በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ የያዘው የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ቢሆንም፣ የማዕድን ዘርፉም ለኢኮኖሚ ዕድገቱ ትልቅ ተስፋ አሳድሯል። ዘርፉ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ከፍ ለማድረግ ከሚኖረው አስተዋጽኦ በተጨማሪ ማዕድኑን ለማውጣት ከሚከናወነው የቁፋሮ ሥራ ጀምሮ በሚፈጥረው የገበያ ሰንሰለት ውስጥ ሰፊ ቁጥር ለበርካታ ሰዎች የሥራ ዕድል በማመቻቸት መንግሥት ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያደርገውን ጥረት በማገዝ ድርሻው ከፍ ያለ ነው።
በተለይም የቁፋሮ በጋራ መሥራትን የሚጠይቅ በመሆኑ በማህበር በማደራጀት በቀላሉ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ምቹ ዘርፍ ስለመሆኑም ይገልጻል። ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን በማስገኘት በአገር የኢኮኖሚ ዕድገት ሚና ባለው የማዕድን ዘርፍ ላይ ተሰማርተው ከሚሰሩ ማህበራት መካከል በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ በ2004 ዓ.ም ማህበር መስርቶ ወደ ስራ የገባው ዋርካዬ የከበሩ ማዕድናት አምራችና ግብይት የህብረት ሥራ ማህበር አንዱ ነው።
በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ ውስጥ ፀሐይ መውጫ በሚባል አካባቢ የሚገኘው የዋርካዬ የከበሩ ማዕድናት አምራችና ግብይት የህብረት ሥራ ማህበር መሪ ሊቀ መንበር ደሳለኝ የሞላ እንደሚሉት፤ ማህበሩ በ2004 ዓ.ም በህብረት ሥራ ማህበራት ማደራጃ አዋጅ መሠረት ህጋዊ ሆኖ ተቋቁሞ ወደ ሥራ የገባው በአካባቢያቸው የኦፓል ማዕድን ሀብት መገኘቱን ተከትሎ ነው። ይህን የተፈጥሮ ፀጋ በጋራ አልመተው በሚያገኙት ገቢ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን ለመፍታት፣ አለፍ ብሎም ለአገር ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ ለማበርከት ነው።
ማህበሩ በ25 አባላት ነው የተመሰረተው። አባላቱ የማዕድን ልማት ሥራው በባህላዊ ቁፋሮ የሚከናወን በመሆኑ በወቅቱ ለመነሻ ሥራ የሚሆን ገንዘብ ወይንም ካፒታል ይዘው አልነበረም ወደ ስራው የገቡት፤ እንደ ዶማ፣ አካፋ፣ መዶሻ የመሳሰሉትን ለቁፋሮ ሥራ የሚያስፈልጉ መሳሪያዎች በመያዝ ብቻ ነው ስራውን የጀመሩት። ከልማት ሥራው ዕቅድ አንዱ ተግባር የአባላትን ቁጥር ማብዛት በመሆኑም ማህበሩ ይህን አሟልቷል።
በአሁኑ ጊዜም የአባላቱ ቁጥር ወደ አንድ ሺ ደርሷል። የአባላት ስብስቡም ከ14 አመት በላይ እድሜ ያላቸውን ሁለቱንም ጾታዎች ያካተተ ነው። በማዕድን ቁፋሮ ወቅት በአካባቢው ላይ የሚደርስ ተጽዕኖን ለመቋቋም የአካባቢ ጥበቃ ቢሮውም በማዕድን ማምረት ፍቃድ አሰጣጥ ሂደቱ ላይ ሚናውን ተወጥቷል። በዚህ ሂደት ውስጥ አልፎ ወደ ሥራ የገባው ዋርካዬ የከበሩ ማዕድናት አምራችና ግብይት የህብረት ሥራ ማህበር ከአባላቱ ባለፈ አገርንም የሚጠቅም ተግባር እየተወጣ ይገኛል።
በማዕድን ልማቱ የተገኘውን ጥቅም አቶ ደሳለኝ ከራሳቸው ተሞከሮ በመነሳት ሲገልጹም እሳቸው በትምህርታቸው እስከ ሁለተኛ ደረጃ ድረስ የመማር ዕድል አግኝተዋል።በተለያየ ምክንያት ከዚያ በላይ መዝለቅ ግን አልቻሉም። ለጥቂት ጊዜያትም ያለ ሥራ ተቀምጠዋል።
የሥራ ዕድል የፈጠረላቸው በአካባቢያቸው የተገኘው የማዕድን ሀብት ነው። ማዕድን ቆፍረው በማውጣት ጥሬ ዕቃውን እሴት ጨምረው ለገበያ ለሚያቀርቡ በመሸጥ የተሻለ ገቢ በማግኘታቸው የተሻለ ኑሮ ለመኖር ከተማ ገቡ፤ በዚያም የመኖሪያ ቤትም ገነቡ። ትዳርም መስርተው ቤተሰብ አፍሩ። የኑሮ መሻሻል ለውጡ የተገኘው ግን ከብዙ ድካም በኋላ ነው።
የማዕድን ቁፋሮ ሥራ ካፒታል የሌለውና ወደ ንግድ ያልገባ በመሆኑ ካመረተ በኋላ ሸጦ በሚያገኘው ገቢ ነው ወደ እድገት ወይንም መለወጥ ደረጃ የሚደርሰው። ለውጡንም የሚያገኘው ባስመዘገበው ልክ ነው።
የማህበሩ አባላት ከልማቱ የሚያገኙት ክፍፍልም በተሳትፎ የሚለካ ነው፤ ጠንክሮ የስራ ጥሩ ገቢ ያገኛል። ጠንክረው በመሥራት ከቁፋሮ ሥራ ወጥተው ጥሬ ዕቃውን በማሻሻል ወይንም እሴት በመጨመር በውጭ ንግድ ላይ የተሰማሩ መሥራች አባላት አሉ። አንዳንዶችም እሴት በመጨመር ሥራ፣ ጥሬ ዕቃውን ከአልሚው በመቀበል እሴት ጨምሮ ለገበያ ለሚያቀርበው በመሸጥ፣ በአዘዋዋሪነት ላይ ይገኛሉ።
በአጠቃላይ ከማህበሩ አባላት ቁጥራቸው ወደ አስር የሚደርስ አባላት ከልማት ዘርፉ ራሳቸውን አሻሽለው ወጥተዋል። 90 በመቶ የሚሆነው የማህበሩ አባል በዘርፉ ኑሮውን ለውጧል። ማሳያዎቹም የኢኮኖሚ አቅም ፈጥሮ ከቤተሰብ ጥገኝነት ወጥቶ በራሱ መተዳደር መቻሉና የሥራ ዘርፉንም በመቀየር ያደርጋቸው ጥረቶች ናቸው።
ይህ በግለሰቦች የተገኘ ጥቅም ነው ያሉት አቶ ደሳለኝ፣ ልማቱ ያስገኘውን አገራዊ ፋይዳ ደግሞ ‹‹በዘርፉ ውስጥ ስለቆየሁ የማዕደን ልማቱ በምን መንገድም ተከናውኖ በአገር ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ አስተዋጽኦ ሊኖረው እንደሚችል አውቃለሁ ሲሉ ይጠቁማሉ። ይሁን እንጂ አቶ ደሳለኝ በዘርፉ ለውጥ በሚያመጣ መልኩ መቶ በመቶ ተሰርቷል የሚል እምነት የላቸውም።
ሥራው አዘዋዋሪና ኤክስፖርተር አለው ቢባልም በልማቱ ተጠቃሚ እየሆኑ ያሉት በህገወጥ የሚንቀሳቀሱ ናቸው በማለትም በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር አቶ ደሳለኝ ይጠቁማሉ። የክልሉ ማዕድንና ቢሮ ይህን የመከታተልና የመቆጣጠር ኃላፊነት እንዳለበትም ነው የሚያስገነዝቡት። የፌዴራል ማዕድን ሚኒስቴር በዘርፉ ዙሪያ የሚሰጠውን መረጃ በተለይም ለውጭ ገበያ የቀረበውን መስማታቸውንና ከደላንታ አካባቢ በኪሎ ግራም የወጣው ኦፓል ማዕድንና ለገበያ የቀረበው መጠን የማይመጣጠን እንደሆነም ይጠቁማሉ። ይህም ህገወጥነቱ ያስከተለው ችግር እንደሆነ ነው ያስረዱት።
ህገወጥነቱ የዋጋ መቀነስ እንደሚያስከትል እንዲሁም ለአገር መግባት ያለበትን የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስቀር ገልጸዋል። ከወር በፊት ማዕድን ሚኒስቴር ያለ ይለፍና ደረሰኝ ሳይቆረጥ አልሚው መከፈል ያለበት ክፍያ (የሮያሊቲ ክፍያ) ሳይፈጸም፤ ማዕድኑ ለገበያ እንዲቀርብ የግብይት ሰንሰለትን ለማሳጠር በሚል ያወጣው የአሰራር መመሪያ ደግሞ ይበልጥኑ ዘርፉን ይጎደዋል ይላሉ። አልሚው ከስድስት እስከ ስምንት በመቶ ክፍያ(ሮያሊቲ) ቢቀርለትም እንደ አገር ሲታሰብ ግን ከዘርፉ የሚሰበሰብ ግብርን የሚያሳጣና የሚጎዳ ነው ብለው በመቆርቆር ይጠቁማሉ።
አቶ ደሳለኝ በአካባቢያቸው ስለሚገኘው የማዕድን ሀብት እንዳስረዱት እርሳቸው በልማቱ ላይ በቆዩባቸው ጊዜያቶች የሚያውቁት የማዕድን ሀብት ኦፓል ብቻ ነው። ክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግስት በአካባቢው ላይ ጥናትና ምርምር እንዲካሄድ ቢያደርጉ ተጨማሪ ማእድናት ሊገኙ እንደሚችሉ ይገምታሉ። ኦፓል ማዕድንም ቢሆን ክምችቱ ምን ያህል እንደሆነ እንደማያውቁና በመላ በመቆፈር ሲያገኙ መደሰት፣ ሲያጡ ደግሞ ማዘን እንደሆነ ነው የተናገሩት። ምርታማነቱ እንዲያድግና የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን እንዲቻል መንግሥትና ረጅ ድርጅቶች ዘርፉን በተለያየ መንገድ እንዲያግዙ ጠይቀዋል።
የማህበሩ የ2014 በጀት አመት የእቅድ አፈጻጸምና የቀጣይ በጀት አመት እቅድ በተመለከተም አቶ ደሳለኝ እንደገለጹት፤ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በነበረው ጦርነት የአባላት የሥራ መሳሪያዎችና ያፈሩት ሀብት ተዘርፏል። የልማት ሥራውም ተስተጓጉሏል።ማህበሩ መልሶ በመቋቋም ላይ በመሆኑ በ2014 በጀት አመት አፈጻጸም አጥጋቢ የሚባል ውጤት አልተመዘገበም። አሁንም ፀጥታው ሙሉ ለሙሉ የተረጋጋ ባለመሆኑ የወደፊቱንም ውጤታማነት ለማረጋገጥ ወይንም ለመተንበይ ያዳግታል። ባለመረጋጋት ውስጥም ሆኖ መስራቱ በራሱ ውጤት ተደርጎ ይወሰዳል።
የማህበራትን አቅም በመገንባትና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም በክልሉ የሚገኘውን የማዕድን ሀብት አደራጅቶ ለልማት እንዲውል በማድረግ ረገድ እየተከናወኑ ስላሉ ተግባራት የአማራ ክልል ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሌ አበበ እንዳስረዱት፤ ከአገራዊ ለውጡ በኋላ በማዕድን ዘርፉ እንደአገር መነቃቃት ተፈጥሯል። ማዕድን የብዝሀ የኢኮኖሚ አማራጮች ተብሎ ከተቀመጡት ዘርፎች መካከል አንዱ ሆኖ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት ይገኛል።
ክልሉም ይህንኑ ታሳቢ ባደረገ ከቢሮ የመዋቅር አደረጃጀት ነው ሥራውን የጀመረው ሲሉ አቶ ኃይሌ ይጠቅሳሉ። የቢሮ አደረጃጀቱ የማስፈጸም ብቃትን ለማሳደግ በሚያስችል መልኩ መዋቀሩን፣ በዞንና በወረዳዎችም በተመሳሳይ መዋቅር የተከናወነ መሆኑን ያብራራሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ አደረጃጀቱም ለልማቱ ግብአት የሚሆኑ የስልጠና እገዛዎችንና አስፈላጊ የቁሳቁስ ድጋፎችን ለማጠናከር የሚያስችል ነው። ለአልሚዎች በተለይም በባህላዊ የማዕድን ልማት ላይ ለሚገኙት። የቢሮው ዋና ተግባር ሥራ መፍጠርና ስለሥራው ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ ነው። አልሚዎቹ በሚፈልጉት ልክ ባይሆንም ባህርዳር እና ጎንደር ዩኒቨርሲቲዎችን በማስተባበር የቁሳቁስና የክህሎት ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል።
ቢሮው የጥናት ሥራዎችንም በማከናወን ባከናወነው ተግባርም በአምስት ዘርፎች የተከፈለ ወደ 35 የማዕድን አይነቶች በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እንደሚገኙ በጥናት ግኝቱ አረጋግጧል። በጥናት የተለዩት የማዕድን አይነቶች ለግንባታ፣ ለኢንዱስትሪ፣ ብረት ነክ፣የኃይል አቅርቦትና የጌጣጌጥ ወይንም የከበሩ ማዕድናት ናቸው።
በነዚህ ዘርፎች በጋራም ሆነ በተናጠል ለማልማት ለሚፈልጉ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በቢሮው ጥረት ማድረጉን አቶ ኃይሌ ይገልጻሉ። እስካሁን ባለው ሂደትም ቢሮው የሲሚንቶ ፋብሪካ ለመገንባት ፍቃድ ለጠየቁ ኩባንያዎች የምርመራ ፍቃድ መስጠቱን ጠቅሰው፣ ከነዚህ መካከል ሁለቱ ኩባንያዎች ሲሚንቶ የማምረት ፍቃድ ወስደው ወደተግባራዊ እንቅስቃሴ መግባታቸውን ነው ያመለከቱት። ኩባንያዎቹ በአንድ አመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ወደ ማምረት ሥራ ውስጥ ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።
እንደ ቢሮ ኃላፊው ማብራሪያ፤ ይህ ሲሆን ከህንድ አገር በውጭ ምንዛሬ በግዥ ወደ አገር የሚገቡትን እንደ ጂብሰም፣ ግራናይት፣ ማርብል ያሉ ለግንባታ ግብአት የሚውሉ የማዕድን ውጤት ምርቶች በአገር ውስጥ መተካት የሚቻልበት ዕድል መኖሩ ተረጋግጧል።
ጥሬ ሀብቱ በአማራ ክልል በተለይም በአባይ ሸለቆ ማዕከል ተደርጎ በተለያዩ አካባቢዎች በተከናወነ ጥናት ሁሉም የማዕድን አይነቶች መኖራቸው ተረጋግጧል። በዚህ ዘርፍም ተሰማርተው ወደ ምርት ሥራ የገቡ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን በማቅረብ ከውጭ የሚገባውን ለመተካት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ቢሮው ከውጭ የሚገቡ የማዕድን ውጤቶችን በአገር ውስጥ መተካት እየሰራ ሲሆን፣ ይሄንንም ከ40 እስከ 50 በመቶ ማሳካት ተችሏል።
እንደ አገር ለግራናይትና ለማርብል ግብአት ግዥ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ይወጣ እንደነበር ያወሱት አቶ ኃይሌ፣ እነዚህን ምርቶች በአገር ውስጥ ጥሬ ዕቃ፣ በአገር ውስጥ ማምረት መቻሉ ይህን ወጪ ለማስቀረት እንዳገዘና በአገር ውስጥ የመተካት ሥራ ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ ማሳያ መሆኑንም አመልክተዋል።
እንደ አቶ ኃይሌ ማብራሪያ፤ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች የኃይል ግብአት ሆኖ የሚያገለግለው የድንጋይ ከሰል እንዲሁም የብረትና የተለያዩ የማዕድን ሀብቶች በክልሉ ይገኛል። ኢትዮጵያ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከቱርክና ከደቡብ አፍሪካ በግዥ ወደ አገር ውስጥ የምታስገባውን የድንጋይ ከሰል ምርት በአገር ለመተካት እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴም በአማራ ክልል ወሎ አካባቢ ለማምረት እንቅስቃሴ ተጀምሯል።
እነዚህ ተግባራት መንግሥት የማዕድን ዘርፉን አንድ የብዝሀነት የኢኮኖሚ አማራጭ ብሎ በእቅድ የያዘውን ግብ ለማሳካት ያስችላል ይላሉ አቶ ኃይሌ። እቅዱን ለማሳካት በሚከናወኑት ተግባራት እንቅስቃሴዎች አልጋ በአልጋ እንደማይሆኑና ተግዳሮት እንደማያጣውም ጠቁመዋል።
እርሳቸው እንዳሉት፤ አንዱ ተግዳሮት ማዕድናቱ በሚገኙባቸው አካባቢዎች የመሠረተ ልማት አቅርቦት አለመኖር ነው። ለልማት ሥራው ፋብሪካ ለሚያቋቁሙ ኩባንያዎች የኃይል አቅርቦት መጓተት ሌላው ተግዳሮት ነው። ልማቱ ለአካባቢውና ለአገር ጠቃሚ እንደሆነ ተገንዝቦ አስፈላጊውን ትብብር አለማድረግም በማህበረሰቡ በኩል የሚስተዋል የግንዛቤ ችግር ነው። ህገ ወጥነትም ሌላው ችግር ሲሆን፣ በተለይም በኦፓል ማዕድናት ላይ የኮንትሮባንድ ችግር ይስተዋላል። ችግሮቹን በመለየትና መፍትሄ ለመስጠት በቢሮ በኩል ጥረት ቢደረግም ተከታታይ ሥራ እንደሚያስፈልግ አቶ ኃይሌ ገልጸዋል።
በተለይም ህገወጥነት (ኮንትሮባንድ) አልሚዎችም በስፋት ያነሱት ጉዳይ በመሆኑ ቢሮው ለመከላከል ያስቀመጠው አቅጣጫ ምን እንደሆነ አቶ ኃይሌ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ እንዳብራሩት፤ በቀበሌ ደረጃ የማዕድን ግብረ ኃይል በመቋቋሙ ግብረ ኃይሉ ውጤታማ ሥራ እንዲሰራ ማድረግ ይጠበቃል። ሌላው የኦፓል ማዕድን መሸጫ ማዕከል በመገንባት ግብይቱን ህጋዊ ማድረግ፣ ክትትልና ቁጥጥሩን ማጠናከር ነው። የጌጣጌጥ ማዕድናት ግብይትን በተመለከተ ከብሄራዊ ባንክ ጋር በመነጋገር በየአካባቢው ከሚገኙ ባንኮች ጋር በማስተሳሰር ግብይቱ እንዲከናወን ማድረግ ሌላው መፍትሄ ነው።
የፌዴራል ማዕድን ሚኒስቴር የማዕድን ሀብቶች ማስተዋወቂያ የማዕድን ጋለሪ እንዳዘጋጀው ሁሉ እንዲህ ያለውን ተሞክሮ በክልላቸው በመተግበር ረገድ እቅድ ይኖራቸው እንደሆንና በ2014 በጀት አመት ከማዕድን ዘርፉ የተገኘ ገቢን በተመለከተ አቶ ኃይሌ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲያብራሩም፣ የማዕድን ሙዚየም ለመገንባት፣ የማዕድን ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት፣ የማዕድን ልማት ቀጠናዎች ለማዘጋጀትና ወደ 20ሺ ካሬ ኪሎ ሜትር በካርታ (ማፕ) ላይ ማሳየት በእቅድ ከተያዙ ተግባራት መካከል መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በ2014 በጀት አመት ከክልሉ 13ሺ140 ኪሎ ግራም የተዋበና ያልተዋበ ኦፓል ለውጭ ገበያ መቅረቡን ጠቅሰዋል፤ ከጌጣጌጥ ማዕድናት አምስት ነጥብ ሰባት ሚሊየን ዶላር ገቢ በማስገኘት በአገር ኢኮኖሚ ላይ አስተዋጽኦ ማበርከት መቻሉን አስታውቀዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 6 /2014