
አዲስ አበባ፡- የጠላትን ሴራ በአስተማማኝ ደረጃ በመመከት ለሕዝቦች ሰላምና አንድነት በትብብር መስራት እንደሚገባ የደቡብ እና የኦሮሚያ ክልሎች ከፍተኛ የሥራ አመራሮች ገለጹ።
የደቡብ እና የኦሮሚያ ክልሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በወቅታዊ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ በሃዋሳ ከተማ ሲመክሩ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ፤ በደቡብ እና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በትብብር መስራት የሚያስችል መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።
በሁለቱም ክልል የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ደህንነት ማስጠበቅ የመንግሥት አብይ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይ የጠላትን እኩይ ተግባር በማክሸፍ ሰላም ማስፈን ይገባል ነው ያሉት።
በደቡብ እና በኦሮሚያ ክልሎች የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን በማጎልበት የቀጠናውን ሰላም በአስተማማኝ ደረጃ ለማስፈን እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው፤ የውስጥ እና የውጭ ጠላቶች የከፈቱትን ዘርፈ ብዙ ወረራ በመመከት የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የሸኔ እንቅስቃሴ ባለባቸው አካባቢዎች መጠነ ሰፊ ዘመቻ በማድረግ የሽብር ቡድኑን የማጽዳት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሕዝቡን ሰላም ለማስፈን የተጀመረው ጥረት ስኬታማ ነው ብለዋል።
በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ዘላቂ ሰላም በማስፈን የተጀመረውን ልማት ማስቀጠል ይገባልም ነው ያሉት።
አሸባሪው ሕወሓት የሚጋልበው ሸኔ እና የውጭ ጠላቶቻችን ሀገሪቱን የትርምስ ቀጠና ለማድረግ እያካሔዱት ያለውን ሴራ በብቃት የመመከት ስራ እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።
በውይይት መድረኩ ከደቡብ እና ከኦሮሚያ ክልሎች የተውጣጡ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች መገኘታቸውን ከደቡብ ክልል ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 25 ቀን 2014 ዓም