
አዲስ አበባ፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት መጀመሩን አስመልክቶ ክልል ርዕሳነ-መስተዳድሮች የእንኳን ደስአለን መልዕክታቸውን ለመላው ኢትዮጵያውያን አስተላልፈዋል፡፡
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ፣ የሀረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና በክልሉ የታላቁ ህዳሴው ግድብ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ሰብሳቢ ወይዘሮ ሚስራ አብደላ፣ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ተርባይን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ የአሸናፊነታችን አርማና የአንድነታችን ውጤት መሆኑን በመግለጽ ለመላው ኢትዮጵያውያንና ለክልሉ ሕዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውስብስብ ችግሮችን አልፎ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከቆምን የማንሻገረው ችግር እንደሌለ ተጨባጭ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ ሕፃን አዋቂ ሳይል ሁሉም ያለውን አዋጥቶ ያስገነባው ታላቁ ግድብ ለእዚህ ደረጃ መብቃቱ የሚያኮራ ተግባር መሆኑንም ገልጸዋል። ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ግድቡ የሁላችንንም አሻራ ያረፈበት፣ ከጨለማ የሚያወጣን የጋራ ብሔራዊ ሀብታችን መሆኑንም አሳይቷል። ግድቡ ኃይል ከመስጠቱና የዘመናት ችግራችን መፍታት ከመጀመሩም በላይ አንድነታችንን ለማጠናከር፣ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠርና በጋራ ማልማት እንደምንችልም አስተምሮናል ብለዋል።
የህዳሴ ግድቡ ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎችን በብርቱ ተቋቁሞ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ሃገራዊ ዲፕሎማሲውን ለማጠናከር፣ የውጭ ጫናውን ለማቃለልና አንድነታችንን ለማጠናክር እንደሚያግዝም ገልጸዋል። የግድቡ ቀሪ የኃይል ማመንጫ ስራዎች ተጠናቀው ሙሉ በሙሉ አገልግሎት እንዲሰጡ እያደረጉት ያለውን ድጋፍ ክልሉና ከተማ አስተዳደሩ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረው፤ የግድቡ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት በመጀመሩ ለመላ ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉ መልዕከታቸውን አስተላልፈዋል። ኢትዮጵያውያን በፕሮጀክቱ ላይ ያሳዩት ጥረትና አንድነት ፍሬ ማፍራት መጀመሩን ያሳየ ነው ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ሃገሪቱ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥም ሆና የታላቁ ህዳሴው ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል እንዲያመነጭ ማስቻሏ ሕዝብና መንግስት ቁርጠኛ ከሆኑ ፈተናዎችን በመቋቋም ውጤታማ መሆን እንደሚቻል የሚያመላክት ነው ሲሉ ተናግረዋል። ይህ ታላቅ ውጤት እንዲገኝ ላደረጉ ባለሙያዎች፣ የፀጥታ አካላት፣ አመራሮች፣ በተለይም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ምስጋና አቅርበው ግድቡ ሙሉ በሙሉ እስኪጠናቀቅ ሕዝቡ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
የልባችን ሙላት ፣ የአንድነታችን ማሰሪያ ፣ የኢትዮጵያዊነታችን አርማ ፣ የሩቅ ትልማችን ወኔና ጉልበት ፣ የመለወጥ ዘመናችን ማብሰሪያ የሆነው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ተርባይን ኃይል ማመንጨት በመጀመሩ ሁላችሁም እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው የኃይል ማመንጫ ዩኒት በይፋ ኃይል ማመንጨት ጀምሯል። ይህ የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ድል፤ የመደጋገፍና አንድነት ውጤት ነው። በአንድነት ከቆምን ለስኬት እንደምንበቃ ማረጋገጫ ነው ብለዋል።
ከሁሉም በላይ የጋራ ጠላት የሆነውን ድህነት ማሸነፍ የምንችለው ያለንን የተፈጥሮ ፀጋ በጋራ አልምተን በአግባቡ መጠቀም ስንችል መሆኑን መረዳት ይገባል ያሉት ዶክተር ይልቃል፤ ከተባበርንና ከተደጋገፍን ዳር የማናደርሰው የልማት ተግባር የለም፤ ለዚህ ደግሞ ታላቁ የህዳሴ ግድብ አንዱ ማሳያ በመሆኑ ግድቡ እውን እንዲሆን በተደረገው ሁለንተናዊ ተሳትፎ የበኩላችሁን ለተወጣችሁ መላ ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ፤ እንኳን ደስ አለን ሲሉ ገልጸዋል።
ሙሳ ሙሀመድ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 6 /2014