
አዲስ አበባ፡– በሕገወጥ መንገድ በኢትዮጵያ የሚኖሩ ከ70 ሺህ በላይ የውጭ አገራት ዜጎች መመዝገባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ አለም ትናንትና በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ኢትዮጵያ የውጭ አገራት ዜጎች ወደ ሕጋዊ ስርዓት እንዲገቡ የሚረዳ ምዝገባ እያከናወነች ይገኛል። ከተለያዩ አገራት የመጡ ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች ተመዝግበዋል።
እንደ አምባሳደር አለም ገለጻ፤ በእስካሁኑ ምዝገባ በተለያዩ መንገድ ወደኢትዮጵያ የገቡ ከካናዳ፣ ከአሜሪካ፣ ከጣሊያን፣ ከኮንጎ፣ ከናይጀሪያ፣ ከየመን፣ ከሶሪያ፣ ከሱዳን፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከቻይና፣ ከኤርትራ፣ ከቡሩንዲ፣ ከጋና፣ ከባንግላዴሽ፣ ከሕንድ፣ ከላይቤሪያ፣ ከካሜሮን የመጡ ዜጎች ተገኝተዋል።
በህገወጥ መንገድ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ የውጭ ሀገራት ዜጎችን ሕጋዊ የማድረግ ምዝገባው የተጀመረው ሐምሌ 11 ቀን 2014 ዓ.ም እንደነበር ያስታወሱት ቃል አቀባዩ፤ ምዝገባው እስከ ነሐሴ 13 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ እንደሚቆይ ጠቁመዋል።
የምዝገባ ጊዜ ገደቡን አልፈው የተገኙ የውጭ አገራት ዜጎች ላይ መንግሥት ዓለም አቀፍ ሕግጋትን በተከተለ መንገድ ሕጋዊ ርምጃ እንደሚወስድ አሳስበዋል።
በተለያዩ የቪዛ ዓይነት ወደ ኢትዮጵያ የገቡና ቪዛቸው የሚፀናበት ጊዜ ያለፈበት፤ የመኖሪያ ፈቃዳቸው የሚፀናበት ጊዜ ያለፈበት፤ ምንም አይነት ቪዛም ሆነ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው የውጭ አገራት ዜጎች ምዝገባው የሚመለከታቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት የስደተኝነት ወይም የጥገኝነት ጠያቂ ዕውቅና አግኝተው በከተማ ስደተኝነት ለመኖር የተፈቀደላቸው፣ያለፈቃድ ከተለያየ የስደተኛ ጣቢያ በመምጣት የሚኖሩ የውጭ ዜጐችም ምዝገባውን ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል መንግሥት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተፈጠረው ግጭት ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲያገኝ ለማድረግ ለሰላም ውይይቱ ቁርጠኛ መሆኑን በተመለከተ ያነሱት ቃል አቀባዩ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ልክ እንደ ሕዳሴ ግድብ ሁሉ የአፍሪካ ችግር በአፍሪካ መፈታት አለበት የሚል ጽኑ አቋም አለው ብለዋል።
የመንግሥት አቋም በአፍሪካ ሕብረት መሪነት የተጀመረው የሰላም ጥረት እንዲቀጥል ነው። ሌላ ምንም አይነት ተመሳሳይ /parallel/ ጥረት ተቀባይነት የለውም ሲሉ ገልጸዋል።
የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ በሰላም ውይይቱ አመቻችነት እንዲቀጥሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ፍላጎት ነው። አስፈላጊ ከሆነ በአፍሪካ ሕብረት አማካኝት ፕሬዚዳንት ኦባሳንጆን የሚደግፉ የአፍሪካ ታዋቂ ሰዎች ቢጨመሩ ኢትዮጵያ አትቃወምም ሲሉ የመንግሥትን አቋም አሳውቀዋል።
በትግራይ የመሰረታዊ አገልግሎት መጀመርን ለሰላማዊ ውይይቱ መንግስት በቅድመ ሁኔታነት አያስቀምጥም፡፡ ሆኖም አገልግሎቶቹን ለማስጀመር ምክክር እና ዝርዝር ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል። የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አካላት የገንዘብ፣ የተቴክኒክና የሎጂስቲክስ ድጋፍ እንዲያደርጉ ይበረታታል ብለዋል።
ስለታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ያነሱት አምባሳደር መለስ፤ ከሰሞኑ በሱዳንና በግብጽ አካባቢዎች ጎርፍ መከሰቱን በማስታወስ የጎርፍ ተጽዕኖው መከሰቱ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ቢከናወንም በአገራቱ የውሃ አቅርቦት ላይ ጉዳት እንደማያደርስ ያሳየ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ፤ የህዳሴው ግድብ የታችኞቹ ተፋሰስ አገራትን የሚጠቅምና ዓለም አቀፍ የግንባታ ደረጃዎችን የተከተለ ፕሮጀክት ነው። ኢትዮጵያም ለቀጣናው ኢኮኖሚያዊ ትስስር ጠቀሜታ ያለውን ፕሮጀክት በመገንባት የተፈጥሮ ሃብቷን የማልማት መብቷን እየተጠቀመች ነው።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ነሐሴ 6 /2014