
ባለፈው ማክሰኞ ለብሔራዊ ምርጫ ድምጻቸውን የሰጡት ኬንያውን ውጤቱን በጉጉት እየተጠባበቁ ነው። የድምጽ ቆጠራው አሁንም እየተካሄደ ባለበት በአሁኑ ወቅት ለፕሬዚዳንትንት የቀረቡት ዋነኛዎቹ ዕጩዎች በጠባብ የድምጽ ልዩነት እየተፎካከሩ ነው።
በአፍሪካ ጠንካራ ምጣኔ ሀብት፣ የፍትሕ እና የምርጫ ሥርዓት እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን ካላቸው ጥቂት አገራት መካከል አንዷ በሆነችው ኬንያ የሚካሄደው ምርጫ ውጤት ከአገሪቱ ባሻገር በአህጉሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ትኩረትን የሚያገኝ ነው።
22 ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ በመራጭነት የተመዘገበበትና 14 ሚሊዮኑ ድምጹን በሰጠበት በዚህ ምርጫ ኬንያውያን ለፕሬዚዳንት፣ ለግዛቶች አስተዳዳሪዎች፣ የብሔራዊ እና የአካባቢያዊ ምክር ቤቶች አባላትን ለመምረጥ ድምጽ ሰጥተዋል። ከዚህ መካከል ከፍተኛ ትኩረትን የሳበው ግን አገሪቱን ለቀጣይ አምስት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ለመምራት የሚደረገው ፉክክር ነው።
ይህ ፉክክር በዋናነት በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት በሆኑት ዊሊያም ሩቶ እና በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መካከል የሚደረገው ፉክክር ከባድ እንደሚሆን ቀድሞም ተጠብቆ ነበር። በሁለቱ ግዙፍ ፖለቲከኞች መካከል ያለው ፉክክር ግጭትን እንዳያስከትል የብዙዎች ስጋት ሲሆን፣ አስካሁን በነበረው ሁኔታ ግን ይህ ነው የሚባል የጎላ የፀጥታ ችግር በተፎካካሪዎቹ ደጋፊዎች መካከል አልተከሰተም።
ነገር ግን ድምጽ ተሰጥቶ ቆጠራው ከተጀመረ ሁለተኛው ቀን ቢሆንም እስካሁን ሩቶ እና ራይላ ከመራጮች ባገኙት ድምጽ ግልጽ የበላይነት ማግኘት አልቻሉም። በምርጫው ድምጽ ከሰጡት መራጮች መካከል ወደ ግማሽ የሚሆነው ድምጽ የተቆጠረ ቢሆንም ልዩነታቸው ጠባብ የሚባል በመሆኑ ኬንያውያን ውጤቱን በጉጉት እየጠበቁ ነው።
በርካታ ሚሊዮኖች ለቀጣዩ አምስት ዓመታት አገራቸውን የሚመራውን ፕሬዚዳንት መርጠው ውጤቱን እየተጠባበቁ ይገኛሉ። የኬንያ የምርጫ ኮሚሽን ሊቀ መንበርም ምርጫ ከተደረገበት ማክሰኞ ነሐሴ 03 እስከ ቀጣዮቹ ሰባት ቀናት ድረስም የምርጫውን ውጤት ማሳወቅ እንደሚኖርባቸው የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል።
አዲስ ዘመን ነሐሴ 6 /2014