የዘንድሮ አምስቱ የጳጉሜን ቀናት በልዩ ሁኔታ ታይተዋል:: ጳጉሜን በመደመር በሚል መሪ ቃል ቀናቱ የየራሳቸው ስያሜ ተሰጥቷቸው በተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተከበሩ ይገኛሉ:: ጳጉሜን 1 የበጎ ፈቃድ ቀን፣ ጳጉሜን 2 የአምራችነት ቀን፣ ጳጉሜን 3 የሰላም ቀን፣ ጳጉሜን 4 የአገልጋይነት ቀን፣ ጳጉሜን 5 የአንድነት ቀን ተብለው ተሰይመው ነው የተከበሩት::
ዛሬ የ2014 የመጨረሻው ቀን የሆነው ጳጉሜን 5 የአንድነት ቀን ተብሎ እየተከበረ ነው:: በእያንዳንዱ የጳጉሜን ቀን ከእለቱ ስያሜ ጋር የተገናኙ መርሃ ግብሮች እና የተለያዩ ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን፣ በዛሬው እለትም ከአንድነት ጋር ቁርኝት ባላቸው እና አንድነትን በሚያጠናክሩ መርሃ ግብሮች እየተከበረ ይገኛል::
የአዲስ ዘመን መሰረተ ልማት አምድም መሰረተ ልማቶች በተለይ እንደ መንገድና ትራንስፖርት ያሉ መሰረተ ልማቶች ሕዝብን፣ አካባቢዎችን፣ ሀገርን በማስተሳሰር የአንድነት ስሜትን ከመፍጠር አኳያ ባላቸው ፋይዳ ላይ የሚያተኩር ይሆናል::
እንደሚታወቀው፤ ኢትዮጵያ በየዓመቱ በተለያዩ ፕሮግራሞች በርካታ ኪሎሜትሮችን የሚሸፍን የመንገድ ግንባታ ታካሂዳለች:: እነዚህ የመንገድ ፕሮጀክቶች የሚገነቡት ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው በተጓዳኝ ሕዝቦችን፣ አካባቢዎችን እንዲሁም ኢትዮጵያን ከሌሎች ሀገራት ጋር በማስተሳሰር አንድነት እንዲጠናከር ከፍተኛ ሚና ይጨወታሉ በሚል ነው::
መረጃዎች እንደሚያሳዩት በኢትዮጵያ ውስጥ የመንገድ ሽፋን ለማሳደግ በተሰሩ ስራዎች አመርቂ ውጠቶች ተመዝግበዋል:: የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴርን የ2014 በጀት ዓመት የ10 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ባዳመጠበት ወቅት የሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸውን እና የተጠሪ ተቋማትን የአፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ለ2014 በጀት ዓመት የተያዙ የፊስካል ስራዎች 1 ሺህ 265 ኪሎ ሜትር ነባር መንገዶችን ለማጠናከር፣ የነባር መንገዶች ደረጃን ለማሻሻል፣ የአዲስ መንገዶች ግንባታን ለማከናወን፣ የፍጥነት መንገድ ግንባታን ለማካሄድ ታቅዶ 935 ኪሎ ሜትር መፈጸም ተችሏል::
በሌላ በኩል በ326 ኪሎ ሜትር መንገዶች ላይ ከባድ ጥገና ለማከናወን ታቅዶ 155 ኪሎ ሜትር ማከናወን መቻሉን ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል:: የ659 ኪሎ ሜትር ወቅታዊ መንገዶች ጥገና ለማከናወን ታቅዶ 523 ኪሎ ሜትር 79 በመቶ መከናወኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ በዚህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ27 በመቶ ብልጫ መታየቱን ነው የተናገሩት:: በተጨማሪም የ 8255 ኪሎ ሜትር መደበኛ ጥገና ለመስራት ታቅዶ 7204 ኪሎ ሜትር ጥገና መካሄዱን፣ በአጠቃላይ በመንገድ ግንባታና ጥገና የተመዘገበው አማካይ አፈጻጸም 84 በመቶ መሆኑን አብራርተዋል::
በመንገድ ዘርፍ የተመዘገበው ውጤት የሕዝቦችን ትስስር በማጠናከር ሀገራዊ አንድነትን እውን ለማድረግ ፋይዳው የላቀ መሆኑን በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የዲዛይን አስተዳደር ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ፍሬው በቀለ ይናገራሉ:: መንገድ ጽንሰ ሃሳቡ ራሱ ሲነሳ ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ባሻገር ዋና ዓላማው ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ማገናኘት ነው:: ከኢኮኖሚያዊ ምክንያት ባሻገር ዋናው ዓላማ ተደራሽነትን ለመጨመር ነው ሲሉ ያመለክታሉ::
ተደራሽነት ሲባል ሰዎች ከመንገድ ያላቸው ርቀት በቅርብ ርቀት እንዲሆን እና በቀላሉ ወደፈለጉበት ቦታ መንቀሳቀስ እንዲችሉ ማድረግ ነው:: ይህም አንድ ቦታ የሚኖር ማሕበረሰብ ሌላ ቦታ በፈለገበት ሰዓት እንዲደርስ ያስችላል:: ሰዎች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚሄዱት ለኢኮኖሚያዊ ተግባራት ሊሆን ይችላል፤ ዘመድ ለመጠየቅም ሊሆን ይችላል:: መንገድ በተለያዩ ምክንያቶች ሰዎች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ያለ እንግልት እንዲንቀሳቀሱ ያስችላል:: በተሳለጠ መልኩ ወደፈለጉበት ቦታ ያለ እንግልት መድረስ መቻል ትስስሩ የተሳለጠ እንዲሆን ይጠቅማል::
ሰዎች ሳይገናኙ ሲቀሩ መግባባት ሊከብዳቸው ይችላል:: ሰዎች ሳይገናኙ ሲቀር እየተራራቀ ሊሄድ ይችላል:: ሰዎች እየተቀራረቡ ሲሄዱ ትስስሩ እየተጠናረ፣ እየተግባቡ እየተስማሙ ይሄዳል:: ይህ ደግሞ የሕዝቦች አንድነት እየተጠናከረ እንዲሄድ እደሚያስችል አቶ ፍሬው ጠቁመዋል
በተለይም የገጠር መንገድ/ ዩራፕ መንገድ/ ፕሮግራም ዋነኛው ዓላማ ቀበሌን ከቀበሌ፣ ወረዳን ከወረዳ ማገናኘት ነው:: ከዚያ በላይ ዞን፣ ከተማ እና ክልል ያሉትን ደግሞ የፌዴራል መንገዶች አስተዳደር እና የክልሎች የገጠር መንገድ የማገናኘት ስራ እንደሚሰሩ የሚጠቁሙት አቶ ፍሬው፤ ወረዳን ከወረዳ፣ ቀበሌን ከቀበሌ፣ ዞን ከዞን፣ ከተማ ከከተማ፣ ክልልን ከክልል ማገናኘት ማለት ቦታዎችን የማገናኘት ዓላማ ብቻ ሳይሆን ሰዎችን የማገናኘት ዓላማ ነው:: ሰዎች የፈለጉበት ቦታ በፈለጉበት ሰዓት እንዲደርሱ የማድረግ ዓላማ ስለሆነ አንድነትን ከማጠናከር ረገድ ያለው ፋይዳ አጠያያቂ አይደለም ሲሉ ያብራራሉ::
እንደ አቶ ፍሬው ማብራሪያ፤ ፕሮግራሞች ሲቀረጹም ይህንኑ ወደ መሬት ለማውረድ ታስቦ ነው:: በአንድ ቀበሌ፣ ወይም ወረዳ ያለው ሕዝብ ወደ ሌላ ቀበሌ ወይም ወረዳ፣ በአንድ ዞን ያለው ሕዝብ ወደ ሌላ ዞን ወይም ከተማ ወስዶ ምርቱን እንዲሸጥ ነው፤ ማግኘት የሚፈልገውን ሰው በቀላሉ እንዲያገኝ ለማድረግ ስለሆነ የመንገዶች የመጀመሪያው ጠቃሜታው ተደራሽነትን መጨመር ስለሆነ፤ ተደራሽነት ደግሞ አንድነትን ያጠናክራል:: የተራራቀ ሰው መቼም አንድ ሊሆን አይችልም::
መንገድ በኢትዮጵያ ውስጥ አንድን ሕዝብ ከሌላው ሕዝብ፣ አንድን ዞን ከሌላው ዞን፣ አንድን ከተማ ከሌላ ከተማ ከማገናኘት ባሻገር ቀጠናዊ ትስስርንም እውን በማድረግ ቀጣናዊ ውህደትንም እውን የማድረግ ዓላማም አለው::
ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ናት:: አብዛኞቹ ትልልቅ ግብዓቶች የሚገቡት በመንገድ ነው:: በዚህ ረገድ በርካታ መንገዶች ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል:: አሁንም በመገንባት ላይ ናቸው:: ቀደም ሲልም ከኢትዮጵያ ወደ ጅቡቲ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ እና ደቡብ ሱዳን የሚወስዱ መንገዶች ተገንብተዋል::
ድሬዳዋን ከጂቡቲ ወደብ ጋር የሚያስተሳስረው የድሬዳዋ ደወሌ የ220 ኪሎ ሜትር መንገድ ከዓመታት በፊት ተጠናቆ ወደ አገልግሎት የገባ ሲሆን፣ ይህን መንገድ ከአዲስ አበባ ጋር ለማስተሰሰር ከአዳማ፣ አዋሽ፣ መኢሶ፣ ድሬዳዋ፣ ደወሌ የሚደርስ የፈጣን መንገድ ግንባታ አካል የሆነው የአዳማ አዋሽ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክትም ከወራት በፊት ግንባታው ተጀምሯል::
ኢትዮጵያን ከሱዳን የሚያገናኘውና የፖርት ሱዳንን ወደብ ተጠቃሚ የሚያደርገው 604 ኪሎ ሜትር ጠጠር መንገድ ወደ አስፓልት ኮንክሪት ደረጃ አድጎ ለአገልግሎት የበቃ ሲሆን፤ ኢትዮጵያን ከበርበራ ወደብ ጋር የሚያገናኘው መንገድ ደግሞ 483 ኪሎ ሜትር መንገድ ካለው ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ጠቀሜታ አንጻር ወደ አስፓልት ኮንክሪት ደረጃ ተገንብቶ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል::
የሞምባሳ ወደብን መጠቀም የሚያስችለው የአዲስ አበባ ሞያሌ መንገድ ደግሞ ከሞጆ እስከ ሀዋሳ የትራፊክ ፍሰቱን መጨመር ተከትሎ የፈጣን መንገድ ግንባታ እየተከናወነለት ይገኛል:: ፕሮጀክቱ በአራት ምዕራፎች ተከፍሎ ነው ግንባታው እየተከናወነ የሚገኘው:: ከሞጆ መቂ፣ ከመቂ ባቱ፣ ከባቱ አርሲ ነገሌ እና ከአርሲ ነገሌ ሀዋሳ ተብሎ በ4 ኮንትራቶች ተከፍሎ ሲገነባ ቆይቷል:: ከሞጆ መቂ እንዲሁም ከመቂ እስከ ባቱ ያሉ የመንገድ ፕሮጀክቶች ተጠናቀዋል፤ ከባቱ እስከ አርሲ ነጌሌ እንዲሁም ከነጌሌ እስከ ሀዋሳ ያለው መንገድ ግንባታ ደግሞ እየተፋጠነ መሆኑን የመንገዶች አስተዳደር መረጃ ያመለክታል::
ኢትዮጵያን ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚያገናኘው የጋምቤላ ኢታሚን ጂካዎ መንገድም በአስፓልት ኮንክሪት ደረጃ ተገንብቶ አገልግሎት እየሰጠ ነው:: የዚሁ አካል የሆነው የሚዛን ዲማራድ 157 ኪሎ ሜትር አስፓልት ኮንክሪት መንገድ በግንባታ ላይ ይገኛል:: ተመሳሳይ መልኩ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ኢትዮጵያን ከኤርትራ ጋር የሚያገናኙ መንገዶች እድሳት እና ግንባታ በሰሜን ኢትዮጵያ ማካሄድ ጀምሮ ነበር::
አቶ ፍሬው እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያን ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚያገናኙ እነዚህ የመንገድ ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ ውስጥ የማይመረቱ ምርቶችን ከውጭ ሀገራት ለማስገባት እንዲሁም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን ወደ ጎረቤት ሀገራት ለመላክ እንዲሁም ከጎረቤት ሀገራት ጋር ትስስርን ለማጠናከር በጣም ጠቃሚ ነው::
ለእነዚህ የመንገድ ፕሮጀክቶች ከኢትዮጵያ መንግሥት ባሻገር የመንገድ ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ በሚያደርጉ እንደ አፍሪካ ልማት ባንክ ያሉ ሌሎች አካላት ጭምር ትልቅ ትኩረት ሰጥተው እውን እንዲሆኑ እንደሚሰሩ የጠቆሙት አቶ ፍሬው፣ እነዚህ አካላት ትኩረት የሚሰጡበት ምክንያት እነዚህ ፕሮጀክቶች ቀጣናውን የሚያስተሳስሩ በመሆናቸው ነው:: ምክንያቱም ንግድ መሳለጥ አለበት:: ወደብ አልባ ሀገራት ከውጭ የሚገቡ ነገሮችን ማግኘት ይኖርባቸዋል:: እነሱም ያላቸውን ምርት ወደ ውጭ ሀገራት መላክ መቻል አለባቸው::
በዚህ የንግድ ትስስር ውስጥም ሰው ከሰው ጋር ይገናኛል፤ ይግባባል፤ ይተዋወቃል፣ እነዚህ ቀጠናዊ ትስስርን የሚያሳልጡ መንገዶች የአንድ ሀገር ሕዝቦች ትስስር እና አብሮነትን ከማሳለጥ ባሻገር ሀገራት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላቸውን ትስስር ያጠናክራሉ:: ትውውቅን ይጨምራሉ፤ የንግድ ግንኙነትን ያሰፋሉ:: ስለዚህ ጠቃሜታቸው ላቅ ያለ ነው::
እንደ አቶ ፍሬው ገለጻ፤ ቀጠናውን ማስተሳሰርን እንደ አንድ መርህ ወስዶ የፌዴራል መንገዶች አስተዳደር ቀጠናዊ ትስስርን እውን በሚያደርጉ መንገዶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው:: በዚህ ረገድም በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል:: እንዲህ አይነት ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ ናቸው::
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኢትዮጵያ በዴቻ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ከጥንት ጀምሮ የተገነቡ መሰረተ ልማቶች የኢትዮጵያውያንን አንድነት የሚገልጹ ናቸው:: በጥንት አያቶች የተገነቡት አክሱም ላሊበላ የመሳሰሉ ቅርሶች ኢትዮጵያውያን አያቶቻችን በአንድነት ገንብተው ያቆዩት ታሪክ ማሳያ ናቸው::
በተመሳሳይ በአሁኑ ጊዜ እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶችም የኢትዮጵያውያንን ትስስር እና አንድነት የሚያጠናክሩ ናቸው:: ለምሳሌ፤ የሁሉንም ኢትዮጵያውያን አንድነት ማሳያ የሆኑ ፕሮጀክቶች የአንድነት መገለጫ ተደርገው ይወሰዳሉ:: በፓርኮች ውስጥ የተገነቡ ቅርሶች የአንድነት ማሳያ የሚሆኑ ናቸው:: የእኢትዮጵያ ሕዝቦች እሴቶች የሚታዩባቸው ናቸው::
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሕዝቦችን አንድነት በሚያጠናክሩ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ከመስራቱ ባሻገር፣ የሀገሪቱ ከተሞች በእኩል ደረጃ እንዲያድጉ እየተሰራ ነው:: አዲስ አበባ ሲያድግ በአካባቢው ያሉ ከተሞች ጭምር እንዲያድጉ፣፤ ሀዋሳ ሲያድግም እንዲሁ በትኩረት እየተሰራ ነው::
በሀገሪቱ ውስጥ እየተገነቡ ያሉ የመንገድ ፕሮጀክቶችም ዞኖችን ከዞኖች፣ ክልሎችን ከክልሎች እንዲሁም ሀገራት ጋር ማገናኘትን ያለሙ እንደመሆናቸው ለአንድነት እርሾ የሚሆኑ ናቸው:: እያንዳንዱ መንገድ ሕዝቦችን ያስተሳስራል:: አንድን ሕዝብ ከሌላ፤ ሕዝብ፣ አንድን ብሄር ከሌላ ብሄር የሚያገናኙ ናቸው::
መላኩ ኤሮሴ
ጳጉሜን 5 ቀን 2014 ዓም