መቸም ”አንጋፋው የኪነጥበብ ባለሙያ፣ የመድረኩ ንጉስ ፍቃዱ ተክለማርያም ከዚህ አለም በሞት ተለየ”ን የሰማ ሁሉ፣ ወደደም ጠላም ”ክው” ያላለ የለም፤ በተለያዩ መድረኮች የተመለከታቸው የፍቄ የተለያዩ ሰብእናዎች ሁሉ እየተግተለተሉ ወደ አእምሮው ጓዳ ያልመጡ፤ ወይንም የፍቄን ትወና በዐይነ ህሊናው ያላያቸው … አለ ለማለት በእውነት ይቸግራል። ፍቄ አይደለም ላወቀውና ቀርቦ ላወራው ባጋጣሚ ላየው ሁሉ ትዝታው ከአይን የሚጠፋ አይደለም፡፡
የሰው ልጅ በምግብ እና ውሃ ነው የሚያድገው እንበል እንጂ የፍቄን ሁለገብ ትወናዊ ብቃት እየተመለከተ፤ በወከለው ገፀባህርይ(ያት) እየተመሰጠ የኖረን ትውልድ ”በምን አደግህ?” ተብሎ ቢጠየቅ፤ ከእህል ውሃው ቀጥሎ ለመልካም እድገቴ የፍቃዱ ሙያዊ አለበት ቢል የማያስኬድበት ምክንያት የለም። አዎ፣ የፍቄን ስራዎች አይቶ መንፈሱን ያልመገበ አለ ለማለት ይከብዳል።
ቀጥለን ፍቃዱን ከራሱ ጋር፤ ፍቃዱን ከሙያው ጋር፤ ፍቃዱን ከሙያ ባልደረቦቹ ጋር፤ ፍቃዱን ከአጠቃላይ አድናቂዎቹ ጋር፤ ፍቃዱን ከህዝቡ ጋር እያዛነቅን እንመለከታለን።
በአገራችን የትያትር ፍቅር እየጎለበተ የመጣው በፍቃዱና እንዲሁም ከፍቃዱ ትንሽ ቀደም ብለው በነበሩት በእነ አርቲስት ደበበ እሸቱ ዘመን እንደሆነ ይነገራል። የተለያዩ ጥናቶችም ይህንኑ ነው የሚያረጋግጡት። በመሆኑም ፍቄ ለጥበቡ ተመልካቾች ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ኪነጥበብ በአጠቃላይ፤ በተለይ ደግሞ ለትያትር ጥበብ እዚህ መድረስ የራሱን አሻራ (ሌጋሲ) አሳርፏል ማለት ነውና ፍቄ ባለውለታ ነው።
ፍቃዱ ተክለ ማርያም ለመጀመሪያ ጊዜ የመሪ ተዋናይነት ሚና ያገኘው በአባተ መኩሪያው “እሳት ሲነድ” በሚለው ቲያትር ሲሆን “እጅህን ስጥ አለኝ ፈረንጅ …” የሚለውን የአጼ ቴዎድሮስ ንግግር ሲጀምር ተመልካቾች በዘመን ወደ ኋላ ሄደው የቴዎድሮስን ጀግንነት በእውንም እየተመለከቱ እስኪመስላቸው ድረስ አስቆዝሟል።
ፍቃዱን በሚገባ ይገልፀዋል ብለን ያሰብነው የቅርብ ወዳጁ የሆነዉ የብሔራዊ ትያትሩ አርቲስት ቴዮድሮስ ተስፋዬ ስለ ፍቄ የተናገረው ሲሆን፤ እሱም፣ «ፍቄ በሱ ዘመን የነበሩ የትያትር ባለሞያዎች አንዳንዶች ከሃገር ወጥተዋል፤ አንዳንዶቹም ከጥበቡ ርቀዋል፤ እሱ ብቻ ነው በዘመኑ ካሉት በሙያው የቀጠለው። ጥበብን የሚያከብር፤ እስዋ ራስዋ ጥበብ የምታከብረው በሰራቸው ስራዎች ሁሉ የማይኩራራ፤ አክብሮቱን ከትንሽ እስከ ትልቅ የሚገልፅ፤ ደከመኝ ሰለቸኝ የማይል፤ ሕዝብ በጠራው ቦታ የሚገኝ ሙያውን የሚወድና ሰውን የሚያከብር፤ ቤተሰቡን የሚወድ ሰው ነው ፈቃዱ። ፍቃዱ የኪነ-ጥበቡ አርማ ነው።» የሚለውና በተለያዩ ፅሁፎች ለንባብ የቀረበው ነው።
ብዙውን ጊዜ በመድረክ ላይ በንግሥናው፤ አልያም ደግሞ አፄ ቴዮድሮስን ሆኖ በመጫወት የሚታወቀው ፍቃዱ እጅግ ገናና ከሆነበት የሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን “ቴዎድሮስ” ቴአትር በተጨማሪ በ”ኤዲፐስ ንጉስ”፣ “ሐምሌት” እና “ንጉስ አርማህ” ተውኔቶችም ንጉስን ሆኖ ተጫውቷል። በዚህም ምክንያት ”ከመድረክ ጀርባ፤ ንጉሱ” የሚል መጠርያ እንደለውም አርቲስት ቴዎድሮስ ተስፋዬ ገልፆአል።
ይህንኑ ሀሳብም፣ በአንድ ስለ ፍቃዱ ሲባል በተዘጋጀ መድረክ ላይ «የተደረገው መነሳሳት እኔን ብቻ ሳይሆን መላውን የጥበቡን ቤተሰቦች እና ኢትዮጵያዊያንን ሁሉ ያስደሰተ ነገር ነው። ምክንያቱም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሕዝቡ ከፍተኛ ርብርብ አድርጓል። ፍቃዱ እስከዛሬ በመድረክ ሙያው ላይ ያደረገውን አስተዋፅኦ በተመለከተ ሕብረተሰቡ ምላሽ እየሰጠ ይመስለኛል። ፍቅሩን እየገለፀለት ነዉ። ይሄ ደግሞ ለፍቃዱ የተደረገ ብቻ ሳይሆን ለሁላችንም እንደተደረገ አድርጌ ነው የማየው።» ያለው ሌላው የመድረክ ንጉስ ደበበ እሸቱም በዚሁ አስተያየት እንደሚስማማ አርቲስት ቴዎድሮስ ተናግሯል።
አዲስ አባባ አራት ኪሎ አካባቢ ተወልዶ ያደገው፤ በ62 አመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው መሪ ተዋናይ ፍቃዱ ተክለማሪያም መነሻው ቴአትር ቢሆንም በተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማዎች (ለምሳሌ “ባለጉዳይ”፣ “ያልተከፈለ እዳ”፣ “የአበቅየለሽ ኑዛዜ”፣ ‘’ገመና’’ …)፣ በፊልሞች እንዲሁም በማስታወቂያ ሥራዎቹ እና በሬድዮ ትረካዎችም ጭምር አገር ያውቀዋል።
በ”ፀፀት” ፊልም ላይ ዳኛ ሆኖ የሰራው ፍቃዱ ዳኝነቱን እንደ ንጉስነቱ ሁሉ አሳምሮ የተጫወተው መሆኑን በወቅቱ የፊልሙ ደራሲ አቶ አለባቸው ደሳለኝ መስክረውለታል።
ከተሳተፈባቸው ወጥና ትርጉም ተውኔቶች መካከል ኦቴሎ፣ ኤዲፐስ ንጉሥ፣ ሐምሌት፣ ቴዎድሮስ፣ ንጉሥ አርማህ፣ መቃብር ቆፋሪውና የሬሣ ሳጥን ሻጩ፣ የሰርጉ ዋዜማ፣ አቡጊዳ ቀይሶ፣ ባለካባ ባለዳባ፣ መልዕክተ ወዛደር እና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ:: ያልተከፈለ እዳ፣ ያበቅየለሸ ኑዛዜ፣ ባለጉዳይ እና የመሳሰሉት በህዝብ ዘንድ የሰረፁና አድናቆትን ያተረፉለት ስራዎቹ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ ራድዮ ይተላለፍ የነበረው “ከመጻሕፍት አለም” ላይ ያቀርባቸው በነበሩ ትረካዎች በርካታ መጻሕፍት ላይ ህይወት ዘርቷል። “ሞገደኛው ነውጤ”፣ “ጥቁር ደም”፣ “ሳቤላ”፣ “ወንጀለኛው ዳኛ” እና “ግራጫ ቃጭሎች” ከተረካቸው መጻሕፍት መካከል ይጠቀሳሉ።
በ1967 ዓ.ም በአዲስ አበባ ቲያትርና ባህል አዳራሽ ቅርብ ጓደኛው በነበረው ከሱራፌል ጋሻው ጋር የመቀጠር እድልን በማግኘት ዘርፉን የተቀላቀለው ፍቃዱ ለ42 ዓመታት ያህል በመድረክ፣ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን፤ አሁን ደግሞ በፊልም (ለምሳሌ “ቀይ ስህተት” በተባለው ፊልም የተዋጣለት ስራ ለመሥራት በመብቃቱ “አቶዝ” አውቶሞቢል የቴዲ ስቱዲዮ ሸልሞታል።) በርካታ ፈታኝ ሚናዎችን እየወከለ ተጫውቷል፡፡
ለ42 ዓመታት በርካታ የመድረክ ጥበብን በሙሉ አቅሙ ሲጫወት የኖረው አርቲስት ፍቃዱ ተክለማሪያም ባደረበት የኩላሊት በሽታ ሳቢያ ውጪ አገር ሄዶ ለመታከም ገንዘብ ቢሰበሰብለትም ከተሰበሰበው ገንዘብ 200ሺህ ብር ”ከእኔ እሷ ልጅ ነች። ብዙ መኖር ያለባት እሷ ነች። እኔ ብዙ አይቻለሁ።” በሚል እሳቤ ለአንዲት ኩላሊት ታማሚ፤ በዚሁ ምክንያትም ትምህርቷን ከ10ኛ ክፍል ያቋረጠች ልጅ አበርክቷል። ሌላውና ፍቄን ለየት የሚያደርገው አንዱ ይህ በጎ ተግባሩ ነው።
ሜላት አሰፋ ምን ትላለች?
ያኔ የፍቃዱ ጥሪ የመጣልኝ በጌታነህ ጸሀዬ በኩል ነበር። ገንዘቡን የሰጠኝ ምንም ባልጠበቅኩበት ወቅት ነበር። በሰዓቱ እጄ ላይ ብር አልነበረኝም። ሲጠራኝ እንዲሁ ሊያናግረኝ የፈለገኝ ነበር የመሰለኝ። መልካም ነገር ነው ያደረገልኝ፤ አመሰግነዋለሁ። በኛ ሀገር የኩላሊት እጥበት ወጪ ከባድ ነው። እሱ ግን ረዳኝ። ከሀገር ውስጥም ከውጪም ሰዎች ባሰባሰቡልኝ ገንዘብ እየታከምኩ ነው። አሁን በኮርያ ሆስፒታል የኩላሊት እጥበት እየተከታተልኩ ነው። ከረዳኝ በኋላ በስልክ እንገናኝ ነበር። ለመጨረሻ ጊዜ የተነጋገርነውን አስታውሳለሁ። ‘በርቺ’ የሚል ቃል ነበር የተናገረው። ‘እንድናለን’ ይለኝ ነበር። ድኖ እንገናኛለን ብዬ ነበር። ነገር ግን አልሆነም። (እዚህ ጋ ዮርዳኖስ ”ፍቄ ከምንም በላይ አባት ነው። የሁሉም ሰው አባት ነው።” ያለውን ስክት ሲል እናገኘዋለን።)
የፍቃዱ መታመምና የሕዝቡ ምላሽ
ሀይማኖቱ ላይ ጠንካራ አቋም የነበረው ፍቄ መታመሙ ይፋ በሆነበት ወቅት የህዝቡን ርብርብ አስመልክተው ለንባብ ሲበቁ የነበሩት መረጃዎች እንዳመለከቱት ፍቄን ለማዳን ወደ ኋላ ያለ አልነበረም። «የህዝቡ ወደር የሌለው ምላሽ እጅግ የሚያስደስት ነው» በማለት የሚጀምረው ጽሑፍም ይህንኑ በሚያጠናክር መልኩ ”የጥበብ ስራን ከማየትና ከማድነቅ በላይ ለተጠባቢው ፍቅርና አክብሮትን የሚለግሰው ውድ ህዝብ አሁንም የጋሽ ፍቃዱን መታመም ከሰማበት ጊዜ ጀምሮ የሰጠው ምላሽ እጅግ የሚያስደስት ነው። በመላው አለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ”ለወገን ደራሽ ወገን ነው” በሚል ከልብ በመነጨ ፍቅር ወገናዊነታቸውን በተግባር እያሳዩ ነው:: በፀሎት ከማሰብ ጀምሮ ’ኩላሊታችንን መለገስ እንፈልጋለን’ የሚሉ እና በሀሳብም በገንዘብም የደገፉ በርካቶች ናቸው።”
ሌላው ለተወዳጅነቱ ማሳያ ፍቃዱን “ለኔ ወንድሜ፣ ጓደኛዬ ነው። ከዚያ በላይ አባቴም ነው።” የሚለው፤ የህዝቡን ትብብር በተመለከተ ”እግዚአብሔር ይመስገን ከውጪና ከሀገር ውስጥም ከ100 ሰው በላይ ኩላሊት ለመስጠት ፍቃደኛ ሆነ።” በማለት የተናገረው ወንድሙ ግርማ ተክለማርያም ”በገዳም ሕግ ገዳም ውስጥ ያረፈ ሰው አስከሬን ከገዳም አይወጣም። ነገር ግን ገዳሙ ትልቅ ትብብር አድርጎልናል። ፍቃዱ የህዝብ ልጅ ነው። ስለዚህ ህዝብ በይፋ እንዲቀብረው አስከሬኑን ሰጥተውናል።” ያለው ነው።
የፍቄን የመጨረሻዎቹን ጊዜያት ”ከትንሳኤ በአል በኃላ ወደ ጸበል ሄደ። ጳውሎስ ሆስፒታል ቀጠሮ ላይ ነበር። የቀጠሮው ግዜ እስከሚደርስ ‘ቤቴ አልቀመጥም ጸበል ቦታ ገብቼ እግዚአብሄርን እማጸናለሁ’ ብሎ ነበር።” በማለት የሚገልፀው፤ ለፍቄ የልጅ አከል የሆነው ዮርዳኖስ “ፍቄ የሀገር ቅርስ ነው። የሀገር ባለውለታ ነው። የሁሉም አባት ነው።” ሲልም ፍቃዱን ከሙያው፤ ሙያውን ካገርና ህዝቡ ጋር አዋህዶ ይገልፃል። ከበቂ በላይ ገንዘብ ተሰባስቧል። እሱም ደስተኛ ነበር። ”የሌላ ሰው ኩላሊት ወስጄ ባልተርፍስ የሚል ስጋት ግን ነበረው።” ሲልም ይናገራል።
«የጤና ጥበቃ ሚ/ር አርቲስት ፍቃዱ ተ/ ማርያም በነጻ ሙሉ የኩላሊት ንቅለ ተከላ በሀገር ውስጥ ማድረግ እንዲችል ፈቃድ ሰጥቷል።» የሚለው ዜናም ሆነ፤ በማህበራዊ ሚዲያው ይታይ የነበረው የፍቄን የጤና ሁኔታ እየተከታተሉ የማጋራቱ ተግባር (”ሼር” የማድረጉ) አሁን በህይወት ባለነው ቀርቶ ለመጪው ትውልድም እንደ አዲስ የሚገርም ሆኖ ነው ያለፈው። (በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የቲቢ አምባሳደር ተደርጎ በተሾመበት ወቅት በርካታ ሥራዎችን ለአገሩ ማበርከቱ ይነገርለታል።)
እርግጥ ነው በ1968 ዓመተ ምህረት በሃምሌት ቴአትር ለመጀመሪያ ጊዜ በመሪ ተዋናይነት የመጫወት ዕድል ካገኘባትና ከተጫወተበት ጊዜ አንስቶ የመድረክ ፈርጥ በመሆን በርካታ ቴአትሮችን መጫወቱ የሚነገርለት ፍቃዱን ብዙዎች ብዙ ብለውለታል። ጉዳዩ ”ከፈረሱ አፍ” እንዲሉ ነውና ከ”ፋዘር” እንጀምር።
አቶ ተስፋዬ አበበ (ፋዘር)
የፍቃዱን ከዚህ አለም መለየት ተከትሎ አስተያየታቸውን የሰጡ ብዙዎች ሲሆኑ፤ አንዱም በቅፅል ስሙ የሚታወቀው ፋዘር ነበር። ፋዘር እንዲህ ነበር ፍቄን የገለፀው፡-
በልጅነቱ የሰለጠነው እኔጋ ነበር። ያኔ ሱራፌል ጋሻው ከሚባል ጓደኛው ጋር የመጣው በ1965 ዓ. ም. ነበር። እኔጋ ከመምጣቱ በፊት በትምህርት ቤቱ ሙዚቃ ይጫወት ነበር። ከተዋናይነቱ ባሻገር መለስተኛ ድምጻዊም ነው። እኔጋ ሲመጣ ልጅ ቢሆንም እንደልጅነቱ ሳይሆን ሁሉም ነገር ላይ ይሳተፍ ነበር። በዝማሬና በአጫጭር ድራማ ውስጥም ይገባል። ከእድሜው በላይ የሚያስብ ነበር። ከዛ እሱ፣ ስዩም ተፈራና ሱራፌል ጋሻው ወደ ማዘጋጃ ቤት ሄዱ። በሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን “ቴዎድሮስ” ቴአትር ላይ አጼ ቴዎድሮስን ሆኖ ትልቅ ስራ የሰራ ጀግና አርቲስት ነው። በጣም ግሩም፣ ድንቅና ብርቅ አርቲስት ነበር። የፊልም ኢንዱስትሪው እየተስፋፋ ከመጣ ጀምሮ እስከአሁን ድረስ ትልልቅ ፊልሞች ሰርቷል። በጣም በቅርቡ ደግሞ ከኔ ጋር “መለከት” በተባለ የቴሌቭዥን ድራማ ላይ ይሰራ ነበር። ፍቃዱ በገሀዱ አለም ውስጥ ሰውን አክባሪና ታማኝ ነበር። ለጥበቡ የቆመ ሰው ነበር። ነገር ግን በኩላሊት ህመም ምክንያት ትልቅ አደጋ ደረሰበት። ለህልፈት በቃ። እናም ሁላችንም ሀዘን ተሰምቶናል።
ቴአትር ሲሰራ እውነታን ይዞ፣ እውነታውን አስመስሎ ነው። መስሎ ሳይሆን ሆኖ ነው የሚጫወተው። በተለይ የማደንቀው ቴዎድሮስን ሆኖ ሲጫወት ነው።
አጼ ቴዎድሮስን ሆኖ ሲጫወት ሰውነቱ ሁሉ ይለወጣል። በቃ ፍጹም ቴዎድሮስን ነው የምናገኘው። ቴዎድሮስ በጣም መወደድና አድናቆት ያተረፈበት ስራ ነው። እኔም በጣም የማከብረው የማደንቀው በዚሁ ስራ ነው።
ፍቄ ሩህሩህ፣ ልበ ግልጽ ነው። የታመመ የሚጠይቅ፣ እከሌ ሞተ ሲባል ፈጥኖ የሚደርስም ሰው ነው።
ፍቄ ቁጭ ብለው ሲያዋሩት ‘የገበታ አርቲስት ነው’። የሚያመጣቸው ጨዋታዎች ያስፈነድቃሉ። አኩርፎ የመቀመጥ ባህሪ ያለው አይደለም።
ሌላውና ከፍቃዱ ተጠቃሽ ስራዎች አንዱ የሆነው “ጉዲፈቻ” ፊልም ደራሲ ቴዎድሮስ ተሾመም ”አባት ነው። አማካሪ ነው። ጓደኛ ነው።” ሲል በወቅቱ ሀዘኑን መግለፁም እዚህ ሊጠቀስ የሚገባው ነው።
ከመንግሥት ወገንስ?
የአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ከፍተኛ የጥናት ባለሙያ መምህር መክብብ ገብረማርያም በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ገልፀውት እንደነበረው፤ አርቲስት ፈቃዱ ተክለማርያም በኢትዮጵያ የቴአትር እና ኪነጥበብ ስራዎች ላይ የጎላ አሻራ አሳርፏል። ለሌሎቸ ሙያተኞችም አርዓያ በመሆን በስራው አንቱታን ያተረፈ ተዋናይ ነው።
አንጋፋው አርቲስት ፍቃዱ ባደረበት የኩላሊት ህመም ምክንያት የህክምና እና የፀበል ርዳታ ሲደረግለት ቆይቶ ሐምሌ 24 ቀን 2010 ዓ.ም አመሻሽ ላይ በ62 አመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
አርቲስት ፍቃዱ ለበርካታ ዓመታት በነገሰበት የብሄራዊ ትያትር መድረክም የሙያ ባልደረቦቹ፣ ቤተሰቦቹ፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና አድናቂዎቹ በተገኙበት ከ5 ሰዓት ጀምሮ ለአርቲስቱ አስከሬን የአሸኛኘት መርሃ ግብር ተደርጎለት የነበረ ሲሆን፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት ባለስልጣናት፣ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አድናቂቆቹ እና የጥበብ ሰዎች በተገኙበት ሀምሌ 26 ቀን 2010 ዓ.ም በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ቀብሩ ተፈፅሟል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 25 /2014