
አዲስ አበባ፡- “የአንድነት ቀን” በሚል የተሰየመው ጳጉሜን 5 ቀን 2014 ዓ.ም በመላው ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች በሚገኙበት በታላቅ ድምቀት እንደሚከብር የበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴ ገለጸ።
የበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት የመከላከያ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር ኮ/ል ጌትነት አዳነ ፤ በዓሉ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበርና አስታውቀዋል።
“ተፈጥሯዊ የሆነውን ልዩነቶቻችን እንደ ችግር ለመጠቀም የሚፈልጉ የውጭና የውስጥ የሀገራችንን ጠላቶች በተለመደው ኢትዮጵያዊ አንድነታችን በመቆም ለዓለም የምናሳይበት በዓል ይሆናል” ብለዋል።
በዓሉ ከግለሰብ ጀምሮ በተለያዩ ተቋማት ደረጃ በታላቅ ድምቀት እንደሚከበርና አዲሱን ዓመት በአዲስ ተስፋ ለመቀበል የምንነሳሳበትና የአንድነት መገለጫ የሆነው ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችንን የምናከብርበት ዕለት ይህናል ሲሉ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ገልጸዋል።
የመንግሥት የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ፤ በዓሉ ከሀገር ውጭ በሃምሳ ሁለት የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንሲላ ፅ/ቤቶች በድምቀት እንደሚከበር ገልጸዋል።
በዕለቱ ሀገራዊ አንድነትን የሚያጎሉ የተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚደረጉና አምስት ሰዓት ላይ “እኔ ለሀገሬ አንድነት” የሚል ልዩ ፕሮግራምም መሰናዳቱን የሀገር መከላከያ ሠራዊት በማህበራዊ ገጹ አስታውቋል።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 25 ቀን 2014 ዓም