አንተነህ ቸሬ
መንግሥት መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግርን እውን ለማድረግ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል ብሎ ትኩረት ከሰጣቸው ተግባራት መካከል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት አንዱ ነው። ፓርኮቹ ለአምራች ኢንዱስትሪው ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር በተጨማሪ በሚገነቡባቸው አካባቢዎች ለሚኖረው የኅብረተሰብ ክፍል የስራ እድል በመፍጠርና ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆነ የሥራ ከባቢ እውን በማድረግ ለሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ተመራጭ ከሚያደርጓቸው መካከል በርካታ አገልግሎቶችን አንድ ሥፍራ ላይ ሰብሰብ አድርገው የሚያቀርቡ መሆናቸው፣ ተገቢ መሰረተ ልማት የሚገነባላቸው እንዲሁም ከሌሎች አምራቾች ጋርም የሚያገናኙ መሆናቸው የሚሉት ይጠቀሳሉ። ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያም ብዙ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማቋቋም እንዲሁም ሰፊ የሰው ሀይልና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን፣ ማሽኖችን ከቀረጥ ነፃ ማስገባትን፣ የብድር አቅርቦትን፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን እና የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን እንደማበረታቻ በማቅረብ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ፋብሪካዎቻቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲከፍቱ ጥረቶች ተደርገዋል።
በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገሪቱ 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ይገኛሉ፤ ፓርኮቹ በስራ እድል ፈጠራ፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ለሀገራዊ ምጣኔ ሀብት እድገት ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የማምረቻ መናኸሪያ እንድትሆን የሚደረገውን ጥረት ለማቀላጠፍ ላቅ ያለ ሚና ይጫወታል ተብሎ እምነት የተጣለበት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ውጤቶች ተገኝተውበታል።
በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙትን የኢንዱስትሪ ፓርኮች በበላይነት የሚያስተዳድረው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ፣ የኮርፖሬሽኑን የ2014 በጀት ዓመት አፈፃፀም አስመልክቶ ሰሞኑን ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ፣ ኮርፖሬሽኑ በበርካታ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ፈተናዎች ውስጥ ሆኖ መልካም የሚባል አፈፃፀም እንዳስመዘገበ አስታውቀዋል።
ነባራዊ ሁኔታዎች፣ ተግዳሮቶችና የበጀት ዓመቱ እቅዶች
የኮርፖሬሽኑ የበጀት ዓመቱ የዕቅድ አፈፃፀም ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ጫናቸውን ያሳረፉበት ነበር። እቅዱ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ስራ እንደሚገቡ ታሳቢ አድርጎ ነበር። ይሁን እንጂ ሰላምና መረጋጋት ከኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው በመሆኑ በአካባቢው የነበረው የሰላምና ፀጥታ ሁኔታ በእቅዱ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል። የፀጥታ መደፍረሱ በኮርፖሬሽኑ ውስጥ የነበሩ ትልልቅ አምራች ድርጅቶችን ትልቅ ጫና ውስጥ አስገብቷቸዋል። አለመረጋጋቱን ተከትሎ የመጣው የውጭ መገናኛ ብዙኃን እንዲሁም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘመቻና ጫና አምራች ድርጅቶች ተረጋግተው እንዳይሰሩና አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች በቀላሉ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጡ ተፅዕኖ አሳድሯል። በተጨማሪም ኤምባሲዎች ዜጎቻቸው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ከፍተኛ ግፊት ሲያደርጉ ስለነበር አምራቾች በጫና ውስጥ ሆነው ለመስራት የተገደዱበት ዓመት ነበር።
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሰሩና ምርቶቻቸውን ለዓለም አቀፍ ገበያዎች የሚያቀርቡ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን በረጅም ጊዜ የግዥ ውል ለገዢዎች ስለሚያቀርቡ ምርቶቻቸውን በሌሎች ሀገራት ወደሚገኙ ቅርንጫፍ ማምረቻዎች እንዲያዞሩ ጫናዎች ነበሩባቸው፤ ግዢዎችም ይሰርዙባቸው ነበር። በበጀት ዓመቱ ሀገራዊ የሕልውና ማስከበር ዘመቻ ስለነበር፣ አጠቃላይ የመንግሥት እንቅስቃሴ ቅኝት በህግና ሰላም ማስከበር ተግባራት ላይ ያተኮረ ስለነበር፣ በልማት እንቅስቃሴዎች ላይ ተፅዕኖ ነበረው።
በሌላ በኩል በስራ ላይ የዋሉ አዳዲስ የሕግ ማሻሻያዎች፣ በተለይም የውጭ ምንዛሬ አጠቃቀምን በተመለከተ የተተገበሩ አዳዲስ መመሪዎች፣ በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው ላይ የራሳቸው አወንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖዎች አሳድረዋል።
ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችም በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ ጫና ነበራቸው። በዚህ ረገድ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ይጠቀሳል። በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያለው አብዛኛው ኢንቨስትመንት ከእስያ የሚመጣ በመሆኑ የኮሮና እንቅስቃሴ ገደቡ በኢንቨስትመንት ፍሰቱ ላይ ተፅዕኖ አሳርፏል። የዩክሬይን-ሩስያ ጦርነትም በእሴት ሰንሰለቱ ላይ ጫና እንዲፈጠርና አምራች ኩባንያዎች በሚፈለገው ደረጃ ኢንቨስትመንታቸውን እንዳያስፋፉ በማድረጉ በኢንቨስትመንት ፍሰት ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል።
በሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ምክንያት በበጀት ዓመቱ የተመዘገበው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት (Foreign Direct Investment/FDI) ዝቅተኛ ነው።
መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለአምራች ኩባንያዎች ለማቅረብ መሰናክል የሆኑ ነገሮችም አሉ። ከእነዚህም መካከል የኃይል አቅርቦት፣ የካሳ ክፍያና ይገባኛል ጥያቄ፣ የፋይናንስ፣ ዋናዎቹ ችግሮች ናቸው።
የእቅድ አፈፃፀምና የተመዘገቡ ውጤቶች
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሦስት ዋና ዋና መሰረታዊ ተልዕኮዎች አላቸው። እነዚህ ተልዕኮዎቻቸው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ፣ የሥራ እድል ፈጠራን ማስፋት እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማከናወን ናቸው።
ሰራተኞችን በተመለከተ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም በተጠናቀረ መረጃ መሰረት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በቀጥታ በምርት ተግባራት ላይ የተሰማሩ 81ሺ ሰራተኞች አሉ። ይህ ቁጥር ከፓርኮቹ ውጭ ያሉና ተዘዋዋሪ በሆነ መንገድ የሥራ እድል የተፈጠረላቸውን ሰዎች አይጨምርም። በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ውስጥ የሚገኙ አምራቾች ከፓርኮቹ ውጭ ካሉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ጋር የስራ ትስስር ስላላቸው በዚህ ሂደትም በርካታ የሥራ እድሎች ተፈጥረዋል። ለአብነት ያህል በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ለሚገኙ 23ሺ ሰራተኞች የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ከ410 በላይ ሀገር አቋራጭ መኪናዎች አሉ። በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ደግሞ ከ230 በላይ አውቶቡሶች አሉ። ለሰራተኞቹ የሚቀርቡት ሌሎች አገልግሎቶች ሲጨመሩበት ፓርኮቹ በተዘዋዋሪ መንገድ በርካታ የሥራ እድሎችን እንደፈጠሩ መገንዘብ ይቻላል።
በ2014 የበጀት ዓመት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከ57ሺ በላይ የስራ እድል ፈጥረዋል። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ስራ ከጀመሩበት ጊዜ ወዲህ ከ61 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ምርቶች ለሀገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ ገበያ ቀርበዋል። በበጀት ዓመቱ 412 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ለገበያ ለማቅረብ ታቅዶ 357 ሚሊዮን ዶላር (18.5 ቢሊዮን ብር) ማሳካት ተችሏል። ከዚህ ውስጥ 196 ሚሊዮን ዶላሩ (10.3 ቢሊዮን ብር) ለውጭ ገበያ ከቀረቡ ምርቶች የተገኘ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት የስምንት በመቶ እድገት ዐሳይቷል። በአጠቃላይ ፓርኮቹ ስራ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ፣ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ፣ ለውጭ ገበያ የቀረበውና በተኪ ምርቶች የተገኘው ዋጋ አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር ሆኗል። ከዚህ ውስጥ፣ 930 ሚሊዮን ዶላር የሚሆነው ገንዘብ ለውጭ ገበያ ከቀረቡ ምርቶች የተገኘ ነው።
ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠውና ጥሩ ውጤት እየተመዘገበበት ያለው ሌላው ዘርፍ ተኪ ምርቶችን የማምረት ተግባር (Import Substitution) ነው። በተለይም የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች ተኪ ምርቶችን በማምረት ላይ እንዲሰማሩ ድጋፍ እንዲደረግላቸው በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ኮርፖሬሽኑ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል። በበጀት ዓመቱ ለገበያ ቀርበው 357 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ካስገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ምርቶች መካከል 161 ሚሊዮን ዶላሩ ለሀገር ውስጥ ገበያ ከቀረቡ ምርቶች የተገኘ ነው። በዚህም የእቅዱን 96 በመቶ ማሳካት ተችሏል። ለሀገር ውስጥ ገበያ ከቀረቡት ምርቶች መካከል የፋርማሲቱካል ምርቶች፣ የግንባታ እቃዎች፣ የኬሚካል ምርቶች፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሳሪያዎችና አልባሳት ይገኙበታል።
ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ የሚፈለገውን ውጤት እንዳያስመዘግቡ መሰናክል ከሆኑ ተግዳሮቶች መካከል አንዱ የአቅርቦትና ትስስር (Linkage) ችግር ነው። አብዛኞቹ አምራች ኩባንያዎች የውጭ ድርጅቶች በመሆናቸው ምርቶቻቸውን የሚያቀርቡት ለውጭ ገበያ ነው። ግብዓቶችን ከሀገር ውስጥ በሚፈለገው መጠን ማቅረብ ባለመቻሉ እስከ85 በመቶ የሚሆነውን የምርት ግብአታቸውን የሚያመጡት ከውጭ ነው። በበጀት ዓመቱ ለአምራቾች ከ69 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ ግብዓት ከሀገር ውስጥ ማቅረብ ተችሏል። ይህም አፈፃፀም ከእስካሁኑ የተሻለው ሆኖ ተመዝግቧል። ኩባንያዎቹ በውጭ ምንዛሬ አጠቃቀም መመሪያው መሰረት ከውጭ እንዲያመጡ የሚፈቀዱላቸው ግብዓቶች በሀገር ውስጥ ሲመረቱ ከውጭ ያለማምጣት እድላቸውን እያሰፉ ነው።
አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ከመሳብ አንፃር በበጀት ዓመቱ 14 የማምረቻ ሼዶችን ለአምራቾች ለማስተላለፍ ታቅዶ 13 ሼዶች ለአምራቾች ቀርበዋል። በአጠቃላይ ካሉት 177 የማምረቻ ሼዶች መካከል 151 የሚሆኑት በውል ለባለሀብቶች ተላልፈዋል።
በበጀት ዓመቱ ከስድስት ሄክታር በላይ የለማ መሬት ለአዳዲስ ኢንቨስትመንቶች በቦሌ ለሚ፣ በጅማ፣ በቂሊንጦና በሌሎች ፓርኮች ቀርቧል። ከለማው መሬት እስካሁን ለባለሀብቶች የተላለፈው አጠቃላይ መሬት 12 ነጥብ አምስት ሄክታር ነው። ኮርፖሬሽኑ እስካሁን ከ526 ሄክታር በላይ የለማ መሬት አለው። ይህ ደግሞ 87 በመቶ የሚሆነው የለማ መሬት ገና ለአምራቾች እንዳልተላለፈ ያሳያል። በእርግጥ ኮርፖሬሽኑ ሼዶችን ከማከራየት በተጨማሪ የለሙ መሬቶችን ማቅረብ የጀመረው ከሁለት ዓመታት ወዲህ ነው።
ኮርፖሬሽኑ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች (የቢሮ፣ የሼድ ኪራይ፣ የለማ መሬት አቅርቦትና ሌሎች አገልግሎቶች) በበጀት ዓመቱ አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ለማግኘት አቅዶ አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በማግኘት እስካሁን ድረስ ካገኘው ገቢ የላቀውን ማስመዝገብ ችሏል። ላለፉት ሰባት ዓመታት በኪሳራ ውስጥ የነበረው ኮርፖሬሽኑ በ2014 በጀት ዓመት የበጀት አስተዳደሩን በጥንቃቄ በመምራትና የገቢ ምንጮቹን በማስፋት ከ330 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ አስመዝግቧል።
የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲገቡ የተጀመረው ስራ አበረታች ውጤቶችን እያስገኘ ነው። ከዚህ ቀደም ወደ ፓርኮቹ የገቡ አምራቾች የተሰማሩባቸው ዘርፎች ጥቂት ነበሩ። የአዋጭነት ጥናት ማሻሻያዎችን በማድረግ የዘርፎቹን ብዝሃነትና የገበያ መዳረሻዎችን የማስፋት ስራዎች እየተሰሩ ነው።
የሮኬት ጥቃት የተፈፀመበትን የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ በፀጥታ ችግር ምክንያት ምርት ያቆመው የመቐለ፣ የተጎዳው የኮምቦልቻ እና ምርት ያልጀመረው የሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በስራ ላይ ቢሆኑ ኖሮ ከዚህም የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገብ ይቻል ነበር።
በበጀት ዓመቱ ካጋጠሙ ችግሮች መካከል አንዱ በአሁኑ ወቅት ወደ ነፃ የንግድ ቀጠና የተቀየረው የድሬዳዋ የኢንዱስትሪ ፓርክ የውሃ አቅርቦት ችግር ነበር። በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ከሚቀርቡ ዋነኛ አገልግሎቶች መካከል አንዱ የውሃ አቅርቦት ነው። በአካባቢው ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ምክንያት በድሬዳዋ የኢንዱስትሪ ፓርክ ቀጠና ውስጥ ውሃ ለማግኘት አስቸጋሪና ከቅጥር ግቢ አስር ኪሎ ሜትር መውጣት ያስፈልግ ስለነበር ለፓርኩ ውሃ ለማቅረብ የሚስችሉ ስራዎችን በማከናወን በዚህ ዓመት ፓርኩ/ቀጠናው የውሃ አገልግሎት እንዲያገኝ አድርገናል።
የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ በወራሪው ኃይል ከፍተኛ ውድመት ደርሶበት ነበር። በኢንዱስትሪ ፓርኩ ላይ የደረሰው ጉዳት በሁለት መልኮች የሚገለፅ ነው። አንደኛው የኮርፖሬሽኑ ሀብት የገጠመው ውድመትና ዝርፊያ ሲሆን፤ በፓርኩ ውስጥ በስራ ላይ የነበሩ አምራች ድርጅቶች የደረሰባቸው ዝርፊያ/ውድመት ደግሞ የጉዳቱ ሌላኛው መልክ ነው። ይህም ከፍተኛ ርብርብ ተደርጎበት በአንድ ወር ውስጥ ወደ ስራ እንዲመለስ ተደርጓል።
በቀድሞው የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስተዳዳሪነት ስራው የተጀመረው የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ (ICT Park) በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን እንዲተዳደር ከተወሰነ በኋላ ፓርኩ የታቀደለትን እቅድ እንዲያሳካ ኮርፖሬሽኑ ልዩ ልዩ ተግባራትን አከናውኗል። ኮርፖሬሽኑ ፓርኩን ሲረከብ የመሰረተ ልማቶች አለመሟላት፣ የግንባታዎች መቋረጥ፣ የአማካሪዎች አለመኖርና ሌሎች ችግሮች ነበሩበት። ኮርፖሬሽኑ መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉ፣ የአስተዳደር ስርዓቶች እንዲዘረጉ የሚያስችል የቢዝነስ ፖርትፎሊዮ ተቀርጾለት በአግባቡ ወደ ስራ እንዲገባ አድርጓል። በቀጣይም ተጨማሪ መሰረተ ልማቶችን በማሟላት የተሻለ የሥራ እድል የመፍጠርና የውጭ ምንዛሬ የማስገኘት አቅም እንዲኖረው ይደረጋል።
ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች
ኮርፖሬሽኑ ከጊዜው ጋር የሚራመዱ የአሰራር ማሻሻያዎችን ለመተግበርም ጥረት እያደረገ ይገኛል። የኮርፖሬሽኑ የጥናት ውጤት የሆነውና በቅርቡ ስራውን የጀመረው የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና የዚሁ ማሳያ ተደርጎ ይጠቀሳል፤ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በሂደት ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጠናዎች (Special Economic Zones) የሚቀየሩበት አሰራር እንዲጠናከር ይደረጋል።
ለበርካታ ዓመታት የማማከር፣ የጥናትና የስልጠና ስራዎችን ሲሰራ የነበረው የኢንዱስትሪ ፕሮጀክት አገልግሎት (Industrial Project Service) የተባለው የመንግሥት ኩባንያ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት ከኮርፖሬሽኑ ጋር እንዲሰራ ተወስኖ የአዋጭነት ጥናት፣ የሀብት ግመታ፣ የኮርፖሬት ሪፎርምና የሥልጠና ስራዎች ተሰርተዋል፤እነዚህም ተጠናክረው ይቀጥላሉ።
ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ ሳንዶካን ደበበ፣ ‹‹ባለፉት ጥቂት ዓመታት በቢሊዮን ብሮች የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ የተደረገባቸውንና ሜጋ ፕሮጀክቶች የሆኑ 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ገንብቶ ወደ ስራ ማስገባት ኮርፖሬሽኑ ከፕሮጀክት አመራር አንፃር የተሳካ አፈፃፀም እንዳለው የገንዘብ ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎች አካላት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።›› ሲሉ ይገልጻሉ። እያንዳንዱን ኢንዱስትሪ ፓርክ አስገንብቶ ወደ ስራ ማስገባቱ ቀላል ስራ እንዳልሆነ ይታወቃል ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፣ ይህን ልምድ መነሻ በማድረግም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከኮርፖሬሽኑ በተጨማሪ የሌሎች ተቋማትን ፕሮጀክቶችን የማማከርና የማገዝ ስራዎችን በመስራት ሀብት የማመንጨት ስራዎችን የሚሰራ ይሆናል›› ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገሪቱ 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ይገኛሉ፤
አዲስ ዘመን ነሐሴ 26 /2014