
ስኬት የበርካታ ትግል ፍሬ ነው፤ ስኬት ለላቀ ለውጥና ከፍታ እንደ መስፈንጠሪያ አንጓም ነው፤ ስኬት የትናንት ልፋት፣ የዛሬ እረፍት እና የነገ የተሻለ ሕልም የተጋመዱበት ህያው የሰው ልጆች የከፍታ ማማ ነው:: በተለይ ደግሞ የስኬት ጉዞው በውስብስብና በበዙ ፈተናዎች ውስጥ ታልፎ ሲገኝ እጅጉን የሚያኮራ ብቻ ሳይሆን፤ ስለነገው የላቀ የከፍታው የስኬት ሰገነት ላይ ለማረፍ ለሚደረገው ትግልና ጥረት ስንቅ ሆኖ ያገለግላል:: ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያውያን እንደ ምስክርም፤ እንደ አብነት ሊጠቀሱ ተገቢ ነው:: እንዴት ቢሉ፤ ከብዙ በጥቂቱ እንዲህ ብሎ ማንሳት ይቻላል፡-
የመጀመሪያው ጉዳይ ኢትዮጵያውያንን ስኬታማና የስኬታማነት ማሳያ የሚያደርጋቸው የግዛት ነጻነታቸው ነው:: ይህን ነጻነታቸውን በቀልድ አላገኙትም፤ ይልቁንም በደምና ሕይወት ዋጋ ከሶስት ሺህ ዘመን በላይ ይዘው የዘለቁት እንጂ:: የመጀመሪያው ድላቸው ለሁለተኛው አቅም እየፈጠረ፤ የቀደሙቱ ለተከታይ ልጆቻቸው ጀግንነትና ድል አድራጊነትን እያወረሱ፤ የነጻነታቸውን የስኬት መንገድ ሳያዛንፉ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ነጻነት ለናፈቃቸው ሕዝቦች ሁሉ ምሳሌ ሆነው እነሆ ዛሬም አሉ::
ይሄ ስኬታማ የነጻነት ጉዟቸው ደግሞ ለሌሎች ድሎቻቸውና የስኬት መንገዶቻቸው ፈር ቀዳጅ ሆኖ አገልግሏቸዋል:: ምክንያቱም ኢትዮጵያ ስትባል ያልተደፈረች ታላቅ አገር መሆኗ በዓለም መገለጡ፤ ኢትዮጵያውያንም አገርን ሳያስደፍሩ፣ ወገንን ቅኝ ሳያስገዙ በአሸናፊነት የስኬት መንገድ ላይ ጸንተው የቆሙ ሕዝቦች ሆነው መታየታቸው ትውልዱ ከአሸናፊነት ሌላ ማሰብን እንዳይለምድ አድርጎታል:: የዚህ አንዱ ማሳያ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ደጋግማ የነገሰችበት ስፖርት በተለይም አትሌቲክስ ነው:: የኢትዮጵያውያን አትሌሎች በተሳተፉባቸው መድረኮች ሁሉ ድል አድርገው ሰንደቃቸውን ከፍ ባደረጉ ጊዜ ማንባታቸው፤ በውድድር ሂደቱም ስለ አገር አሸናፊነት እንጂ ስለ ግል ሜዳልያ ባለቤትነታቸው ሳይሳሱ ተባብረው የአረንጓዴ ጎርፍ ስማቸውን መትከላቸው የዚህ ያለመሸነፍ ሰብዕና ገጻቸው ነው::
ይህ በነጻነት የነገሰው ማንነት በአትሌቶቻችን ልብና ማንነት ላይ የፈጠረው አዎንታዊ ገጽ ቢኖርም፤ የኢኮኖሚ ነጻነቷ ያልተረጋገጠ አገርና ሕዝብ ሙሉ ነጻነቱ ተረጋግጧል፤ ስኬታማ መንገዱም ከሚፈለገው ቦታ ላይ አርፏል ማለት አይቻልም:: ለዚህም ነው የዘመናት ሕልማችን የነበረውን ዓባይ ገድበን ወደ ኤሌክትሪክ መለወጥ የቻልነው፤ ከስንዴ ጥገኝነታችን ለመላቀቅም እጅን በአፍ ያስጫነ የስንዴ ልማት ስራ ውስጥ የገባነው፤ ዓለም እየተፈተነችበት ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ታሳቢ በማድረግም ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ነድፈን በአራት ዓመት ከሃያ ቢሊዮን በላይ ችግኝ መትከል የቻልነው::
እነዚህን ተግባራት ጀምረን ለስኬት ስናበቃ ግን ያለ ችግር አልነበረም:: ይልቁንም በውስጥ ባንዳዎች፣ በውጭ የኢትዮጵያን እድገትና ብልጽግና የማይሹ ታሪካዊ ጠላቶች እጅጉን የበረታ ፈተና ገጥሞን፤ አገር የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ እስከመግባት የደረሰችበትን አስጨናቂ ሁኔታ ጭምር ተቋቁሞ በማለፍ እንጂ:: የሕዳሴው ግድብ ዛሬ ላይ ሶስተኛ ዙር ውሃ ሲይዝ እና ሁለት ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት ሲጀምሩ፤ የግብጽን ሁሉን አቀፍ የማደናቀፍ ሩጫ በማክሸፍ፤ የአሸባሪው ሕወሓት ዘመን የብዝበዛና የዘረፋ ተግባር ታሪክ በማድረግ፤ የሕዝቦችን ያልተቋረጠ ድጋፍ በማስቀጠልና ኃይል በማድረግ ነው:: የስንዴ ልማትና የአረንጓዴ አሻራ ስራዎችም ቢሆኑ፤ ከሰላምና ጸጥታ ጋር ተያይዘው የተስተዋሉ በርካታ ፈተናዎች ውስጥ በተደረገ ትጋት ነው::
እነዚህ በፈተና ውስጥ የተገኙና እየተገኙ ያሉ ስኬቶች፣ ከስኬትነት ባለፈ ዛሬ ላይ ከችግሮች እንዴት ከፍ ብሎ ውጤት ማግኘትን፤ ውጤትና ስኬቶችንም እንዴት ለችግሮች መሻገሪያ ማድረግ እንደሚቻል የሚያስተምሩ ናቸው:: ለምሳሌ፣ የህዳሴው ግድብ ከነበረበት ችግር ተላቅቆና የእነ ግብጽና ግብራበሮቿን ሴራ አሸንፎ የመጀመሪያ ዙር ሙሌት ሲከናወን የነበረው ስሜት ኢትዮጵያውያን የነበረባቸውን ወቅታዊ ችግር መሻገሪያ ሃይል ሆኖ ነበር:: ሁለተኛው ዙር ውሃ ሲያዝና የመጀመሪያው ተርባይን ሃይል ማመንጨት ሲጀምር ደግሞ በሕልውናቸው ላይ የተደቀነው አደጋ ሳይበግራቸው ደስታቸውን የገለጹበት፤ የሕልውና አደጋ የሆነባቸውን ሃይል በአንድ ተሰባስበው እንዲያስወግዱ ያጎናጸፋቸው ብርታት ቀላል አልነበረም::
ይህ ሁሉ ሆኖ እያለም፤ ዛሬም ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን በበዛ ፈተና ውስጥ ይገኛሉ:: የሰላምና ጸጥታ ስጋትን የደቀኑ በርካታ ገፊ ምክንያቶችን አሸንፎ መውጣት የዚህ ዘመን የቤት ሥራ ነው:: የኢኮኖሚ እድገትን አስመዝግቦ የዳቦ ጥያቄን መመለስና እንደ ቋጥኝ የተጫነውን የኑሮ ውድነት ማሸነፍ ተደማሪ ሸክም ሆኗል:: በዘርና ሃይማኖት በመከፋፈል ኢትዮጵያውያንን ነጣጥሎ አገር ለመበተን እየሰሩ ያሉ ድኩማንን አደብ ማስያዝና በህብረ ብሔራዊነት የተገነባ አንድነትን ይዞ መዝለቅም ሌላው አቅምም፣ ስሜትም የሚፈትን ጉዳይ ነው::
በዚህ ረገድ አትሌቶቻችን በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ እንዲሁም ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ላይ ያስመዘገቡት ድልና ስኬት ትልቅ አቅምና ስንቅ ሆኖናል:: ይሄ አቅማችን ሳይደክም፣ ስንቃችንም ሳይመነምን ዛሬ ደግሞ በግብርናው ስንዴን በማምረት፤ በሕዳሴው ግድባችን ደግሞ ተጨማሪ ኃይል በማመንጨት ስኬታችንን ከፍ አድርገናል:: በዚህም አገራዊ ስሜታችንን አሙቀን አንድነትና ብርታትን ተጎናጽፈናል:: ለነገ የብልጽግና ጉዟችንም ተጨማሪ ጉልበት ሰጥተውናል:: እዚህጋ ልንገነዘበው የሚገባው ጉዳይ ግን፤ በዚህ መልኩ በየዘርፉ የምናገኛቸው ስኬቶች ከስኬትም በላይ መሆናቸውን ነው::
ምክንያቱም እነዚህ ስኬቶች ፈተናዎችን አሸንፈን ያስመዘገብናቸው፣ ዳግም ያለመንበርከክ ጉዟችን ቀጣይነት ማሳያዎች ናቸው:: እናም ችግሮች ከስኬት መንገዳችን የማያግዱን፤ የጥፋት መልዕክተኞች የሴራ ትብብር ከጉዟችን የማያስቀሩን መሆናቸውን ያረጋገጥንባቸው ናቸው:: ሆኖም ይህ የአሸናፊነት ጉዞ ያደረሰን የስኬት ደረጃ በቂ አይደለም፤ እናም የብልጽግናችን ዋስትና የሚሆኑ ሌሎች ታላላቅ ስኬቶችን ማስመዝገብ የግድ ይላል:: ይሄ ደግሞ እንደ ትናንቱ ሁሉ ፈተና የማያጣን፤ ይልቁንም በስኬት ጉዞ ከፍታችን ልክ ከፍ ያሉ ችግሮች የሚገጥሙን መሆኑ እሙን ነው:: ለዚህ ደግሞ ትናንት ችግሮችን የተሻገርንባቸውን ልምዶች በመቀመር፤ በችግሮች ውስጥ ሆነን ያስመዘገብናቸውን ስኬቶች የነገ ችግሮቻችን መሻገሪያ አቅም አድርገን ልንጠቀምባቸው ይገባል:: ይሄን ስናደርግ ስኬቶቻውን ዘላቂ፤ ብልጽግናችንም እውን ይሆናሉ::
በየኔነው ስሻው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 8 /2014