
የሐሙስ ምሽት ነሐሴ 5 ቀን 2014 ዓ.ም ፋና 90 ዜና ከወትሮው በተለይ በጋሸ አበራ ሞላ /አርቲስት ስለሽ ደምሴ ዘመን ተሻጋሪ የትውልድ ዜማ “አባቱ ደጀን…፣”ን ከፊት በማስቀደም ነው የጀመረው ። ዕለቱን የዋጀ ስልት ሆኖ ነው የተሰማኝ ። አዎ!
“አባቱ ደጀን እናቱ ጣና ፣
የኢትዮጵያ ልጆች መጡ እንደገና ፤… “
ስምን መልዓክ ያወጣዋል እንዲሉ “ታላቁ የኢትዮጵያ ‘ሕዳሴ’ ግድብ፤” የተባለው እኮ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን እንደገና ኃይላቸውን እንደ ንስር አድሰው በከፍታ መምጣትን ለማብሰርም አይደል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንደ ስሙ አንድምታው ከኢኮኖሚያዊ አውታርነት አድማስ ባሻገር ነው። የኢትዮጵያን የሕዳሴ ጉዞ የለኮሰ ብቻ ሳይሆን የሕዳሴውን ማርሽም የቀየረ የተዋጣለት ሹፌርም ነው። ከሁለት አመት በኋላ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ የብርሃን ጭላንጭል ለናፈቃቸው ከ50 ሚሊየን በላይ ወገኖች ጸዳል ሊሆን አሽቷል። በተደጋጋሚ በሚከሰት የኃይል መቆራረጥና እጥረት አሳሩን እየበላ ለሚገኘው ኢንዱስትሪም ሆነ ሌላ የኢኮኖሚ ዘርፍ የምስራች ይዟል። የኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥ በአመት ከ1 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘትም አልሟል። ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ በቀጣናው ከፍ ሲልም በአፍሪካም ሆነ በዓለም የሚኖራትን ጂኦፖለቲካዊ ተጽዕኖ ከፍ ያደርጋል። ይህ አንድ ላይ ሲደማመር ለኢትዮጵያ ሕዳሴ መበሰር ነጮች እንደሚሉት የመስፈንጠሪያ ሰሌዳ /spring- board/ ይሆናል። ገጥሞት ከነበረው የለየለት ክሽፈት በለውጡ አመራር ቆራጥ ውሳኔ ድኖ ለዚህ መብቃቱ ታላቅ ገድል ነው።
የኢትዮጵያ ሕዳሴ ወሳኝ መታጠፊያ /critical juncture/ የሆነው ይህ ግዙፍ ሕልምና ራእይ እውን ሆኖ ከአንድም በሁለት ተርባይን በአሁናዊ አቅሙ 550 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የበቃው በመላው ኢትዮጵያዊ ርብርብ ነው። ከሊስትሮ እስከ እንጨት ለቃሚ፤ ከሕጻናት እስከ አረጋውያን፤ ካጣ ከነጣ ድሃ እስከ ባለጠጋና ባለሀብት፤ ከአገሬው እስከ ዲያስፓራው፣ ወዘተረፈ ጠጠር ያልጣለ የለም። ከእለት ጉርሱ ቀንሶ፣ ከልጆቹ ጉሮሮ ቀምቶ የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቦንድ ገዝቷል። ገንዘብ አበርክቷል። ለግሷል። ጉልበቱንና እውቀቱን አዋጥቷል። ከፍ ሲልም ሕይወቱን ሰውቷል። በድምሩ ወደ 20 ቢሊየን ብር የሚጠጋ አዋጥቷል።
በአገሪቱ ታሪክ ኢትዮጵያዊ በሞላ ያለ ልዩነት እስላም ክርስቲያን፤ አማራ ኦሮሞ ትግሬ ጉራጌ ሃድያ፤ ሳይል በአንድነት ሰራዊትና ደጀን የሆነለት ግዙፍ ፕሮጀክት ነው። በነገራችን ላይ በአገሪቱ ታሪክ በብዙ ሚሊየን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ለአንድ ሜጋ ፕሮጀክት ይሄን ያህል ገንዘብ አዋጥተው አያውቁም። በአሜሪካ ኦሪገንና በኮሎምቢያ ካሊ አትሌቶቻችን በነጠላም ሆነ በቡድን እንደ አገር ክብረወሰኑን እንደሰባበሩት መላ ኢትዮጵያዊ ደግሞ በሕዳሴው የቀደሙትን ትውልዶች ክብረ ወሰን ሁሉ ሰባብረውታል። ተደቅኖበት ከነበረ የለየለት የክሽፈት አደጋ ታድጎ በእነዚህ ቀውጢና ፈታኝና እልህ አስጨራሽ አመታት ሁሉ ጥርሱን ነክሶ በአጭር ታጥቆና ህልቆ መሳፍርት ለሌለው ጫና አንድ ጊዜም ሸብረክ ሳይል ለዚህ ያበቃው በክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የሚመራው የለውጥ ኃይልም ያለ ምንም ስስትና ንፍገት በልኩ እውቅና ሊቸረው ይገባል።
የእንችላለን መንፈስን ለኢትዮጵያውያን ከፍ ሲልም ለመላው አፍሪካ ያጋባው የሕዳሴው ግድብ ዳግማዊ ዓድዋ ነው። ካለምንም እርዳታና ብድር በዜጎች አበርክቶና በመንግስት በጀት እየተገነባ ያለ ተምሳሌታዊ ብሔራዊ ፕሮጀክት ነው። እስካሁን ከ163 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገለት ሲሆን የሲቪል፣ የኤሌክትሪካልና የብረታ ብረት ገጠማው የስራ አፈጻጸም ከ83 በመቶ በላይ ደርሷል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ሁለተኛ ተርባይንን የኃይል ማመንጨትን ካስጀመሩ በኋላ ባስተላለፉት ጥልቅና ወካይ መልዕክት፤ “በታሪክ ውስጥ ማለፍና ታሪክ ሠርቶ ማለፍ የሚባሉ ሁለት ነገሮች አሉ። በታሪክ ውስጥ ማለፍ ዕድል፣ ታሪክ ሠርቶ ማለፍ ግን ዕድልም ድልም ነው። ይሄ ትውልድ በዓባይ ግድብ ጉዳይ ባለ ዕድልም ባለ ድልም ነው። የሺ ትውልድ ጥያቄ በሚመለስበት ዘመን ተገኝቶ ግድቡ ሲገደብ በዓይን ማየት፣ በእጅ መዳሰስ፣ በእግር መርገጥ ባለ ዕድል ሲያደርግ፤ ለግንባታው ገንዘባቸውን፣ ዕውቀታቸውንና ጉልበታቸውን ከለገሡት፣ በዲፕሎማሲና በሚዲያ ለዓባይ ከሚከራከሩት፣ ታሪክ ሠሪ ጀግኖች ወገን መሆን ደግሞ ባለ ድል ያደርጋል። እነሆ አሁን የሕዳሴ ግድብ ከንድፍ አልፎ፣ ግንባታው ተገባድዶ፣ ግዙፍ ውኃ በጉያው ይዞ ኃይል ማመንጨት ጀምሯል። ዛሬ ዓባይ ተረት ሳይሆን የሚጨበጥ እውነት ነው፤ ከዘፈን-እንጉርጉሮ ወጥቶ ኢትዮጵያን በብርሃኑ ሊያደምቃት፣ ኃይል ሆኖ ሊያበረታት ከጫፍ ደርሷል። በፈጣሪ እርዳታና በኢትዮጵያዊ ወኔ ሙሉ በሙሉ ግንባታውን አጠናቅቀን የልባችን እንደሚሞላ አልጠራጠርም። እንኳን ደስ ያለን!!”ብለዋል።
የሽብር ቡድኑ በአፈ ቀላጤዎቹ በኩል የዛሬ ሶስት አመት የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ተሽጧል እያለ ሲያናፋ፤ ኢትዮጵያውያን ግን የመጀመሪያውን የውሃ ሙሊት ሐምሌ 15 ቀን 2012 ዓ.ም 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ እንዲይዝ አድርገዋል። ሁለተኛው የውሃ ሙሊት ደግሞ ባለፈው ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም 13 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ በመያዝ ተጠናቋል። ሟርተኛውና አሸባሪው ሕወሓት ተሽጧል ያለው ይህ አገራዊ ግዙፍ የብርሃን እሸት የምስራች እንካችሁ ብሏል። ካለፈው የካቲት 13 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአንድ ተርባይን ብቻ 275 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት ጀምሯል። የሁለተኛው ተርባይን ደግሞ ባለፈው ሀሙስ 275 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ጀምሯል። ሶስተኛው የውሃ ሙሊት ደግሞ በበነጋው ዓርብ ተጠናቋል። ግድቡ የያዘው የውሃ መጠንም ወደ 22 ቢሊየን ሜትር ኩብ አድጓል። የቀሪዎቹ ተርባይኖች ገጠማ፤ የግድቡ ግንባታና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎችም በሁለት አመት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 3ኛ ዙር የውሃ ሙሌት ባለፈው ዓርብ ረፋድ በድል መጠናቀቁን በግድቡ ቦታ ተገኝተው ሲያበስሩ፤ “የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ ደስ የሚያሰኝ ታላቅ ድል ነው። ሆኖም ዓባይ ለኢትዮጵያ ብቻ የተሰጠ ሳይሆን ለዓለም ተሰጥቷል።” ብለዋል፤ በክቡር ጠቅላይ ሚንስትር አመራር ግድቡ ገጥመውት የነበሩ ስር የሰደዱ ብልሹ አሰራሮች፣ ሙስናና ደካማ የኮንትራት አስተዳደር ተለይተው የእርምት እርምጃ መወሰዱ ታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ከክሽፈትና ከለየለት ውድቀት ከመታደግ አልፎ ለኢትዮጵያውያን እራትና መብራት ሊሆን ሁለተኛ እሸት አቅምሷል። የግብፅን የሱዳንን የአሜሪካና የምዕራባውያንን የአረብ ሊግን አለማቀፍ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ጫናን በጥበብና በማስተዋል በመቋቋም እና ግብፅ የግድቡን ጉዳይ የዓለም የደህንነትና የሰላም ስጋት አድርጋ ለማሳየት መጀመሪያ ራሷ በኋላ በአረብ ሊግ አይዞሽ ባይነት ቱኒዚያን በመጠቀም ጉዳዩን ከአፍሪካ ሕብረት በማውጣት ወደ መንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አጀንዳነት ለማሳደግ ያደረገችው ጥረት አገራችን በጥብቅ ዲፕሎማሲያዊ ዲስፕሊንና በጥበብ በተመራ ዓለም አቀፍ ግንኙነት አገራትን ከጎኗ በማሰለፍ የተደገሰላት ደባ እንዲከሽፍ ከማድረጓ ባሻገር የግድቡ ጉዳይ የተፋሰሱ አገራትና የአፍሪካ ሕብረት እንጂ የመንግስታቱ ድርጅት አለመሆኑን ማረጋገጥ ችላለች።
ድርድሩም ለሁለተኛ ጊዜ ወደ አፍሪካ ሕብረት ተመልሷል። ምንም እንኳ ግብጽና ሱዳን ሰበብ አስባብ እየደረደሩና ፍላጎታቸውን በሌላ መንገድ ለማራመድ ላይ ታች እያሉ ቢሆንም። ጣልቃ ለመግባት አሰፍስፈው የነበሩ ምዕራባውያንም እርማቸውን እንዲያወጡ አድርጋለች። ሆኖም ዛሬም ሆነ ጥንት ግብፅ አልተኛችልንም። ዓባይን ከመነሻው ለመቆጣጠር ከ11 ጊዜ በላይ ልትወረን ልታስገብረንና ቅኝ ልትገዛን ሞክራ እንዳልተሳካላት የታሪክ ድርሳናት ያትታሉ። በዲፕሎማሲው መድረክ ብትረታም በሱዳን አማካኝነት የውክልና ጦርነት ከፍታ መሬታችንን አስወርራለች። አገርን ለከዱ ጡት ነካሾች የገንዘብ የጦር መሳሪያ የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ድጋፍ በማድረግ አገራችንን ወደ ለየለት ቀውስና ትርምስ ለመክተት ቀን ከሌት እየሰራች ነው። ይህን የተገነዘቡ ኢትዮጵያውያንም ልዩነታቸውን ትተው በአንድነት አገራቸውን ከውስጥ ተላላኪዎችና ከውጭ ጥቃት ለመከላከል ቀፎው እንደተነካ ንብ በአንድነት ተነስተዋል።
ግድቡ በአሁኑ ሰዓት ከ22 ቢሊዮን ሜትር ኩብ በላይ ውሃ በመያዝ ራሱን መከላከል የሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ግብፅ ለዘመናት ኢትዮጵያ ሰላም ሆና አንድነቷ የሚጠናከርና ልማቷም የሚፋጠን ከሆነ አባይን ጨምሮ ገና የውሃ ሀብቷን ታለማለች በሚል በስጋት ላይ ያነጣጠረ ስጋት ከውስጥ ተላላኪዎቿ ጋር በመሆን ኢትዮጵያውያንን ለመበታተን ሰርታለች። በወንዝ በጎጥ የተከፋፈለች ደካማ አገር እንድትሆን ሌት ተቀን ሰርታም በተወሰነ ደረጃም ተሳክቶላታል። ዛሬም አሸባሪውን አልሻባብን ፣ ሕወሓት ሸኔንና ሌሎች ቅጥረኛ ምንደኞችን ተጠቅማ ከውስጥ እየወጋችን ነው ። ሆኖም የግብፅና የተላላኪዎቿ የቀን ቅዠት በጀግኖች ልጆቿ ይመክናል። እየመከነም ይገኛል። ሰሞኑን በምስራቁ የአገራችን ክፍል በሱማሌ ክልል በአልሻባብና በጭፍሮቹ ላይ የተወሰደው የማያዳግም እርምጃ ለዚህ ጥሩ አብነት ነው።
አይደለም ዛሬ ሶስተኛ ዙር ግድባችንን ሞልተን፣ ሁለተኛ የብርሃን እሸት ቀምሰን፤ ያለአንዳች ኮሽታ ብሔራዊ ምርጫ አካሂደንና በሚያስገርም ሁኔታ በአገራችን ተደቅኖ የነበረን ቀውስ ቀልብሰን፤ ከሶስት አመት በፊት በሴራ ፖለቲካ፣ በተላላኪውና በባንዳው የትህነግ ገዢ ቡድንና ተባባሪዎች ደባ በየእለቱ ቅርጹንና ይዘቱ እየቀያየረ በሚቀፈቀፍ ቀውስ መሀል ሆነን የጀመርነው አንደኛው የውሃ ሙሊት ዛሬ 3ኛ ዙር ደርሷል። ከዚህ በኋላ የሚቀሩን ሙሊቶችም ያለ ምንም ስጋት ይከናወናሉ። በዚህም ቅኝ ካለመገዛት ጋር ብቻ ተያይዞ የነበረውን ነጻነትና ሉዓላዊነት በኢኮኖሚያዊ በብልጽግና ለመድገም ጉዞዋን ጀምራለች። በድህነትና በተመፅዋችነት አንገታቸውን ደፍተው የነበሩ ዜጎች አንገታቸውን ቀና አድርገው በኩራት እንዲራመዱ የሚያደርግ ብሔራዊ (ፍላግሺፕ)ፕሮጀክት ባለቤት መሆን ችላለች።
ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ እንዳሉት በድህነትና በኋላ ቀርነት የሚማቅቅ ሕዝብ የተሟላ ሉዓላዊነት ሊኖረው አይችልምና። ስንዴ እየለመኑ፣ እየተመጸወቱ ሉዓላዊነቷን ያላስደፈረች፤ በነጻነት ታፍራና ተከብራ የኖረች ብሎ መመጻደቅን ድሉን ሙሉኡ አያደርገውም። መቼም አሸባሪው ትህነግ ለዘረፋና ለስልጣን ሲል የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ በመስጠትና በሌብነት ጥርሱን የነቀለበት ስለሆነ እሱ እንደሚያደርገው ግድቡ ተሸጧል ቢል የሚያስገርም አይደለም። እሱ ሽጦት ስለነበረ አይደል ለአጠቃላይ ክሽፈት አንድ ሐሙስ ቀርቶት እያለ የለውጥ ኃይሉ ደርሶ የታደገው። በረሀብ ለተጎዱ ትግራዋይ ተልኮ እንደነበረው ስንዴ ከአንዴም ሁለት ሶስቴ ሽጦት የነበረውስ እሱ ራሱ ሕወሓት ነው። እንጨት ሽጣ ከልጆቿ ጉሮሮ ቀምታ መቀነቷን ፈታ የሰጠችውን ገንዘብ ከመስረቅ በላይ ግድቡን መሸጥ ምን አለ። ተራ የመጠጥ ውሃ ኤሌክትሮ ሜካኒካል እንኳ በቅጡ ገጥሞ ለማያውቅ፤ በብልሹ አሰራርና በሙስና ለበሸቀጠው ሜቴክ ያለ ጨረታ ከመስጠት በላይ ግድቡን መሸጥ ምን አለ?።
ያው ሁላችን እንደምናውቀው የትህነግ እፉኝት ቡድን ለፖለቲካዊ ጥቅምና ስልጣን ሲል ወላጅ እናቱንም ሆነ አገሩን እንደ አስቆርቱ ይሁዳ ከመሸጥ አይመለስም። ለትህነግ ፖለቲካ ማለት ብሔራዊ ጥቅምን አሲዞ መገበያየት፣ የንግድ ውል መፈጣጠም (Transactional) ነው። በዚህ የልቡና ውቅር (ማይንድሴት) ነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ተሽጧል ሲል የነበረው። በፈጸመው ግፍና ክህደት በሰራው ስህተት በተናገረው ውሸት ወዘተረፈ ጸጸት የማያውቅና ያልፈጠረበት ሆኖ እንጂ ዛሬ ላይ በጸጸት ጸጉሩን በነጨ። እሱ እቴ ይገረማችሁ ብሎ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እወርዳለሁ ያለ ጉድ እኮ ነው።
ሆኖም መጀመሪያ ሁለተኛውና ሶስተኛው የሕዳሴው ግድብ ውሃ ሙሊት፤ አሁን ደግሞ 2ኛው ዩኒት ኃይል ማመንጨት መጀመሩ የቀጣናውን ጂኦፖለቲክስ እንደ አዲስ በይኖታል። የግብፅን የውሃ ዲፕሎማሲና ፖለቲካም ከንቱ አድርጎታል። ለዚህ ነው ዛሬ አሸባሪውን አልሻባብና ሕወሓት ተጠቅማ አገራችንን ለመበቀል ሌት ተቀን እየሰራች ያለችው። ሱዳንን ግፊ የምትለው። ከ100 ሺህ በላይ ዜጎቻችን ከሳኡዲ አረቢያ መብታቸው ተገፎና ሰብዓዊ ክብራቸው ተዋርዶ እንዲወጡ ያሴረችው። የቀሩት በሳውዲ ማጎሪያዎች ታስረው እየማቀቁ ያሉት። ሆኖም ውሾች እየጮኹ ግመሉ ጉዞውን ያለማቋረጥ ቀጥሏል።
አገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ፈጣሪ አብዝቶ ይባርክ ! አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ነሐሴ 8 /2014