ያኔ ዓለም በሁለት ጎራ ተከፍሎ አንዱ ባንዱ ላይ በጠላትነት አሲሯል። ዓለም ከየ አቅጣጫው ጭንቅ ብሏት በጦርነት ነበልባል ስትነድ፤በሰውል ልጆች ስቃይ ስትናጥ ከርማለች። አንዱ ዓለም ሌላኛውን ዓለም በጠላትነት ፈረጇል።ጦር ተማዟል፤ ሻሞላ ተማዞ ተሞሻልቋ። ቃታ ስቦ ክቡር የሆነው የሰው ልጅን ህይወት አንደ ዘበት ቀጥፋል።
በሁለት አገራት ግጭት የተጀመረው ጦርነት በብዙ ዓለም ክፍል ሰቆቃና ዋይታ ፈጥሮ አልፋል። በዓለም ታሪክ ከተከሰቱ አስከፊ ገፅታዎች መሀል ዋንኛው ሆኖ ተመዝግቧል። በሰው ልጆች ታሪክ ሲታወስ “ባይደገም” ሲነሳ “ባይመለስ” የሚያስብል እልቂት ተፈፅሟል። በዓለም ታሪክ ጥቁር ነጥብ ጥሎ አልፏል። ከ70 ሚሊዮን በላይ ህዝብ አልቋል። ያ ክስተት ከአለም ታሪክ ገፅ ላይ ተገልፆ ሲነበብ እንዲህ ይነበባል።
በዓለም ካስተናገደቻቸው ጦርነቶች ሁሉ በታሪክ የጨፈገገ ገፅታን ፈጥሮ ያለፈው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት፤ መነሻና ማብቂያው በዚሁ ጭጋጋማ ወቅት ነሀሴ በሳምንት ነበር። ጦርነቱ ለአምስት ተከታታይ አመታት ማለትም ከነሀሴ 26 1926 እስከ ነሀሴ 27 1927 ዓ.ም ድረስ ዘልቋል።
ዓለም ያኔ ይህን ሁነት አስተናግዳለች። ምድር ያኔ ይህንን ጥቁር ወቅት አልፋለች።ይህ ጦርነት የዓለምን ገፅታ የቀየረ፤ ቀድሞ የነበረውንም ሁኔታ በብዙ መልኩ ያፋለሰ ሆኖ አልፋል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ዛሬ ድረስ ያለውን የዓለም የፖለቲካዊ ሁኔታና የሀይል አሰላለፍ ቀይሮ አሸናፊዎቹን ከፊት አሰልፎ ይገኛል።
የጦርነቱ ጅማሮ
አንደኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቂያ ላይ የተፈጠረው ማህበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ሁሉ ለሁለተኛ የዓለም ጦርነት መቀስቀስ እርሾዎች ነበሩ። ኋላ ላይ እየሰፋ ሄዶ በርካታ አገራት የተሳተፉበት ጦርነት መነሻው እንዲህ ነበር። በወቅቱ ጀርመን በአንደኛው የአለም ጦርነት ዳፋ ግዛትዋ በፖላንድ ለሁለት ተከፍሎባት ነበር። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ፖላንድ በለስ ቀንቷት፤ጀርመንን ለሁለት ከፍላ የባህር በር ባለቤት ሆነች።ይህ ደግሞ ጀርመንን አስከፍቶ አለፈ።እዚህ ጋር አንድ ትልቅ ምክንያትም ተወለደ።
በተጨማሪም ጀርመን በብዙዎች የአንደኛው የአለም ጦርነት ጠንሳሽና ደጋሽ ነኝ በሚል ውግዘት በረከተባት። ለጦርነቱ መቀስቀስ ምክንያትና ተጠያቂው አንቺ ነሽ፤ ተብላ በጦርነቱ ለተጎዱ አገራት ካሳ ክፈይ የሚል ጥያቄዎች ቀርቦላትም ነበር።ባጎራበቾችዋ ፈረንሳይና እንግሊዝም በበጎ አለመታየትዋ አስኮረፋት።
የሌላው አለም የእርስ በርስ ሽኩቻም ለጀርመን ድጋፍ በመስጠትና በመቃወም ተስፋፋ። መሰል ጫናዎች የበዙባት ጀርመን እነዚህ ሁናቴዎች አላስደሰትዋትም፤ መገለልና መፈረጅዋ አስከፋት።ለሁለት መከፈልዋ ምክንያት የሆነችው ጎረቤትዋ ፖላንድ በኋላም እስዋን የሚፃረሩ ሀይላት ላይ ጥርስዋን መንከስ ጀመረች።
ወዲያ ተሻግሮ ደግሞ አሜሪካ በሴኔትዋ በአንደኛው የዓለም ጦርንት መጠናቀቂያ ላይ የተመሰረተው ሊግ ኦፍ ኔሽን የሚያወጣቸው ህጎች ተግባራዊ እንዳይሆን ውድቅ ተደረገ። በእርግጥ በወቅቱ የነበሩት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የሊግ ኦፍ ኔሽን የተባለው ዓለማቀፉ ተቋማ ይጠነክር ዘንድ ፍላጎት ነበራቸው። ያወጣቸው ህጎች ደጋፊ ነበሩ። ለህጎቹ ተግባራዊ መሆን ስልጣኑ የሴኔቱ በመሆኑ ተቋሙ ተቀባይነት አጣ። አዲስ የተቋቋመው ሊግ በወቅቱ ጠንካራ በነበሩት እንደ አሜሪካ ባሉ ሌሎች አገራትም ላይ እምብዛም ተቀባይነት ማግኘትም አልቻለም ነበር።
ይህ ዓለማቀፍ ተቋሙ እዳይጠነክር አደረገው። በዚህም በአገራት መሀከል የሚፈጠረውን ውጥረት በቀላሉ እንዳይፈታና ውጥረት እንዲባባስ አደረገ። ሌላው ቀርቶ ተቋሙን የመሰረቱትና የአንደኛው የአለም ጦርነት አሸንፈው የነበሩት መስራቹ አገራት እርስ በርሳቸው መግባባት እንዳቃታቸው ማሳያም ነበር። በዚህም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የጦርነትና የግጭት ንፋስ ሽው ማለት ጀመረ።
በወቅቱ ከድርጅቱ ተገልላ የነበረቸው ሩሲያም የተወሰነ ክፍልዋ ወደ አውሮፓ ሸሽቶባት ቅሬታ ውስጥ ወድቃ ነበር። በአውሮፓም ሌላ ታሪክ የሚቀይር ሁለት ክስተቶች ተፈጠሩ። የሁለተኛው የአለም ጦርነት ጠንሳሾች በይፋ ወደ ሰልጣን በሁለቱ አገራት ጣሊያንና ጀርመን ላይ ብቅ አሉ። የጀርመኑ ናዚ ፓርቲና የጣሊያኑ ፋሽት።
በጣሊያን የፋሽስቶች ወደ ስልጣን መምጣትና በጀርመን የናዚ ፓርቲ አሸንፎ ወደ ስልጣን መምጣት ጉዳዩን አከረረው። በተለይ በጀርመን የተመረጠው የናዚ መንግስት በሂትለር መሪነት አክራሪ ብሄርተኝነትን ሆን ብሎ ማበረታታትና ማግነን ቀጠለ።በጣሊያን በኩልም አንባገነንነቱ ተስፋፋ።
ጣሊያንና ጀርመን ጋር ይህንን አጋጣሚውን ተጠቅመው መወዳጀት ጀመሩ። በተለይም በጀርመን የሂትለር ወደ ስልጣን መምጣት በኋላ ጀርመንን አንድ ለማድረግ በሚል ሰበብ ጠንካራ ሰራዊት ማደራጀት ቀጠለ። ሂትለር ሌሎችን መተንኮስና እራሱን በወታደራዊ መስክ ከተፃራሪ ወገኖች የተሻለ ማድረጉን ተያያዘው።
በሌላ በኩል ጣሊያን የቅኝ ግዛት ይዞታዋን የማስፋት ሙከራ ማድረግ ጀመረች። በተለይም በወቅቱ የሊግ ኦፍ ኔሽን አባል የነበረችውን ኢትዮጵያን መውረርዋ የሚታወስ ነው።የጣሊያኑ ፋሺስት ቡድን የአምባገነንነቱ ማሳያ የሆኑ ተግባራት በወቅቱ መፈፀሙ የታሪክ መዛግብት ያወሳሉ። በዚህም በኢትዮጵያዊያን ዘንድ በርካታ ተቃውሞዋችና ግጭቶች ተስተናግደዋል።
እዚያው አውሮፓ ያሉት አገራት እንደ ፈረንሳይ እና እንግሊዝ ያሉት ደግሞ የጀርመንና የጣሊያን ጥምረትና ተግባር አልጣማቸውም ነበርና አገራቱን በአይነቁራኛ እየተመለከቱ ውስጥ ለውስጥ የራሳቸውን ዝግጅት ማድረግ ተያያዙት። በጀርመን ትንኮሳ የሚፈፀምባት ፓላንድ በእነዚህ አገራት አይዞኝ እኛ አለንልሽ ተባለች።
ወደ እሩቅ ምስራቅ ስናማትር ደግሞ ጃፓን የቻይና የእርስ በርስ ግጭት ላይ የራስዋን ተፅዕኖ መፍጠር እንዲያስችላት በማሳብ እጅዋን በግጭቱ ላይ አስገባች።በአንፃሩ ደግሞ ከጀርመን ጋር የነበራትን ግንኙነትም አጠነከረች። በዚህም ቻይና ቅራኔ ውስጥ ገባች። ቀስ በቀስ ይባስ ብሎ ጃፓን ከቻይና ጋር በቀጥታ ግጭት ውስጥ ገባች።
በኋላ ላይ ጀርመን አካባቢዋ ያሉ አገራትን መተንኮስ ስትጀምር ለአሜሪካ ታቀርብ የነበረው የኢንዱስትሪ ጥሬ እቃ ማስተላለፊያውን በተፃራሪዎችዋ ተዘጉባት። እስዋም ይህን ተግባር ዝም ብላ አልተመለከተችም። በዚህ ሰበብ ቀድማ ከወረረቻት ፖላንድ በተጨማሪ ዴንማርክና ኖርዌይን ወረረች። ፍትጊያው እየበረታ መጣ።
የጀርመኑ ናዚና የጣሊያኑ ፋሽስት መንግስታት የሚያደርጉት እንቅስቃሴዎች ሁሉ የዓለም ሰላም ስጋት ላይ እንዲወድቅ አደረገው።ሌሎች የእነሱ ተፃራሪዎች ደግሞ ያገባኛል በሚል ከእነዚህ ተቃርኖ መቆም ጀመሩ።ከሁለቱም ወገኖች በደጋፊና በተቃራኒ የቆሙ መንግስታት ከየአቅጣጫው ብቅ እያሉ ህብረት መፍጠር ጀመሩ።
በአሜሪካም ጅማሮው ላይ እጅግ ዳብሮ የነበረው ኢኮኖሚዋ መቀዛቀዙ ከሌሎች እርስዋን ከማይወግኑ አገራት ጋር ቅሬታ ውስት ገባች። ከተለያዩ ወዳጅ አገሮችዋ ጋር ያላትን ዘርፈ ብዙ ትስስር ማጠናከር ትፈልግ ነበርና ያወጣኛል ካለቸው ጋር ተሰለፈች።
ጀርመን በበኩልዋ ከሀንጋሪ ጋር አብራ ስሎቫኪያን ወረረች። ፈንሳይና እንግሊዚ ደግሞ የጀርመንን አካሄድ በክፋት አዩት። ጀርመን ፖላንድን ከወረረች እንደሚደግፍዋት ቃል ገቡ። ይሄኔ ከጀርመን ጋር ተፋጠጡ። ጀርመን ፖላንድን ማጥቃት ስትጀምር ፈረንሳይና እንግሊዝ ጀርመን ላይ ጦርነትን አወጁ። ይሄኔ የሁለቱ ቡድኖች ወደ ጦርነት አውድማው ገቡ።ጀርመን ፖላንድን ስትወር የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጅማሮ ሆነ።
በጦርነቱ ተሳታፊ የነበሩት አገራት በሁለት ቡድን ተከፍለው ጦር ተማዘዙ። አገራት አላይድ ሀገራትና የአክሲስ ኃያላት በሚሰኙ ሁለት ጎራዎች ተከፍለው ነበረ። አላይድ ሀገራት ቡድን ውስጥ፡- የሶቪዬት ሕብረት፣ አሜሪካ፣ ብ ሪ ታ ን ያ ፣ ቻ ይ ና ፣ ፈ ረ ን ሳ ይ ፣ ፖ ላን ድ ፣ ካ ና ዳ ፣ አውስትራሊያ፣ ኒው ዚላንድ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዩጎዝላቪያ፣ ቤልጅግ፣ ኔዘርላንድስ፣ ግሪክ፣ ኖርዌይ በቀጥታ የተሳተፉ አገራት ሲሆኑ እነዚህ አገራት በጥምርና በተናጠል በአንድነት አብረው ጠላት ያዋቸውን አጥቅተዋል።
በሌላኛው ጎራ ተሰልፈው የነበሩት የአክሲስ ኃያላት ያቋቋሙት ደግሞ ጀርመን፣ ጃፓን፣ጣሊያን፣ሮማንያ፣ ሀንጋሪ፣ ቡልጋሪያ፣ በዋናነት በአጋዥነ የተሳተፉት ደግሞ ፊንላንድ፣ ኢራቅ፣ታይላንድ፣ ፈረንሣይና ሌሎችም ነበሩ። እነዚህ አገራት ያለ ሀይላቸውን ሁሉ በመጠቀም ከተፃራሪ ጎን የተሰለፉትን አገራት ለመርታት በጦር ሜዳ ተፋልመው የሰው ልጆች ትልቁ እልቂት አስከትሏል።
የዓለም ሁለንተናዊ ለውጥ መሰረት የሆነው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ነሀሴ 27 1927 ዓ.ም ጀርመን ሆላንድን መውረርዋ ተከትሎ ተጀመረ። ጀርመን ወረራዋን አስፍታ ኖርዌይን እንደ ኤሮፓውያን አቆጣጠር ሚያዝያ 9 ቀን 1941 ወረረች። በኖርዌይ ውስጥ ያለው ጦርነት ኖርዌይ ከመያዟ በፊት ለጥቂት ሳምንታት ብቻ ቆየ። ንጉሱ እና የመንግስት ኣካላቱ ወደ እንግሊዝ አገር ሸሹ። ኖርዌይዊያን በወቅቱ ከጀርመኖች ነፃ ለማውጣት ብዙ ትግል አደረጉ።
በጦርነቱ ላይ ከተከሰቱ አበይት ክስተቶች መካከል በጃፓን ከተሞች ሂሽማና ናጋሳኪ ላይ በአሜሪካ አውሮፓላኖች የዘነቡ ጅምላ ጨራሽ የአውቶሚክ ቦንቦችና በሁለቱ ከተሞች የረገፈው የሰው ልጅ በአለም ታሪክ በጥቁር መዝገብ ሰፍሮ ይገኛል።
በእነዚያ ሁለት ከተሞች ላይ በ11 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ህይወት ያለው ሁሉ በድን ያደረገ የክፍለ ዘመኑ ታለቅ ውድመት ሆኖ ተመዝግቧል። በዚህም መግለፅ የማይቻል ሰቅጣጭ የፍጥረታት እልቂት ተከሰተ። ቦንቡን ጭኖ እዚያ ምድር ላይ የጣለው አውሮፕላን ቢ29 ይሰኝ ነበር።
ከዚህ ጋር በተያያዘም የጦርነቱ መደምደሚያ በነበረችው የጀርመን ርዕሰ ከተማ በርሊን የወደመችበትና የከተማዋ ነዋሪ ለሞት ለስደትና ለመከራ የዳረገው አጋጣሚ የማይረሱና ትልልቅ ሁነቶች ነበሩ። በየ አቅጣጫው የሰዎች እልቂት ወሬ ይሰማ ጀመር። በየሁለቱም ወገን አንዱ አንደኛውን ድል እያደረገ መሆኑ በዜና ማሰራጫዎች ይዘገባል።
በዚህ አስከፊ ጦርነት በጠቅላላው በአለም ዙሪያ 70 ሚልዮን ሕዝብ በጦርነቱ ረገፈ። ከጦርነቱም በኋላ አሜሪካ ና የሶቭየት ኅብረት የዓለም ዋና ኃያላት ሆኑ። በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት ዋናው ተዋናይ የጀርመኑ ናዚ መሪ ሂትለር ነበር።
ይህ አውዳሚው 2ኛው ዓለማዊ ጦርነት ከ1932 ዓ.ም. እስከ 1937 ዓ.ም የቀጠለ ሲሆን በሁለቱ ጎራዎች መካከል በተደረገው ጦርነት የዓለም ማህበራዊ ፓለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ምክንያት ሆነ።
በመጨረሻም፡ ጀርመኖች በብዙ ግንባሮች ጦርነቱን እየተሸነፉ በመሄድ እ.ኤ.አ በ1945 ዓ.ም በጦርነቱ ተሸንፈው እጅ ሰጡ። የዚህ አስከፊ ጦርነት መጨረሻ የአክሲስ ሃያላት ማለትም ጀርመን፣ ጣልያንና ጃፓን ተሸነፉ። ይህ ጽሁፍ ስናዘጋጅ በዋቢነት የተለያዩ ድህረ ገፆችና የደራሲ ጥላሁን ጣሰው “የኢትዮጵያና የጣልያን ሁለተኛው ጦርነት ታሪክ” በሚል ርእስ የተዘጋጀው መፅሀፍ ተጠቅማናል።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 29/2014