ከልጅነት ጊዜያቸው ጀምሮ ቢዝነስ ነክ ነገሮች በእጅጉ ያስደስታቸዋል ፤ ይማርካቸዋል።ቢዝነስ ሲባል ታዲያ ትላልቆቹን ብቻ አይደለም።ከትንሹ የጉልት ንግድ ጀምሮ ያሉ የቢዝነስ ሥራዎችን አጥብቀው የሚወዱና የሚያከብሩ ናቸው።ቢዝነስ የሰው ልጆችን በሙሉ የሚ ያገናኝ፣ የሚያሰባስብ፣ የሚያስተዋውቅ የሥራ ዘርፍ መሆኑን ይገልጻሉ፤ እጅግ የተከበረና የተባረከ ሥራ አርገውም ይመለከቱታል።
በየአካባቢው የሚጀመሩ ትናንሽ ንግዶች ዓለም አቀፍ ወደሆነው ንግድ ማደግ የሚችሉ ከመሆናቸውም በላይ የንግድ ዓለምን ማነቃነቅ የሚችል ኃይል አላቸው። የዓለም አገራት በሙሉ ሁሉም ነገር የላቸውም፤ አንዱ ያለው ሌላው የለውምና አገራት የሌላቸውን ካላቸው በመውሰድ፣ እነሱ ያላቸውን ደግሞ ለሌሎች በማካፈል ፍላጎቶቻቸውን ያሟላሉ።በዚህ ምክንያት የሰው ልጆች በአንድ ማዕቀፍ ውስጥ ሆነው የሚቀባበሉትና የሚከፋፈሉት እንዳለ በቢዝነስ ውስጥ ባላቸው ቆይታ መረዳት የቻሉ ናቸው።
ለበርካታ ዓመታት በመንግሥት መስሪያ ቤት አገልግለዋል፤ በግላቸውም በተለያዩ የቢዝነስ ሥራዎች እየተሳተፉ የሚገኙት የእለቱ እንግዳችን የእርካብ ትራንዚት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መስራችና ባለቤት ወይዘሮ እመቤት ታፈሰ ናቸው።
ወይዘሮ እመቤት፤ በመንግሥት መስሪያ ቤት በተለይም በኢትዮጵያ ቆዳ ፋብሪካ ለረዥም ዓመታት በሥራ አስኪያጅነት አገልግለዋል፤ በኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበርም ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል።
በአሁኑ ወቅትም በሥራ ዘመናቸው ያካበቱትን ልምድና ዕውቀት መነሻ ካፒታላቸው በማድረግ በግላቸው በከፈቱት እርካብ ትራንዚት አማካኝነት በወጪ ገቢ ንግድ በርካታ አገልግሎቶችን ለበርካታ ወገኖች ተደራሽ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
በቢዝነስ ውስጥ ረዘም ያለ ጊዜን ያስቆጠሩት ወይዘሮ እመቤት፤ ተወልደው ያደጉት በአዲስ አበባ ከተማ ነው።የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስ ያገኙ ሲሆን፤ የተለያዩ የምስክር ወረቀቶችን እና ዲፕሎማዎችን ደግሞ በአካውንቲንግ አግኝተዋል።ከልጅነት ዕድሜያቸው አንስተው ለቢዝነስ የነበራቸውን ፍላጎት ተግባራዊ ለማድረግ ተማሪ እያሉ ጀምሮ በተለይም እንስሳትና የእንስሳት ውጤቶች በእጅጉ ያጓጓቸው እንደነበር በማስታወስ በዘርፉም በርካታ መጻህፍት ስለማንበባቸው አጫውተውናል።
ስለኢትዮጵያ የወተትና የወተት ተዋጽኦ እንዲሁም የስጋ ምርት በነበራቸው ጥልቅ ንባብ ብዙ ዕውቀት መቅሰም ችለዋል።ለእንስሳት ካላቸው ቅርበት የተነሳ የቆዳ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሲቀጠሩ በጣም ደስተኛ ሆነውም ነበር።ረዘም ላለ ዓመታትም በዚሁ ዘርፍ ቆይተዋል።‹‹ቆዳ በተፈጥሮ ከእንስሳት የምናገኘው አስተዋጽኦ ነው›› የሚሉት ወይዘሮ እመቤት፤ እንስሳት የሚሰጡት ጥቅም ዘርፈ ብዙ ከመሆኑ የተነሳ ለእንስሳት ልዩ ፍቅርና እንክብካቤ አለኝ ይላሉ፡፡
ከእንስሳት የሚገኘው ቆዳ የተለያዩ ሂደቶችን አልፎ ጋርመንት ውስጥ ገብቶ በፋሽን ኢንዱስትሪ አልፎ ዓለም ለብሶት ሲታይ በጣም ያስገርማልም ይላሉ።በተለይም የኢትዮጵያ ቆዳ በዓለም ላይ እጅግ ተፈላጊና ተመራጭ እንደሆነ የሚያነሱት ወይዘሮ እመቤት፤ በወቅቱም ትላልቅ የተባሉ ኤግዚብሽኖች የሚካሄዱባቸውን በርካታ የዓለም አገራት የማየት ዕድል አጋጥሟቸዋል፤ ትላልቅ የተባሉትን የሌዘር ኢንዱስትሪዎችን ጎብኝተዋል።በዚህም ዓለም ቆዳን እንዴት እየተጠቀመበት እንደሆነ መረዳት በመቻላቸው የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ እንዲያድግ ከፍተኛ ምኞት ነበራቸው።ምኞታቸው እንዲሳካም በነበራቸው ቆይታ ያላሰለሰ ጥረት ያደረጉ ስለመሆናቸው ያስታውሳሉ።
የኢትዮጵያ ቆዳ በተፈጥሮ የታደለና እጅግ ተመራጭ መሆኑን ጠቅሰው፣ በተለይም የጎጃም፣ ጎንደር፣ ሲዳሞና ኢሊባቦር አካባቢዎች የሚገኘው ቆዳ በዓለም ገበያ እጅግ ተፈላጊና ተመራጭ ይላሉ ወይዘሮ እመቤት። የፍየል ቆዳን በሚመለከትም ከባቲ ፍየሎች የሚገኘው ቆዳ በዓለም ላይ የትም ቦታ የማይገኝ እንደነበርና ዓለም አለኝ የምትለው የቆዳ ውጤቶችን የምታገኘው ከኢትዮጵያ ስለመሆኑሙም ይናገራሉ።
‹‹የዓለምን ትኩረት መሳብ የቻለውን ይህን በተፈጥሮ የተሰጠንን እምቅ ሃበት በአግባቡ አልተጠቀምንበትም›› የሚሉት ወይዘሮ እመቤት፤ ዛሬ የኢትዮጵያ ቆዳ ከደረጃው ወርዶ በየቦታው ተጥሎ ሲመለከቱ በእጅጉ ያዝናሉ።እዚህ ደረጃ ሊደርስና ሊያስቆጭ እንደሚችልም በወቅቱ የነበራቸውን ስጋት ለሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በጽሁፍ ሲያደርሱ እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡
እንስሳትና የእንስሳት ውጤቶች እጅጉን የሚያጓጓቸው ወይዘሮ እመቤት፤ ለእነዚህ ውጤቶች ልዩ ፍቅር እንዳላቸውም ይገልጻሉ።ለበርካታ ዓመታት የመሩትን የኢትዮጵያ ቆዳ ፋብሪካ ለቀው በግል ሥራ መሠማራት ሲያስቡ ታዲያ ለዘርፉ ካላቸው ፍቅር የተነሳ የመጀመሪያ ምርጫቸው ያደረጉት በቆዳ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ውስጥ መሰማራት ነበር።ይሁንና በተለያዩና ውጫዊ በሆኑ ምክንያቶች ፍላጎታቸው ሳይሳካለቸው ቢቀርም፣ ሌሎች ውስጣዊ ፍላጎቶታቸውን በማዳመጥ ምላሽ መስጠት ችለዋል፡፡
ማንም ሰው ቀልጣፋና መልካም የሆነ አገልግሎት ሲሰጠው እንደሚደሰት ሁሉ ወይዘሮ እመቤትም ይህን ሰዎችን በብዙ ሊያስደስትና ሊያረካ የሚችለውን አገልግሎት የመስጠት ሥራ ለመሥራት ተዘጋጅተው ወደ ሎጅስቲክስ ሥራ ተሰማሩ።በድጋሚ ውስጣቸው የሚመኘውን ሥራ ለመሥራት ወደ ሎጅስቲክስ ዘርፍ ሲያመሩ ታዲያ ኢትዮጵያ በዘርፉ እጅግ ወደኋላ መቅረቷን በመረዳትም ነው።
ሰዎች በሚሰጡት ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ምክንያት የሚያገኙት በርካታ ጥቅሞች እንዳሉ ሁሉ አገልግሎት የሚያገኘው አካልም በሚያገኘው አገልግሎት ልክ ተጠቃሚ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል የሚሉት ወይዘሮ እመቤት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ክፍተት ስለመኖሩ ብዙዎች የሚስማሙበት እንደሆነና እርሳቸው ደግሞ በተደጋጋሚ የገጠማቸው ጉዳይ በመሆኑ ነው ወደ ሎጅስቲክስ ዘርፍ የገቡት፡፡
‹‹አገልግሎት ፈልጌ በሄድኩባቸው አብዛኞቹ ቦታዎች የምፈልገውን አገልግሎት በተገቢው መንገድ አላገኘሁም›› የሚሉት ወይዘሮ እመቤት፤ ለግላቸው ሥራ በሄዱበት ቦታ ሁሉ ያጡትን አገልግሎት እኔ ብሆን እያሉ ይቆጩ እንደነበርና የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ምን ባደርግ ይበጃል፤ እኔ ያልረካሁበትን አገልግሎት ሌሎችን እንዴት ማርካት እችላለሁ በማለት ያወጡና ያወርዱም ነበር፡፡
በእነዚህና መሰል ገፊ ምክንያቶች ወደ ሎጅስቲክሱ የገቡት ወይዘሮ እመቤት፤ በተለይም በዓለም አቀፍ ንግድ ውስጥ ኢትዮጵያ ጥራት ያለው አገልግሎት በወቅቱ ባለማድረስና መረጃ ባለመስጠት ብዙ ጊዜ ወቀሳ ይደርስባት ስለመሆኑ ያስታውሳሉ።በዚህ ምክንያት ደግሞ ዓለም አቀፍ የንግድ ሂደቱን ይደናቀፋል ስለዚህ ለሌሎች የሚከፈለው ዋጋ ለኢትዮጵያ አይገባትም በማለት በዓለም አቀፍ ንግዱ ማግኘት የሚገባትን ገቢ እንዳታገኝ ሆና ቆይታለችም ይላሉ።
አንድን ምርት ከተመረተበት ቦታ አንስቶ እሴት በመጨመርና ወደ መጨረሻው ተጠቃሚ ለማድረስ የምንሄድበት መንገድ የተመቻቸ እንዲሆን የግድ ነው።ይህም ማለት በፍጥነት፣ በጥራትና በጊዜ ማከናወን ሲሆን ይህን ማድረግ ሲቻል፤ አቅራቢው ተወዳዳሪና የተሻለ ተጠቃሚ ይሆናል።የመጨረሻ ተጠቃሚውም እንዲሁ በሚያገኘው ቀልጣፋ አገልግሎት እርካታን ከማግኘት ባለፈ እርሱም ተጠቃሚ መሆን ይችላል።ይህም ማለት ሻጩም ሆነ ገዢው ከሚከውኑት ንግድ የሚገባቸውን ጥቅም ያገኛሉ ማለት ነው፡፡
በዚህ እሳቤ የሎጅስቲክስ ዘርፉን የተቀላቀሉት ወይዘሮ እመቤት፤ በተለይም የቡና ወጪ ንግድን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እያሳለጡ ይገኛሉ።አብዛኞቹ ደንበኞቻቸው ቡና ላኪዎች ይሁኑ እንጂ ወደ ውጭ ገበያ ከሚላከው ቡና በተጨማሪም የተለያዩ ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ ለሚያስመጡ አስመጪዎችም አገልግሎቱን ይሰጣሉ።
በሎጅስቲክስ አገልግሎት ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የተለያዩ ምርቶችን ከጅቡቲ በማንሳት ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋሉ።ወጪ ምርቶችንም እንደዚሁ ከደንበኞቻቸው በመረከብ አስፈላጊውን ሂደት በመከተል በጥሩ ሁኔታ ወደ ውጭ ገበያ ይልካሉ።ወደ አገር ውስጥ ለሚገቡትም ሆነ ለውጪ ገበያ ለሚላኩ ምርቶች ድልድይ በመሆን የሚያሳልጡት ወይዘሮ እመቤት፤ የሚሰጡት አገልግሎት ጊዜውን የጠበቀና ቀልጣፋ በመሆኑ ተመራጭነታቸው እየሰፋ መጥቷል።
ከዚህ ቀደም ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚሰበሰበው ቡና አዲስ አበባ ለመድረስ ነጋዴው ይፈተን እንደነበር በማስታወስ፤ ሎጅስቲክስ ይህን እና መሰል ችግሮችን በማቃለል ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ስለመሆኑም ይናገራሉ።ይህም በወጪ እና ገቢ ንግዱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀሬ እንደሆነ ወይዘሮ እመቤት ይናገራሉ።ይህ ደግሞ በዓለም አቀፍ ገበያ የሚኖር ተወዳዳሪነትን ይቀንሳል፤ ስለዚህ የሎጅስቲክስ መሟላት በተለይም ለወጪ ገቢ ንግድ ወሳኝ ነው ይላሉ።
አስፈላጊ በሆነበት ጊዜ ሁሉ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ እንደሆነ ያነሱት ወይዘሮ እመቤት፤ ጅቡቲ ላይ ባሏቸው ወኪሎች አማካኝነት የላኪውን እና የአስመጪውን ፍላጎት መሰረት በማድረግ ከጉምሩክ ጋር ባላቸው የኔትዎርክ ግንኙነት እንዲሁም ከጅቡቲ ውጭ ከኬኒያና ከሌሎችም አገራት ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት አገልግሎቱን ይሰጣሉ።በሚሰጡት ቀልጣፋ አገልግሎትም የወጪ እና የገቢ ንግዱን በመደገፍ አገሪቷ ይበልጥ ተጠቃሚ እንድትሆን እንዲሁም ድርጅታቸው እንዲያድግ ከላይ ታች እያሉ እንደሆነ አጫውተውናል፡፡
በዚሁ አገልግሎታቸው በተለይም በቡና ዘርፍ ሰፊ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ በቀጣይም ሥራቸውን አጠናክረው የሚቀጥሉ ስለመሆኑ ሲናገሩ፤ በተለይም ለወጪ ንግዱ አዲስ የሆኑ ነጋዴዎችን በማቅረብ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችል የማማከር አገልግሎት ይሰጣሉ።
በሎጅስቲክስ አቅርቦትና አስተዳደር ላይ እንደ አገር በርካታ ችግሮች እንዳሉ የሚያነሱት ወይዘሮ እመቤት፤ የመሰረተ ልማት ችግር አንዱ ስለመሆኑ ያስረዳሉ።የተሟላ መሰረተ ልማት ባለመኖሩ መኪኖች የምልልስ ጊዜያቸው እጅግ የረዘመ ነው።በመሆኑም እኤአ በ2016 በዓለም ከሚገኙ 160 አገራት መካከል ኢትዮጵያ 126ኛ እንደነበረችና በ2018 ደግሞ ወደ ኋላ በመሄድ 136ኛ ላይ የተቀመጠችበት ጊዜ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
ይህ ማለት ደግሞ ኢትዮጵያ በሎጅስቲክስ ዘርፍ እየሰጠች ያለችው አገልግሎት ዝቅተኛ ሲሆን በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን አልተቻለም ማለት ነው፤ በአጭር ጊዜ ሊሰራ የሚችለውን ሥራ በረዥም ጊዜ በመሥራት፤ አላስፈላጊ ለሆነ የመጋዘን ወጪ በመዳረግ ከግለሰቦች ባለፈ አገር ትልቅ ዋጋ እየከፈለች ያለበት ዘርፍ ነው ሲሉም ኢትዮጵያ በዘርፉ ያለችበትን ሁኔታ ያብራራሉ።በአንድ ምርት ውስጥ የሎጅስቲክስ ድርሻ 40 በመቶ እንደሆነም አጫውተውናል፡፡
ወይዘሮ እመቤት፤ በተሰማሩበት አጠቃላይ የሎጅስቲክስ ዘርፍ 26 ለሚደርሱ ዜጎች በቋሚነት የሥራ ዕድል መፍጠር የቻሉ ሲሆን፤ በተለየ ሁኔታ ደግሞ በቡናው ዘርፍ በተለያየ ጊዜ የተለያየ ቁጥር ያለው የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ።ቡና በሚደርስበት ወቅት ሰፊ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል ያስፈልጋልና በአንድ ጊዜ እስከ 60 ለሚደርሱ ሠራተኞ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ፡፡
ማህበራዊ ኃላፊነትን በተመለከተም በተለያየ መንገድ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ እንደሆነ ያጫወቱን ወይዘሮ እመቤት፤ የሥራ ዕድል መፍጠር በራሱ አንድ ነገር ሆኖ፤ ሰዎች በሚሠሩት ሥራ ሁሉ ደስተኞች ሆነው መሥራት እንዲችሉ የተለያዩ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራሉ።ለአብነትም ወላጆች ከወሊዳቸው ጊዜ ጀምሮ ለልጆቻቸው ጊዜ መስጠት እንዲችሉ ያደርጋሉ።ከዚህም ባለፈ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ሁሉ ወይዘሮ እመቤት ከሠራተኞቻቸው ጎን ይገኛሉ።በመሆኑም ከሠራተኞቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት ጥሩ መንፈስ ያለውና ቤተሰባዊ እንደሆነ ይናገራሉ።ከዚህ ባለፈም በአገር ደረጃም ሆነ በአካባቢያቸው ለሚደረጉ ማንኛቸውም ጥሪዎች በአቅማቸው ይሳተፋሉ፡፡
‹‹ማንም ሰው መጥቶ ድንጋይና እሾሁን የሚያነሳልን የለም፤ ለእኛ ያለነው እኛው ራሳችን ነን›› የሚሉት ወይዘሮ እመቤት፤ በሎጅስቲክስ ዘርፍ በሚደረጉ ማንኛቸውም ሴሚናሮች ላይ በመሳተፍ ያላቸውን ዕውቀትና ልምድ ያካፍላሉ።በዚህም ኢትዮጵያ በተለይም ወደ ኋላ በቀረችበት በሎጅስቲክስ ዘርፉ የተሻለች ሆና ውጤት እንድታስመዘግብ ያላቸውን ዕውቀት ለማካፈል ጊዜያቸውን ሳይሰስቱ አሟጠው ይጠቀማሉ፡፡
‹‹ኢትዮጵያ በተፈጥሮ በታደለችው ጸጋ ከራሷ አልፋ ሌሎችን መመገብ የምትችል እንጂ፤ መራብ ያለባት አገር አይደለችም›› የሚሉት ወይዘሮ እመቤት፤ በቀጣይ በግብርናው ዘርፍ በመሰማራት ቡና እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬዎችን አልምተው ከአገር ውስጥ ገበያ ባለፈ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ዕቅድ አላቸው።በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የቅድመ ዝግጅት ሥራቸውን አጠናቅቀው ወደ ሥራው ለመግባት በመንገድ ላይ ናቸው፡፡
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 14 /2014