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 16 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ በመስኖ ማምረት ተችሏል። በሁለተኛው ዙር ደግሞ ከ208 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ዘር በመሸፈን ስምንት ነጥብ 35 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ተመርቷል::
የቆላና የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በአፋር፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሌና በሌሎች ክልሎች እየተስፋፋ መጥቷል፤ ለብዙ የኢትዮጵያውያን አርሶና አርብቶ አደሮች እንግዳ፤ ለቆላማ አካባቢዎች ባዳ የነበረው የቆላ ስንዴ ምርት ዛሬ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ አምራቾች እየተሳተፉበት ይገኛሉ:: በደጋና ወይና ደጋ ላይም አርሶ አደሩ በኩታ ገጠም ማሳ ወንዞችን በመጠቀም በበጋው ወቅት ስንዴ በመስኖ ማልማቱን ተያይዞታል::
በግብርና ሴክተሩ ላይ ተግባራዊ የተደረገው ተሃድሶ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ጉልህ ሚና ማበርከቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል። ሚኒስቴሩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚያስፈልግ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ የስንዴ ግዥን በመስኖ ስንዴ ልማቱ ማዳን መቻሉንም ነው ያመለከተው።
በዘርፉ በተገኘው ውጤት ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚያስፈልገውን የስንዴ ምርት ፍላጎት በመሸፈን በሚቀጥለው ዓመት ስንዴን ወደ ውጭ አገር ለመላክ የሚያስችል ቁመና ላይም መደረሱንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድም በተለያዩ ጊዜያት አስታውቀዋል።
ሀገሪቱ በተያዘው በጀት ዓመት የስንዴ ልማቱንም ወደ አንድ ሚሊዮን ሄክታር ከፍ ለማድረግ ውጥን እንዳላትም ተጠቁሟል። ከዚህ የሚገኘው የስንዴ ምርት ከመኸር ወቅቱ የስንዴ ምርት ጋር ሲዳመር ሀገሪቱ ከሚያስፈልጋት በላይ 10 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ማምረት እንደምትችልም የግብርና ምርምርን ዋቢ ያደረገ ዘገባ አመልክቷል::
የሀገሪቱ የስንዴ ልማት የዓለም አቀፍና የአፍሪካ ተቋማትን እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት በእጅጉ መሳብ ችሏል:: ኢትዮጵያ እስከ ሁለት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ ለጎረቤት ሀገራት የማቅረብ አቅም ያላት ሀገር ነች ሲሉ የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንትም አስታውቀዋል:: በጋና አክራ ባለፈው ግንቦት በተካሄደ የቡድን ሰባት ሀገሮች የልማት ሚኒስትሮች ዓመታዊ ስብሰባ መዝጊያ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ በ650ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ሰንዴ ማምረት በሚያስችል ደረጃ ላይ መገኘቷን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መስማታቸውን ገልጸዋል።
ብሉምበርግ፣ የኬንያው ኔሽን ጋዜጣም እንዲሁ የስንዴ ልማቱን በስፋት ዘግበውታል:: ብሉምበርግ ባለፈው ሰኔ ወር በሰራው ዘገባ ሀገሪቱ በፈረንጆቹ በ2021 አንድ ነጥብ 42 ሚሊዮን ቶን ስንዴ ማምረቷን አስታውሶ፣ በ2022 ደግሞ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ቶን ስንዴ ለማምረት ማቀዷን በዘገባው አመልክቷል:: ሀገሪቱ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ከሕወሓት ጋር እየተዋጋች ብሄራዊ የስንዴ ልማት በማካሄድ ከውጭ የምታስገባውን ስንዴ በሀገር ውስጥ ለመተካት እየሰራች ነው ሲልም ዘግቧል::
የኬንያው ኔሽን ጋዜጣም እንዲሁ ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ስለምን ተሳካላት? በሚል ርዕስ ሰፋ ያለ ሀተታ አስነብቧል። ቀደም ባሉት ዓመታት የአገሪቷ የግብርና ፖሊሲ በመኸር እና በበልግ ወቅት እርሻ ላይ ብቻ ያተኮረ መሆኑን ጠቅሶ፣ ባለፉት ሶስት ዓመታት ግን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግስት ስንዴን በበጋ ወራት መስኖ በክላስተር ማምረት እንደሚቻል በማመን ሶስተኛ የእርሻ ወቅትን አስተዋውቋል ሲል አትቷል::
ሲኤን ኤን በበኩሉ የፕላን ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋን ዋቢ አድርጎ በሰራው ዘገባ ሀገሪቱ የበጋ የስንዴ መርሐ ግብርን በመጠቀም የዝናብ ወቅትን ብቻ በመጠበቅ ይከናወን ከነበረው የግብርና ሥርዓት በመውጣት በመስኖ የታገዘ የስንዴ ልማት እያከሄደች መሆኗን፣ በተሰራው ስራም 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቶን ስንዴ ማምረት መቻሉን መግለጻቸውን ዘግቧል:: ይህ የተቀናጀ ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሥርዓትም የተዳከመውን ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ ያግዛል ማለታቸውንም ጠቅሷል::
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 5 ቀን 2014 ዓም