አንድ ዋና ማሳለጫ መንገድ ብቻ ያላቸው ከተሞች ለትራፊክ መጨናነቅ የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው። በዚህም ምክንያት በነዚህ ከተሞች የትራፊክ አደጋዎች በተደጋጋሚ የመከሰት እድሉ ይጨምራል። በሀገራችን ውስጥ እንድ ዋና ማሳለጫ መንገድ ካላቸው ከተሞች እንዱ ጂግጂጋ ከተማ ነው። ከተማዋ አንድ ብቻ ማሳለጫ መንገድ ባለቤት ከመሆኗ ባሻገር ከተማውን አቋርጠው ወደ አዲስ አበባ እና ደገሃቡር የሚመላለሱ በርካታ ከባድ ተሸከርካሪዎች የሚመላለሱበት እንደመሆኗ የትራፊክ ከተማዋ ለትራፊክ መጨናነቅ ተጋላጭ እንድትሆን አድርጓታል። በዚህም ምክንያት የከተማዋ ነዋሪዎች ላይ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጫናዎች ለማስተናገድ ተገደው ኖረዋል። አሽከርካሪዎችም ለአላስፈላጊ ወጪ ሲዳረጉ ቆይተዋል።
ይህን ችግር ለመቅረፍ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከተማዋን አቋርጠው የሚያልፉ ተሸከርካሪዎች ከተማዋን አቋርጠው ማለፍ ሳይጠበቅባቸው በከተማ ጎን አልፈው እንዲሄዱ የሚያስችል (ባይፓስ) መንገድ እያስገነበ ይገኛል። የመንገዱ ግንባታ ግንቦት 2013 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን ህዳር 2015 ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ ነው ወደ ስራ የተገበው። ሰባት (7) ኪ.ሜ የሚረዝመው ይህ የባይፓስ የመንገድ ፕሮጀክት 30 ሜትር የጎን ስፋት አለው። የመንገዱ ግንባታ የፌዴራል መንግስት በመደበው 672 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተከናወነ ይገኛል።
የመንገድ ግንባታው በትላልቅ ከተሞች የመንገድ ደረጃ በኮንክሪት አስፋልት እየተገነባ የሚገኝ ሲሆን፤ የእግረኛ እና የብስክሌት መተላለፊያ እንዲሁም የአረንጓዴ ሥፍራ በፕሮጅክቱ የተካተቱበት መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የጂግጂጋ ፕሮጀክት ግንባታ ማስተባበሪያ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር በላይ ተናግረዋል።
የመንገዱን ግንባታ እያከናወነ የሚገኘው ይርጋለም ኮንስትራክሽን ነው። የማማከሩን ስራ እያከናወነ የሚገኘው ደግሞ ኤልዳ ኢንጅነሪንግ ኮንሰልታንትሲ ሲሆን የድጋፍና ክትትል ሥራውንም እያከናወነ እንደሚገኝም ነው የጠቆሙት።
የዚህ መንገድ ጠቃሜታው ከፍ ያለ ነው የሚሉት ኢንጂነር በላይ፤ ከቀብርዳር የሚመጡ ተሸከርካሪዎች ወደ አዲስ አበባ ሲያልፉ እና ከአዲስ አበባ ወደ ቀብርዳር የሚያልፉ መኪናዎችም ከዚህ ቀደም ጂግጂጋ ከተማን መሃል አቋርጦ የሚያልፈውን መንገድ ተጠቅመው ነበር የሚያልፉት። የጂግጂጋን ከተማ መሃል ለመሃል አቋርጠው በሚያልፉበት ወቅት የከተማውን ነዋሪ እንቅስቃሴ ላይ ጫና ሲያሳድር ነበር።
ከቀብርዳሃር ወደ አዲስ አበባ የሚያልፉት አብዛኞቹ መኪኖች የከባድ ጭነት መኪኖች እንደመሆናቸው የጂግጂጋ ከተማ የተሸከርካሪ እንቅስቃሴን በጣም ሲያስተጓጉል ነበር። ተሸከርካሪዎች ለረጅም ደቂቃዎች ለመቆም ይገደዱ ነበር። ይህ የከተማውን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን ሲገድብ ነበር። ገበያ ደርሶ መመለስ ወይም ዘመድ ጥየቃ ወጥቶ ሰው በፍጥነት መመለስ አለመቻል ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ላይ የራሱን ጫና ሲያሳርፍ ነበር። ይህ መንገድ እየተገነበ ያለው ይህን ችግር ታሳቢ በማድረግ ነው ይላሉ።
ተሸከርካሪዎቹ ጂግጂጋ ከተማ ሳይገቡ በጎን እንዲያልፉ ለማድረግ ታስቦ የሚገነባ መንገድ ነው።ስለዚህ ተሸከርካሪዎች ከቀብርዳር ይመጡና ከተማ ሳይገቡ ማለፍ ይችላሉ ማለት ነው። ከአዲስ አበባ ወደ ቀብርደሃር የሚያልፉ ተሸከርካሪዎችምጂግጂጋ ሳይገቡ በጎን ማለፍ ይችላሉ። የፕሮጀክቱ ዋነኛው ፋይዳው የትራፊክ ፍሰቱን ለማሳለጥ ነው።
የመንገዱ ኢኮኖሚያዊ ጠቃሜታም ለከተማው ነዋሪዎች ብቻም ሳይሆን ለጭነት መኪናዎች አሽከርካሪዎች ጭምር ነው የሚሉት ኢንጂነር በላይ፤ ምክንያቱም መኪናዎች ጂግጂጋ ከተማ ገብተው ወደ አዲስ አበባ ወይም ወደ ቀብርደሃር ሲያልፉ የሚያጋጥመውን መጨናነቅ እና መጓተት ስለሚቀርፍ ለአሽከርካሪዎቹ ኢኮኖሚያዊ ጠቃሜታ ያስገኛል። ተሸከርካሪዎቹን ሹፌሮች ያለ መንገላታት እንዲያልፉ የሚያስችል ነው።
የጅግጅጋ ባይባስ ግንባታ ሲጠናቀቅ የንግድ እንቅስቃሴዎችን በማሳለጥ፤ ለከተማዋ ዕድገት ምቹ ዕድል ይፈጥራል የሚሉት ኢንጂነር በላይ ከዚህ ቀደም መሃል ከተማ ተብለው ከሚታወቁ አካባቢዎች በተጨማሪ አዲስ መንገድ የሚገነባበት አካባቢ ላይ ከተማው እንዲስፋፋ ስለሚያደርግ ከተማው የበለጠ እንዲሰፋ ያደርጋል ብለዋል።
በክልሉ ለሚደረጉ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችም የጎላ ሚና አለው። አማራጭ መንገዶች መኖራቸው በአካባቢው መዋዕለ ንዋይ ሊያፈሱ የሚፈልጉ ባለሃብቶች ፍላጎት እንዲጨምር እንደሚያደርግም ኢንጂነር በላይ ጠቁመዋል። ይህም ለአካባቢው ተጨማሪ እድል ይዞ እንደሚመጣ ነው ያብራሩት።
ኢንጂነር በላይ እንደሚሉት፤ የፕሮጀክቱ ፋይዳ ከፍ ያለ ቢሆንም፤ የፕሮጀክቱ ግንባታ ግን በተያዘለት እቅድ መሰረት እየሄደ አይደለም። በእቅዱ መሰረት የፕሮጀክቱ መጠናቀቂያ ጊዜ ተቃርቧል። ቀጣይ ህዳር ወር መጠናቀቅ ይጠበቅበታል። መሬት ላይ ያለው ሁኔታ ሲታይ ግን ብዙ ይቀራል። በቀጣይ ጥቂት ወራት ውስጥ ማጠናቀቅ የሚቻል አይመስልም። በእስካሁኑ የግንባታ ሂደት የአፈር ቆረጣና ሙሌት፣ የሰብቤዝ፣ የውኃ መፋሰሻ ቱቦ ቀበራና የ94 ሜትር ድልድይ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ከሶስት ወር በኋላ እንዲጠናቀቅ የሚጠበቅ ቢሆንም ፕሮጀክቱ ግን ገና 25 በመቶ ላይ ነው ያለው። ግንባታው ከአንድ ዓመት በላይ የተካሄደ ቢሆንም 75 በመቶ ይይቀረዋል። በቀጣይ 3 ወራት ውስጥ 75 በመቶ ግንባታ ማጠናቀቅ ይከብዳል ይላሉ። ስለዚህ ፕሮጀክቱ መራዘሙ የማይቀር መሆኑን ያብራራሉ
ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ እንዳይሄድ ያደረጉ ዋና ዋና ምክንያች አሉ የሚሉት ኢንጂነር በላይ፤ የግብዓት አቅርቦት ችግር በተለይም የሲሚንቶ እጥረት፣ የብረት እና የአስፋልት ቁሶች እጥረት ለፕሮጀክቱ መጓተት የበኩሉን አበርክቷል ይላሉ። በተለይም የመንገድ ግንባታው ዋነኛ ግብዓት የሆነው የሲሚንቶ ዕጥረት ለስራው ፈተና እንደሆነበትም ታውቋል።
ፕሮጀክቱ ሲፈረም የነበረው የግብዓቶች ዋጋ በእጥፍ መጨመሩን የሚያነሱት ኢንጂነር በላይ የግብዓት አቅርቦቱ አለመገኘቱ ብቻም ሳይሆን ኮንትራክተሩ ውል ሲፈርም የነበረው ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ያነሳሉ። እስከ ሶስት እጥፍ መጨመሩን ነው የሚያነሱት። እሱንም ለማግኘት ከባድ ችግር እየተፈጠረ ነው ይላሉ።
እንደ ኢንጂነር በላይ ማብራሪያ፤ የመንገድ ግንባታው እንዲጓተት እያደረገ ያለው ሌላኛው ችግር ከወሰን ማስከበር ጋር የተያያዘ ነው። መንገዱ በሚገነባበት ወሰን ውስጥ ቤቶች፣ የኤሌክትሪክ መስመሮች፣ ውሃ ፍሳሽ ቱቦዎች በጊዜ ባለመነሳቱ ለግንባታው እንቅፋት በመሆኑ ፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብ መሰረት ሊሄድ አልቻለም ይላሉ። የወሰን ማስከበር ችግር ለብዙ ፕሮጀክቶች እንቅፋት በመሆኑ የወሰን ማስከበር ችግሮችን በሚመለከት የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር መርህ አስቀምጧል። መርሁም የሆነ አካባቢ ላይ ፕሮጀክት መስራት ሲፈለግ ፕሮጀክት ከመሰራቱ በፊት በዲዛይኑ መሰረት መንገዱ የሚያልፍበት ወሰን እንዲጸዳ የሚል መርህ አለ። ይህ መርህ ያስፈለገበት ምክንያት የወሰን ማስከበር ችግር እንቅፋት እየፈጠረ በመሆኑ ነው።
የጂግጂጋ ባይፓስ መንገድ በሚያልፍበት ወሰን ውስጥ የሚገኙ አብዛኛዎቹን ንብረቶችን በመርሁ መሰረት ቀድሞ ማስነሳት ተችሎ የነበረ ሲሆን በዚሁ መሰረት በርካታ ቤቶችን ማስነሳት ተችሏል። ውስን ችግሮች አሉ። የኤሌክትሪክ መሶሶዎች እና ሱቆች በመንገድ ወሰን ውስጥ እንደሚገኙ ነው የጠቆሙት።
የስራ ተቋጩ አቅም ውስንነት ሌላኛው ችግር ነው ይላሉ። ይህ ችግር በሀገራችን ውስጥ የሚገነቡ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን የሚያጋጥም ችግር ነው። ሌላኛው ክፊያ በጊዜው አለመፈጸም ነው። የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ክፊያ በጊዜው መክፈል እየቻለ አይደለም። ይህም እየሆነ ያለው አስተዳደሩ ባለበት የባጀት እጥረት ምክንያት ነው። ይህም ለመንገዱ መጓተት አንዱ ምንጭ ነው።
ችግሮቹን ለመቅረፍ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ጥረት እያደረገ ነው የሚሉት ኢንጂነር በላይ፤ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የመንገዱ ባለቤት እንደመሆኑ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የግብዓት አቅርቦት ችግሩን ለመቅረፍ እየሰራ ነው። ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የድጋፍ ደብዳቤዎችን እየተጻጻፈ እንዲሁም በአካል እየሄደ ስራ ሀላፊዎችን በማናገር በግብዓት አቅርቦት ረገድ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ጥረት እያደረገ ነው። የግንባታ ፕሮጀክቶች በተለየ ሁኔታ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው የማሳመን ስራዎችን እየሰራ ነው።
ለአብነት ያህል የሲሚንቶ አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ። ከሲሚንቶ ፋብሪካዎች፣ ከንግድና ቀጣናዊ ትብብር ሚኒስቴር ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች እየተካሄደ ነው። ካላቸው ፋይዳ አንጻር ቅድሚያ የሚሰጣቸው ፕሮጀክቶችን አስተዳደሩ እየለየ ፋብሪካዎቹ እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት ቅድሚያ እንዲሰጡ እያደረግን ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዝርዝር ውስጥ ካሉት ፕሮጀክቶች ውስጥ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ፕሮጀክቶች ውስጥ የጂግጂጋ ተለዋጭ መንገድ አንደኛው እና የመጀመሪያው ነው ያሉት ኢንጂነር በላይ መንገዱ ለከተማው እና ለአካባቢው ወሳኝ በመሆኑ እና መንገዱ በጊዜ አለመጠናቀቅ የህዝቡንም የቀን ተቀን እንቅስቃሴ የሚጎዳ በመሆኑ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው መንገዶች አንዱ እንዲሆን ሆኗል ይላሉ።
በተጨማሪም የክልሉ መንግስትም ከብሄራዊ ሲሚንቶ ፋብሪካ ጋራ እየተነጋገረ ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው። በዚህ ረገድ ውጤቶች እየታዩ ነው ያሉት ኢንጂነሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ችግሩ ይቀረፋል የሚል እምነት እንዳላቸው ጠቁመዋል።
እንደ ኢንጂነር በላይ ማብራሪያ፤ ለፕሮጀክቱ ተጨማሪ እንቅፋት የሆነውን የብረት እጥረት ችግርን ለመቅረፍ ለሚመለከተው አካል ደብዳቤዎች እየተጻፉ ነው። የማስተማመኛ ደብዳቤዎችም እየተጻፉ ነው። ለአብነት ያህል የብረት አቅርቦት ቀድሞ እንዲገባ እና የስራ ተቋራጩን ክፊያ ቀጥታ ለእቃ አቅራቢዎች ለመክፈል መተማመኛ ተሰጥቷቸዋል። ይህም አቅራቢዎቹ ዘንድ መተማመን ለመፍጠር ነው።
ከወሰን ማስከበር ጋር ተያያዥነት ያለው ችግር መፍትሄ የሚፈልግ በመሆኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ ነው። ከቤቶች ቢሮ እና ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ውይይቶች እየተካሄደ ነው። እነዚህ ቤቶች ስራ እንቅፋት እንዳይሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሄ ይሰጣል ብለው እንደሚያስቡ ጠቁመዋል። ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት ውይይቶች እየተካሄደ ነው። በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሄ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
ለፕሮጀክቱ መጠናቀቅ እንቅፋት እየሆኑ ያሉ ችግሮችን ከመቅረፍ ጎን ለጎን አስፋልት ለማንጠፍ የሚረዱ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችም እየተሠሩ መሆኑንም ኢንጂነሩ አብራርተዋል።
ፕሮጀክቱ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ለፕሮጀክቱ መጓተት ምክንያት እየሆኑ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ትብብር በማድረግ ችግሮቹ ተፈተው ፕሮጀክቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 28 /2014