ስለ ሕይወት መርሆችና መመሪያዎች ስናነሳ ልዩ ልዩ እንደሆኑ ብዙዎች ይናገራሉ:: በዚያው ልክ ደግሞ ከሚከሰቱባቸው አጋጣሚዎች በመነሳት አንድ ዓይነት ናቸው የሚሉም አይጠፉም:: ምክንያቱም መነሻቸው ማኅበራዊ እሴቶች እንደሆኑ ይታመናልና ነው:: ይህ ማኅበራዊ እሴት ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ እንደግለሰብ በአለን እይታና ግላዊ እርምጃ ይለያያል:: በዚያ ሂደት ውስጥ ስንጓዝም አንዱ ጣፋጩን ሌላው ደግሞ መራራውን እንዲጠጣ ይሆናል:: የራሱን የሕይወት ውጣውረድ እንዲያከብድ አለያም እንዲያቀል የሚያደርገውም ከዚህ የተነሳ እንደሆነ ይገለጻል:: ለዛሬ የመረጥናቸው ‹‹የሕይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳችን ይህንን ሀሳብ የሚያረጋግጡ ናቸው::
እንግዳችን ሕይወት በፈተና የተሞላች ነች፤ ግን ደግሞ ድልም ነች የሚሉ ናቸው:: ድል የምትሆነው ችግር ችግር ሆኖ እንዳይቀጥል ሲሆን ነው:: መከራን ለስኬት መድረሻ ድልድይ ማድረግ ከተቻለ ድል የማይሆንበት መንገድ እንደሌለም ያምናሉ:: በዚህም ገና ከአፍላነት እድሜያቸው ጀምሮ ፈተናዎች ቢያጋጥሟቸውም ከአሰቡት ማማ ላይ ከመድረስ ግን አልገደባቸውም:: እራሳቸውን ብቻ ሳይሆን ያለእናትና አባት የቆዩ እህትና ወንድሞቻቸውን ያሰቡት ላይ ያደረሱ ናቸው እንግዳችን አቶ ጥላሁን ደጀኔ:: በአሁኑ ወቅት የደቡብ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪና በጦርነቱ ወቅት ብዙ ጀብድ የፈጸሙ የቁርጥ ቀን ልጅ ናቸውም::
ኢትዮጵያዊነትን ከልጅነት
በቀድሞ ጎንደር ክፍለ ሀገር በአሁኑ ደቡብ ጎንደር ውስጥ ፎገራ ወረዳ ሴፍአጥራ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር በ1965 ዓ.ም የተወለዱት እንግዳችን፤ በቤተሰብ ፍቅር የታነጹ ናቸው:: በግብርናው ዘርፍ ላይ የተሻለ አቅም ኖሯቸውም እንዲያድጉ ታድለዋል:: ምክንያቱም የቤተሰቡ የገቢ ምንጭ ግብርና ስለነበር እነርሱን በማገዝ ልምድን አዳብረዋል:: ከዚህ ውጪ እንግዳችን በአባታቸው አገር ወዳድነት የተቀረጹም ናቸው:: ለሀገራቸው ካላቸው ፍቅር አንጻር ልጆቻቸውን ጭምር አገር ወዳድ አድርገዋቸዋልና ሀገሬ ብለው እንዲሠሩ፤ እንዲዘምቱ ሆነዋል:: እንደውም አባታቸው ሀገራቸውን ሲጠሯት ‹‹ጦቢያዬ›› እያሉ እንደነበርም አይረሱትም:: ‹‹ለጦቢያዬ አንተ መከታ ሁናት›› የሁልጊዜ ጉትጎታቸው እንደነበረም ያስታውሳሉ:: በዚህም ልጅነታቸው በኢትዮጵያዊነት ስሜት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን በማሻገርም የታጠረ ነበር:: እንደውም ፍላጎታቸው ጭምር ለሀገር መከታ በመሆን ላይ የታጠረ ነው:: ይህም ወታደርነት ሲሆን፤ የተማረና በስነምግባር የታነጸ መሆንን ደግሞ ለዚህ ሙያ ያስፈልገዋል ብለው ያስባሉና ያንን ለመሆን ገና በጨቅላ አዕምሯቸው እያሰቡ ያደርጉት ነበር::
መታዘዝና የተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ የጀመሩትም ከዚህ ሕልማቸው ጋር ተያይዞ እንደነበር ያወሳሉ:: ቤተሰባቸውን በተለያዩ ሥራዎች ሲያግዙም የተለየ ጥንካሬ እንደሚሰጣቸው ያምናሉም:: እናም በእርሻ ሥራው፤ በከብት መጠበቁና ከዚያም ባሻገር የሚሉ የወንድ ሥራዎችን በፍላጎት ይተገብራሉ:: በእርግጥ እነርሱ ቤት ግዳጅ የሚባል ነገር አይታወቅም:: ሁሉም በነጻነት እንዲተገብሩ ነው እድሉ የሚሰጣቸው:: ይህ ደግሞ ጥሩ ተናጋሪ ጭምር ያደረጋቸው እንደነበር ይናገራሉ:: በተጨማሪም ለአካባቢው ሽማግሌዎችና ማንበብ ለማይችሉ ሰዎች ደብዳቤና ማመልከቻ እንዲሁም ወቅታዊ ጋዜጣዎችን የሚያነቡት እርሳቸው በመሆናቸው ጥሩ አንባቢና አብራሪም አድርጓቸዋል::
እንግዳችን ጥሩ አድማጭም ናቸው:: ምክንያቱም ከአባቶች እግር ስር ቁጭ ብለው ታሪክና ባህልን ይማራሉ:: የሚሰጧቸውን አስተያየቶችም ይቀበላሉ:: ከዚያ ባሻገር ተጨዋችም ናቸው:: ከእኩዮቻቸው ጋር በአብዛኛው በወቅቱ የነበረውን ባህላዊ ጨዋታ በፍቅር ይጫወታሉ:: ይህ ደግሞ ለዛሬ ማንነታቸው መሠረት የሆናቸውና ለልጆቻቸው ጭምር እንዲያስተምሩት ያገዛቸው ነው::
ሰው የልምዱ ውጤት ነው የሚል እምነት ያላቸው ባለታሪካችን፤ ኃላፊነትን መቀበል የጀመሩት ገና ወጣት ሳሉ ነው:: ለዚህም ማሳያው ለቤተሰቡ ሁለተኛ ቢሆኑም እናትና አባታቸውን በሞት ሲነጠቁ ዝም ብለው አለመቀመጣቸው ነው:: ታናናሾቻቸውን ከቤተሰቦቻቸው በተማሩት ልክ አሳድገው ለቁምነገር አብቅተዋል::
ትምህርትና ፈተናው
ትምህርታቸውን አሀዱ ያሉት ገና ትምህርት ቤት ሳይመዘገቡ ነው:: አባታቸው ለትምህርት ባላቸው ጉጉት የተነሳ ልጅ ሳሉ ከመምህራን ጋር ተቀራርበው ፊደላትና ቁጥሮችን እንዲያውቁ አግዘዋቸዋል:: ስለዚህም የእርሳቸው ቀለምን የመቅሰም ጅማሮ በትምህርት ቤት ብቻ አልነበረም:: ከዚያ በቅርባቸው በሚገኘው ሴፋጥራማርያም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመዝግበው ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ያለውን ትምህርታቸውን ተከታተሉ:: ቀጠሉናም ከአካባቢው በትንሽ ርቀት ላይ በምትገኘው ወረታ ከተማ በመሄድ ወረታ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍልን ተከታትለዋል:: ከዚያ ደግሞ በወረታ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን ተማሩ::
እስከ12ኛ ክፍል በነበራቸው ቆይታ በጣም ጎበዝ ተማሪ ነበሩ:: ነገር ግን ጊዜው ዝቅተኛ ተማሪ ወደ ዩኒቨርስቲ የሚገባበት በመሆኑ እርሳቸው በኮታ ምክንያት ያንን ሳያደርጉ ቀርተዋል:: ውጤታቸው በወቅቱ ከሦስት ነጥብ በላይ እንደነበርም ያስታውሳሉ:: ያም ሆኖ ግን ዩኒቨርስቲ አልገቡም:: ስለዚህ ለእርሳቸው ይመጥን ወደነበረው ኮሌጅ እንዲገቡ ሆነዋል:: ይህም ቢሆን በጣም የተመረጠና ጎበዝ የሆነ ሰው የሚገባበት ነው:: በወቅቱ ስመ ገናናም እንደነበር ታሪክ ጭምር የሚናገርለት ነው:: እናም እርሳቸው በዚህ ኮሌጅ ማለትም አምቦ ግብርና ኮሌጅ ገብተው ዲፕሎማቸውን በጀነራል አግሪካልቸር በከፍተኛ ማዕረግ አጠናቀዋል::
እንግዳችን ወዲያውኑ የዲግሪ ትምህርታቸውን መቀጠል አልቻሉም ነበር:: ምክንያቱ ደግሞ መጀመሪያ የአባታቸው ሞት ከዚያም ይህ ኅዘናቸው ሳይሽር የእናታቸው ሞት በመደገሙ የተነሳ የቤተሰቡ አስተዳዳሪ ለመሆን ተገደዱ:: ስለዚህም ከአራት ዓመት በኋላ ነበር ዲግሪያቸውን በርቀትና ተከታታይ ትምህርት ከዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በሕግ መመረቅ የቻሉት:: ይህም ሲሆን ቤተሰባቸውን ጎን ለጎን እያስተማሩ ነበር::
ቀጣዩ የትምህርት ጉዟቸው የሆነው ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፤ በሶሻል ሳይኮሎጂ በሁለተኛ ዲግሪ የተከታተሉት ነው:: ከዚያ ባሻገር ዓለማቀፍ ስልጠና ወስደው በኢንተርናሽናል ስፖርት ማኔጅመንት (ኦሎምፒክ) ዲፕሎማ አላቸው:: አሁንም ቢሆን ትምህርት አቁሜያለሁ የሚል እምነት የሌላቸው እንግዳችን፤ በሚገቡባቸው ዘርፎችና የሥራ አጋጣሚዎች ሁሉ ስልጠናዎችን ይወስዳሉ:: ሥራው በራሱ የሚያስተምር በመሆኑ ሁልጊዜ እየተማርኩም ነው ይላሉ::
ሥራና ኃላፊነት
የሥራቸው ‹‹ሀሁ›› የጀመረው ከትውልድ ቀያቸው ብዙም ሳይርቁ ደቡብ ጎንደር ዞን ውስጥ ነው:: በጊዜው ከትምህርት በኋላ ክልል ስለሚመድባቸው ዋግኽምራ ላይ እንዲቀመጡ ሆነዋል:: ዋና ሥራቸው የግብርና ባለሙያ ሲሆን፤ ከአርሶአደሩ ጋር ተቀራርበው የሠሩበት እንደነበር ያስታውሳሉ:: እንደውም የቀደመ ልምዳቸውን በእውቀት እንዲመሩትና እንዲያግዙበት የሆኑበት ስለነበር ሙያው ቢቀየርም ሕልማቸውን ማሳካት እንዲችሉ ረድቷቸዋል:: የተማረ ወታደር የመሆን ሕልማቸውን በተማረ የግብርና ሠራተኛነት ስላረጋገጡትም ደስተኛ ነበሩ:: ይህ ሲሆን ደግሞ እህት ወንድሞቻቸን ሳይረሱና አንድም ቀን ብቻቸውን ሳያድሩና ሳይበሉ ነበር::
ለስምንት ዓመታት በቦታው ላይ የቆዩ ሲሆን፤ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሕግ ከተመረቁ በኋላ ደግሞ የአመራርነት መስመሩን ጀመሩት:: ይህም የወረዳው አመራር አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊነት ነው:: በዚህ ላይ ግን ከሁለት ዓመት በላይ አልቆዩም:: በተሠማሩበት ሥራ ላይ ውጤታማ ነበሩና ለተሻለ ሥራ ታጭተዋል:: ቦታውን ለቀው ወደ ደቡብ ጎንደር ሊቦከምከም ወረዳ ተዛውረው የድርጅት ጽሕፈት ቤት ኃላፊነትን ተረክበዋል::
ከደቡብ ጎንደር ዞን ሳይወጡ ወረታ ከተማ ላይ ሌላኛውን ሥራቸውን የጀመሩት እንግዳችን፤ በዋና ከንቲባነት ለሁለት ዓመት ከስድስት ወር አገልግለዋል:: በቆይታቸውም በርካታ አስመስጋኝ ተግባራትን ፈጽመዋል:: ከዚያ ወደ ፎገራ ወረዳ ሊቦ ላይ አመሩ:: የድርጅት ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ ሆነውም ማኅበራዊ አገልግሎታቸውን ቀጠሉ:: በአካባቢው ዓመት ብቻ ቢቆዩም ምርትና ምርታማነት መጨመር ላይ ትልቅ ሥራ ሠርተው ነው የወጡት:: ከፎገራ በኋላ ደግሞ በቀጥታ ወደ ዞን ያመሩ ሲሆን፤ የደቡብ ጎንደር ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ በመሆንም ሥራቸውን አሀዱ ብለዋል:: ሦስት ዓመታትንም በቦታው ላይ አሳልፈዋል::
በቆይታቸውም በርካታ ተግባራት ያከናወኑ ሲሆን፤ ለአብነት እንደዞን ያልነበረውን የአትሌቲክስ ክለብ ማቋቋማቸው ከሚያስደስታቸው መካከል ነው:: ዛሬ ድረስ ስማቸውን ያስጠራውን ‹‹የጉና አትሌቲክስ ክለብ›› የሚል ቡድን መሥርተዋልም:: በተጨማሪም ብዙ ወጣቶች በስፖርቱ ዘርፍ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ የራሳቸው ገቢ እንዲያገኙም አስችለዋል::
ያላቸው የፖለቲካ ንቃትና የመናገር አቅም ከፍተኛ በመሆኑ ወደ ዞን ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊነት የተዛወሩት እንግዳችን፤ ተቋሙንም በተሻለ መንገድ በመምራት ኅብረተሰቡ እንዲጠቀምም አድርገዋል:: በተለይም አመራሩን ከሕዝቡ ጋር በማቀራረብ የአካባቢውን የመልማት አቅም ከፍ እንዲል፤ የኅብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲታዩና መፍትሔ እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ የማይተካ ሚና ተጫውተዋል:: በተጨማሪም ሕዝቡን በማነቃቃትና ግንዛቤው እንዲሰፋ በማድረግም የሥራ አርበኛ የሚሆንበትን መንገድ ፈጥረዋል::
ቀጣዩ የሥራ ቦታቸው የዞኑ የንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊነት ነበር:: በጊዜው የዞኑን ንግድና ምጣኔ ሀብት የሚገዳደሩ በርካታ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመኖራቸው ያንን የሚፈታ ሰው ያስፈልጋል:: እርሳቸው ደግሞ ለእዚህ ይመጥናሉ ተብለው ከተመረጡት መካከል ሆነዋል:: እናም ምንም እንኳን ቆይታቸው ከዓመት ባይበልጥም የተመረጡበትን ዓላማ ከግብ ከማድረስ ግን አልገደባቸውም:: ወደሌላኛው የሥራ ምዕራፍ ሲሻገሩም አስመስጋኝ ሥራዎችን በመከወን ነበር:: ከእነዚህ መካከል ደግሞ ተጠቃሽ የሚሆነው የንግዱን ማኅበረሰብ ለማነቃቃት ያደረጉት እንቅስቃሴ ሲሆን፤ እውቅናና ሽልማቶችን በክልል ደረጃ ጭምር አግኝተዋል ::
ይህ የሥራ ትጋታቸው ደግሞ ወደቀጣዩ የሥራ ከፍታ
አድርሷቸዋል:: የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ እና የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊነትን አግኝተዋል:: በቦታው ላይ ሳሉም በርካታ ተግባራትን ከውነውበታል:: በተለይም ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ ያደረጉት ነገር የቁርጥ ቀን ልጅነታቸውን ያስመሰከሩበት ነው:: ስለዚህም በሥራው ዓለም በአጠቃላይ በአመራርነት 14 ዓመታትን፤ በባለሙያነት ደግሞ ስምንት ዓመታትን ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን በታማኝነት እንዲያገለግሉ ሆነዋል፤ እያገለገሉም ይገኛሉ::
የሕይወት ፈተና
‹‹ጨለማውን በሻማና በመብራት እንደምናልፈው ሁሉ ችግርንም የመፍትሔ መንገድ ካደረግነው እናልፈዋለን ›› የሚሉት አቶ ጥላሁን፤ ፈተናዎቻቸው በርካታ ቢሆኑም ሦስቱን ብቻ ያነሳሉ:: የመጀመሪያው አባታቸውንና ሌሎች ቤተሰቦቻችው በቦንብ የተደበደቡበት ገጠመኝ ነው:: ሁኔታው ደግሞ በደርግና ኢሕአዴግ ጦርነት በአየር ድብደባ መፈጸሙ እጅግ ሰቅጣጭ ስለነበር ቶሎ ለመርሳት ተቸግረው ነበር:: ነገር ግን እናታቸው ስለተረፉላቸው ትምህርታቸውን ለዓመት ያህል ቢያቋርጡም ነገሮችን በሂደት ረስተዋል::
ሁለተኛው ፈተና ግን የሚቋቋሙት አይነት አይመስልም ነበር:: ምክንያቱም ለመማር ቋምጠው ወደ ኮሌጅ ሲሄዱ የሸኙዋቸውን እናት ሲመለሱ አላገኙዋቸውም:: እናታቸውን ሞት ነጠቃቸው:: ወንድምና እህቶቻቸው እናት አባት የሌላቸው ሆነዋል:: ደጋፊያቸውና አጽናኛቸው ከጎናቸው የሉም:: የቤቱ እማወራም አባወራም ስለሌለ ቤቱ ኦና ሆኗል:: እንደውም በኃላፊነት የሚረከብና እናት አባት የተሸከሙትን ቀንበር የሚሸከም ልጅ ይፈልጋል:: ይህ ደግሞ ከእርሳቸው ውጪ የሚሆን አይደለም:: ታላቅ ወንድማቸው ትዳር ይዞ ስለወጣ ሌሎችን መንከባከብ አይችልም:: ኃላፊነቱ የውዴታ ግዴታቸው ቢሆንም ‹‹ትምህርቴስ?›› የሚል ሀሳብ ውስጥ ከቷቸዋል::
ድርብ ድርብርብ ጭንቀት ውስጥ ሳሉ ነበር መጽናናትን በራሳቸው ላይ ለማምጣት የተጣጣሩት:: እንዳሰቡትም አደረጉት:: በጋውን በትምህርት እያሳለፉ ክረምቱን ከእነርሱ ጋር እየሆኑ ቤቱን ሙሉ ወደማድረጉ ገቡ:: በዚህ ውስጥ ደግሞ ወንድማቸው ከጎናቸው ነበር:: የአካባቢው ማኅበረሰብና ዘመድ አዝማዱም እንዲሁ:: ስለዚህ ያንን የጨለማ ጊዜ በብርሃን ለውጠው ሁሉንም ለቁምነገር አበቁ:: የዚህን ጊዜ ፈተናቸው ከሁሉም በላይ ከባድ ቢሆንም ጫንቃቸው ጠንካራ መሆኑ ግን አሸንፈውታል::
ሌላው ፈታኝ የነበረው ጊዜያቸው ማይጸብሪ ግንባር ላይ የገጠማቸው ሲሆን፤ ነገሩ እንዲህ ነው:: ጠላት የነበረው የሰው ኃይልና ዝግጅት ከፍተኛ ነው:: በዚያ ላይ በእነርሱ በኩል የሚደረገው ውጊያ መከላከልን መሠረት ያደረገ ነው:: በዚህም የጠላት ጦር ምሽጋቸውን ያዘባቸው:: ይህ ደግሞ ሦስት ቀን ሙሉ ያለምንም ረፍት ዝናብ እንዲደበድባቸው ሆኑ:: ከቅዝቃዜው የተነሳም የሚተርፉ ጭምር አልመሰላቸውም ነበር:: በወቅቱ ሞታቸው አላሳሰባቸውም:: ለሀገር የሚከፈል መስዋዕትነት እንደሆነም ያውቃሉ:: ነገር ግን ቤተሰብን ላለማስጨነቅ በሚል ‹‹ጎንደር ለስብሰባ ደርሼ ልምጣ›› ብለው ስለተናገሩ አሳስቧቸዋል:: ግን ባለታሪክ አይሞትምና ያሰቡት አልሆነም:: ይልቁንም ታሪኩን ገልብጠው ጠላት ለሃጩን እያዝረከረከ እንዲወጣ አድርገውታል:: በዚህም ይህንን ጊዜ ደስታም ኃዘንም ማሳለፍ የቻሉበት ጊዜ እንደነበር ያስታውሱታል::
የሀገር አበርክቶ
‹‹አመራር ማለት አገልጋይ ነው:: ሲሾም እንደሚወርድ አውቆ ባለበት ኃላፊነት ልክ የሚሠራ::›› የሚሉት አቶ ጥላሁን ፤ በአመራርነትም ሆነ በባለሙያነት ለሀገራቸው በርካታ ነገሮችን እንዳበረከቱ ያምናሉ:: ምክንያቱም ‹‹አገርን ማገልገል ደረጃው ሊለያይ ይችላል እንጂ በሕይወት ያለ ሰው ሁሉ ኃላፊነት አለበት ›› የሚል እምነት አላቸው:: ፡ ‹‹እኔ አገሬን ማገልገል ጀመርኩ ብዬ የማስበው ገና ከልጅነቴ ጀምሮ ነው:: ቤተሰቤ ያዘዘኝን ነገር አደርጋለሁ:: ያ ደግሞ ሀገርን አንድ ደረጃ ከፍ ለማድረግ የሚተገበር እንደሆነ ይሰማኛል:: ምክንያቱም በእኔ ሥራ ውስጥ የቤተሰቤ ተደምሮበት ልማት ይኖራል›› ባይም ናቸው::
ኢትዮጵያዊነት በተፈጥሮና በባህል የተገነባ ማንነት እንደሆነ የሚያምኑት ባለታሪካችን፤ እኛ የእነዚህ ሁለት ነገሮች ድምር ውጤት ነን:: በዚህም ሕዝቡን ማገልገል ግዴታችን ይሆናል:: ሕዝብ ተገለገለ ማለት ደግሞ ለሀገርም ተሠራ ነው:: እናም ሕዝብ ያለ ተፈጥሮ መኖር አይችልም፤ ከባህሉም መነጠል አይፈልግምና ያንን አክብሮለት መጓዝ በራሱ ልማትን ማስፋፋት እንደሆነ አምናለሁና ያንን አድርጌያለሁም ይላሉ::
በዋናነት ሠራሁበት ከሚሏቸው መካከል የግብርና ባለሙያ ሳሉ የከወኑት ተግባር አንዱ ሲሆን፤ ዘመናዊ የግብርና ሥርዓት ለአርሶአደሩ እንዲደርስ የበኩላቸውን አስተዋፅዖ አድርገዋል:: ከዚያ ከፍ ሲል ደግሞ ምንም እንኳን ዋና ተግባራቸው ፖለቲካውን ማሳለጥ ቢሆንም ማኅበረሰቡን የማያገለግል ፖለቲካ ፖለቲካ አይባልምና የእርሳቸውን ውሳኔ በሚያስፈልግበት ሁሉ እየገቡ ማኅበረሰቡ እንዲጠቀም አስችለዋል:: ከዚህ ውጪ በሁለቱ ተግባራታቸው እንደሚኮሩ ይናገራሉ:: እነዚህም በከንቲባነት በተቀመጡበት ወቅትና በጦርነቱ ወቅት የከወኑት ሥራ ሲሆን ፤ ከንቲባ በነበሩበት ወቅት በሕዝብ ዘንድ የእርስ በእርስ መተማመንና መከባበርን በመፍጠር ትልቅ ሥራ ሠርተዋል:: እርሳቸውን ጭምር የሚያስደስታቸውም ነው::
እነዚህ ሥራዎቻቸው በሁለት መንገድ ተከፍለው የሚታዩ ሲሆኑ፤ የመጀመሪያው ሃይማኖታዊ መስተጋብር ነው:: እርሳቸው ቦታውን ሲረከቡ ከፍተኛ የሆነ ሃይማኖታዊ የመልካም አስተዳደር ችግር ነበረ:: ችግሩ ደግሞ በሁሉም ቤተ እምነቶች ውስጥ የነበረ ሲሆን፤ በቀላሉ ካልተፈታ ማኅበራዊ ቀውስ ውስጥ የሚከት ነው:: እናም እንደመልኩ በማየት መፍትሔ የመስጠት ሥራ ሠርተዋል::
ኦርቶዶክሱ የመስቀል ማክበሪያ ቦታ መቀማት ያጋጠመው ሲሆን፤ ፕሮቴስታንቱ ደግሞ መንገድ አይከፈትልህም ተብሎ መገናኘት አቅቶት ቆይቷል:: በተመሳሳይ የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ደግሞ የመስኪድ ቦታው በወረራ በመያዙ ሃይማኖታዊ አገልግሎቱን መፈጸም አልቻለም ነበር:: እናም ሁሉንም በመፍታት ከሁሉም አክብሮትን ያስገኘላቸው ተግባር በመፈጸማቸው አሁን ድረስ መተሳሰብ የሰፈነበት ከተማ እንዲሆን አስችሏል:: አንዱ ለአንዱ የሚሰጠው ቦታም እንዲጎላ እድል ፈጥሯል:: በዚህ ደግሞ ተመስጋኙ እርሳቸው መሆናቸው እጅጉን ከሚደሰቱበት መካከል መሆኑንም ነግረውናል::
ሌላውና ሁለተኛው የኢኮኖሚ ጥያቄ ሲሆን፤ በተለይም የቤት ጉዳይ ብዙዎችን ለስቃይ የዳረገ ነበርና ለዚያ የሰጡት መፍትሔ ያስደስታቸዋል:: የጦር ጉዳተኞች፣ፖሊሶችና የድሃ ድሃ የሚባሉ እንዲሁም አካል ጉዳተኞችና የጎዳና ተዳዳሪዎች መኖር እስኪያቅታቸው ድረስ ተፈትነዋል:: በዚህም የአመራሩ ቁርጠኝነት ያስፈልግ ነበርና በየደረጃ ችግራቸው እንዲፈታ የተደረገበትን ሁኔታ ቀይሰው ሁሉንም የቤት ባለቤት አድርገዋል:: ለሀገር ብለው የቆሰሉና የደሙ የመከላከያና የፖሊስ አባላት በፊት ቤት እንዳልተሰጣቸው እስስከተረጋገጠ ድረስ ከሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች ቀድመው ቤቱን እንዲያገኙ ወስነዋል፤ አድርገውታልም:: የተቀረው የማኅበረሰብ ክፍልም ቢሆን በመኖሪያ ቤት እጦት መሰቃየት የለበትምና በማኅበር እየተደራጀ እንዲሠራም አድርገዋል::
ሀገር ማለት የነጻነት ቦታ ማለት ነው:: እናም ለዚህ ነጻነት ደግሞ የማይከፈል ዋጋ ሊኖር አይገባውም የሚሉት እንግዳችን፤ ሀገር ፈተና በገጠማት ጊዜ ሁሉ የሚገቡም ናቸው:: አንዱ ማሳያው ደግሞ የሰሜኑ ጦርነት ሲሆን፤ ለቤተሰባቸው ሳይናገሩ ጭምር ዘምተው ተፋልመዋል:: በዚያ ላይ በወቅቱ ለጦርነቱ የሚሆን ሎጅስቲክ አቅራቢ ዘርፉን የሚመሩ ነበሩ:: ከጥምር ኃይሉ ጋር በመሆንም ግብዓቶችን ከማቅረብ ባሻገር በማይጸብሪ ግንባር ዘምተው ተዋግተዋል:: አዋጊም በመሆን አገልግለዋል:: በጋሸና ግንባርም ይህንኑ ደግመውታል:: አዝምተዋል፤ ዘምተዋል:: ከጦርነቱ በኋላም ቢሆን ማኅበረሰቡ እንዲረጋጋ የማድረግ ሥራን እየሠሩ ናቸው::
እርሳቸው ይህንን ብቻ በዋናነት ጠቀሱ እንጂ በወረታ ከተማ የቀይ መስቀልና የመብራት ኃይል አገልግሎት መስጫ ተቋማት እንዲገነቡ ያደረጉ ናቸው:: በተጨማሪም ባለሀብቱ ኢንቨስት እንዲያደርግ ቦታዎችን በማመቻቸት ለማኅበረሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ያስቻሉም ናቸው:: ሁሌም ለሀገራቸው ዲፕሎማት የመሆን ሕልምን አንግበው የሚንቀሳቀሱም እንደሆኑ ይመሰክርላቸዋል:: በእርግጥ በእርሳቸው እምነት የእኔ ድርሻ የጎላ አይደለም ይላሉ:: ምክንያታቸው ደግሞ ኢትዮጵያ እንዳለች እንድትቀጥል ለማድረግ የተደረገው ርብርብ ወሰን የሌለው መሆኑ ነው:: እርሳቸውና መሰል አመራሮች የደም ዋጋ ጭምር ለመክፈል ዝግጁ በነበሩበት ወቅት የተመለከቱትን የሀገር ፍቅር በችግር ጊዜ ብቻ ሳይሆን በደስታም ቢኖር የሚሉት አይነት ነው:: በወቅቱ እንደ ዥረት ወንዝ ሰው በየአቅጣጫው የሀገሩን ፍቅር ለመግለጥ ይወጣ ነበር:: ጥይት ባይዝም ከጥይቱ ባልተናነሰ መንገድ ለማገዝና ወታደር ለመሆን የማይቋምጥ አርሶአደር፣ ባለሀብት፣ የንግዱ ማኅበረሰብ አልነበረም:: ይህ ደግሞ ብዙዎችን ‹‹ለካ አገሬ በችግር አትበገርም›› የሚያስብል ነው:: የቀጣዩንም ተስፋ የሚያለመልም እንደሆነ ማየታቸው ነው::
እንግዳችን በአገር አበርክቷቸው በዞንም ሆነ በክልል ደረጃ የተለያዩ ሽልማቶችንና እውቅናዎችን ያገኙ ሲሆን፤ በክልል ደረጃ ዋንጫ እስከመሸለም ደርሰዋል:: በሕልውናው ዘመቻም በሰሜን ምዕራብ እዝ 33ኛ 34ኛ የእውቅና ሰርተፊኬት ያገኙ ናቸው::
‹‹ልጅህን ለልጄ››
ኢትዮጵያውያን አንዱ ከሚታወቁበት ባህላቸው መካከል ዝምድናን ለማጥበቅ የሚሄዱበት መንገድ ነው:: ይህም ‹‹ ልጅህን ለልጄ›› በሚል የአንዱን ቤተሰብ ከአንዱ ጋር በጋብቻ ዘመድ ማድረግ ነው:: ይህ ዝምድና ደግሞ ልጆች ጭምር ሳያውቁ የሚፈጠር ሊሆን ይችላል:: ነገር ግን የሚቀራረቡበት መንገድ ስለሚከፈትላቸው ጥሩ ፍቅር እንዲኖራቸው ያደርጋል:: እናም የዛሬው እንግዳችን አቶ ጥላሁንም የውሃ አጣጫቸውን ያገኙት በዚህ ሁኔታ ነበር:: እጅግ ተዋደውና ተላምደውም ነበር ሚስትህ ናት የተባሉት::
ይህ ደግሞ የጥያቄውንና እንቢ የማለቱን መንገድ ቀንሶላቸዋል:: በፍቅር የተሳሰረው ትዳርም የስድስት ልጆች እናትና አባት አድርጓቸዋል:: በእርግጥ እርሳቸው ባህል አክባሪ በመሆናቸው ቤተሰብ ባያስብም ከቤተሰብ አይወጡም ነበር:: ሆኖም ባህሉ በራሱ የሠራላቸውን እንስት በማግኘታቸው ደስተኛ ናቸው:: ልጆቻቸውም ቢሆኑ እነርሱ ባይቀበሏቸውም ከባህል ባልዘለለ መልኩ ትዳራቸውን ቢመሰርቱ ደስተኛ ናቸው:: ያው አባት መልካሙን አይደል ለልጆቹ የሚመኘው:: የእርሳቸውን ደስታ ማጋባት የሚፈልጉት በዚህ መንገድ እንደሆነም ይናገራሉ::
አርባ ዓመታትን በትዳር ሲያሳልፉም ፍቅርን እንጂ ሌላ ነገርን አያውቁም:: ችግር እንኳን ቢያጋጥማቸው በመቻቻልና በመተሣሠብ ያልፉታል እንጂ ቅራኔ ውስጣቸው እንዲቆይ አይፈቅዱም:: በዚህ ሕይወታቸው ደግሞ ልጆቻቸው ጭምር ይደሰቱባቸዋል::
መልዕክት
ሕይወታችን ስኬታማ መንገድን እንዲከተል ከፈለግን ለራሳችን ትልቅ ግምት መስጠት አለብን:: ይህ ሲሆን ሌሎችን መውደድ ይመጣል:: ምክንያቱም ራስን ለማስደሰት በሚደረግ ጥረት ውስጥ ሌሎችን መደገፍ አለ:: በአጉል ይሉኝታ ራስ ወዳድ እባላለሁ በሚል ራስን መጣል ተገቢ አይደለም:: ምክንያቱም በራስ ውስጥ የሚታዩ ብዙ ሰዎችን አብሮ መርሳትን ያስከትላልና ነው:: ሰው ራሱን ባከበረ፤ ባወቀና ከፍ ባረገ ማግስት ሌሎችን የሚያይበት ዓይን ይጨምራል:: ስለሆነም ያንን ተረድቶ መንቀሳቀስ ይገባል የመጀመሪያው መልእክታቸው ነው::
ሌላው ያነሱት ሀሳብ በሕይወት ውስጥ ዓላማና ግብን ጠንቅቆ ማወቅና ለዚያ ስኬት መትጋት ያስፈልጋል የሚለው ሲሆን፤ የራስ የሆነን ፍልስፍና መመሪያ በማድረግ ወደፊት መራመድ ይገባል:: ለዚህ ደግሞ ሁልጊዜ ተማሪና ተመራማሪ መሆን ያስፈልጋል:: ራስን ለተፈጥሮ አጋልጦ በመስጠት ውስጥ እውቀትን ማዳበርም ይገባል:: ከሁሉም በላይ አወንታዊ አስተሳሰብ ያለው ሰው መሆን ያሻልም ሲሉ ይመክራሉ::
እንደ ሀገር ሲታይ ደግሞ ለራሳችን የምናስበውን ያህል ለሀገራችንም ማሰብ ያስፈልጋል:: ምክንያቱም ማንም መኖር የሚችለው ሀገር በምትሰጠው እድልና በአለችበት ሁኔታ ልክ ነው:: ነጻ ካልሆነች ነጻነትን ልትቸረው አትችልም፤ ኢኮኖሚዋ ካላደገም እንዲሁ ፍላጎቱን ልትሞላለት አይቻላትም:: ስለሆነም ለእኔ ብሎ ሲሠራ ለሀገሬም የሚል ነገር በእያንዳንዱ ነገር ውስጥ መኖር አለበት ሌላው መልእክታቸው ነው::
አሁን ድል ልናደርጋቸው የሚገቡ በርካታ ችግሮች አሉብን:: በተለይም በአወንታዊ የአሸናፊነት ስሜት የምንመክታቸው:: ይህም በየትኛውም ቦታ ላይ በነጻነት የመኖርና የመንቀሳቀስ መብት ሲሆን፤ የሰው ሞትን መልመድ ሳይሆን ለአንድ ሰውም ቢሆን መሟገት ነው:: ምክንያቱም አንድ ሰው ሌላ ሰው ሊተካው እንደማይችል ይታወቃል:: እናም ለሰው ዋጋ መስጠት ዋነኛ ሥራችን መሆን እንዳለበትም መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ:: እኛም መልዕክታቸው እውን ይሁን እያልን ለዛሬ አበቃን:: ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 1 ቀን 2014 ዓ.ም