የዘንድሮው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በአስራ አንድ የተለያዩ ዘርፎች በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እየተሰጠ የሚገኝ ሲሆን በመላው አገሪቱ የሚገኙ ከ19 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ተሳትፈዋል። በሚከናወነው በዚሁ የበጎ ፍቃድ አገልግሎትም መንግስትና ህብረተሰቡ ሊያወጡ የሚችሉት 11 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ወጪ ይድናል ተብሎ ይጠበቃል። አገልግሎቱም ከሰኔ 15 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ እንዲከናወን መርሃ ግብር ተይዞለታል።
የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በአረንጓዴ አሻራ፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ ሰላም፣ መንገድ ደህንነት፣ ኮቪድ-19 መከላከልና ሌሎችም የጤና አጠባበቅ ስራዎችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት ግንዛቤ መፍጠር ላይ አተኩሮ እየተሰራበት ነው። ከዚህ ባለፈ የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት፣ የአረጋውያንና አቅመ ደካማ ቤት እድሳት፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን መከላከልና ግንዛቤ መፍጠርን ጨምሮ በሌሎች አስራ አንድ ዘርፎች ላይ እየተሰራበትም ይገኛል። በዋናነት ደግሞ የወጣቶችን እርስ በርስ ግንኙነቶች እንዲጠናከሩና አጠቃላይ የወጣቶች ተሳትፎ የጎላ ሚና እንዲኖረው በሰላም ዙሪያ ያተኮሩ ግንኙነቶችም እየተካሄዱ ነው።
በአዲስ አበባ ከተማም ወጣቶች በተለያዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ውስጥ በመሳተፍ በገንዘብ ሊተመኑ የማይችሉ ከፍተኛ ስራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ። በዘንድሮ በጀት ዓመትም በከተማዋ ነዋሪዎች ዘንድ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ግንዛቤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ በተለያዩ ዘርፎች በተሰራው ሥራ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከሶስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማዳን ተችሏል።
በእንዲህ አይነቱ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሊወጣ የሚችል ወጪን ማዳን ከቻሉና ለበርካቶች በበጎ ፍቃድ ተደራሽ መሆን ከቻሉት ውስጥ አንዱ በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ መርካቶ እህል በረንዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው ማህበር አንዱ ነው።
ወጣት ሄኖክ ወንድሙ በመርካቶ እህል በረንዳ አካባቢ የጌትነት፣ ሄኖክና ጓደኞቻቸው የደረቅ ቆሻሻ ህብረት ሽርክና ማህበር ሰብሳቢ ነው። በማህበሩ ውስጥ ከስደት፣ ከእስር የተለቀቁና ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ 80 የሚጠጉ ወጣቶች እንዳሉ ይናገራል። አብዛኛው ስራዎቻቸውም ከበጎ ፍቃድ አገልግሎት ጋር የተገናኙ መሆናቸውን ይጠቅሳል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወደ አገሪቱ ከገባበት ጊዜ አንስቶ በርካታ የበጎ ፍቃድ ስራዎችን እንዳከናወኑም ይጠቁማል።
ከእጅ ማስታጠብ ጀምሮ የማህበሩን አባላት በማሰማራት የተለያዩ ድጋፎች እስከ ማድረግ ድረስ የደረሱ የበጎ ፍቃድ ስራዎችን ማከናወናቸውንም ወጣት ሄኖክ ይገልፃል። ይህ የበጎ ፍቃድ ስራቸው እንደ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባ ከተማ ሁለተኛ ደረጃን እንዲቆናጠጡ ያደረገ መሆኑንም ያመለክታል።
በተለይ ደግሞ እህል በረንዳ አካባቢ ከአራቱም አቅጣጫ ተሽከርካሪዎች እህል ጭነው እንደሚመጡና አሽከርካሪዎችና ረዳቶች ስለኮቪድ-19 እምብዛም ግንዛቤ የሌላቸው በመሆኑ ስለበሽታው ግንዛቤ በመስጠት፣ የእጃቸውን ንፅህና እንዲጠብቁ በማስታጠብና የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ እንዲያደርጉ በማድረግ ማህበራቸው ከፍተኛ ስራ እንዳከናወነ ያስታውሳል። በዚህም ከአዲስ አበባ ነጋዴዎች ማህበርና ከአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ምስጋና እንደተቸራቸው ይናገራል።
በሌላ በኩል ደግሞ አቅመ ደካሞችንና አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በበአላትና በሌሎችም ቀናት የመጎብኘትና የመንከባከብ ስራዎችንም የማህበሩ አባላት ሲያከናውኑ እንደነበርም አስታውሶ፤ በክረምትም ወቅት የፈረሱ ቤቶችን አባላትን በመሰብሰብና መልሶ በመጠገንና በማደስ የጉልበት አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱም ወጣት ሄኖክ ይናገራል።
ማህበሩ ከተመሰረተ ሁለት አመት ሊሞላው እንደሆነ የሚናገረው ወጣት ሄኖክ፤ እስካሁን ድረስ የማህበሩ አባላት ከደመወዛቸው በሚያዋጡት ገንዘብ በቋሚነት የሚረዱ ከአስራ አምስት ያላነሱ አቅመ ደካሞችና ዝቀተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እንዳሉ ይገልፃል።
ከዚህ ውጭ በሁለት ዓመታት ውስጥ በአመት ሁለት ጊዜ የአቅመ ደካማና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎችን ቤት እንዳደሱ ይጠቁማል። በዚህም ቢያንስ በአመት ውስጥ ከሰባት ቤት ያላነሰ እድሳት ማድረጋቸውን ይጠቅሳል። የእህል በረንዳና አካባቢውን ፅዳት በመጠበቅ ረገድም ተመሳሳይ ስራ እየሰሩ እንደሚገኙም ይገልፃል። በዚህ የክረምት ወቅትም ከሌላው ጊዜ በተለየ የአካባቢውን ፅዳት ይበልጥ እንደሚጠብቁም ነው ወጣት ሄኖክ የሚናገረው።
በዚህ የክረምት ወቅትም ሶስት የአቅመ ደካማና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ሰዎች ቤት እያደሱ እንደሚገኙም ይናገራል ወጣት ሄኖክ። ነገም ከነገ ወዲያም እንዲህ አይነቱን የበጎ ፍቃድ ስራ ከመንግስት ጋር በመሆን ከመስራት ወደኋላ እንደማይሉም ይገልፃል።
በዚህ ማህበር ውስጥ ያሉት አብዛኛዎቹ ወጣቶች የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ነዋሪና ተወላጆች መሆናቸውን የሚናገረው ወጣት ሄኖክ፤ ከተለያዩ አካባቢዎች መጥተው ማህበሩን በመቀላቀል በዚህ የበጎ ፍቃድ ስራ የሚሳተፉ ወጣቶች እንዳሉም ይጠቅሳል።
ከዚህ በፊት በዚህ ማህበር ውስጥ ያሉ ወጣቶች በተለያዩ ሱሶች ውስጥ የነበሩ፣ ከስደት የተመለሱና ከእስር የተፈቱ መሆናቸውንና ነገር ግን ማህበሩ ከተመሰረተ በኋላ በአሁኑ ጊዜ የራሳቸውን ቤተሰብ መስርተው ልጆች ወልደው የሚያሳድጉና ቤተሰባቸውንም የሚረዱ ለመሆን እንደቻሉም ያስረዳል። ‹‹ይህም ወጣቶቹ ቀደም ሲል የነበረውን ሕይወታቸውን ከአሁኑ ጋር ሲያወዳደሩት ትልቅ የአእምሮ እረፍት የሚሰጣቸው ነው ይላል›› ወጣት ሄኖክ።
‹‹በዚህ ማህበር ለታቀፉና በፅዳት ስራ ለተሰማሩ አባላት ክፍያ የሚፈፅመው ራሱ ማህበሩ ነው›› የሚለው ወጣት ሄኖክ፤ አባላቱ በሳምንት አንድ ቀን እረፍት ስላላቸው ክፍያው የሚፈፀመው እንደሚመጣው የተሽከርካሪ ብዛት እንደሆነ ይገልፃል። አባላቱ እያንዳንዳቸው በወር እስከ 1ሺ500 ደመወዝ እንደሚከፈላቸውም ይጠቅሳል።
የአባላቱን ቁጥር በመቀነስ ደመወዙን ከፍ ማድረግ የሚቻል ቢሆንም አብዛኛው ወጣት ስራ አጥ በመሆኑ ሁሉም ስራ እንዲኖረው ለማድረግ ካላቸው ፍላጎት የአባላቱን ቁጥር ማብዛት እንዳስፈለገ ያስረዳል። የአካባቢው ወጣት ሰርቶ እንዲበላና እንዲጠቀም፣ አንዱ አግኝቶ ሌላኛው እንዳያጣ ካላቸው ፍላጎት አንፃር መሆኑንም ይጠቅሳል።
ከነጋዴው ጋር ግንኙነት በመፍጠር ወደ ጎጃም በረንዳ እህል ጭኖ ከሚገባው ተሽከርካሪ በሚሰበስቡት ገንዘብ ራሳቸውን እንደሚደጉሙና ነገር ግን ለአካባቢው ፅዳት ለሳሙናና መጠረጊያ የሚያወጡት ወጪ ከሚያገኙት ገቢ ጋር የሚመጣጠን እንዳልሆነ ይጠቁማል። በየአስራ አምስት ቀኑ የማህበሩ አባላት ደመወዛቸውን እንደሚወስዱም ይጠቅሳል።
በጋራ መመካከርና መስራትን የጀመሩት ማህበሩ ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ መሆኑንም የሚገልፀው ወጣት ሄኖክ አብዛኛው ወጣት በአፍላ እድሜ ክልል ውስጥ ያለ በመሆኑና ስራ ሰርቶ የማያውቅ በመሆኑ ይህን ወጣት ወደ ስራ ለመሳብና ለመምከር ትልቅ ዋጋ እንዳስከፈለ ያስረዳል።
የተወሰነው ወጣት ስራ ላይ ያለ ቢሆንም የተወሰነው ደግሞ በስደት፣ በፀብና በተለያዩ ምክንያቶች በእስር ያሳለፈ በመሆኑ ወደአካባቢው ሲመጣ መግራት እንዳስፈለገ ይገልፃል። ማህበሩ ሲመሰረት ይህን ወጣት በመሰብሰብ መክሮ ወደስራ ለማስገባት ትንሽ ፈተናዎች እንደነበሩትም ያስታውሳል።
ከዛ በኋላ ግን ወጣቶቹ ቀደም ሲል የነበሩበትን ሕይወት እንደአማረሩ ይገልፃል። አብዛኛዎቹም አግብተውና ወልደው ቤተሰቦቻቸውን በገቢ እያስተዳደሩ እንደሚገኙ ይጠቁማል። የተለያዩ ሱሶችን ያቆሙ አባላትን ይዞ ማህበሩ ስራውን እያከናወነ እንደሚገኝም ይጠቅሳል።
ከመደበኛ ስራቸው ባሻገር በተለያዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች የሚሳተፉ አባሎች ማህበሩ እንዳሉትም ወጣት ሄኖክ ጠቅሶ፤ እስካሁን ድረስ በምድባቸው መሰረት ማታ ላይ አካባቢያቸውን የመጠበቅ፣ መብራት የማስበራት፣ አካባቢውን የመቃኘትና ፀጉረ ልውጥ ሰዎችን የመለየት ስራዎችን እንደሚያከናውኑ ያብራራል። ከዚህ ባለፈ አባላቱ ግንባር ድረስ በመሄድ የመከላከያ ሰራዊቱን አብልተው የመጡበት ጊዜ እንዳለም ይጠቅሳል። በየሶስት ወሩ አባላት ደማቸውን በቋሚነት እንደሚለግሱም ይገልፃል።
‹‹ዋናው ትልቁ እርካት ለሰው ልጅ መድረስ ሲቻል ነው›› የሚለው ወጣት ሄኖክ በጎጃም በረንዳ አካባቢ ገንዘብ ተዋጥቶ ሴቶች በቡና ማፍላት ተሰማርተው ልጆቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ሲያስተዳድሩ ማየት ትልቅ እርካታ እንደሚሰማው ይገልፃል። ከዚህ ውጭ የአቅመ ደካሞችና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎችን ቤቶች አድሰው ሲያጠናቅቁና ሰዎቹ ሲደሰቱ ማየት ከእርካታም በላይ ነው ይላል። በዚሁ ስራ የአባቶችና እናቶችን ምርቃትና ምስጋና ማግኘት በራሱ ተጨማሪ ደስታ የሚፈጥር እንደሆነም ይናገራል።
የተለያዩ የመንግስት አካላትም ሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ወጣቱ በእንዲህ አይነቱ መንገድ ሲሰራና ለመለወጥ ሲታትር ወርዶ ማየትና ማበረታት ብሎም በተለያዩ መንገዶች መደገፍ እንደሚገባ በዚህ አጋጣሚ መልእክቱን ያስተላልፋል።
እንደ ጌትነትና ሄኖክ የወጣቶች ማህበር በአረንጓዴ አሻራ በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆናቸውንም የሚናገረው ወጣት ሄኖክ የማህበሩ እያንዳንዱ አባላት ቤታቸውን፣ ግቢያቸውንና አካባቢያቸውን እያስዋቡ እንደሚገኙም ይናገራል።
ወጣት መስፍን አክሊሉም ጌትነት፣ ሄኖክና ጓደኞቻቸው የደረቅ ቆሻሻ ህብረት ሽርክና ማህበር አባል ሲሆን ማህበሩ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ እጅግ በብዙ የበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ ሲሳተፍ መቆየቱንና አሁንም እየተሳተፈ እንደሚገኝ ይናገራል። በተለይ ከኮቪድ-19 ጀምሮ ባለው ሂደት ውስጥ በአካባቢው የእጅ ማስታጠብ፣ ሳኒታይዘር የማቅረብ አልፎም ተርፎ አቅመ ደካማና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎችን የማህበሩ አባላት ከሚያገኙት ገቢ ቀንሰው የምግብ ግብአት ድጋፍ ሲያደርጉ እንደቆዩም ይመሰክራል።
በአሁኑ ጊዜ ደግሞ መንግስት ያዘጋጀውና የአቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤቶችን የማደስ መርሃ ግብርን ለማገዝ በዚሁ የክረምት ወቅት ያረጁ ቤቶችን የማደስና መልሶ የመጠገን ስራዎችን ማህበሩ ማከናወኑን ይጠቅሳል። በሌላ በኩል ደግሞ ማህበሩ ከተቋቋመ ጀምሮ በርካታ እርዳታዎችን ለተረጂዎች ሲያደርስ መቆየቱንም ይጠቅሳል። ለአብነትም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው ሲጠይቁ የማህበሩ አባላት ከደመወዛቸው ተቆራጭ በማድረግ ስራ የሚጀምሩባቸው እቃዎች እንዲገዛላቸው የሚደረግ መሆኑንም ያስረዳል።
በዚህም አስራ አምስት የሚሆኑ ሴቶች በተደረገላቸው የገንዘብ ድጋፍ ቡና እያፈሉ፤ ትንሽ ከፍ ብለው ደግሞ ብስኩትና ሻይ እየሸጡ ራሳቸውን እየደጎሙ እንደሚገኙም ወጣት መስፍን ይናገራል። በቅርቡም ለአካል ጉዳተኞች ተሽከርካሪ ወንበሮችን ለመግዛት እንቅስቃሴዎች እንደተጀመሩ ይገልፃል። በቀጣይ ደግሞ ማህበሩ ሊያደርጋቸው የሚያስባቸው በርካታ ነገሮች እንዳሉና ከነዚህ ውስጥም አቅመ ደካማ እናቶችን በመሰብሰብ ቋሚ ድጋፍ ለማድረግ ሀሳብ እንዳላቸውም ይጠቁማል።
‹‹ማህበሩ ቅፅል ስሙ እናት ማህበር ነው የሚባለው›› የሚለው ወጣት መስፍን ይህን ቅፅል ስያሜ ሊያገኝ የቻለው በርካታ መልካም ስራዎችን በመስራቱ እንደሆነ ይናገራል። ሁሉም የማህበሩ አባላት ከነበሩበት አስከፊ ሕይወት ወጥተው በአሁኑ ጊዜ በስራ ላይ በመሆናቸው ተጎዳሁ ብሎ ወደእነሱ የሚመጣን ሰው የሚያይበት መንገድ ስስ መሆኑና በዚህ የተነሳ ወደማህበሩ ለመጣ ሁሉ ድጋፍ ተደርጎለት እንደሚሄድ ያስረዳል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 6 /2014