የ2014 ዓም የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ ቻምፒዮኑ ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ኢትዮጵያን ወክሎ እንደሚሳተፍ ይታወቃል። ፈረሰኞቹ በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎችን በአዲስ ዘመን መለወጫ እለት መስከረም 1/2015 ዓ.ም ከሱዳኑ አል-ሂላል ጋር ያደርጋሉ።
ለዚህም ከጨዋታው በፊት የተለያዩ የአቋም መፈተሻና የወዳጅነት ጨዋታዎችን ለማድረግ በያዙት እቅድ መሰረት ትናንት ሁለተኛውን የወዳጅነት ጨዋታ ከሱዳኑ አል ሜሪክ ኤስ.ሲ ክለብ ጋር በቢሾፍቱ ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚ አድርገዋል። ከእረፍት በፊት በተቆጠሩ ሦስት ግቦች ተጋጣሚያቸውን መርታት የቻሉት ፈረሰኞቹ በጨዋታው አንድ ግብ ብቻ አስተናግደዋል፡፡
አማኑኤል ተርፋ በ24ኛው ደቂቃ፣ ቢኒያም በላይ ደግሞ 41ኛ ደቂቃዎች ላይ በጨዋታ ባስቆጠራቸው ግቦች መምራት የቻሉት ፈረሰኞቹ 42ኛ ደቂቃ ላይ ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ ባስቆጠራ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ መሪነቱን ይዘው የመጀመሪያውን የጨዋታ ክፍለጊዜ አጠናቀዋል፡ ፡ በሁለተኛው አጋማሽ ፈረሰኞቹ ሌሎች ግቦችን ያክላሉ ተብሎ ቢገመትም የኤል ሜሬክን መረብ ዳግም መድረፍ አልቻሉም፡፡ ተጋጣሚያቸው በአንፃሩ ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ በማድረግ 55ኛ ደቂቃ አካባቢ በዜሮ ከመሸነፍ ያዳነችውን ግብ ማስቆጠር ችሎ ጨዋታው 3ለ1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡
ፈረሰኞቹን በምክትል አሰልጣኝነት እየመሩ ለቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ ቻምፒዮንነት ክብር ያበቁት አሠልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ከቀናት በፊት የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ሆነው መሾማቸው የሚታወስ ሲሆን ለቻምፒዮንስ ሊጉ ዝግጅታቸውን በቢሾፍቱ ይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚ እያደረጉ ይገኛሉ። ፈረሰኞቹ ከሳምንት በፊትም የመጀመሪያ የአቋም መፈተሻ ጨዋታውን ወደ ታንዛኒያ በማምራት ከሲምባ ጋር አከናውነው የሁለት ለዜሮ ሽንፈት ገጥሟቸዋል።
በቻን አፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ የመጨረሻው የማጣሪያ ምእራፍ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) ከሩዋንዳ አቻቸው ጋር ለሚያደርጉት ወሳኝ ጨዋታ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ስብስብ ውስጥ ተካተው ዝግጅታቸውን በታንዛኒያ እያደረጉ ከሚገኙ የፈረሰኞቹ ተጫዋቾች መካከል አብዛኞቹ በትናንቱ የወዳጅነት ጨዋታ መሰለፋቸው ታውቋል። ከነዚህም መካከል ጋቶች ፓኖም ፣ ቸርነት ጉግሳ፣ ሄኖክ አዱኛ፣ ሱሌይማን ሀሚድ፣ ረመዳን የሱፍ እና ምኞት ደበበ ከታንዛኒያ ተመልሰው ፈረሰኞቹን ተቀላቅለዋል። ከውል ማደስ ጋር ተያይዞ እስካሁን በፈረሰኞቹ መለያ መቆየቱ ያልተረጋገጠው የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቹ አማኑኤል ገብረሚካኤል ግን ከታንዛኒያ መጥቶ ፈረሰኞቹን እንዳልተቀላቀለ ዘገባዎች አመልክተዋል።
የሱዳኑ ክለብ ኤል-ሜሪክ በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ከጅቡቲው አርታ ሶላር ጋር የሚያደርገውን የሜዳው ላይ ጨዋታ በባህርዳር ስቴድየም ለማድረግ መወሰኑን ተከትሎ ነው ትናንት ከፈረሰኞቹ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ የቻለው። አልሜሪክ ለአቋም መፈተሻ ጨዋታው ከቀናት በፊት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ዝግጅት አድርጓል። ሌላኛው የሱዳኑ ክለብ አል-ሂላል ኡንዱርማን ላይ አል-ሂላል ስታዲየምን ለመጠቀም ካፍ ፍቃድ ቢሰጠውም የከተማው ተቀናቃኝ ክለብ ሜሪክ ግን እንዲጠቀምበት አለመፈለጉን ተከትሎ ሜሪክ የሜዳ ላይ ጨዋታውን ከሀገር ውጪ ለማከናወን ግዴታ ውስጥ ገብቷል። ይህንን ተከትሎም ክለቡ የባህር ዳር ስታዲየምን ለመጠቀም እንደወሰነና ለካፍ እንዳሳወቀ ይታወሳል። ሜሪክ በባህር ዳር ስታዲየም ጨዋታውን የሚያደርገው መስከረም 7/2015ዓ.ም ነው።
የቀጣዩ ዓመት የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ካፕ ውድድር የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ከቀናት በኋላ መደረግ ይጀምራሉ። የሀገራችን ተወካዮች ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ፋሲል ከነማም ለውድድሮቹ እየተሰናዱ የሚገኙ ሲሆን የሜዳ ላይ ጨዋታቸውንም በባህር ዳር ስታዲየም እንደሚያከናውኑ ይፋ መሆኑ ይታወሳል።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በ2022/23 የውድድር ዘመን የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ እና ካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ፍቃድ ያገኙ ስታዲየሞችን ዝርዝር ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቀደም ሲል አሳውቋል።
ካፍ ፍቃድ ያገኙ የ39 ሀገራት ስታዲየሞችን በላከበት ዝርዝር ላይ ከኢትዮጵያ የባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታዲየም ፍቃድ ማግኘቱ የተገለፀ ሲሆን በዚህም መሰረት በቻምፒየንስ ሊጉ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሱዳኑ አል ሂላል፣ በኮንፌዴሬሽን ዋንጫው ፋሲል ከነማ ከቡሩንዲው ቡማሙሩ ክለብ ጋር የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ባህር ዳር ስታዲየም ላይ የሚከናወኑ ይሆናል።
ካፍ ከላከው ዝርዝር ጋር በላከው መግለጫ ይህ ፈቃድ የሚያገለግለው ለቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች መሆኑን በማውሳት ለምድብ ጨዋታዎች ግን በድጋሚ ግምገማ እንደሚያደርግ ታውቋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 25 /2014