ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ፣ የሶስት ሺ ዓመት ታሪክ ያላት፣ የበርካታ እምነት፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ ጥበብና ፍልስፍና መኖሪያ ናት እየተባለ ሲነገር በተደጋጋሚ ይደመጣል ሕዝቧም ሰው አክባሪ፣ በጉርብትና ተዋዶ የሚኖር እንደሆነ ይነገርለታል ጠላትን በጋራ ተባብሮ መዋጋትም የጥንት ባህሉ ነው መረዳዳት፣ መተባበርና ፈጣሪን መፍራትም ሁነኛ መገለጫው እንደሆነ ይጠቀሳል
እነዚህ መልካም የሆኑ የኢትዮጵያ እሴቶች ከትውልድ ትውልድ በቅብብሎሽ በረጅም የታሪክ ኡድት ውስጥ ተጉዘው የዛሬው ትውልድ ላይ ደርሰዋል ሆኖም እነዚህ እሴቶች ልክ እንደበፊቱ በዛሬው ትውልድ ይበልጥ ጎልተው መውጣት አልቻሉም እያደጉና እየጎለበቱ ከመሄድ ይልቅ እየደበዘዙና እየኮሰሱ መጥተዋል
ወጣት ሽማግሌ መስማት ትቷል እርስበርስ መከባበርም ጠፍቷል አንዱ በአንዱ ላይ ጨክኗል እርስበርስ መገዳደልም እየተለመደ መጥቷል ፈጣሪን መፍራት እየተረሳ የመጣ ይመስላል ለመሆኑ እነዚህ መልካም ሀገራዊ እሴቶች በጊዜ ሂደት እንዴት እየተሸረሸሩ ሊመጡ ቻሉ? የተሸረሸሩ እሴቶችንስ እንዴት ወደነበሩበት መመለስ ይቻላል? በሚሉና መሰል ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ‹‹የጋራ እሴቶቻችን ስለ ኢትዮጵያ›› በሚል መሪ ሃሳብ የፓናል ውይይት አካሂዷል ሁለት ጽሁፎች ቀርበዋል
በዚህ የፓናል ወይይት ለውይይት መነሻ የሚሆን ጽሁፍ ያቀረቡት የሃይማኖት አስተምህሮ ሊህቅ ኡስታዝ አቡበክር አህመድ እንደሚናገሩት ሀገር ሲታሰብ እንደማሕረሰብ እድገትን፣ የተሻለ ነገርን፣ በመልካም መሸጋገርንና ተስፋን ሰንቆ መጓዝ ያስፈልጋል ችግሮች ሲከሰቱም በመነጋገር፣ የጋራ እሴቶችን በማጎልበት፣ የጠፉትን በመፈለግ፣ እንደ አዲስ ወደፊት ለመራመድ እጅ ለእጅ በመያያዝና በመነጋገር ብሎም አብሮ በመሆን ነው ሀገሪቷን ወደተሻለ ደረጃ ማሸጋገር የሚቻለው ይህም የሁሉም ዜጋ ድርሻና ሃላፊነት ነው
ኡስታዝ አቡበከር እንዳብራሩትም የጋራ እሴቶችን ምሁራን ሀገራዊ፣ የማሕረሰብና የግለሰብ እሴቶች እያሉ በብዙ መንገድ ያቀርቧቸዋል አሁን ካለው ሀገራዊ ሁኔታ አንፃር ሀገራዊና ማሕረሰባዊ የሥነ-ምግባር አሴቶች ጋር ማተኮሩ መልካም ነው እየተሸረሸሩ ያሉት እሴቶችም በአብዛኛው እነዚህ ናቸው
እንደሀገር በሚደርሱ የተለያዩ ውጣውረዶች ሲታለፍ የኢትዮጵያዊነት ትልቁ መሰረት በታሪክ የረጅም ጊዜ ተሞክሮ ያላቸው ሕዝቦች መኖራቸው ነው ወደኋላ ለመመለስም እድል አለ ወደኋላ በመመለስ ፍተሻ ቢደረግ ቆም ብሎ ለማሰብና ወደተሻለ አቅጣጫ ለመሄድ የሚያስችሉ መሰረቶች አሉ እነዚህን መሰረቶች በማሰብም ነው ኢትዮጵያውያን ወደቀደመው ማነነታቸው ለመመለስ የሚቸገሩ ሕዝቦች አይደሉም የሚባለው
ኢትዮጵያውያን ትናንት የመጡ ወይም ትናንትና ላይ ቆመው መውጪያ መግቢያ የሚፈልጉ ሕዝቦችም አይደሉም ከዚህ አኳያ በብዙ መልኩ የኢትዮጵያውያን ታሪክ ማንነት አንድ የሚያደርግና በብዙ መልኩ እድል የሚሰጥ ነው
እንደ ኡስታዝ አቡበከር ገለፃ ዛሬ ላይ ትልቅና ሃያል ሀገር ተብሎው ከሚቆጠሩት እንደአሜሪካ ያሉ ሀገራት እንደትልቅ እሴት ከሚያነሷቸው ውስጥ ስድስቱ ግለሰባዊ ነፃነት፣ ራስን ችሎ መቆምና በራስ መመካት፣ የስኬት እድሎችን ሁሉ በእኩልነት እንዲያገኙ ማድረግ፣ የውድድር መንፈስ፣ ጥሩ ሕይወት መኖርና ጠንክሮ መስራት ናቸው አብዛኛዎቹ እሴቶች ከግለኝነት ጋር ይቆራኛሉ ለዛም ነው ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ዓለምን መምራት የቻለ ግን በኑሯቸውና በማንነታቸው ሲታዩ የኢትዮጵያውያንን ማንነትና እሴት ግዝፈት ይነሳል
አብሮነት፣ የጋራ የሆነ ማንነትና መከባበር እንደ ኢትዮጵያዊነት ታሪካዊ መገለጫዎችና ማሳያዎች ናቸው ተመሳሳይ ያጋራ መሰረቶችና ብዙ ኢትዮጵያውያኖችም የሚገለጹባቸው ሀብቶች ነበሩ እነዚህ እየጠፉ ሲመጡም ነው ሀገሪቱ አደጋ ላይ እየወደቀች የመጣችው ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሶስት ኢትዮጵያዊ እሴቶች ማለትም ሃይማኖተኛነት፣ መተባበር (መተጋገዝ) እና አብሮነት የተገነቡት በጋራ አብሮ ከመኖርና በታሪክ ውስጥ ካለፉ የአብሮነት ሂደቶች ናቸው
ከተለያዩ እምነቶች ተቀድተው የኢትዮጵያን አካል የሆኑ፤ ባህልና ልምድ የተደረጉ እንዲሁም በተለያዩ ውጣውረዶች ውስጥ በማለፍ አንዱ ከአንደኛው ጋር ፈተና ሆኖ ወድቆ ተነስቶ ከጥፋት በመማር የተገነቡ አብሮነቶች፤ እነዛና መሰል ሂደቶች የኢትዮጵያውያን ትልቅ እሴቶችና መገለጫዎች ናቸው ዛሬ ላይ ግን እነዚህ እሴቶች በመሸርሸራቸው ሀገር ፈተና ላይ ወድቃለች የምትታሰበው ኢትዮጵያም በብዙ መልኩ ለችግር ተጋልጣለች
የአባቶች በጎነት፣ ደግነትና መልካምነት የኢትዮጵያውያን የሚኮሩበት ማንነት ነው ይህን ፈለግ መከተል ካልተቻለ ግን የአሁኑ ትውልድ ማፈሩ አይቀርምሀገርም ለአደጋ መጋለጧ ሳይታለም የተፈታ ነው
የቀድሞ ኢትዮጵያዊ እሴቶችንና መገለጫዎችን ወደነበሩበት ለመመለስ ተረኛው ትውልድ ራሱን ማየትና መመልከት ይኖርበታል የጋራ የሆኑ የሥነ -ምግባር እሴቶች ተጠብቀው እንዲሄዱና የቀድሞ አባቶቻችንና እናቶቻችንን መስለው እንዲኖሩ ሊጠበቁ፤ ከተበላሹ ሊስተካከሉ፤ ከጠፉ ደግሞ ሊመለሱ ይገባል ለዚህም መፍትሄው የጋራ ነው
ኢትዮጵያ ስትታሰብ ነገን እንድናስብና ተስፋ እንድናሳድር ያደርገናል በተቃራኒው ክፋቱን፣ ፈተናውንና መከራውን የምናስብ ከሆነ ወድቀናል ከዚህ አንፃር በጋራ ወደፊት መንቀሳቀስ ያስፈልጋል በርገጥኝነትም የትናንት ማንነት እያለ ኢትዮጵያ አትጠፋም ወደከፍታው ለመመለስና የያኔዋ ኢትዮጵያ ተመልሳ እንድትመጣ ትልቅ ስራ ይፈልጋል ይቅርታ፣ መከባበር፣ አውቅና መሰጣጣት፣ አብሮነትን ማመንና በጋራ መቀበል ያስፈልጋል
ሌላኛው ጽሁፍ አቅራቢ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ናቸው ፕሮፌሰር መስፍን እንደሚሉት ኢትዮጵያ የበርካታ ሃይማኖቶችና ባህሎች መገናኛ ቦታ ነች የፍቅር ብቻ ሳይሆን የባህል መነሻ ነች እያንዳንዱ ዜማም የሚነሳው ከዚህች ሀገር ነው አምስቱም የዜማ አይነቶች የፈለቁት ከዚች ሀገር ነው ትልልቅ የሃይማኖት አባቶችና እናቶች ከዚች ሀገር ፈልቀዋል
ትግራይ የክርስትናና የእስልምና በር እንደሆነ ሁሉ ወሎም የእስልምናና የክርስትና መዳበሪያ ቦታ ነች የምትከበርና እንደተምሳሌት የምትወሰድ ከተማም ነች ታዲያ ይህ ሁሉ የሚነገርላት እነዚህ ሁሉ እሴቶች አሏት የምትባል ሀገር ምን ነካት? ምን ሆነች? ለምንድን ነው እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰችው? የሚለውን መጠየቅ ያስፈልጋል
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋናውና ትልቁ ስራው ሕዝቦች እንዲደማመጡ ማገዝ ነው አስካሁን ሕዝቦች ተነጋግረዋል ንግግራቸው ከአንደበትና የምልክት ንግግር አልፎ ወደመሳሪያ ንግግር ከተሸጋገረ አስርት ዓመታትን አስቆጥሯል ስለዚህ በመሳሪያ ንግግር የመጣው ውጤት ታይቷል መገዳደልን፤ መፈናቀልንና ስደትን ይዞ መጥቷል
ለዘመናት ጸንተው የቆዩ ኢትዮጵያዊ እሴቶች ተሸራርፈው ድምጥማጣቸው የጠፋበት ዘመን ላይ ተደርሷል ይህ ሲባል ትልልቅና ተምሳሌት የሚሆኑ ሰዎችን አላሳጣም ትልልቅ አባቶችንና እናቶችን አልከለከለም ግን እነዚህ እናትና አባቶች 120 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ አንድ ወለል ለማምጣት ምን ያህል አቅም ፈጥረዋል? የሚለው ወሳኝ ጉዳይ ነው ለዚህም ነው ወጣቶች ላይ ላለፉት ሰላሳ፣ አርባ፣ ሃምሳና ስልሳ ዓመታት ምን ያህል ሰርተናል? ብለን የምንጠይቀው
ዋና ኮሚሽነሩ እንደሚያብራሩት የኢትዮጵያ እሴቶች በየእንዳንዱ ዝርዝር ሲታዩና አብሮ መብላት፣ መስገድ፣ ማምለክና ጠላት ሲመጣ በጋራ ሆኖ መመከት የመሳሰሉትና ሌሎች እሴቶች የት ጋር ነው የታጠፉት? ብሎ መጠየቅ ግዴታ ነው እጥፋቱ የት ጋር ነው የሚለውን መርምሮ ለማግኘት ለባለሙያዎች ሃላፊነቱን መስጠቱ ተገቢ ነው እጥፋቱ የዛሬ ሰላሳና አርባ አመት ወይም ከዛም በፊት እየታጠፈ መጥቷል ማለት ይቻላል አንድ በጋራ የሚያስማማው ጉዳይ ግን እጥፋቱ በጣም ከፍተኛ መሆኑ ነው
ኢትዮጵያ የደጋጎች፣ የሃይማኖተኞች፣ የመቻቻል ሀገር ከሆነች እንዲህ አይነት የእርሰበርስ ግጭት ይከሰታል ተብሎ አይታሰብም ሆኖም በሚያሳዝን ሁኔታ ይህ ነገር ተከስቷል አንድ ሚሊዮን ሕዝብ አልቋል፤ በኢትዮጵያ ደረጃ የተከሰተው በሩዋንዳ ደረጃ ከተከሰተው በምን ይለያል የሚለውን ለታሪክ ምርምርና ለሚመለከተው አካል መተው ነው
ከዚህ አንፃር በዚች በተረፈች አነስተኛ ጊዜ ኢትዮጵያኖች መነጋገር አለባቸው በመሳሪያ ተነጋግረዋል፤ የትም አልደረሱም ስለዚህ ተቀራርበው መመካከር መቻል አለባቸው ምክክሩ ሲካሄድ ታዲያ ኢትዮጵውያን የእኩልነትን ንግግር ወደ ጠረጴዛ ማምጣት አለባቸው
ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚያደርገው ዋናው ስራው ሁሉም ኢትዮጵያውያን ያለምንም አድልዎና መገለል ስለኢትዮጵያዊነት ምንድን ነው የሚሉት? አጀንዳዎቻቸው ምንድን ናቸው? ምንን ማቅረብ ይፈልጋሉ? በምን አካባቢዎች ላይ መወያየት ይፈልጋሉ? በሚሉና እጅግ መሰረታዊ በሆኑ ችግሮች ላይ እንዲወያዩና መፍትሄ እንዲያመጡባቸው ነው
የምክክር ኮሚሽኑ ዋና ስራ ሀገራዊ እሴቶችን እንደመሳሪያ በመጠቀም ዋናውና ትልቁ ስራ ሕዝቡ ከላይ ወደታች ብቻ ሳይሆን ከታች ወደላይ ሃሳቦችን እንዲያፈልቅ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው ሌሎች የጎንዮሽ ውይይቶችም ያስፈልጋሉ፣ ከዚህ በኋላም ወደመግባባት መደረስ አለበት፣ መግባባት ላይ ከተደረሰ የሚቀጥለው ምእራፍ ሀገራዊ እርቅ ነው፣ ከብሄራዊ እርቅ በኋላ ደግሞ ሀገርን የመገንባት ሂደቱን እያጠናከሩ መሄድ የሚል ነው
ይህንንም በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ የመነጋገርና የመደማመጥ እንዲያም ሲል ደግሞ አንድ መግባባት ላይ መድረስ፤ መግባባት ላይ እንኳን መድረስ ባይቻል መግባባት ባልተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይ በመግባባት ኢትዮጵያዊነትን ይዞ ለመቀጠል የተቋቋመ ብሄራዊ የምክክር ኮሚሽን የሕዝቡ በመሆኑ በቀጣይነት ሁሉም ጋር መምጣቱ አይቀሬ መሆኑን ፕሮፌሰር መስፍን ጠቁመዋል
በመሆኑም ይህ ሀገራዊ እሴቶችን የመገንባትና ወደነበሩበት እንዲመለሱ የማድረጉ ጥረት የመንግሥትና የመገናኛ ብዙሃን ሚና ብቻ ሊሆን አይገባም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በተለይ የአሁኑ ትውልድ አባቶቹና እናቶቹ ያቆዩለትን እነዚህን መልካም እሴቶች ወደነበሩበት እንዲመለሱ ከባድ ሃላፊነት አለበት ለዚህም ከአሁኑ ወገቡን ጠበቅ አድርጎ መነሳት አለበት ተብሎ ይጠበቃል ያን ጊዜ የኢትዮጵያ እሴቶች ይፈካሉ
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 6 /2014