ሀገራት የወጪና ገቢ ንግዳቸውን ለማቀላጠፍና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰታቸውን ለማሳደግ ብሎም አጠቃላይ ምጣኔ ሀብታዊ እድገታቸውን ለማሻሻል ከሚተገብሯቸው አሰራሮች መካከል አንዱ ነፃ የንግድ ቀጠናዎችን (Free Trade Zones) ማቋቋም ነው።
ነፃ የንግድ ቀጠና ‹‹ልዩ የኢኮኖሚ ቀጠና›› (Special Economic Zones) የሚባሉት የንግድና ኢንቨስትመንት መከወኛ ስፍራዎች አካል ናቸው፤ ቀጠናው እሴት የሚጨምሩ የምርት፣ የሎጅስቲክስ፣ የፋይናንስ አቅርቦትና መሰል ተግባራትና አገልግሎቶች የሚከናወንበት ቦታ ነው። በዚህ ስፍራ ምርቶችን ከማምረት በተጨማሪ አስመጪና ላኪዎች ዕቃዎችን ወደ አገር ውስጥ በማምጣት በቀጠናው ውስጥ የሚያከማቹበት፣ የሚያቀነባብሩበት እንዲሁም መልሰው ለውጭ ገበያዎች የሚያቀርቡበት እንዲሁም ሒደቱን ለማሳለጥ ቀልጣፋ የሆነ የሎጂስቲክስ አገልግሎት የሚቀርብበትም፣ የተቀናጁ የፋይናንስና የምክር አገልግሎቶችም የሚሰጡበት ነው።
ነፃ የንግድ ቀጠና ኢንቨስትመንትን የሚጨምር፣ አዳዲስ የሥራ ዕድሎች ለመፍጠር የሚያግዝ፣ ቢሮክራሲያዊ የአሰራር ውጣ ውረዶችን የሚቀንስ አማራጭ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ ቀጠና የንግድ እንቅፋቶች የሌሉበት እንዲሁም ቀረጥና ግብር ያነሰበት የንግድና ኢንቨስትመንት ማሳለጫ አካባቢ እንደሆነም ይገለፃል። በነፃ የንግድ ቀጣናዎች ውስጥ የሚተገበሩ ህጋዊ አሰራሮች በሌሎቹ አካባቢዎች ከሚተገበሩት ጋር ሲነፃፀሩ የላሉና አንፃራዊ ነፃነትን የሚያጎናጽፉ ናቸው።
ነፃ የንግድ ቀጠናዎች የሚፈጥሩትን የስራ እድል፣ ለአገር በቀል የሎጂስቲክስ ኢንዱስትሪው መስፋፋት የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግርና የባለሙያዎችንና የሠራተኞችን ክህሎት ለማሳደግ እና ለዋጋ ግሽበት መቀነስ የሚኖራቸውን ወሳኝ ሚና፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግ እንዲሁም የወጪና ገቢ ንግድን ለማቀላጠፍ ያላቸውን አበርክቶ በአጠቃላይ ለሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት መሻሻል የሚኖራቸውን ጉልህ ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነፃ የንግድ ቀጠናዎችን ያቋቁማሉ፤ ያስፋፋሉ።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በዓለም ላይ ከአምስት ሺ በላይ ነፃ የንግድ ቀጠናዎች አሉ። በርካታ ሀገራት ነፃ የንግድ ቀጠና ያላቸው ሲሆን፣ ለእዚህም የኢትዮጵያ ጎረቤቶች የሆኑት ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሱዳን ተጠቃሽ ናቸው። ዛሬ በምጣኔ ሀብታቸው የበለፀጉት ሀገራትም ይህን የነፃ ንግድ ቀጠና አሰራር ተግባራዊ አድርገዋል፤ እያደረጉም ነው።
ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር እንዲሁም መሬትን ጨምሮ ሌሎች እምቅ ሀብቶች ያላት ኢትዮጵያ ነፃ የንግድ ቀጠናን እስካሁን ድረስ ባለማቋቋሟ ማግኘት የሚገባትን ምጣኔ ሀብታዊ ጥቅም ማጣቷ ተደጋግሞ ሲገለፅ ቆይቷል። የሀገሪቱን የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ እግር ከወርች አስረው የያዙት አንዳንዶቹ መሰናክሎች ነፃ የንግድ ቀጠናዎች በሚያስገኟቸው ጥቅሞች የሚፈቱ ናቸው።
ስለሆነም ነፃ የንግድ ቀጠና በማቋቋም የሀገሪቱን ተጠቃሚነት ማሳደግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ልዩ ልዩ የመሰረተ ልማትና ሕግ ማዕቀፍ ዝግጅቶች ሲደረጉ ቆይተው ነሐሴ 8 ቀን 2014 ዓ.ም የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ተመርቆ ተከፍቷል። የንግድ ቀጠናው በድሬዳዋ የሚገኘውን የኢንዱስትሪ ፓርክና ደረቅ ወደብን ከዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት፣ ከባቡርና ከመንገድ ትራንስፖርት ጋር በማቀናጀት፣ አስፈላጊ የሆኑ የባንክና የጉምሩክ አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ ወደ አገልግሎት እንዲገባ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል።
በነጻ የንግድ ቀጠናው ምረቃ መርሃ ግብር ላይ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፣ ነፃ የንግድ ቀጠና ኢትዮጵያ በእጅጉ ወደ ኋላ ከቀረችባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ እንደሆነ ተናግረዋል። ‹‹ብዙ ወደ ኋላ የቀረንባቸው ዘርፎች አሉ። ከሁሉም የበለጠ እጅግ የሚያስገርመው ነፃ የንግድ ቀጠና ሳናቋቁም እስካሁን ድረስ መቆየታችን መተኛት ብቻም ሳይሆን በጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ እንደነበርን የሚያረጋግጥ ነው። ›› ሲሉ አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ 40 እና 50 ሚሊዮን ሕዝብ በነበራት ጊዜ በነበረው አሰራር ልትቀጥል እንደማትችልም ጠቅሰው፣ ቀልጣፋ አገልግሎት ለማቅረብ የሚያስችሉ አዳዲስ አሰራሮችን ማወቅና መተግበር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል። ዛሬ በምጣኔ ሀብታቸው የዓለም ቁንጮ የሆኑት ኃያላን ሀገራት የነፃ ኢኮኖሚ እና ነፃ የንግድ ቀጠናዎችን ምስረታ ቀደም ብለው መጀመራቸውና በዘርፉ ያከናወኗቸው ተግባራት የምጣኔ ሀብት አቅማቸውን በከፍተኛ ሁኔታ እንዳሳደገው ጠቁመዋል።
‹‹ነፃ የንግድ ቀጠና አጠቃላይ አገራዊ ምርትን፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትንና የወጪ ንግድን ለማሳደግ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው። የበለፀጉት አገራት በንግድና ኢንቨስትመንት ስራቸው ትልቅ ለውጥ ያስመዘገቡት እንደ ነፃ የንግድ ቀጠና ያሉ አሰራሮችን በመዘርጋታቸው ነው። በድሬዳዋ የተቋቋመው ነፃ የንግድ ቀጠና የራሱ ሕግና አሰራር ያለው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረ ሌላ ትንሽ ኢትዮጵያ ነው›› ሲሉ አብራርተዋል።
ነፃ የንግድ ቀጠናው እንዲቋቋም የተፈለገበት ምክንያት የተቀላጠፈ የሎጂስቲክስና የንግድ ስርዓት ለመዘርጋት መሆኑን ገልፀው፤ ቀጠናውን በአግባቡ በመጠቀም በጥቅል ሀገራዊ ምርት፣ በወጪና ገቢ ንግድ እንዲሁም በኢንቨስትመንት ፍሰት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ነፃ የንግድ ቀጠናን መመስረት የንግድ ዘርፍ ችግሮችን ለመቀነስና የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግ አወንታዊ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ተዋንያን ተደጋግሞ ይገለፃል። ነፃ የንግድ ቀጠናዎች የምርትና የሎጂስቲክስ ተግባራት ተቀናጅተው በቀልጣፋ አሰራር የሚከወኑባቸው ስፍራዎች በመሆናቸው ለኢንቨስትመንት ማደግ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራሉ። የኢንቨስትመንት እድገት የመንግስትን ብቻ ሳይሆን የባለሀብቶችን ተግባራዊ ተሳትፎና ቁርጠኝነት የሚጠይቅ በመሆኑ ባለሀብቶችም ነፃ የንግድ ቀጠናው የፈጠራቸውን እድሎች መጠቀም ይገባቸዋል።
በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ‹‹የነፃ ንግድ ቀጠና ስርዓትን እስካሁን ሳንጠቀምበት የቆየን ቢሆንም በተለይ ኢትዮጵያውያን ኢንቨስተሮች አሁን በተቋቋመው ነፃ የንግድ ቀጣና የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሊነቁ ይገባል። በዚህ ቀጠና የሚወጡ ሕጎች ከሌሎቹ ቀለል ያሉ በመሆናቸው ከፋይናንስና ከጉምሩክ ጋር የተያያዙ አሰራሮች ፈጣንና ቀልጣፋ እንዲሆኑ ይደረጋል። ሁሉም ባለሀብቶች የተጋበዙ ቢሆንም በተለይ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች በገቢና ወጪ ንግድ ላይ እመርታ እንዲመጣና ውጤት እንዲመዘገብ ከመንግሥት ጎን ሆናችሁ መስራት ይኖርባችኋል›› በማለት ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ተሳትፏቸውን እንዲያሳድጉ አሳስበዋል። የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ከሚያስመዘግባቸው ስኬቶች ልምድ በመቀመር በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ተጨማሪ ነፃ የንግድ ቀጣናዎች እንደሚቋቋሙም ተናግረዋል።
በነፃ የንግድ ቀጠናዎች ውስጥ የሚተገበሩ ህጋዊ አሰራሮች ቀለል ያሉና ቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረዶችን የሚቀንሱ በመሆናቸው ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ለመሰማራት የሚያደርጉትን ጥረት በአንፃራዊነት ቀላል ያደርጉላቸዋል። በነፃ የንግድ ቀጠናው ውስጥ ገብተው የሚሠሩ ባለሀብቶች፣ አስመጪና ላኪዎችም ሆኑ ድርጅቶች የልዩ ልዩ ማበረታቻዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ። ይህ ደግሞ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ጉልህ ሚና ይኖረዋል።
የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና በየጊዜው እያደገ የመጣውን የአገሪቱን የገቢና ወጪ ንግድ በተፋጠነ የሎጂስቲክስ አቅርቦት ለማገዝ ነፃ የንግድ ቀጠና ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት የተቋቋመ እንደሆነ ገልፀዋል።
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ የልዩ ኢኮኖሚ ቀጠናዎች መስፋፋት የሀገራችንን የገቢ ጭነቶች ባጠረ የአቅርቦት ሰንሰለት በብዛት በማስገባትና ከብዛት የሚገኘው የሎጂስቲክስ ቅናሽ ለዋጋ መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል። በተጨማሪም ተደጋጋሚ የሎጂስቲክስ ወጪዎች ለማዳን ያግዛል፤ በዚህም ይባክን የነበረውን የውጭ ምንዛሬ ያስቀራል። በልዩ የኢኮኖሚ ቀጠናዎች ምርቶች እሴት ተጨምሮባቸው ወደ ውጭ ሲላኩ የውጭ ንግድ ምጣኔያችንን ከማሳደግና የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ከመሆን ባሻገር የሐገር ውስጥ የምርት ግብዓት አቅራቢዎችንና መለስተኛ አምራቾችን አቅም በመጨመርና የሀገር በቀል ኢንዱስትሪዎችን በማሳደግ የገቢ ንግድን የመተካት ግባችንን ያሳካል። ከዚህ በተጨማሪም ከፍተኛ አቅም ያላቸው የውጭ ባለሀብቶችን የሚስብ በመሆኑ ሀገራችንን ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ተጠቃሚ ያደርጋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር አረጋ ሹመቴ እንደሚናገሩት፣ ነፃ የንግድ ቀጠናው የምጣኔ ሀብት ትስስርን ለማጎልበት ይረዳል። ኢንቨስትመንትን በማሳደግና ተጨማሪ የስራ እድሎችን በመፍጠር የሥራ አጥ ቁጥር እንዲቀንስ ያግዛል። የገበያ አማራጮች እንዲጨምሩ በማድረግ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲያድግም አስተዋፅኦ ያበረክታል። ይህም የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ ተጨማሪ አቅምና አማራጭ ይፈጥራል።
ነፃ የንግድ ቀጠናው የሀገር በቀል ባለሀብቶች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና አሰራሮችን እንዲለምዱ እድል እንደሚፈጥርላቸው ጠቅሰው፣ ይሁን እንጂ ነፃ የንግድ ቀጠናው የባለሀብቶቹን ተወዳዳሪነት የማሳደግ ዓላማውን እንዲያሳካ ስለነፃ ንግድ ቀጠናው ለባለሀብቶች ግንዛቤ ማስጨበጥ እንደሚስፈልግና ባለሀብቶችም አቅማቸውን ለማሳደግ ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸውም ዶክተር አረጋ ይመክራሉ።
በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህርና በ‹‹ፍሮንቲየርአይ (Frontieri)›› ጥናትና አማካሪ ድርጅት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሞላ አለማየሁ በበኩላቸው፤ ‹‹ነፃ የንግድ ቀጠናው የወጪና ገቢ ንግድን ያቀላጥፋል። የወጪ ንግዱ በተፋጠነ መልኩ መከናወኑ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ኢንቨስት እንዲያደርጉ ያበረታታቸዋል ሲሉ ይገልጻሉ። የንግዱ መፋጠን የምርት ፍላጎትን ለመጨመርና ደንበኞችን ለማፍራት ያስችላል። ስለዚህ ነፃ የንግድ ቀጠና ከንግድ ልውውጥ በተጨማሪ የሀገር ውስጥና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን ለማሳደግም አወንታዊ አስተዋፅኦ ይኖረዋል›› በማለት የነፃ ንግድ ቀጠናው መቋቋም ለኢንቨስትመንት ዘርፉ እድገት የሚኖረውን በጎ ሚና ያስረዳሉ።
ነፃ የንግድ ቀጠና አዳዲስና ሰፊ የሆኑ የሥራ እድሎችን ለመፍጠር፣ ተተኪ ምርቶችን ለማምረት፣ የእውቀት ሽግግርን ለማሳደግ እንዲሁም ለአገር ውስጥ የቀረቡ ምርቶችን ለማከማቸትና የሎጀስቲክስ ወጪን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል። ይህም ሀገራዊ የሎጂስቲክስ ተወዳዳሪነትን ትርጉም ባለው መልኩ ሊለውጥ የሚችል በመሆኑ የሀገሪቱን የገቢና ወጪ ንግድ ስርዓት ለማቀላጠፍ ያግዛል። አሰራሩ የሚያስገኛቸው ጥቅሞችና የሚፈጥራቸው እድሎች የምርት ወጪን በመቀነስ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋትም ትልቅ ሚና ይኖረዋል። እነዚህ ሁሉ ጥቅሞች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለጥቅል አገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት ዓይነተኛ ፋይዳ አላቸው።
ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ከሚሰጠው ከነፃ የንግድ ቀጠና ስርዓት ርቃ መቆየቷ ብዙ ጥቅሞችን አሳጥቷታል። የእነዚህ ጥቅሞችና እድሎች መታጣት ደግሞ በአጠቃላይ እድገቷ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደረባት አይካድም። ስለሆነም በድሬዳዋ የተቋቋመውን ነፃ የንግድ ቀጠና በሚገባ በመጠቀምና መልካም ተሞክሮችን በመቀመርና በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎችም ተጨማሪ ነፃ የንገድ ቀጠናዎችን በማቋቋም አገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገቱ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲያስመዘግብ ማድረግ ይገባል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 12 /2014