ለኢንዱስትሪው ዘርፍም ሆነ ለአጠቃላይ አገራዊ ምጣኔ ሀብቱ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥሩ አምራቾች በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ወደሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየገቡ በማምረት ስራ ላይ መሰማራታቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዚህም ምርቶቹን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ እያስገኙም ናቸው፡፡
‹‹ኤልአውቶ ኢንጂነሪንግ›› (Elauto Engineering) የተሰኘ ኩባንያም ሰሞኑን እነዚህን አምራች ኢንዱስትሪዎች ተቀላቅሏል፡፡ ይህ ፋብሪካ ስራውን የጀመረው የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና እንዲሆን በተደረገው የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ነው፡፡
የኩባንያው መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፡- ድርጅቱ ሰሞኑን ከተመረቀው የድሬዳዋው ፋብሪካ በተጨማሪ ዱከም፣ ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን (Eastern Industry Zone) ውስጥም የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ አለው። ይህኛው ፋብሪካ መኪናዎችን መገጣጠም ከጀመረ ሁለት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ እስካሁን ድረስም አንድ ሺ መኪኖችን መገጣጠም ችሏል፡፡ ሰሞኑን የተመረቀውና በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና (Dire Dawa Free Trade Zone) ውስጥ አሁን ስራ የጀመረው የኩባንያው ፋብሪካም ለቤትና ለመስሪያ ቤቶች አገልግሎት የሚውሉ አነስተኛ ተሽከርካሪዎችን የሚገጣጥም ነው፡፡
የ‹‹ኤልአውቶ ኢንጂነሪንግ›› ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ በቀለ አበበ እንደሚናገሩት፣ ኩባንያው የላዳ ታክሲዎችን የመቀየር ፕሮጀክትን ጨምሮ አነስተኛ ተሽከርካሪዎችን የመገጣጠም ተግባራትን ያከናውናል፡፡ የሚገጣጠሙት ተሽከርካሪዎች የከተሞችን ገፅታ በበጎ መልኩ በመቀየርና በስራ እድል ፈጠራ ረገድ ፋይዳ ያላቸው በመሆኑ መንግሥት ለፋብሪካው የሚያስፈልጉ የመኪና አካላት ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ፈቅዷል፡፡
ድሬዳዋ ላይ ስራ የጀመረው የ‹‹ኤልአውቶ ኢንጂነሪንግ›› ፋብሪካ በከፊል የተበተኑ መኪኖችን የሚገጣጥም ሲሆን፣ አጠቃላይ ኢንቨስትመንቱ 700 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ የፋብሪካው የመጀመሪያ ምዕራፍ፣ የግብዓቶቹ (የሚገጣጥማቸውን ተሽከርካሪዎች)፣ የሥራ ማስኬጃ እና አጠቃላይ የሰው ኃይል ወጪን ጨምሮ፣ የ400 ሚሊዮን ብር ኢንቨስትመንት ነው፡፡
ፋብሪካው በመጀመሪያው ምዕራፍ በአንድ ፈረቃ ለ80 ሰዎች የስራ እድል ይፈጥራል፡፡ በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምርና ሙሉ የሎጂስቲክስ ሰንሰለቱ ተቀናጅቶ ወደ ስራ ሲገባ ደግሞ ለ300 ሰራተኞች ቋሚ የስራ እድል የሚፈጥር ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ፋብሪካው በሚያመርታቸው ተሽከርካሪዎች አማካኝነት ተሽከርካሪዎችን ለሚገዙ ሰዎችና ለአሽከርካሪዎች፣ ለጥገና ባለሙያዎች፣ ለመለዋወጫ እቃዎች አቅራቢዎችና አከፋፋዮች እና ተዛማጅ ባለሙያዎችም ተጨማሪ የስራ እድሎችን ይፈጥራሉ፡፡
ፋብሪካው አሁን ባለው አቅም በቀን፣ በሦስት ፈረቃዎች 35 ተሽከርካሪዎችን የመግጠም አቅም አለው። በመጀመሪያው ምዕራፍ፣ ከአራት እስከ አምስት ወራት ባሉ ጊዜያት ሦስት ሺ መኪናዎችን ለማምረት እቅድ አለው። በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ደግሞ ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ እንዲያመርት ይደረጋል ተብሏል፡፡ በዚህም በከፊል የተበተኑ ብቻ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ የተበተኑ ተሽከርካሪዎችን ለማምረት የሚያስችለው የአምራችነት ቁመና ላይ ለማድረስ እንደታቀደም ተገልጿል፡፡
ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ኩባንያው አሁን ስራ ከጀመረው ፋብሪካ ጋር በጥምረት የሚከናወን የማስፋፊያ ግንባታ አለው፡፡ በከፊል የተበተኑ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ የተበተኑ መኪኖችን ለመገጣጠም እንዲችል የብየዳ፣ የቀለምና የዝገት መከላከያ ቅብ ስራዎች የሚከናወኑባቸው ሶስት የመስሪያ ስፍራዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ስለሆነም አሁን ስራ ከጀመረው ፋብሪካ የሚወጣውን ምርት የተሟላ አድርጎ ለማጠናቀቅ የእነዚህ ስራዎች መሟላት አስፈላጊ በመሆኑ ስራ ከጀመረው ፋብሪካ ጎን ለጎን፤ በሙሉ አቅሙ ለማምረት የሚያስችሉትን ተጨማሪ ተግባራትን ያከናውናል፡፡
ፋብሪካው እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ጊዜ ውስጥ የእሴት ሰንሰለቱ ላይ ብዙ ጭማሪ የሚኖራቸውን በኢትዮጵያ የተመረቱ (Made in Ethiopia) ተሽከርካሪዎችን ለማምረት አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝ ነው አቶ በቀለ የሚናገሩት፡፡
የ‹‹ኤልአውቶ ኢንጂነሪንግ›› መኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ ስራውን የሚያከናውነው ባለፈው ሳምንት በተመረቀው የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ውስጥ ነው። ነፃ የንግድ ቀጠናን ማቋቋም የንግድ ዘርፍ ችግሮችን ለመቀነስና የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግ አወንታዊ አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡ ነፃ የንግድ ቀጠናዎች የምርትና የሎጂስቲክስ ተግባራት ተቀናጅተው በቀልጣፋ አሰራር የሚከወኑባቸው ስፍራዎች በመሆናቸው ለኢንቨስትመንት ማደግ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራሉ፡፡
ነፃ የንግድ ቀጠና ኢንቨስትመንትን የሚጨምር፣ አዳዲስ የሥራ ዕድሎች ለመፍጠር የሚያግዝ፣ ቢሮክራሲያዊ የአሰራር ውጣ ውረዶችን የሚቀንስ አማራጭ ነው፡፡ ይህ ቀጠና የንግድ እንቅፋቶች የሌሉበት እንዲሁም ቀረጥና ግብር ያነሰበት የንግድና ኢንቨስትመንት ማሳለጫ አካባቢ እንደሆነም ይገለፃል፡፡ በነፃ የንግድ ቀጠናዎች ውስጥ የሚተገበሩ ህጋዊ አሰራሮች በሌሎቹ አካባቢዎች ከሚተገበሩት ጋር ሲነፃፀሩ የላሉና አንፃራዊ ነፃነትን የሚያጎናጽፉ ናቸው፡፡
የ‹‹ኤልአውቶ ኢንጂነሪንግ›› መኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ ከላይ የተጠቀሱትን ጥቅሞች ያስገኛል ተብሎ ተስፋ በተጣለበት የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ የነፃ ቀጠናው ትሩፋቶች ተጠቃሚ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ፋብሪካው ነፃ የንግድ ቀጠናው ውስጥ መገኘቱ ነፃ የንግድ ቀጠናው የሚስገኛቸው እድሎችና መልካም አጋጣሚዎች ሁሉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የሚናገሩት አቶ በቀለ፣ ‹‹ነፃ የንግድ ቀጠናው ውስጥ እንደሚገኝ አንድ አምራች ኢንዱስትሪ ምርቶቻችንን ለማሳደግ ያስችለናል፡፡
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ነጻ የንግድ ቀጠናው በከፊል የተበተኑ መኪናዎችን ከማምረት ሙሉ በሙሉ የተበተኑ ተሽከርካሪዎችን ወደማምረት ለመሸጋገር ያግዛል፡፡ በዚህም የምናመርታቸው ተሽከርካሪዎች ተኪ ምርቶች በመሆናቸው የውጭ ምንዛሬን ለማዳን እገዛ ያደርጋል፡፡ የሎጂስቲክስ ወጪያቸው የቀነሰ ተሽከርካሪዎችን ለአገር ውስጥ ገበያ ለማቅረብም ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡ በብዙ የአፍሪካ አገራት በርካታ ተሽከርካሪዎችን የሚያመርቱ ብዙ ፋብሪካዎች ስለሌሉ ምርቶችን ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ ለመላክ እድል ያስገኛል፤ ይህም ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል፡፡ ከፋብሪካው ምርቶች ከፊሉን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ከመንግሥት ጋር ስምምነት ተፈርሟል፡፡
የኢንቨስትመንት ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ቅንጅትና ትብብር እንደሚያስፈልግ እሙን ነው፡፡ በዚህ ረገድ ‹‹ኤልአውቶ ኢንጂነሪንግ ፋብሪካ›› የድሬዳዋ ፋብሪካው እውን እንዲሆን እገዛ ያደረጉለት ተቋማት እንዳሉ የፋብሪካው ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ በቀለ ይገልፃሉ፡፡ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከሁለት ዓመታት በፊት፣ ኩባንያው ድሬዳዋ ላይ ስራውን ለመጀመር ሲዘጋጅ፣ ጀምሮ ብዙ ድጋፎችን እንዳደረገላቸው የሚያስረዱት አቶ በቀለ፤ ‹‹ተሽከርካሪዎችን ሙሉ በሙሉ ለማምረት ለተሽከርካሪው አካላት መስሪያ የሚሆኑ ግብዓቶችን ለማሟላት ለምናከናውናቸው ስራዎች እገዛ እያደረገልን ነው›› ብለዋል፡፡ የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀርም በፋብሪካው ምርቃ ላይ የከተማ አስተዳደሩ በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሀብቶች ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ‹‹የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የተከራየነው የማምረቻ ሼድ በኃይል አቅርቦትም ሆነ በሌሎች ግብዓቶች የተሟላ እንዲሆን ከማድረግ አንፃር፣ ለፓርኩ የሚከፈለውን ኪራይ ለጊዜው በብር እንድንከፍልና ምርቶችን ለውጭ ገበያ አቅርበን የውጭ ምንዛሬ በምናገኝበት ጊዜ ኪራዩን በውጭ ምንዛሬ የምንከፍልበትን እድል በማመቻቸት ከፍተኛ ድጋፍ አድርጎልናል›› በማለት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንም ከፍተኛ እገዛ እንዳደረገላቸው ይገልጻሉ፡፡
የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩትም የምርት ደረጃዎችን በማውጣትና ፋብሪካው በደረጃው መሰረት እንዲተከል እገዛ እንዳደረጉላቸውና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንም ለኩባንያው አስፈላጊ ድጋፎችን እንዳደረገ ተናግረዋል፡፡
የ‹‹ኤልአውቶ ኢንጂነሪንግ›› ኩባንያ የቀጣይ ጊዜ ዋነኛ እቅድና ትኩረት ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ የተመረቱ (Made in Ethiopia) ተሽከርካሪዎችን ለገበያ ማቅረብ እንደሚሆን አቶ በቀለ ይጠቁማሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ የተመረቱ ተሽከርካሪዎችን አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ የእሴት ጭማሪ ሰንሰለቱ የራሱ የሆነ አሰራር አለው፡፡ በኢትዮጵያ የተመረተ የሚል ማረጋገጫ ለማግኘት የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ደረጃዎችን ማሟላት ያስፈልጋል። ‹‹ኤልአውቶ ኢንጂነሪንግ›› ኩባንያም በኢትዮጵያ የተመረቱ ተሽከርካሪዎችን አምርቶ ለገበያ የማቅረብ እቅዱን ለማሳካት እሴት ጭማሪው (ተፈላጊው ደረጃ) ምን ያህል መሆን እንዳለበት ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ ይሆናል፡፡
በኢንቨስትመንት ዘርፉ የሚሰማሩ ባለሀብቶች የሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች ብዙ እንደሆኑ ተደጋግሞ ይገለፃል፡፡ ከእነዚህም መካከል በግብዓት (ጥሬ ዕቃ)፣ በሰው ኃይል፣ በቦታ፣ በኃይል፣ በፋይናንስና በውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ረገድ ያሉ ችግሮች በተደጋጋሚ ይጠቀሳሉ፡፡
‹‹ኤልአውቶ ኢንጂነሪንግ›› በስራው ሂደት ስላጋጠሙት ችግሮች አቶ በቀለ ሲያስረዱ፣ ‹‹በእኛ አገር በተለይ ለምርታቸው የውጭ ግብዓቶችን የሚጠቀሙ ፋብሪካዎች የሚያጋጥማቸው ዋነኛው ችግር የውጭ ምንዛሬ እጥረት ነው፡፡ በእርግጥ እኛን በተመለከተ ታክሲዎችን ለመቀየር በተያዘው እቅድ መሰረት መንግሥት ለስራው የውጭ ምንዛሬ ስለፈቀደ ለጥቂት ጊዜ ያህል እፎይታ ይሰጠናል ብለን እናምናለን፡፡ በሌላ በኩል ኩባንያው ምርቶቹን ለውጭ ገበያዎችም ስለሚያቀርብ የማሽንና የጥሬ እቃ ፍላጎቶቹን ከምርቶቹ የውጭ ገበያ ሽያጭ በሚያገኘው ገቢ ለመሸፈን እየሰራ ነው›› ይላሉ፡፡
ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ መፍ ትሄ ያገኘ ቢሆንም፣ በሕግ ማዕቀፎች አለመስተካከል ምክንያት የታክሲ ቅያሬ ስራውን ለማሳለጥ የሚስችለው የቀረጥ ነፃ ውሳኔ በመዘግየቱ ኩባንያው ለሰባት ወራት ያህል መኪና ሳይገጣጥም መቆየቱና ለከፍተኛ የማከማቻ ኪራይ ወጪ መዳረጉ ሌላው ኩባንያውን ያጋጠመው ችግር እንደነበርም አቶ በቀለ ጠቅሰዋል። ስለሆነም እንዲህ ዓይነት የሕግ ማሻሻያ ተግባራት አምራቹን፣ የገዢውን እንዲሁም የአጠቃላይ ኢኮኖሚውን ታሳቢ ሊያደርጉ እንደሚገባም አቶ በቀለ ይናገራሉ፡፡ ‹‹እቃዎች ወደብ ላይ ተከማችተው እንዲቆዩ በመደረጋቸው በአገራዊ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ ኢንዱስትሪውን በሚያግዙ የሕግ ማዕቀፎች ላይ ፈጣን ውሳኔ ማካሄድ ያስፈልጋል። ያን ማድረግ ከተቻለ በአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎች ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉ ብቁና ትኩስ ኃይል ያላቸው ወጣቶች ስላሉ በስፋት ለማምረትና ለአገራዊ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ በጎ አስተዋፅኦ ማበርከት ይቻላል›› ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ እምቅ አቅም ያላት አገር ናት፡፡ አገሪቱ የአምራች ኃይል አቅም፣ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ፣ ሕጋዊ ማዕቀፎችና ለዘርፉ እድገት አወንታዊ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ ሌሎች መልካም አጋጣሚዎችና አስቻይ ሁኔታዎች አሏት፡፡ በኢንዱስትሪ ያላትን አቅም በመጠቀምና ከዚሁ ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የምታደርገውን መዋቅራዊ ሽግግር እውን ለማድረግ ባለፉት ዓመታት በርካታ ተግባራትን ብታከናውንም በዓይነትም ሆነ በብዛት በርካታ የዘርፉ ችግሮች፤ ከዘርፉ የሚፈለገውን ያህል ውጤት ማግኘት እንዳይቻል ስለማድረጋቸው በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል፡፡
የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና የዘርፉን ችግሮች ለማቃለል ከተተገበሩ የመፍትሄ አማራጮች መካከል አንዱ ተደርጎ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ ነፃ የንግድ ቀጠናው አዳዲስና ሰፊ የሆኑ የሥራ እድሎችን ለመፍጠር፣ ተኪ ምርቶችን ለማምረት፣ የእውቀት ሽግግርን ለማሳደግ እንዲሁም ለአገር ውስጥ የቀረቡ ምርቶችን ለማከማቸትና የሎጀስቲክስ ወጪን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡ ይህም አገራዊ የሎጂስቲክስ ተወዳዳሪነትን ትርጉም ባለው መልኩ ሊለውጥ የሚችል በመሆኑ የአገሪቱን የገቢና ወጪ ንግድ ስርዓት ለማቀላጠፍ ያግዛል፡፡ አሰራሩ የሚያስገኛቸው ጥቅሞችና የሚፈጥራቸው እድሎች የምርት ወጪን በመቀነስ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋትም ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ጥቅሞች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለጥቅል አገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት ዓይነተኛ ፋይዳ አላቸው፡፡
በነፃ የንግድ ቀጠናዎች ውስጥ የሚተገበሩ ህጋዊ አሰራሮች ቀለል ያሉና ቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረዶችን የሚቀንሱ በመሆናቸው ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ለመሰማራት የሚያደርጉትን ጥረት በአንፃራዊነት ቀላል ያደርጉላቸዋል፡፡ በነፃ የንግድ ቀጠናው ውስጥ ገብተው የሚሠሩ ባለሀብቶች፣ አስመጪና ላኪዎችም ሆኑ ድርጅቶች የልዩ ልዩ ማበረታቻዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ይህ ደግሞ የአገር ውስጥ እና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡፡
ስለሆነም ሰሞኑን በቀጠናው ውስጥ ስራውን የጀመረውን ‹‹ኤልአውቶ ኢንጂነሪንግ››ን ጨምሮ ሌሎች አምራቾችም ነፃ የንግድ ቀጠናው የፈጠራቸውን እድሎች ተጠቅሞ፤ የወጪና ገቢ ንግዱን በማቀላጠፍና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ውጤታማነት በማሳደግና አገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገቱ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲያስመዘግብ ማድረግ ይገባል፡፡
በአንተነህ ቸሬ