የኢትዮጵያን የፋሽን ኢንደስትሪ ለማሳደግ የተለያዩ የፋሽን ትርኢቶች የሚጫወቱት ሚና ትልቅ ነው። የፋሽን ትርኢቶች በዘርፉ የተሰማሩ የተለያዩ ባለሙያዎች ስራዎቻቸውን ለሕዝብ የሚያስተዋውቁባቸው መድረኮች ናቸው። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ የመድረኮቹ በስፋት አለመኖር በኢንደስትሪው አዝጋሚ እድገት ላይ የራሱን ተፅዕኖ እንዳሳረፈ የዘርፉ ባለሙያዎች ይስማማሉ።
በዚህ ረገድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የተለያዩ የፋሽን ትርኢት መድረኮችን በማመቻቸት ያሳየው አበረታች ጅምር ተጠናክሮ መቀጠል ከቻለ ትልቅ ተስፋ እንዳለው እያሳየ ነው።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የ2014 ዓ.ም ተመራቂ ተማሪዎች ከሰባት በላይ በሆኑ የፈጠራ ዲዛይኖች የተሰሩ አልባሳትና በልዩ ልዩ ማስጌጫዎች የተዘጋጀ እና በአገራችን የመጀመሪያ የሆነ የተማሪዎች የጎዳና ላይ ፋሽን ትርኢት በባሕር ዳር ከተማ አቅርበዋል:፡ ባለፈው ነሐሴ 21/2014 ዓም የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ 60ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓል እና የ2014ዓ.ም የምረቃ ቀንን በማስመልከት የጎዳና ላይ የፋሽን ትርኢቱ ሲካሄድ በዩኒቨርሲቲው ታሪክ የመጀመሪያ መሆኑ ታውቀል።
አዘጋጆቹ የትርዒቱን ስያሜ አዲስ ገፅ ያሉት ሲሆን የባሕርዳር ከተማ እና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ እንዲሁም በእለቱ በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የሚመረቁ ተማሪዎች እስከ ቤተሰቦቻቸው ተገኝተው መመልከት ችለዋል።
ዝግጅቱን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ብርሃን ሀይሉ፣ ተቋሙ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን ትርኢት ማዘጋጀቱ ለከተማውም ሆነ በዘርፉ ላሉ አካላት ትልቅ ምዕራፍ መክፈቱን ተናግረዋል። ኩነቱም በፋሽን ቴክኖሎጂ ላይ ያተኮረ በመሆኑ የአገራችንን ቴክስታይልና አልባሳት ኢንዱስትሪን በማሳደግ ረገድና የስራ ዕድል በመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው መናገራቸውን ከዩኒቨርሲቲው የማህበራዊ ገፅ ትስስር የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምራት ተስፋዬ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በ24 ፕሮግራሞች የፒኤች ዲ፣ የሁለተኛ ዲግሪ እና በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ በማስተማር የባሕር ዳር ከተማን የፋሽን ከተማ ለማድረግ አልሞ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ዶ/ር ታምራት አክለውም፣ ትርኢቱን ያቀረቡት የዩኒቨርሲቲው ተመራቂ ተማሪዎች በሀገሪቱ ውስጥ ተሰማርተው የፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪን ለማዘመን የሚሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል። በዚህም ኢንስቲትዩቱ ከሚያስመርቃቸው 26% የራሳቸውን ስራ ፈጥረው የሚሰሩ ሲሆን ከ85% በላይ የሚሆኑት ደግሞ በተመረቁበት ሙያ የስራ ዕድል ማግኘታቸው እንደ ሀገር የመጀመሪያው ኢንስቲትዩት እንደሚያደርገው ጠቁመዋል።
የዕለቱን ፕሮግራም ያስተባበሩት የፋሽን ዲዛይን ትምህርት ክፍል ኃላፊ መምህር ሰላማዊት መላኩ፣ ተመራቂ ተማሪዎች ሀገር በቀል የሆኑ እና የውጪውን አልባሳት በማቀናጀት ያላቸውን የፈጠራ ስራ በማሳየታቸው ተቋሙንም ሆነ ዩኒቨርሲቲውን ለማህበረሰቡ በማስተዋወቅ ረገድ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
በፋሽን ትርኢት ስነ-ስርዓቱ ላይ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቦርድ አባላት እና የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና ሰራተኞች እንዲሁም የከተማው ማህበረሰብ ታድመውበታል። የፋሽን ትርኢቱም ከስካይ ላይት ሆቴል እስከ ዩኒሰን ሆቴል ባለው የጎዳና መንገድ ላይ የተካሄደ ነበር።
ዩኒቨርሲቲው በቅርቡም ለ10ኛ ጊዜ በጥጥ፣ ጨርቃጨርቅ እና አልባሳት የእሴት ሰንሰለት በአፍሪካ በሚል ርዕስ ጉዳይ ዓለም አቀፍ አውደ ጥናት በቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ትምህርት ክፍሉ አዘጋጅነት ባቀረበበት ወቅት ደማቅ የፋሽን ትርዒት ማዘጋጀቱ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አገራዊ የኢንደስትሪ ልማት ግባችን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት እያሳየ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ሲሆን፣ ይህን ለማሳደግም የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በቴክስታይል ኬሚካል ፕሮሰስ ምህንድስና ፤ በቴክስታይል ምህንድስና፣ በፋሽን ዲዛይን፤ በጋርመንት ምህንድስና ፤ በቴክስታይል እና አፓራል መርቻን ዳይዚንግ እና በሌዘር ምህንድስና የትምህርት መስኮች ላይ ኢንዱስትሪ መር ስርዓተ-ትምህርት በመቅረፅ በተግባር የታገዘ ትምህርት በማስተማር በዘርፉ በርካታ ባለሙያዎችን በመጀመሪያ ዲግሪ፤ በሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲግሪ የትምህርት ደረጃ እያስተማረ ይገኛል። በመሆኑም አሁን ላይ ኢንስቲትዩታችን በቴክስታይል ዘርፍ ያሉ የምርምርና ማስተማሪያ ቤተ-ሙከራዎች አደረጃጀትን እያዘመነ ይገኛል።
በISO/IEC 17025:2017 አለማቀፋዊ ይዘት ይዘው ተማሪዎች እና ተመራማሪዎች የምርምር ስራቸውን እንዲያከናውኑባቸው ከማድረግ አንፃር ኢንስቲትዩቱ በቴክስታይል ፊዚካል (Textile physical testing laboratory) እና የቴክስታይል ኬሚካል (Textile chemical testing laboratory) የፍተሻ ቤተ-ሙከራዎች ላይ የጥራት ደረጃ በኢትዮጵያ ብሔራዊ አክሬዲቴሽን ጽ/ቤት እውቅና እንዲያገኙ ለማድረግ በርካታ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል። በዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ አክሬዲቴሽን ጽ/ቤት ባደረገው የመጀመሪያ ደረጃ ምዘና የቴክስታይል ፊዚካል እና ኬሚካል የፍተሻ ቤተ-ሙከራዎች (Textile physical and chemical testing laboratory) የሚጠበቅባቸውን የጥራት ደረጃ መመዘኛዎች አሟልተው የመጀመሪያ ዙር ሂደት አልፈዋል። ከዚህ ምዘና በኋላም እነዚህ ላብራቶሪዎች በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለውን ISO/IEC 17025:2017 የላብራቶሪ አደረጃጀት አሟልተው እውቅና የሚያገኙ ይሆናል። ኢንስቲትዩቱ በቀጣይ በሌሎች ቤተሙከራዎች ላይም በተመሳሳይ አለማቀፋዊ እውቅና እንዲኖራቸው የማድረጉን ስራ በስፋት እንደሚሰራም ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 30 ቀን 2014 ዓ.ም