ብዙዎች በተማሩት የትምህርት ዘርፍ መሥራትን ይመኛሉ:: ያ ካልሆነ ደግሞ ያገኙትን አጋጣሚ ሁሉ ወደ ሥራ ለመቀየር ይተጋሉ:: አንዳንዶች ግን ሥራ ደጃቸውን እስኪያንኳኳ በመጠበቅ በዙሪያቸው ያሉ በረከቶችን ሳያስተውሉ ጊዜያቸውን ያመክናሉ:: ከጊዜ ጋር የሚሽቀዳደሙ ብርቱዎች ግን አካባቢያቸውን በማስተዋል ለራሳቸው የሥራ እድል ለማኅበረሰቡና ለሀገርም ቱሩፋት ሲሆኑ ይስተዋላሉ :: ቆም ብለው ለሚያስተውሉ አሁን ደግሞ ሰዎች የተማሩትን ከነባራዊ ሁኔታው ጋር ማዋደድ የሚያስችሏቸው ምቹ ሁኔታዎች እየተበራከቱ መጥተዋል:: ብዙዎች ሥራ ፈጣሪ ሆነው ለሌሎች ሲተርፉ የሚታየውም አንድም በዚህ መንገድ ነው::
አካባቢያቸውን በማስተዋል ሥራ ጠባቂ ሳይሆኑ ሥራ ፈጣሪ በመሆን የተማሩትን በተግባር ማዋል ከቻሉ በርካቶች መካከልም ለዛሬ አንድ እንግዳ ይዘን ቀርበናል:: ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች በቀጥታ ሥራ ማግኘት በማይችሉበት በዚህ ዘመን የተማረችውን የአርክቴክቸር ትምህርት ወደ ሥራ የቀየረችው ወጣት ከራሷ አልፋ ለሌሎች መትረፍ ችላለች::
ወይዘሪት ሳምራዊት ሽፈራው ትባላለች:: የዛየን ኢንቴሪየር ፊኒሽንግ ሥራ እንዲሁም የዛየን ብሪጅ መሥራችና ምክትል ሥራ አስኪያጅ ናት:: ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ነው:: የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷንም ያጠናቀቀችው በእዚሁ በአዲስ አበባ ነው:: ከፍተኛ ትምህርቷን ደግሞ በአዳማ ዩኒቨርሲቲ መከታተል ብትጀምርም ልትቀጥልበት አልወደደችም ፣ ወደ አዲስ አበባ በመመለስ አዲስ ኮሌጅ በማታው ክፍለ ጊዜ የአርክቴክቸር ትምህርቷን ተከታትላለች::
በሙያዋ አርክቴክትና ኢንቴሪየር ዲዛይነር የሆነችው ሳምራዊት፤ ተማሪ እያለች ጀምሮ ነው ይህን ሥራ የጀመረችው:: ቀን እየሠራች በማታው ክፍለጊዜ ትምህርቷን ትከታተል ነበር:: በውስጧ ያለውን እውቀትና የሙያ ፍላጎት ማውጣት የምትችልበትን አጋጣሚ ባለማግኘቷ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሠማርታም ሠርታለች:: ለአብነትም ቡቲክና ሞባይል ቤት ከፍታ ሠርታለች፤ ይሁንና ሁለቱም የንግድ ዘርፎች አዋጭና ዘላቂ ሊሆኑላት አልቻሉም:: ይሄኔ በውስጧ ላለው ፍላጎትና ችሎታ ትልቅ ቦታ በመስጠት ጥረቷን ቀጠለች::
በውስጧ ያለውንና በትምህርት ያስደገፈችውን የኢንቴሪየር ዲዛይን ወይም የቤት ውስጥ ውበት ሞያ በሥራ ለማዋል እስክትመረቅ አልጠበቀችም:: ትምህርት ላይ እያለች ጀምራ ሥራውን ለማስተዋወቅ በብዙ ጥራለች:: በማኅበረሰቡና በተማረው ሰው መካከል ያለውን ሰፊ ክፍተት ለማጥበብና ሙያውን ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ፈቃድ በማውጣት ድርጅት ከፍታ ለመሥራት አላመነታችም::
‹‹ተማሪ እያለሁ ጀምሮ ተቀጥሮ መሥራትን አላስበውም ነበር›› የምትለው ሳምራዊት፤ ከውስጥ ፍላጎቷ በተጨማሪ በትምህርት ያጎለበተችውን ዕውቀት ይዛ ገበያ ውስጥ ለመግባትና ከሰው እኩል ለመሆን ብዙ ዋጋ ከፍላለች:: የቤት ውስጥ ውበት ሲባል ለብዙዎች ቀለም ከመቀባት ያለፈ እንዳይደለ የምታነሳው ሳምራዊት፣ አሁን ግንዛቤውን በመፍጠር ለውጥ ማምጣት እንደቻለች ትናገራለች::
‹‹ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ወደ ሥራው ስንገባ ሥራው የማይታወቅ ከመሆኑም ባለፈ የሕንጻ እድሳትም ብዙም አልነበረም›› የምትለው ሳምራዊት፤ አሁን አሁን ሥራው በደንብ እየታወቀና እየሰፋ መምጣቱን ትናገራለች:: በተለይም ከመልሶ ማልማት ጋር በተያያዘ የተለያዩ ተቋማት እንዲሁም መኖሪያ ቤቶች በሚያካሂዱት የማጠናቀቂያ ሥራ /የፊኒሽኒግ ሥራ/ ኢንቴሪየር ዲዛይን ወይም የቤት ውስጥ ውበት እየታወቀ መምጣቱን ትገልጻለች::
ድርጅቱ በዋናነት ሙሉ የሕንጻ ማጠናቀቅ ሥራ ይሠራል:: ማንኛቸውንም የሕንጻ ግንባታ ሥራዎችን እየተከታተለ የውስጥ ውበትን ይሠራል:: የእንጨት፣ የብረትና ሌሎች የውስጥ ውበት ማጠናቀቂያ ቁሳቁስን በመጠቀም የቀለም፣ የጂብሰም፣ የዲዛይንና አጠቃላይ የአርክቴክቸር ሥራዎችን ያከናውናል:: ለአብነትም የጋራ መኖሪያ ቤቶችንና ሌሎች ማንኛቸውንም መኖሪያ ቤቶችንና ቢሮዎችን ጨምሮ አመቺ የማድረግ ሥራ ይሠራል::
አንድ ክፍል ቤት ያለው ሰው አንዷን ክፍል ቤት የቤት ውስጥ ውበትን ተጠቅሞ ቤቱን አመቺ ማድረግ ይቻላል የምትለው ሳምራዊት፤ ሙያው በትንሽ ቦታ ላይ ቦታውን ሊመጥኑ የሚችሉ የቤት ውስጥ ዕቃዎችን በመጠቀም ቤቱን ለነዋሪው አመቺ ማድረግ ያስችላል:: ይህም ቦታን በአግባቡ ከመጠቀም ጀምሮ የተለያዩ ጠቀሜታዎችን ይሰጣል ትላለች::
ሳምራዊት ሥራውን የሙሉ ጊዜ ሥራ በማድረግ ድርጅት ስታቋቁም በዘርፉ ዕውቀት ያለው አቶ ቸርነት ተካም አብሯት ነበር፤ አሁን ድርጅቱን አብረው እያንቀሳቀሱ ይገኛሉ:: እነሳምራዊት ሙያቸውን ወደ ተግባር ለመለወጥና ድርጅቱን ለማቋቋም ትልቁ ፈተና የፋይናንስ ችግር ነበር:: ከፋይናንስ ባለፈም ግንዛቤ መፍጠሩ ደግሞ አድካሚው ሥራ እንደነበር ታስታውሳለች:: ድርጅቱን በ18 ሺ ብር መነሻ ካፒታል በማቋቋም ዛሬ ላይ በዘርፉ ታዋቂ በመሆን ውጤታማ ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ:: በአሁኑ ወቅትም ድርጅታቸው ዛየን ኢንቴሪየር የፊኒሽንግ ሥራ በብዙዎች ዘንድ የታወቀና ከ60 ለሚበልጡ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ድርጅት ሆኗል::
በሀገሪቱ ብዙም ያልተለመደው የቤት ውስጥ ውበት ሥራን ለማስተዋወቅ በብዙ ደክመናል የምትለው ሳምራዊት፤ አሁን ብዙዎች ዘንድ መድረስ እንደቻሉና በርካቶችም አገልግሎታቸውን ፈልገው ወደ እነሱ እንደሚሄዱ ትናገራለች:: ለዚህም ዋናው ምከንያት ሥራ ሰው በሰው መተዋወቅ መቻሉን ትገልጻለች:: ይህም ማለት በአገልግሎታቸው እርካታን ያገኘው ሰው ለሌሎች በመናገር ሰው በሰው በርካቶች ጋር መድረስ ችለዋል::
ሥራው በተግባር የሚታይና ምስክር መሆን የሚችል ነው:: ለዚህም ሥራውን የሚመለከት ማንኛውም ሰው በሥራው ከተማረከ ማነው የሠራው ብሎ በመጠየቅ የሚገኙ ሲሆን በተለይም በአሁን ወቅት ዛየን ኢንቴሪየር ፊኒሽንግ ሥራ ሰው በሰው መተዋወቅ የቻለና ሥራውን አስፍቶ እየሠራ የሚገኝ ነው::
ዘርፉ የተለያዩ ችሎታዎችን የሚጠይቅ እንደመሆኑ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ራሴን አብቅቻለሁ የምትለው ሳምራዊት፤ ሰባት የሚደርሱ ሶፍትዌሮችን በመሥራት ራሷን ብዙ ያስተማረች መሆኑንም ትናገራለች:: የምትቀጥራቸው ሠራተኞችም የተለያየ ዕውቀት እንዲኖራቸው ይፈለጋልና አንድ አይነት ዕውቀት ይዘው ቢመጡ ቀሪዎቹን ክህሎቶች ደግሞ እርሷ በስልጠና የምትሰጥና የምታበቃቸው እንደሆነም አጫውታናለች::
አንድ ሰው አንድ ዕውቀት ይዞ ሊመጣ ይችላል:: ነገር ግን የቤት ውስጥ ውበት ሥራ ሲባል፤ የተለያዩ ሥራዎችን አርክቴክቸር ዲዛይን፣ ኢንቴሪየር ዲዛይን፣ ስትራክቸራል ዲዛይንና ሌሎችንም ይፈልጋል:: እነዚህ ሥራዎች ደግሞ በአንድ ሶፍትዌር ላይ የሚሠሩ አይደሉም:: ስለዚህ በሁሉም ሶፍትዌር ባለሙያዎች ብቁ መሆን ይጠበቅባቸዋል:: በመሆኑም ወደ ድርጅቱ የሚመጡ ባለሙያዎች ወደ ሥራው ከመግባታቸው አስቀድሞ የማብቃት ሥራ በስልጠና ይሰጣል ትለናለች::
የኢንቴሪየር ዲዛይን ሥራ ማሠራት የተለያዩ ጠቀሜታዎች እንዳሉት የምትናገረው ሳምራዊት፤ ገንቢዎች ለግንባታ ከሚያወጡት ወጪ ጀምሮ በርካታ ነገሮችን የሚቆጥብላቸው እንደሆነም ነው ያስረዳችው:: ለአብነትም አንድ ቤት ከሚቀባው ቀለም ጀምሮ የመጋረጃና የሶፋ ጨርቁ፣ የሶፋ ጠረጴዛውና ሌሎችም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች እርስ በእርስ መጣጣም ይኖርባቸዋል:: ለዚህ ደግሞ የቤት ውስጥ ውበት ሙያን ይጠይቃል:: ያ ካልሆነና በቤት ውስጥ ያሉ ነገሮች ሁሉ እርስ በእርስ መስማማት ካልቻሉ ባለቤቱን ለሌላ ወጪ ይዳርገዋል::
አንድ ቤት በኢንቴሪየር ዲዛይን ሲሠራ ሁሉም ነገር በወረቀት ስዕል ላይ የሚያልቅ ይሆናል:: ሥራው ሶፍትዌር ላይ እያለ ደንበኛው በሚፈልገውና በሚያመቸው መንገድ ይዘጋጃል:: በተዘጋጀው መሠረትም አስፈላጊው ቁሳቁስ ቀርቦ እጅግ ባጠረ ጊዜ የቤት ውስጥ ውበት ሥራው ይጠናቀቃል:: ሥራው በየዘርፉ ይከናወናል:: ቁሳቁስ የሚያቀርበው ቁሳቁሱን ያቀርባል:: ቀለም ቀቢውን ጨምሮ አጠቃላይ የዲዛይን ሥራው በቡድኑ የሚሠራ ሲሆን፤ ይህም ሥራውን በጥራትና በፍጥነት እንዲጠናቀቅ በማድረግ የጊዜ፣ የገንዘብና የጉልበት ኪሳራን ያስወግዳል::
በቤት ውስጥ ውበት ሥራ ትልቁና ቦታ የሚሰጠው ቀዳሚው ጉዳይ የቀለም ሳይኮሎጂ እንደሆነ ሳምራዊት ትጠቁማለች፤ ለአብነትም ቀይ ቀለም በባህሪው ቦግ ይላል:: ታዲያ ቀይ ቀለምን ሆቴል ላይ መቀባት ለመዝናናት አልያም አረፍ ብሎ ሻይ ለመጠጣት የሚገባን ደንበኛ ቦግ የማድረግና የማናደድ ባህሪ አለው:: ስለዚህ ኢንቴሪየር ዲዛይን ሥራ በተለይም ቀለም ላይ ትልቅ ትኩረት ያስፈልጋል:: ሰዎች እንደየአካባቢያቸው፣ እምነታቸውና ባህላቸው የከለር ምርጫ ያላቸው በመሆኑ ደንበኛው በሚፈልገውና በሚያመቸው መንገድ ይሠራል::
በአብዛኛው የድርጅቱን አገልግሎት ፈልገው የሚመጡ ሰዎች ሥራቸው በጊዜ የተገደበ ነው:: ለዚህም ፕሮጀክቱ በዚህ ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ብለው የሚመጡ ደንበኞች ይበዛሉ:: መሰል ፕሮጀክቶች በአንድ ጊዜ በርከት ብለው ከመጡ እስከ 100 የሚደርሱ ጊዜያዊ ሠራተኞችን በመቅጠር ሥራውን በተባለው ጊዜ ለማድረስ በሁለትና በሶስት ፈረቃ እንደሚሠሩ ሳምራዊት ትናገራለች::
የኢንቴሪየር ዲዛይን አገልግሎት ከሚፈልጉ አካላት መካከል አብዛኞቹ የፋይናንስ ተቋማት ናቸው፤ አጠቃላይ 60 በመቶ የሚሆኑት ደንበኞች ድርጅቶች እንደሆኑና ከድርጅቱ ጋር ጥሩ ግንኙነት ያላቸው ስለመሆናቸውም ትናገራለች::
ኢንቴሪየር ዲዛይነርና ኢንቴሪየር ዲኮሬተር የተለያዩ ነገሮች ስለመሆናቸው የምታነሳው ወይዘሪት ሳምራዊት፤ አንዳንዶች በተፈጥሮ በተሰጣቸው ችሎታ የተለያዩ ነገሮችን ተጠቅመው ቤታቸውን ያስውባሉ:: ዲኮሬት ማድረግና ዲዛይን ማድረግ ግን ይለያያሉ:: ይህን ልዩነት ብዙዎች የሚያውቁት ባለመሆኑ የዘርፍ መደበላለቅ ይታያል:: ለዚህም በዘርፉ ስልጠና የመስጠት ዕቅድ ያላቸው መሆኑን ትናግራለች::
ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ከሚማሩት ትምህርት በበለጠ በሥራው ዓለም ሲገቡ በርካታ ነገሮችን ያውቃሉ የምትለው ሳምራዊት፤ ለተማሪዎች የተለያዩ ስልጠናዎችን የመስጠት ዕቅድ አላት:: ስልጠናውንም በዘርፉ ለሚማሩና ተመርቀው ለወጡ ተማሪዎች መስጠት ጠቃሚ ነው ትላለች:: ምክንያቱም በዩኒቨርሲቲ የሚሰጠው ትምህርት ብቻ በቂ አይደለም:: በተለይም ሙያውን ስፔሻላይዝድ ለማድረግ ተማሪዎች ማሰብና ወደው ፈቅደው መሆን አለበት::
ሳምራዊት ‹‹ሴቶች በተፈጥሮ የማስዋብ ልምድ አላቸው፤ ጽድት ያለ ነገርም ይፈልጋሉ:: እኔም ሴት መሆኔ ወደ ሙያው እንድገባና ዘርፉን ይበልጥ ስፔሻላይዝድ እንዳደርግ ጠቅሞኛል›› ስትል ትገልጻለች፤ ሴት የሚሰጣትን ሥራ በጥልቀት፣ በትዕግስትና በጥራት ትሠራለች:: የኢንቴሪየር ዲዛይን ሥራም ነገሮችን በጥልቀት ማየትን፣ ጽናትንና ትዕግስትን ይፈልጋል:: ለዚህ ሁሉ ታዲያ በቅድሚያ ሥራው ውስጥ ወደንና ፈቅደን መግባት አለብን:: እኔም ከውስጤ የምፈልገው ሥራ በመሆኑ ውጤታማ ሆኛለሁ›› ትላለች::
ሳምራዊት ከአንድ ጓደኛዋ ጋር ባቋቋመችው በዚህ ድርጅት ውስጥ አጠቃላይ የዲዛይን ሥራውን ትመራለች:: የሥራ አጋሯ ደግሞ ሳይት ላይ ያሉ ሥራዎችን ይመራል:: በጋራ እየመሩት ያለው ድርጅት ታዲያ ውጤታማ ሆኖ ሌላኛው ድርጅት ዛየን ብሪጅ እንዲወለድ አድርጓል:: በአሁኑ ወቅትም የዛየን ኢንቴሪየር ዲዛይን እህት ድርጅት የሆነውን ዛየን ሪልስቴትን እየደገፈ ይገኛል::
ዛየን ብሪጅ ሪልስቴት መሸጥና ኪራይ ላይ የሚሠራ ድርጅት ነው:: ወደዚህ ሥራ ለመግባት በዘርፍ የሚታዩ ችግሮች መነሻቸው ነበር:: አንድ ሰው ሪልስቴት ለመግዛት ብዙ ቦታዎች ላይ በመመላለስ ጊዜውን ይጨርሳል:: ሰዎች ገንዘብ ይዘው የሚፈልጉትን ቤት መግዛት እንዲችሉ የሚያግዘው ይህው ድርጅት የሰዎችን ፍላጎት በማሟላት ዘመናዊ የሆነ የድለላ ሥራን ይሠራል:: በመሆኑም ሰዎች ከእነሱ ጋር ቢሰሩ ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን በማትረፍ በቀላሉ ፍላጎታቸውን ማሟላት እንደሚችሉ ነው የሚያስረዱት::
ከዚህ በተጨማሪም ድርጅቱ የተለያዩ ፕሮፖዛሎችን ያዘጋጀ በመሆኑ በቀጣይ ወደ ተግባር የሚገቡ የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል:: ከእነዚህ ሥራዎች መካከልም ድርጅቱ የኢንቴሪየር ዲዛይን ሥራን ወደ አፍሪካ አገራት ማስፋት አንዱ ሲሆን ለዚህም ዛምቢያና ደቡብ አፍሪካን ተመራጭ አድርገዋል::
እነ ሳምራዊት ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችንም ወደ እነዚሁ ሀገራት ኤክስፖርት የማድረግ ዕቅድ አላቸው:: ለአብነትም ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኝ ግድግዳው በብሎኬት ከተሠራ በኋላ ሲሚንቶ ሳይፈልግ ከቀለም በፊት ቻክ የሚደረግበት በፕራይም ኮት የተባለ ግብዓት አለ:: ይህ ፕራይም ኮት ጅብሰም ሆኖ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኝ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በስፋት እየተሠራበት ይገኛል:: ይህንኑ ኤክስፖርት በማድረግ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ለማምጣት እየሠሩ ይገኛሉ::
ፕራይም ኮት የሲሚንቶን ወጪ ከመቀነሱም በላይ ሥራውን በጥቂት ሠራተኞችና ባጠረ ጊዜ መሥራት የሚያስችል ግብዓት ነው:: ይህን ግብዓት ወደ አፍሪካ ሀገራት በማስፋት የዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን እነሳምራዊት በአሁኑ ወቅት ዛምቢያና ደቡብ አፍሪካ ላይ ጥናት አድርገው ጨርሰዋል፤ በቅርቡም ዛየን ኢንቴሪየር ዲዛይን በዛምቢያ ሥራውን የሚጀምር ስለመሆኑ ሳምራዊት አጫውታናለች
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 30/ 2014