ጥበብ ትክክለኛ እና እውነተኛ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ የምንጠቀምበት ኃይል ነው። በተጨማሪም ለማንኛውም ሁኔታ ትርጉም ያለው መፍትሄ ለመምረጥ የሚያስችል አቅም የሚፈጥርልን ነው። ጥበብ በሕይወታችን ዘመን ሁሉ በሰው ዘንድ አስደሳች የሆነ አስተሳሰብን፣ ንግግርን እና ድርጊትን የሚያቀዳጅ ነው። ከዚያም ሻገር ሲል ጥበብ አሸናፊ የሆነ ሕይወትን ለመምራት የሚያስችል ነው። ምክንቱም በጥበብ ያልተመራ ሕይወት ምንግዜም ውድቀትን እንጂ ስኬትን ሊያመጣ አይችልም። እናም ማስተዋላችን ከጥበብ ጋር የተቆራኘ ከሆነ ውጤታማ እንሆናለን።
ማስተዋል አንድን ነገር የምንገነዘብበት፣ ከባለፈው ስህተቶቻችን በመነሳት የወደፊቱን የምናስተካክልበት መሳሪያ ነው። ያለ ማስተዋል የሚራመድ ሰው በሕይወት ጎዳና ላይ ከሚያጋጥመው ነገሮች በመነሳት በግራ መጋባት ሊሞላ÷ ቶሎ ተስፋ ሊቆርጥ ወይንም በቀላሉ ወጥመድ ውስጥ ሊገባ ይችላል። በመሆኑም ‹‹ጥበብን ባንፈልግ ችግር እና መከራ በቤታችን ላይ እንጋብዛለን። ጥበብን ብንሻት ግን ህይወትን እና ሞገስን ያገኛል {መጽሐፈ ምሳሌ 8፡35-36›› እንዲል መጸሐፍ ቅዱስ ይህንን ተገን አድርገን መንቀሳቀስ ይኖርብናል። ይህንን ያነሳነው ያለምክንያት አይደለም። ጥበብን ከብልሃቱና ከድርጊቱ ጋር አስተባብረው የዘለቁና የተጠቀሙ አንዲት እንስትን ልናስተወውቃችሁ ስለፈለግን ነው።
እንግዳችን አርቲስት እጅጋየሁ ተስፋዬ ይባላሉ። በሥዕልም ሆነ በሐውልቱ ሥራ አንቱታን ያተረፉ ናቸው። በእጃቸው ፍሬ የሁሉንም ቤት ያንኳኩና ያስተማሩም ናቸው። አገራቸውንም በማስተዋወቁ ረገድ ትልቅ አሻራ ያስቀመጡ እንደሆኑ ታሪካቸው ይመሰክራል። በሥዕሎቻቸውም ሆነ በሐውልት ሥራቸው ህይወትን ሲኩሏት ኖረዋል።
ስዕል የእርሳቸው የልጅነት ስጦታቸው ብቻ አልነበረም። ለአገራቸው የሚያግዙበትና ችግርን እንድታልፍበት ያደረጉበት መፍቻቸው ነው። ተማሪ ሳሉ በ1977 በድርቅ ምክንያት የተጎዱ ወገኖችን ለማገዝ በሚደረግ ዘመቻ ላይ አሳዛኝ ሀውልት በመስራት የእርዳታ መሰብሰቢያ አድርገውት ብዙ ገቢ ያስገኙ እንደነበሩም በወጋችን መካከል አጫውተውናል። ከዚያም በኋላ የተለያዩ መረጃዎችን ለማስተላለፍ፤ ፖለቲካውን ለማሳለጥና ልጆችን ለማስተማርም ተጠቀመውበታል።
በነጻነት የተገነባው ልጅነት
ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ እቴጌ መነን አካባቢ በተለምዶ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሆስፒታል የሚባል ቦታ ነው። ልጅነታቸው የነጻነት መድረካቸው ስለነበረም ወንዳወንድ ሆነው ነው እድገታቸውን ያጣጣሙት። ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ሳይቀሩ ከወንዶች እኩል ያደርጋሉ። በተለይ ክብደት ማንሳት ላይ ማንም አያህላቸውም። የእግር ኳሱም ላይ እንዲሁ ጥሩ ተጨዋች ነበሩ። በዚህ ባህሪያቸው ብዙዎች ይደነቁ ነበር። ምክንያቱም ለሁሉም ታዣዢና ተላላኪ ናቸው። የተባሉትን በፍጥነት ያደርጋሉም።
እንግዳችን እንደሴቶችም የቤቱ ሥራ ላይ በጣም ጎበዝ ናቸው። በተለይ የመጀመሪያ ልጅ በመሆናቸው የማይሰሩት ሥራ አልነበረም። ሙያ ያላት ግን ደግሞ ጨዋታ የምትወድ ሴት ሆነው ነው ያደጉት። ለዚህ ደግሞ በሁለት ቤት ውስጥ ማደጋቸው ትልቅ አስተዋዕጾ አበርክቷል። ማለትም ከእናትና አባታቸው ቤት ባለፈ አቶ አበበ ከበደና ወይዘሮ ጥርወርቅ አስፋው በሚባሉ አሳዳጊያቸው ቤትም ልጅነታቸውን አሳልፈዋል። እንደውም ሰፊው የልጅነት ጊዜያቸው ያለፈው የደጅአዝማች አስፋው ቤተሰብን በመቀላቀል ነው።
በወቅቱ ባላባት እየተባሉ በሚጠሩ ሰው ቤት በማደጋቸውም ብዙ ነገራቸው በቅንጦት የተሞላ እንዲሆንላቸው አድርጓል። ነጻነት ተሰምቷቸው የፈለጉትን እያደረጉ እንዲጓዙም ፈቅዶላቸዋል። በተለይም በሚሰሩት ሥራ እርግጠኛ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ይህ መሆኑን ይናገራሉ። አልችለውም የሚል ስሜት እንዳይሰማቸውም ሆነው አድገዋል። በዚህም በመሞከር ብቻ ያምናሉ እንጂ መውደቃቸውን አይቆጥሩትም። ሌላው በዚህ ቤት ማደጋቸው የጠቀማቸው ነገር አገር ወዳድ እንዲሆኑና ታሪካቸውን እንዲያውቁ መደረጋቸው ነው። ሁሌም በአገራቸው እምነትና ተስፋ ያላቸውም ሆነውም አድገዋል። ለጋሽና ነጻ መሆንንም የተማሩበት ቤት ነው። አድማጭና ታሪክ አዋቂም አድርጓቸዋል። በተጨማሪ ጠያቂነትን ያዳበሩበት ቤታቸው እንደሆነም አጫውተውናል።
አሳዳጊያቸው እንደእርሳቸው ብዙ ልጆችን በመውሰድ ተንከባክበው ለወግ ማዕረግ አብቅተዋል። ለእርሳቸው ዛሬ ላይ መድረስም የእነርሱ ሚና ምንም መተኪያ የለውም። ይህ ደግሞ አርአያነታቸውን ተከትለው እንዲሰሩ መስመር የጠረገላቸው እንደሆነም ያስረዳሉ። በተለይም ሕጻናት ላይ በቻሉት ሁሉ ለመሥራት ያነሳሳቸው ይህ ምስጢራዊ እድገታቸው መሆኑንም ያነሳሉ።
ልጅነታቸውን ከስፖርቱ ጋር በተያዘ ቴሌቪዥን ላይ እስከመቅረብ ያደረሳቸው ነው። ምክንያቱም በአካባቢያቸው የስፖርት አሰልጣኝ የነበረ አቶ ግርማ ቸሩ የሚባል ሰው ነበረ። እናም እርሱ ጋር እየሄዱ ይሰሩ ነበርና በቀረጻው ላይ በስፋት ይታዩ እንደነበር ያስታውሳሉ። ይህ ደግሞ ከሥዕል ሙያቸው ጋር ተዳምሮ ተዋቂነትን እንዲያተርፍላቸው አድርጓቸዋል። ልዩ ፍላጎታቸውና የልጅነት ሕልማቸው የተጣጣመውም ከዚህ አንስቶ እንደነበር ያወሳሉ። ሕልማቸው እውቅ ሰዓሊ መሆን ሲሆን፤ እንዳደረጉትም ያምናሉ።
ቢቆራረጥም ስኬታማ የሆነው ትምህርት
የትምህርት ጅማሮዋቸው ህልማቸውን ሳይረሳ የሄደ ነው። በእያንዳንዱ ቅጽበት ከሥራቸው ጋር በማያያዝ ለዛሬ በቅተውበታል። ገና የመጀመሪያ ትምህርታቸውን በእቴጌ መነን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትቤት ሲማሩ ጀምሮ የሥዕል ዝንባለያቸው እስከ ዩኒቨርስቲ ዘልቋል። መጀመሪያ እስከ ዘጠነኛ ክፍል ተምረው መደበኛውን ትምህርት በማቋረጥ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ወደ ሥዕል ትምህርትቤት አመሩ። በጊዜው ደግሞ 12ኛ ክፍልን ማጠናቀቅን አይጠይቅምና ጊዜ ሳይሰጡ ህልማቸውን እውን ለማድረግ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር ባለው አለፈለገ የስነጥበብ ትምህርትቤት ገቡ።
በወቅቱ ትምህርቱ የሚሰጠው አምስት ዓመት ቢሆንም ድግሪ የሚል ስያሜ አልነበረውም። ዲፕሎማ እየተባለ ነው የሚሰጣቸው። ስለሆነም ሥዕልና የተለያዩ ትምህርቶችን በሦስት ዓመት ውስጥ አጠናቀው በአንድ መስክ ማለትም በሐውልት ሥራ ሁለት ዓመታትን በመከታተል ነበርም የተመረቁት። ምርቃታቸውም በማዕረግ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት ሐውልተኛ በሚል ነው። ለዚህም በትምህርትቤቱ አሻራቸውን ያኖሩበት ሐውልት ምስክር እንደሆነ ያስረዳሉ።
አርቲስት እጅጋየሁ የጀመሩትን ነገር አለማጠናቀቅ መሸነፍ እንደሆነ ያስባሉ። በዚህም ያቋረጡትን ትምህርት በማታው ክፍለጊዜ በተፈሪ መኮንን ትምህርትቤት መከታተል ችለዋል። ማለትም ከዘጠነኛ ክፍል ያቋረጡትን ትምህርት እስከ 12ኛ ክፍል ተምረው በከፍተኛ ውጤት አጠናቀዋል። ማታ የተማሩበት ምክንያት ቀን ሥራዎችን ስለሚሰሩና የስዕል ትምህርትቤት ስለሚማሩ ነው። እናም ሁለቱን አጣጥመው ተገቢውን እውቀት ጨብጠው ትምህርቱን ማጠናቀቅ ችለዋል።
ቀጣዩ የትምህርት ቆይታቸው የሚወስደን ደግሞ ጣሊያን አገር ሲሆን፤ ብዙ ልምድ የቀሰሙበት ነበር። በተለይም የደረሳቸው ዩኒቨርሲቲ ብዙዎች የሚመኙት አካዳሚ ኦፍ ፋይን አርት እስኩል ኦፍ ካራራ የተባለ ዩኒቨርስቲ መሆኑና የሐውልት ትምህርትን ለመማር እንደ ማርብልና እምነበረድን እንዲሁም ነሐስን በቀላሉ ማግኘት የሚችሉበት መሆኑ በሙያቸው የላቁና የሚፈለጉ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። የመጀመሪያ ድግሪያቸውን በተሻለ ውጤት ያጠናቀቁትም ለዚህ ነው። በእርግጥ ከዚህ በፊትም ቢሆን የትምህርት እድል አግኝተው ነበር። ራሺያ ላይ። ሆኖም አገሪቱ ላይ ያለው የሶሻሊዝም የፖለቲካ አመለካከት ሲያዩት ምንም እንኳን በዚያ ሄደውም አርት ስኩል ያስተማሯቸውን መምህራን ዳግም የሚያገኙባት ቦታ ቢሆንም ፖለቲካው ብዙም ምቾት ስላልሰጣቸው ሊመርጡት አልፈለጉም። በዚህም ዓመታትን ያለትምህርት ቆዩ። የጣሊያኑ ውድድር ሲመጣም ተወዳድረው ገቡ።
ባለታሪካችን ወደ እንግሊዝ አገር በማቅናትም ሌላ ትምህርት ተምረዋል። ይህም በኦፕን ዩኒቨርስቲ የተከታተሉት የሳይኮሎጂ ትምህርት ሲሆን፤ በሁለተኛ ድግሪ የተመረቁበት ነው። ይህንን የተማሩበት ምክንያትን ሲያነሱም ከሕጻናት ጋር ያላቸውን ቅርበት ለማጠንከር አስበው እንደነበር ያወሳሉ። ፍላጎታቸው በእውቀት የተገነባ መምህር መሆን ነበርና አሳክተውታል። የማዕረግ ተመራቂም ነበሩ።
ሥዕልና ገጸ በረከቱ
መምህሮቻቸው ሳይቀሩ ማስተማሪያ ሲቸግራቸው እርሳቸውን መርጠው ያሰሯቸዋል። በዚህም አበርክቷቸው መማሪያ ስዕሎችን ከመስራት ይጀምራል። ገና አርት እስኩል ላይ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ እያሉ ነበር በቴሌቪዥን ጣቢያው ውስጥ የሚሰራው የስዕል ፀሐፊው በመታመሙ የተነሳ ተክተው በወቅቱ ኮምፒውተር ስላልነበረ ለቴሌቪዥን የሚሆን ጽሁፍ እንዲሰሩ የታዘዙት። በዚህም ለወራት ያህል ደሞዝተኛ ሆነው አሻራቸውን ያሳረፉ ኢትዮጵያዊት ሰዓሊ ሆነዋል።
የሥዕል ሥራ ኤግቢሽንን ማሳየት የጀመሩትም እንዲሁ የሦስተኛ ዓመት ተማሪ ሳሉ ነበር። ይህ ደግሞ የገቢ ምንጫቸው ከማድረጋቸው ባለፈ ብዙዎችን የሚያስተምሩበትና የውጪ ሀገራትን ጭምር የሚስቡበት ማስተማሪያ እንዲሆንላቸው ረድቷቸዋል። እንደውም ከዚህ ኤግዚቢሽን ጋር በተያዘ ተምሮ ማስተማር ስለነበር በምስካዬ ሕዙናን መድሀኒአለም አዳራሽ ተሰቷቸው እነሎሬት አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በተገኙበት አቅርበው በስዕል ስራዎቻቸው ብዙዎችን ማስደመም ችለዋል።
በተከታታይም ሳይመረቁ ለአራት ጊዜ የሥዕል አውደርዕይ ማዘጋጀት የቻሉና የራሳቸውን እድል በራሳቸው ያመቻቹት ወይዘሮ እጅጋየሁ፤ ይህ አጋጣሚ የውጪ ኤግዚቢዥኖች ላይ እንዲሳተፉ ዕድል ፈጥሮላቸዋል። በዚህም ውጪ ሄደው ስለአገራቸው ከመመስከርና ከማሳወቅ ባለፈ ያላቸውን አቅም ያሳዩበትን አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል። እነዚህ ጥረቶቻቸው በሥዕሉ ዘርፍ ወንድ እንኳን የማይደፍረውን የሐውልት ሥራ መርጠው ዛሬ ድረስ የዘለቁ ናቸው። ምክንያቱም ጠንካራ ድንጋይን መፈልፈልን ጭምር ይችሉበታል። መስተዋትን ፣ እምነበረድንና ነሐስንም በሚፈልጉት ቅርጽ እያሳመሩ ማስደመምን የተካኑም ናቸው። ለዚህ ደግሞ ከልጅነታቸው ጀምሮ አዘውትረው ሲሰሩት የነበረው የስፖርት እንቅስቃሴ ትልቅ ድርሻ ነበረው። በቀላሉ የማይፈተኑ አድርጓቸዋልና።
ጣሊያን አገር እንኳን ሳሉ በደማሚት ተራራውን ከናዱ በኋላ በቅርጽ በቅርጽ የሚሰራውን ሐውልት በእጅ ጥበባቸው ከማንም በተሻለ መልኩ የሚከሽኑት በጸና መሰረት ላይ በማደጋቸው ነው። የንሀስ ሥራዎቻቸውም ቢሆኑ ፈታኝነት ያላቸውም ቢሆኑም ወርቅ ናቸው። ምክንያቱም ለአገራቸው አምጥተው ያስረከቡት አንዱ ማሳያ ሆኗል።
እንግዳችን በእጅ ጥበባቸው በአገር ውስጥ ብቻ ሳሆን ባህር ማዶ ተሻግረውም እውቅናን አግኝተዋል። መጀመሪያ በትናንሽ ትምህርትቤቶች በማስተማር ከዚያም በቤታቸው የተለያዩ የሐውልትና የሥዕል ሥራዎችን በመሥራትና በመሸጥ እንዲሁም ኤግዚቢሽኖችን በማዘጋጀት ተዋቂነታቸውን አጎልብተዋል። ይህ ከሆነላቸው በኋላ ደግሞ ትልቅ በሚባሉ ተቋማት የማገልገል ዕድል አግኝተዋል። አንዱ የአውሮፓውያን ኮሚሽን ሰራተኞች የሚማሩበት ትምህርቤት ሲሆን አሁን ድረስ በቦታው ላይ እያስተማሩ ይገኛሉ። በተጨማሪም የማስተማሪያና ለልጆች የሚሆኑ መጸሐፍት ዝግጅቶች ላይ ሥዕል በመሥራት በስፋት ይሳተፋሉ። በእርግጥ ይህ ሥራቸው በአገር ውስጥ የጀመረ ነበር። ይኸውም በስፖርት መምህሩ ግርማ ቸሩ አማካኝነት ሲሆን፤ የስፖርት መጸሐፍትን ሲያዘጋጅ ሥዕሉን የሰሩት እርሳቸው ነበሩ።
እንግዳችን በቤተመንግስት ውስጥ ጭምር እየተወሰዱ ትልልቅ ፖስተሮችን የሰሩ ናቸው። አለማቀፍ የሥዕል አውደርዕዮችንም እንዲሁ አገራቸውን በመወከል በተለያየ ጊዜ ተሳትፈዋል። ወደ ቤልጅየም በማምራት ሙያቸውን መሰረት አድርገው በርካታ ተግባራትን ፈጽመዋል። አንዱ ማስተማር ሲሆን፤ በዚያው አካባቢ ይኖር የነበረ የሥዕል ትምህርትቤት አንድ ክፍል ሰጥቷቸው የሥዕል ፍቅር ያላቸውና በትርፍ ጊዜያቸው መማር የሚፈልጉ ሰዎችን ያስተምሩ ነበር። ሁለት ዓመትም በዚህ ሥራ ላይ ቆይተዋል። ሉክሰን በርግ ላይም እንዲሁ ይህንኑ ሥራቸውን ከውነዋል። ከላይ እንዳልነው የአውሮፓውያን ስኩል ውስጥ የኮሚሽኑ ሰራተኞችና የተለያዩ ድርጅቶች ዳይሬክተር ልጆች የሚማሩበት ሲሆን፤ ከ16 ዓመት በላይ የቆዩበትና አሁንም የሚያስተምሩበት ነው።
እንግዳችን የሥዕል መምህር መሆናቸው በብዙ መልኩ ጠቅሟቸዋል። አንዱ ሁሉም ቦታ ላይ መግባት ስለሚችሉ በእያንዳንዱ ቦታ ላይ ሲሄዱ የቋንቋ ጉዳይ እንዳያሳስባቸው ቋንቋ መማራቸው ነው። አሁን ቢያንስ ከአምስት በላ ቋንቋዎችን ጠንቅቀው ያውቃሉ። ለአብነትም ጣሊያንኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛና ጀርመንኛ ተጠቃሽ ናቸው።
አበርክቶ
አርቲስት እጅጋየሁ ገና ልጅ ሳሉ ነው ለሀገራቸው ማበርከትን የተለማመዱት። ጣሊያን ከመሄዳቸው በፊት ‹‹ደስተኛ ልጅ›› የሚል ርዕስ ያለው ሐውልት ሰርተው ለብሔራዊ ሙዚዬም አበርክተዋል። በተመሳሳይ በቅርቡ እንዲሁ ከንሐስ የሰሩትን ስምንት ኪሎ ክብደት ያለው የልጅ ምስል ከፍተኛ ወጪ የወጣበት ቢሆንም ለብሔራዊ ሙዚዬም በማስረከብ አገር ወዳድነታቸውን አሳይተዋል።
አርቲስት እጅጋየሁ ‹‹የቃኘው ጦር ሰፈር›› እየተባለ የሚጠራውን የስብሰባ አዳራሽ በውብ የእጅ ጥበባቸው ያስዋቡም ናቸው። በእርግጥ በወቅቱ በግዴታ ያደረጉት ነበር። የሠሯቸው ሥዕሎችም ፖለቲካው የሚፈልገውን ብቻ ነው። ነገር ግን ምንም አይቆጫቸውም። ምክንያቱም ሰፊው አዳራሽ የእርሳቸውን የእጅ ጥበብ ውጤት ይዞ ወጥቷል፤ ታሪክ አድርጎ አስቀምጦላቸዋል። ሌላው የሠሩት ነገር ወደ ሁለት መቶ የሚሆኑ የሌሊን፤ የማርክስና ሄንግልስ መሰረታዊ ጽንሰ ሀሳቦችን የያዘውን ፖልትሬት ነው። ሦስት ሜትር በሁለት ሜትር ይደርሳልም። ለሁሉም ማህበረሰብ በሚደርስ መልኩ የሠሩት ተግባር ሲሆን፤ ኢትዮጵያን በእነዚህ ሥዕሎች መድረሳቸውም ከአበርክቷቸው አንዱ እንደነበር ያነሳሉ።
ከሁሉም በላይ ዛሬ ድረስ የሚያስደስታቸው ሌላው ሥራቸው ለድርቅ ኮሚሽን ማስተባበሪያ ወይም በዛሬው የእርዳታ ኮሚሽን ማስተባበሪያ ድጋፍ ማሰባሰቢያ የሚሆን ሐውልት ሰርተው ያስረከቡ ነው። ብዙ ሰው አይቶ የሚያዝንበትና ኪሱን የሚዳብስበት ነበር። ካለው ላይ ሳይሰስት እንዲሰጥ የገፋፋ በመሆኑም ብዙ ገቢ እንዲሰበሰብበት ሆኗል። በገቢውም ብዙዎች ከችግራቸው ተላቀዋል።
እንግዳችን ለሀገራቸው ዲፕሎማትም ናቸው። ማለትም በተለይም ተማሪዎችን ከማስተማር አንጻር በሥዕሉ ብቻ ሳይሆን ከዚያም አልፈው ይሄዳሉ። ለአብነት ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን ሉሲን በመጥቀስና የሰዎች ሁሉ እናት መሆኗን በማስረዳትም ይሰብካሉ። ለዚህ መነሻቸው ደግሞ የተማሪዎች ጸብ እንደሆነም ያነሳሉ። ጣሊያን ላይ እያሉም ከኢትዮጵያ ኢንባሲ ጋር በቅርበት ይሰሩ ነበር። የእጅ ሥራ ውጤቶቻቸውን ማለትም በነሐስና በእምነበረድ የተለያዩ ቅርጻቅርጾችን የሠሯቸውን ለአንባሲው አበርክተዋል። ኢትዮጵያዊያን በሚሳተፉባቸው መድረኮች ሁሉ እየተገኙ የቻሉትን የሚያበረክቱም ሆነው ቆይተዋል። ከዚያም በኋላ አሁን በሚሰሩበት ሉክሰንበርግ ወይዘሮ ሄኖኬ ወልደ መድህን በምትባል ኢትዮጵያዊት በተቋቋመ ‹‹REE›› የሚባል ድርጅት ውስጥም ይሳተፋሉ። ድርጅቱ በሕጻናት ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ የሚሰራ ሲሆን፤ ከ20 ዓመት በላይም በድርጅቱ ውስጥ በማገልገላቸው ብዙ ነገር ለአገራቸው እንዲበረከት አስተዋዕጾ ካደረጉ መካከል ናቸው። የኢትዮጵያ ሕጻናት በሚደገፉበት ሁሉ እርሳቸው አሉ።
በቅርቡም በጦርነቱ ለተጎዱ አካባቢዎች የሚያደርጓቸው ነገሮች እንዳሉ የነገሩን አርቲስት እጅጋየሁ፤ አንዱ የድርጅቱ ፕሬዚዳንት በሆነችው እንስት አማካኝነት የተሰበሰበው የህክምና ቁሳቁስ ሲሆን፤ ሁለተኛው እርሳቸው ከሚያስተምሩበት ትምህርትቤት የተሰጣቸው ኮምፒዩተር ነው። ይህም በኮንቴነር ታሽጎ እየተጓጓዘ ያለ ነው። በአጭር ጊዜ ለተጎዱት ተቋማትም ይደርሳል የሚል እምነት አላቸው ። እርሳቸው በምክትል ፕሬዚዳንትነት የሚመሩት ይህ ድርጅት ቀደም ባሉት ጊዜያትም ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመነጋገር ድጋፎችን አድርጓል። በተለይም የአገር ውስጥ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ላይ ሰፊ ሥራ ሰርቷል። ከእነዚህ መካከልም ድርጅቱ ‹‹ ጸረ ወባ ›› ከሚባል ድርጅት ጋር በመተባበር በባህርዳር ክሊኒክ ማሰራቱ አንዱ ነው።
‹‹ስለ እናት ›› ከሚባል ድርጅት ጋርም እንዲሁ በመንግስት ፈቃድ መሰረት እየሰሩ ይገኛሉ። አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰሩና ድጋፍን የሚሹ ብዙ ነገሮች ስላሉ መንግስት ከፈቀደላቸው ከድርጅቶች ጋር በመሆን ለመስራት ቁርጠኛ ናቸው።
መልእክተ እጅጋየሁ
‹‹ዘረኝነት አይገባኝም ነበር። ጥቁር ነች ተብዬ መገለልን እንኳን ያወኩት በብዙ ነገር ከተፈተንኩ በኋላ ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያዊያን ከልጅነታችን ጀምሮ ያደግነው ጠንካራ፣ ነጻና ማንም የማይወስንልን መሆናችንን እየተነገረን ነው። አሁንም የኃያልነታችንና የአልደፈርም ባይነታችን ምንጭ ያ አስተዳደጋችን ነው ብዬ አስባለሁ። ነገር ግን ማንነት በጥቅም ሲለወጥ ነገሩ ተበላሸ። ፍቅር ቦታውን ለገንዘብ ለቀቀና መቃቃር መጣ። ይህም ቢሆን ግን ተስፋችን ሁሌም ይኖራል። ምክንያቱም እኛ በችግር የተፈተን እንጂ የወደቅን አይደለንም። ስለዚህም ምንም እንኳን ጨለማው የበዛብን ቢመስለንም ብርሃኑ ግን እሩቅ አይደለምና በእምነታችን ይህንን ልናጠነክረው ይገባል›› የመጀመሪያው መልእክታቸው ነው።
የቤት ቆሻሻ በቤተሰብ እንደሚጠረግ ሁሉ የአገርም ችግር በጥበብ ኃይል ይጸዳል የሚሉት ባለታሪካችን፤ አሁን የመቃቃራችን ምስጢር ከየትም የመጣ ሳይሆን እኛ በከፈትነው ቀዳዳና ባለመሥራታችን እንደሆነ ይናገራሉ። አንድነትን በሚያመጡ ጉዳዮች ሁሉ ላይ አለመሥራታችን ቤተሰባዊ ግንኙነታችንን አላልቶታል ባይ ናቸው። ያለንን ተሞክሮና ሙያ ተጠቅመን ብንሰራ አይደለም አገራችንን ሌላንም መታደግ እንችል ነበር። ሆኖም ሥነ ጥበቡም ላይ ሆነ ሌሎች ዘርፎች ላይ ያለነው ባለሙያዎች አቅማችንን አሟጠን ስለ አገራችን አልመሰከርንም። አልሰራንምም። ይህ ደግሞ የውጪው ጣልቃ ገብነት እንዲሰፋ አድርጎታል። እናም አሁን ነቅተን ጥፋታችንን ወይም ችግራችንን እኛው በእኛው መፍታት አለብን። ሌላ እንዲፈታልን አንፍቀድ። በራችንን ከከፈትን አጣልተውን በእኛ ገንዘብና ሀብት ይከብራሉ። ከዚያም አልፎ ሴረኞችን እናበረክታለን። ስለሆነም በጥበብ ኃይል ቆሻሻውን አጽድተን ጥፋተኞች ይቅርታ እንዲጠይቁና አንድነታችን እንዲጎለብት እንስራ ይላሉ።
ለውጪዎች ራሳን አሳልፈን መስጠትም መቆም እንዳለበት የሚጠቁሙት ባለታሪካችን፤ እነርሱ የእኛን ውድቀት እንጂ ልማት አይፈልጉም። እንዳሸማቀቅናቸው ማሸማቀቅ እንጂ ቀና እንድንል አይፈቅዱልንም። እየደረሱ ያሉ ጫናዎችም መልከ ብዙ የመሆናቸው ምስጢር ይህ ነው። እናም አሁን ያለንበት ጊዜ ከምንም በላይ ሁላችንም በያለንበት መስክ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል በጋራ የምንቆምበት ጊዜ ላይ ነን። ኢትዮጵያ የጋራ አገራችን እስከሆነች ድረስ የሚደረገው መስዋዕትነትም አገር ለማሻገር እንጂ የአንድን አካል ፍላጎት ለማሟላት እንዳልሆነ መረዳቱ ተገቢ ነው። የምናደርገው ርብርብ የሁላችንን ፍላጎት የሆነችውን ኢትዮጵያ ወደፊት ለማስቀጠል መሆን ይገበዋልም ሲሉ ይመክራሉ።
ከውስጥም ከውጪም የሚሰነዘርብን ጥቃት በጋራ ከቆምን መመከት እንችላለን። እስካሁን በመጣንበት መልኩ ከተጓዝን ደግሞ ምንም እንኳን መልከ ብዙ ባህሪ ያላቸው ጥቃቶች ቢደርሱብንም እንደምናሸንፈው መጠራጠር የለብንም። ጸንተን ቆመንና ጥንካሬያችንን በአንድነት ገንብተነው ከተሻገርነው የማንቆፍረው ድንጋይ ሊኖር
አይችልም። ለዚህ ደግሞ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በያለበት በጎ አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት ሌላው ምክራቸው ነው።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 15 ቀን 2014 ዓ.ም