ለምን እንደሆነ አላውቅም አራት ሰአት አለፍ ሲል ይደብተኛል ድብርቴን የምሸሸው የሆረር ፊልም በማየትና በደረቴ በመተኛት ነው የዛሬውም አራት ሰአት እንደተለመደው ምርግ ነበር አብሮኝ ከሚኖረው ፍታወቅ ጋር አዋተን በገዛናት ፍራሽ ላይ በደረቴ ተኝቼ የረፋድ ድብርቴን አጎንብሼ አሳልፋለው በጣቴ መሬት እየጫርኩ የማላውቀውን ነገር ማዲያው ላይ እጽፋለው በዚህ መሀል ስሜን ከውጪ ሲጠራ ሰማሁት.. ሮቤል? አንተ ሮቤል?
ነፍሴ ሳቀች.. ጀምበር ፈንጥቃ ስፍራዋን ለረፋድ ስትለቅ ማንም የማያስቀኝ ሰው ነበርኩ ከሰአት እስኪሆን ማለዳ በጉያው ውስጥ የሸሸገው የአራት ሰአት አጋንት ከላዬ ላይ ጮሆ እስኪወጣ ድረስ ማንም የማያዝናናኝ ሰው ነበርኩ ለዘመናት የተላመድኩት ድባቴዬ የት እንደገባ ሳላውቀው በሄመን ድምጽ ነቃሁ ‹ሮቤል.. አንተ ሮቤል? ድምጽዋ ወዳለሁበት እየቀረበ መጣ ከአልጋዬ ላይ እንዴት እንደተፈናጠርኩ አላውቅም ራሴን በሩ ላይ አገኘሁት እኔ ስወጣ እሷ ስትገባ ተጋጨን መቼም የማይደገም ግጭት አይኖቼን የት ላድርጋቸው? አፈርኳት ፊት ለፊቴ በግንባሬ የተገጨ ግንባሯን እያሻሸች ቆማለች አይኖቿ የእፍረት ዝናር ታጥቀው ያዩኛል ጡቶቿ በስስ የቤት ውስጥ ፒጃማ ተወድረው ደረቴ ላይ ተነጣጥረዋል ከንፈሯ ሩብ ያህሉ በጥርሶቿ በቄንጥ ተነክሶ ተደቅኖብኛል አይኖቼን የት ላድርጋቸው?
መደናበሬን አይታ ይሆን እንጃ ‹ቤት ማንም የለም ናና ተጫወት› ብላኝ ወደ ቤት ተመለሰች
ከበሩ ላይ አልተንቀሳቀስኩም ፊልም የሚመስለውን አጋጣሚ በአእምሮዬ እየመለስኩ ቆሜአለው ቆይቼ ሳስበው ከመጋጨትም በላይ የሆነ ነገር ያስተናገድን ይመስለኛል ደረቴ ላይ አሁንም ድረስ የሚሰማኝ ደስ የሚል የውጋት ህመም አለ.. በጡቶቿ የተወጋሁት ጉንጬ ላይ ጸጉሯ የገረፈኝ አንዳች የሚያክል ሰንበር አለ ራሴን በመስተዋት ሳየው ቀይ የከንፈር ቀለም ከንፈሬ ላይ ተለጉዶ ነበር ይሄ እንዴት ሆነ? ደስ የሚል የሚያሳፍር ሳቅ ሳኩኝ ሰው እንዴት በአንድ ጊዜ ደስ የሚልና የሚያሳፍር ሳቅ ይስቃል? ሄመንን አፈርኳት መንገድ ላይ ስንገናኝ ለመሳሳም የተቀጣጠርን እንጂ ለመጋጨት የተገናኘን አንመስልም ነበር
አንዳንድ ቀኖች አሉ.. የሰው ልጅ አስቦና ተዘጋጅቶ የማይደግማቸው አንዳንድ አጋጣሚዎች አሉ እንዴት እንደመጡ፣ እንዴት እንደሆኑ ታስቦ የማይደረስባቸው ከሄመን ጋር የተጋጨንበትን የዛሬውን ቀን ጻፍኩት መቼም እንዳይረሳኝ ስለምፈልግ
እፎይ ብያለው.. መቼም እንደዛሬ እፎይ ብዬ አላውቅም አንዳንድ ድምጾች አሉ ከሕይወት እስራት፣ ከመኖር ስብራት ነጻ የሚያወጡ አንዳንድ አንደበቶች አሉ ከካህን አፍ ጥመው ለጆሮ የሚጣፍጡ አንዳንድ ቀኖች አሉ ሚሊዮን ዘመነ ፍዳን ሽረው አርነት የሚያወጡ እንዲህ ባለው የድባቴ ጊዜ ውስጥ ድንገት ተከስተው ወደ ገነት የሚወስዱኝ አንዳንድ ድምጮች አሉ.. የሄመንን አይነት ድምጽ ነፍሴ ሳቀች በሕይወት ውስጥ ነፍስ የምትስቅበት ቅጽበት አለ እላለሁ .. ለእኔ ያ ቅጽበት የሄመን ጥሪ ነው ለእኔ ያ ቅጽበት ቆንጆ ሴት በርህን ቆርቁራ ካለህበት ስትመጣ ነው ዓለም ከነግሳንግሷ ከፊቴ ላይ ገለል ያለችልኝ ሄመን ስትጠራኝ ነው
ተነስቼ ወደነ ሄመን ቤት ሄድኩ ሁሌ እንዲህ እንደአሁኑ ቤት ብቻዋን ስትሆን ትጠራኛለች እንደ እኔ አራት ሰአት ይደብራት ይሆን አላውቅም ብዙ ቀን ደብቶኝ በተኛሁበት የአራት ሰአት ማግስት ላይ ጠርታኝ ቤት ሄጄ አውቃለሁ እነሄመን ቤት ከተከራየሁ ስምንተኛ ወሬን ይዣለሁ በወር አንድ ጊዜ የሚመጣ ፍታወቅ የሚባል ጓደኛ ቢኖረኝም አብሮኝ እንዳለ አልቆጥረውም እሷም ይሄን ብቸኝነቴን ስለምታውቅ ነው መሰለኝ ቤተሰቦቿ ወጣ ሲሉ መጥህ ተጫወት ብቻዬን ነኝ ትለኛለች
ቤት ስገባ ለስለስ ያለ ሙዚቃ ተቀበለኝ.. ዛሬም ሚኪያ እየዘፈነች ነው ሁሌ እዛ ቤት ጠርታኝ ስሄድ በሚኪያ በላይነህ ሙዚቃ ነው የምትቀበለኝ እዛ ቤት የሚኪያ በላይነህ መብዛት አልገባህ እንዳለኝ ወደ ሳሎን አቀናሁ ሄመን ከሙዚቃው ጋር አብራ እየሞዘቀች ቅድም በተላተምኩበት ፒጃማዋ አገኘኋት
‹ምነው ብቻሽን.. እነማዘር የት ሄደው ነው? አልኳት ድምጼን አጥፍቼ ከምገባ ብዬ
‹ማዘር ክፍለ ሀገር ሄዳለች…
‹እና ብቻሽን ነሻ!..
‹አዎ ሰሞኑን ብቻዬን ነኝ…› አለችኝ በሚያሳዝን ድምጽ ድምጽዋ ውስጥ ከብቸኝነት የገዘፈ ሌላ ብቸኝነትን አደመጥኩ እኔ ሆኜ እንጂ ፍታወቅ ቢሆን ከዚህ ንግግሯ ውስጥ ብዙ እውነቶችን መዞ ያወጣ ነበር ብዙ ጊዜ ነገር አይገባህም ይለኛል እሱ ብቻ አይደለም እስከዛሬ የተዋወኳቸው ሴቶች ነገር አይገባህም ሲሉኝ አድምጫለው የሄመን ‹ሰሞኑን ብቻዬን ነኝ› ማለቷ ከወሬ ባለፈ ምን ማለት እንደሆነ ሳይገባኝ ዝም አልኩ ወር ሙሉ ከአጠገቤ ሲርቅ ያልናፈቀኝ ጓደኛዬ በአይኔ ላይ አንጃበበ
‹አባዬም እንደምታውቀው በስራ ምክንያት አምሽቶ ነው የሚገባው..› ሳልጠይቃት ነገረችኝ ይሄን ብላ ትታኝ ወደሚቀጥለው ክፍል አመራች ምሳ እየሰራች እንደሆነ ከሚሰነፍጠኝ የወጥ ሽታ ተረዳሁ ማዕድ ቤቱ ከሳሎኑ ፊት ለፊት ስለሆነ እንቅስቃሴዋ ሁሉ ይታየኛል እኔ ሳሎን ሶፋ ላይ ሆኜ እሷ ማዕድ ቤት ሆና እስኪበቃኝ ቀላወጥኳት
ቤት ጠርታኝ የሆነ የምወደውን ነገር ሳታደርግልኝ ቀርታ አታውቅም ሁሌም አዲስ ነገሬ ናት ማዕድ ቤት በስስ ፒጃማዋ ውስጥ የማይታየኝ ነገር የለም እንደ ጣዝማ ማር የጠየመ ገላዋ የጠለለ የምንጭ ውሃ ይመስል ነበር ቀይ ፓንት፣ ጥቁር ጡት ማሲያዣ ደረቷንና ወገቧን ዞረው ሳይ ሀጢአት ተሰማኝ እዛ ቤት ስገባ የማያቸው የሁልጊዜም ትዕይንቶቼ ነበሩ ብዙ ጊዜ አትገባኝም.. የማልረዳት ሴት ናት ለምንና እንዴት እንደምታስበኝ ሳላውቅ በምትሆነው መሆን እጨነቃለሁ ቆይ አንድ ሴት ለአንድ ወንድ እህት ብቻ መሆን አትችልም? እኛ ወንዶች ሴት ልጅ ለፍቅር ብቻ ነው የቀረበችን ብለን እንድናስብ የሚያደርግ የተሳሳተ ሶፍት ዌር የጫነብን ማነው?
በእጇ ምሳ ይዛ ወደሳሎን ተመለሰች የዛሬ አዲስ ነገር አብሬአት ምሳ መብላት ነው ከእሷ ጋር ምሳ መብላት ምን እንደሚመስል ዛሬ ላየው ነው እስከዛሬ ቤታቸው ሄጄ በቻዬን ነበር ስበላ የነበርኩት ከእሷ ጋር መብላትን በእለተ ሀሙስ ከጌታ ጋር በአንድ መዐድ ከመቀመጥ ጋር አገናኘሁት ሳላውቀው ሄመንን እንደ እህት አምኖ መቀበል እየከበደኝ መጣ አውቃም ይሁን ሳታውቅ የምታደርገው ነገር ወደማላውቅ ደስታ እየወሰደኝ ነው
እጄን አስታጥባኝ የመጀመሪያውን ጉርሻ ወደ እኔ ስትሰነዝር የሆንኩትን አረሳውም ጉርሻዋ ብርቅ ሆኖብኝ ለረጅም ጊዜ አላመጥኩት ያን ጉርሻ ወደ ሆዴ ሳልሰድ ቀን ሙሉ እያላመጥኩት ብውል በወደድኩ ነበር ከዛ በኋላ ያልቆጠርኳቸውን ብዙ ጉርሻዎች አጎረሰችኝ ሳላጎርሳት ዝም ብዬ መብላት ጀመርኩ ባልተቀየመ ልብ ማጉረሷን ተያያዘችው
እፎይ አልኩ..
ሕይወት እፎይ ማያ ሲኖራት ምን እንደምትመስል ያን ቀን አወኩ ፍቅር የሕይወት ሱስ ነው.. ሳላውቀው በምታደርግልኝ ነገር ሄመንን ወደድኳት ነፍሷ እፎይ ማያዬ ሆኖ አረፈ..
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ነሐሴ 6 /2014