
አዲስ አበባ፡- በጦርነት ወቅት በሃሰት መረጃዎች እንዳንወናበድ ከመንግሥት አካላት የሚሰጡ የአንድ ማዕከል መረጃዎችን ብቻ ልንጠቀም ይገባል ሲሉ በዲላ ዩኒቨርሰቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን መምህርና የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪው አቶ አለበል ጓንጉል ገለጹ።
አቶ አለበል ከኢፕድ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንደገለጹት፤ በጦርነት ወቅት መረጃን ከሚመራ አካልና ታማኝ ከሆኑ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ብቻ መውሰድ አስፈላጊ ነው። መገናኛ ብዙሃንም ለሕዝብ የሚሰጡትን መረጃ በጥንቃቄና ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ በወቅቱ ሊሰጡ ይገባል። ምክንያቱም የጦርነትና የቀውስ ጊዜ ኮሙዩኒኬሽን ጥንቃቄ በተሞላበት ሊከናወን ይገባል። በዚህ ጊዜ የአገርን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ መረጃዎች ሊተላለፉ ስለሚችሉ ከመቼው ጊዜ በበለጠ በጥንቃቄ መስራት ተገቢ ነው።
በአሁኑ ወቅት የማሕበራዊ ሚዲያዎች በርካታ ተከታይ እንዳላቸው ይታወቃል ያሉት አቶ አለበል፤ ነገር ግን በርከት ያለ ተከታይ ያላቸው የማሕበራዊ ሚዲያዎችና አንቂዎች ሁሉ ትክክለኛ መረጃ ይሰጣሉ ማለት እንዳልሆነ በመገንዘብ ሕብረተሰቡ ከዚህ ውዥንብር እንዲወጣ መረጃውን ከማን ነው መውሰድ ያለብኝ፣ መረጃን የሚሰጡ አካላት ከዚህ በፊት የሚሰጡት መረጃ ትክክለኛነት ምን ያህል ነው፣ የሚለውን ማረጋገጥ መቻል አስፈላጊ ነው ብለዋል።
እንደ አቶ አለበል ገለጻ፤ መረጃ የሚሰጡ አካላትም ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ እንዳይሰጡ ከሚመለከተው አካል ማሳሰቢያ ሊሰጣቸው ይገባል፤ ማሕበረሰቡም መረጃ ከየትና ከማን መውሰድ እንዳለበት መገናኛ ብዙሃን በተከታታይ ማሕበረሰቡን የማስገንዘብ ስራ ሊሰሩ ይገባል።
በአንጻሩ በጦርነት ወቅት ሕዝብ ለሀሰተኛ መረጃ እንዳይጋለጥና መደናገር እንዳይኖር ከአንድ ማዕከል የሚሰጥ መረጃ ሊኖር እንደሚገባም አቶ አለበል ጠቁመዋል።
አቶ አለበል እንዳሉት፤ በጦርነትና በቀውስ ጊዜ አንድ ሀገር ሊከተለው የሚገባ የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ አለ። ይህም ወቅቱን የጠበቀ መረጃ በአንድ የኮሙዩኒኬሽን ሰንሰለት መስጠት ነው። ለዚህም በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽንና የአገር መከላከያ ሠራዊት ትልቅ ኃላፊነት ያለባቸው ተቋማት ናቸው። የመከላከያ ሠራዊት የኮሙዩኒኬሽን ዘርፉና የመንግሥት ኮሙኒኬሽን በአንድ ማዕከላዊ ዕዝ በመሆን ተናበው በየጊዜው ለሕዝቡ መረጃዎችን ማድረስ ይጠበቅባቸዋል።
“መረጃ የሚፈልገው ማሕበረሰብ በጣም ብዙ ነው። ስለዚህ መረጃ በአግባቡ ሳይሰጥ ሲቀር ሕብረተሰቡ ለተለያዩ የሀሰት መረጃዎች ሰለባ ይሆናል። ይህን የመረጃ ፍላጎት በተገቢው መንገድና ወቅቱን በጠበቀ መንገድ መስጠት ይገባል። ለዚህ ደግሞ አንድ ወጥ የሆነ ማዕከላዊ የሆነ የመረጃ አሰጣጥ መዘርጋት ወሳኝ ነው” ብለዋል።
እንደ አቶ አለበል ገለጻ፤ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃንና አንዳንድ የማሕበራዊ ሚዲያዎች የመገናኛ ብዙሃን አሰራርና የሙያ ሥነምግባሩን በመጣስ ያልተገባና ሀሰተኛ መረጃ እያሰራጩ ሕዝብ እያደናገሩ ነው። መደናገሩን ለመግታት የተደራጀ፣ የተቀናጀና ከአንድ የመረጃ ቋት የሚሰጥ መረጃ መኖር አስፈላጊ ነው። ለሀሰተኛ ዘገባዎች ምላሽ እየሰጡ መቀጠል ሳይሆን የመረጃ ምንጫቸው ለመሆን መስራት ያስፈልጋል።
ባለፈው ዓመት የነበረው የኮሙዩኒኬሽን ሥርዓት የወረዳ ኮሙዩኒኬሽን ሳይቀር መረጃ ሲሰጥ እንደነበር አስታውሰው፤ ይህም መረጃ ወጥነትና ከሌሎች የኮሙዩኒኬሽን መረጃ ልዩነት ያለው ስለነበር ሕዝብ እንዲደናገር በር ከፍቶ ተስተውሏል ብለዋል። “መረጃው በዋናነት ከአንድ ማዕከል ሊሰጥ የሚችልበት መዋቅር መኖር አለበት። አሁን የመረጃ አሰጣጡ በተወሰነ መንገድ መሻሻሎች አሉ። ይህም ወጥ በሆነ መንገድ መቀጠል አለበት” ሲሉም ተናግረዋል።
ባለፈው የግጭት ወቅት የተለያዩ አክቲቪስቶች በኩል ሰበር ዜና እያሉ “እዚህ ቦታ በእከሌ ተያዘ፣ ይህንን አካባቢ ይህ ሃይል ተቆጣጠረ፤ ወዘተ” እያሉ የተሳሳተ መረጃ በመንዛት ሕብረተሰቡ ውዥንብር ውስጥ እንዲገባ ሲያደርጉ እንደነበር የጠቆሙት አቶ አለበል፤ የማሕበራዊ ሚዲያ ተከታይን ቁጥር ለማብዛት ሲሉ ብቻ አገር የሚያተራምሱ በርካታ የማሕበራዊ ሚዲያ አወናባጆች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
መረጃ የሚሰጡ አካላት ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ እንዳይሰጡ ከሚመለከተው አካል ማሳሰቢያ ሊሰጣቸው ይገባል ያሉት አቶ አለበል፤ ማሕበረሰቡም መረጃ ከየትና ከማን መውሰድ እንዳለበት መገናኛ ብዙሃን በተከታታይ ማሕበረሰቡን የማስገንዘብ ስራ ሊሰሩ ይገባል ሲሉ ጠቁመዋል።
ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ነሀሴ 25 ቀን 2014 ዓም