የሰው ልጅ ሁለት ዓይነት ሀብቶች አሉት። አንዱ መንፈሳዊ ሀብቱ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ቁሳዊ ቅሪቱ ነው። ይህንን ወደ ቱሪዝም ቋንቋ እንተርጉመው ብንል የምናገኘው በ«ሀብቶች» ስፍራ «ቅርሶች» ተተክቶ፤ ቅርሶቹም «የሚዳሰሱ» እና «የማይዳሰሱ» ሆነው እናገኛቸዋለን። ከማይዳሰሱት አንዱ ደግሞ ይህ የዛሬ ርእሰ ጉዳያችን ያደረግነው አገር በቀል እውቀት ሰራሹ ሥነቃል ነው።
አንድ ምንጭ (ፊኒጋ (1970)ን እና ፈቃደ (1991)ን) ጠቅሶ ለንባብ የበቃ ጽሑፍ እንደሚያሳየው ሥነቃል የአንድ ሕዝብ ቁሳዊና መንፈሳዊ እሴት መግለጫ፣ የኑሮውና የስሜቱ ነፀብራቅ ነው፡፡
በዱንዴስ (Dundes፡ 1965:5) የተጠቀሰውን ዊሊያም ጆን ቶምስ በመጥቀስ ፎክሎር፤ የነገራትን አሠራርና አኳኋን፣ ልማዶችን፣ በአላትንና ሥርዓተ አክብሮን፣ ዘፈኖች፣ ምሳሌያዊ ንግግሮች፣ እምነትና አምልኮ የሚያጠና የሙያ መስክ መሆኑም ስለሥነቃል ሲነሳ ተቀባይነትን ካገኙት ብያኔዎች አንዱና ሳይጠቀስ የማይታለፈው ነው፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህል አካዳሚ የአማርኛ ቋንቋ መምህር የሆኑት አቶ መስፍን መሰለን ጥናት እየጠቀሱ የሚያረጋግጡ ሰዎች እንደሚሉት ሥነቃል ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ የራሱ መከወኛ አጋጣሚ ያለው ሲከወን ደግሞ ግጥሙን የሚደረድር ወይም ተረቱን የሚተርክ ወይም እንቆቁልሹን የሚጠይቅ፤ ተረቱ ሲወራ የሚያዳምጥ፤ ግጥሙ ሲደረደር የሚቀበል፤ በባህላዊ ልብሶችና በባህላዊ መሣሪያ ሊታጀብ የሚችል፤ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ የአንድ ኅብረተሰብ ሀብት ነው።
ቀደም ሲል የጠቀስናቸው አጥኚዎች እንደሚሉት «ሥነቃል የአንድ ማህበረሰብ ባህል መግለጫ ከሆኑት መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል በዋነኛነት ይጠቀሳል።» እንዲሁም፤ «ሥነ-ቃል የሰው ልጅ ለረዥም ጊዜ ቆይታው ያጠራቀመውንና ዛሬ ያለውን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ገጠመኞቹን የሚያንፀባርቅበትና ለመጪው ትውልድ በቃላዊ መልኩ የሚገልፅበት የሥነጽሑፍ ዘርፍ» ነው። «ሥነቃል ለረጅም ዘመናት በሰዎች አዕምሮ ውስጥ ያለውን ሀሳብ በማስታወስ ለሌሎች ሰዎች በመንገር፣ በመተረት ወይም በመዜም የሚተላለፍ ጥበብ ሲሆን ጥበቡም የማኅበረሰቡን ፍልስፍና፣ ባህል፣ ኑሮ፣ ርዕዮተዓለም፣ ወግ፣ ልማድ፣ ታሪክ፣ የሕይወት ገጠመኝ ወዘተ. ማስተላለፊያ፣ ማስታወቂያና መግለጫ ጥበብ ነው።»
ሥነቃል ለሰው ልጅ የእርስ በርስ መስተጋብር ወቅት በተወሰኑ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚቀርብ የሕዝብ ፈጠራ ውጤት ሲሆን፣ ቃላዊ ተላልፎን መሠረት በማድረግ በትውስታ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር የፎክሎር ዐቢይ ዘርፍ ነው። በመሆኑም ነው ሥነ-ቃል ለፍልስፍና ቀዳሚ ምንጩ፤ ወይም መሠረቱ መሆኑ ላይ እየተነጋገርን ያለነው።
ሥነ-ቃል የአንድ ማህበረሰብ መገለጫ መሆኑ ይሁንታን ካገኘ ሰንብቷል። በዘመናዊው የጥናት መስክም በፎክሎር (ቀጥሎ ያለውን አንቀፅ ይመልከቱ) ስር መታቀፉና ቃላዊ ቅርስና የሕዝብ ሀብት መሆኑ ተደርሶበታል። ከሰው ልጅ የዕለት ተዕለት ሕይወትና ተግባር ጋር ጥብቅ ግንኙነት እንዳለው፤ መገለጫዎቹም ተረት፣ ተረትና ምሳሌ፣ እንቆቅልሽ፣ እንካ ሰላንቲያ … መሆናቸው ተለይቷል። የኢትዮጵያውያን እሴት እንደሆነና ግብረ ገብን የሚያስተምር፣ ታሪክን፣ ልማድን … (ancestral tradition) ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚያስተላልፍ መሆኑም በተመሳሳይ። እንዲሁም፣ «ሥነቃል ልክ እንደ ሥነጽሑፍ ሁሉ የተነገረበትን ማህበረሰብ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች በጥበባዊና በጠለቀ መንገድ ያቀርባል።» የሚለው የጋራ ስምምነትን አግኝቷል። ፍልስፍናዊ፣ ሥነልቦናዊ … የሚሉትንም በዚሁ መንገድ ማየት ይቻላል። በመሆኑም፣ በከፍተኛ ደረጃ ተጠብቆ ለትውልድ መተላለፍ ይገባዋል።
ፎክሎር ብቻውን አየር ላይ የተንጠለጠለ ሳይሆን ዘርፎች አሉት። አጥኚዎቹ (ለምሳሌ ፈቃደ አዘዘ፣ 1991) እንዳገኙት፣ ሥነቃል፣ ቁሳዊ ባህል፣ ሀገረሰባዊ ልማድ እና ሀገረሰባዊ ትውን ጥበባት ናቸው።
ከፋይዳው አኳያ ካየነው ደግሞ ሥነቃል ያስተምራል (ለምሳሌ ተረት)፤ ያመራምራል (እንቆቅልሽ)፤ ያነቃቃል (የሥራ ግጥም)፤ ያስፏጫል ወይም ይነሽጣል (ፉከራ፣ ሽለላ …)፤ ሀሳብን ባጭሩ ለመግለፅ ያገለግላል (ምሳሌያዊ አነጋገር፣ ዘይቤያዊ አገላለፅ …)፤ ታሪክን የማሳወቅ ሚና ይጫወታል (አፈታሪክ)፤ ስለ ነገሮች አመጣጥና አፈጣጠር ያትታል/ያብራራል (ሚት) … ወዘተርፈ። በመሆኑም የአንድን ሕዝብ አጠቃላይ ፍልስፍና ይዟል ማለት ነው። በመሆኑም ከፍልስፍና እውቅና ማግኘት በፊት ሥነቃል ነበር ማለት ነው። በመሆኑን፣ ሊጠበቅና ከትውልድ ወደ ትውልድ በአግባቡ ሊተላለፍ ይገባል እንጂ «በከተሞች ከደበዘዙት ባህሎች ሥነ-ቃል አንዱ ነው» በሚለው የጥናት ግኝት ቆሽታችን ሲቃጠል መኖር የለበትም።
ወደ ዋናው ርእሰ ጉዳያችን ከመሄዳችን በፊት በፎክሎር ጥናትም ሆነ ንባብና ትንታኔ ወቅት በመግቢያነት ሳይጠቀስ የማይታለፈውን፤
ፎክሎር በሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመው ዊሊያም ጆን ቶምስ (Wiliam John Thoms፣ 1803-1885) የተባለ እንግሊዛዊ የጥንታዊ ቅርስ ተመራማሪ (antiquarian) ሲሆን ነሐሴ 22 ቀን 1846 (እ.አ.አ.) አቴንየም (The Atheneum) ለተባለ ትምህርታዊ መጽሔት በጻፈው ደብዳቤ ላይ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን እንግሊዝ አገር ውስጥ የዳበሩ የጥንታዊ (የአሮጌ) ጥናቶች (antiquarian scholarship) ማለትም የጥንታዊ ሕንፃ፣ የጥንታዊ ተረት፣ የጥንታዊ ባህል፣ የጥንታዊ ዘፈን፣ የጥንታዊ መዝገብ ወዘተ ጥናቶች ሲሆኑ የሚጠሩባቸው ስሞች ሕዝባዊ ቅሪት (popular antiquities)፣ ሕዝባዊ ሥነጽሑፍ (popular literature) ወዘተ ነበር፡፡
ቃላዊ ሥነጽሑፍ የሆነው ሥነ-ቃል (በሥሩ የሚካተተው ቃል ግጥምን ጨምሮ) ሀሳብን/መልዕክትን በአጭሩና በማይረሳ መልኩ ለመግለጽ አመች መሆኑ ተጠንቶ ማረጋገጫዎችን ካገኘ ቆይቷል። ሁሉም እንደ አገሩ ቋንቋና ባህል በተለየና በራሱ በሆነ መንገድ ቢጠቅምበትም ሥነ-ቃል በኢትዮጵያውያን (እንደ አጠቃላይም በአፍሪካውያን (ለምሳሌ የመላክነህን Map of African Literature፤ እንዲሁም ፈቃደ፣ 1991፣ 22 እዝስከ 26 ይመለከቷል።)) ዘንድ ለየት ያለ ቦታና ፋይዳ አለው።
እንደምናውቀውም ሆነ በተደጋጋሚ የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት እኛ ኢትዮጵያውያን ሥነ-ግጥምን በተለያየ መልኩ እንጠቀምበታለን፤ … ለደስታ፣ ለኀዘን፣ ለጦርነት፣ ለፍቅር፣ ለጥላቻ፣ ለእምነት መግለጫ፣ ለፈጣሪያችን ምስጋና (ወቀሳንም ጨምሮ) ማቅረቢያ፤ በሕዝብ ላይ የተንሰራፋ የፖለቲካ ዝቅጠትንና የከፋ አገዛዝን፤ እንዲሁም ሙስናን ለመግለጽና በመሳሰሉት አጋጣሚዎች ሥነ-ቃልን እንጠቀማለን። በጉዳዩ ላይ አብዝተው የሠሩት፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎቹ ዘሪሁን አስፋው፤ ዶ/ር ፍቃደ አዘዘ (ሥነቃልን «ኪነተ-ቃል» (1989) ይለዋል)፣ ዶ/ር መላክነህ መንግሥቱ፤ ትውልደ ካናዳዊውና በምርጫ ኢትዮጵያዊው፣ በኢትዮጵያ ፍልስፍና ላይ ተወዳዳሪ በሌለው ደረጃ በርካታ ሥራዎችን የሠሩት፣ የፍልስፍና ፕሮፌሰር ክላውድ ሰምነር (1919–2012)፤ ሩዝ (Ruth Finnegan) እና የመሳሰሉት አጥብቀው የሚነግሩን ይህንኑ ነው። (www.folklore.et የተባለው ድረ-ገጽም በዚሁ ላይ ያተኮረ እንደ መሆኑ መጠን እዚህ ሊጠቀስ ግድ ይላል።)
(እዚህ ላይ «ፎክሎራዊ ጉዳዮችን በመሰብሰብ (አንዳንዶች በማጥናት ይሉታል) በዓለማችን በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱት የግሪም ወንድማማቾች /The Grimm Brothers/ የሚባሉ ሁለት ጀርመናውያን ናቸው፡፡ ሙሉ ስማቸውም ያኮብ ሉድቪክ ካርል ግሪም (Jacob Ludwing Karl Grimm 1785-1863 እ.አ.አ.) እና ቪልሄልም ካርል ግሪም (Wilhelm Karl Grimm 1786-1859 እ.አ.አ.) በመባል ይታወቃል::» የሚለውን በቅንፍ አስቀምጠነው ብናልፍ ከውለታ አንፃር ያስኬደናል ብለን እናስባለን። «ምርጥ የግሪም ተረቶች» በሚል ርእስ ወደ አማርኛ የተመለሰው የእነዚሁ ወንድማማቾች ሥራ መሆኑንም ማስታወሱ አይጎዳምና አድርገነዋል።)
በቋሚና ዘላቂ የኅብረተሰብ ሀብትነቱ የሚታወቀው ሥነቃል «በአንድ ኅብረተሰብ ውስጥ ያለውን ማንኛውንም ክንዋኔ የሚገልጽ ነው። የሚገልጸውም የኅብረተሰቡን አስተሳሰብ፣ አመለካከት፣ እርስ በርሱ ያለውን ግንኙነት» ነው። «ሥነ-ቃል ለአንድ ማኅበረሰብ ዛሬም ሀብት ሆኖ ያገለግላል»። ይሁን እንጂ፣ በከተሞች እየደበዘዙ በመምጣት ላይ ካሉት የሕዝብ ሀብቶችና ማህበረ ባህላዊ እሴቶች መካከል አንዱ መሆኑ በብዙዎች እየተነገረ ይገኛል።
ሥነቃል በከተማ ተቀይጦም ቢሆንም በኅብረተሰቡ ዘንድ አገልግሎቱን እየሰጠ እንደሚገኝ፤ ከከተማው በበለጠ ግን በገጠሪቱ ክፍል መሠረቱን አልለቀቀም የሚለውን የመምህር መስፍንን ጥናት በማስረጃነት የሚያቀርቡ ሰዎች አሁን አሁን ጉዳዩ እየባሰበትና ፈሩን እየለቀቀ መምጣቱን ነው አዝወትረው የሚናገሩት። «ፈሩን አልለቀቀም …» የሚሉት አቶ መስፍንም ቢሆኑ አደጋ ላይ አለመሆኑን አይናገሩም። በመሆኑም፣ ጉዳዩ ያሳስባል፣ ያጠያይቃል፣ ያመራምራልም።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነጽሑፍ «የአማርኛ ቋንቋ ማስተማር ሥነ ዘዴ» ላይ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የሠሩትና ለ32 አመታት በመምህርነት ያገለገሉት አቶ ሚሊዮን ዘውዴ ከጀርመን ሬዲዮ ጣቢያ ጋር አድርገውት በነበረ ቆይታ እንደተናገሩት የሥነቃል ሀብታችን አደጋ አጥልቶበታል። […] ምንም እንኳን ሥነ-ቃል የተለዋዋጭነት ባህርይ ቢኖረውም ሥነቃላችን የመጥፋትና የመረሳት ነገር እየታየበት ነው ያለው። በመሆኑም «ማንነት ማጣት ስለሆነ [ጉዳዩ] ትኩረት ሊሰጠው፤ መፍትሄ[ም] ሊበጅለት ይገባል። ትውልዱ ባህሉን [ወደ] ማወቅ መምጣት አለበት።»
እርግጥ ነው ዛሬ በከተሞች በርካታ ቱባ ቱባ ሕዝባዊ ባህሎች፣ እንዳ’ጠቃላይም የሕዝብ የአኗኗር ፍልስፍናዎች ባልተጠበቀ ፍጥነት እየተቀየሩ ይመስላል። ከእነዚህም መካከል አንዱ ተማራማሪዎቹ ከላይ እንደገለፁት ሥነቃል ሲሆን፤ ይህም በመጽሔት ሁሉ ሳይቀር እየታገዘ እንደሚከናወን እየታየ ይገኛል። (እስኪ አሁን «አባይ ማደሪያ የለው ችክ ይዞ ይዞራል» የሚለውን ምን ይሉታል? መፍጠሩ እንኳን ቢያቅት ነባሩን ይዞ ማቆየቱ ምን ያቅታል?)
«ሰንበሌጥ» ከ’ነተሸከመው ፍልስፍናና ትርጓሜው ወዲያ ተጥሎና ተነጥሎ «የ’ነ ቶሎ ቶሎ ቤት፣ ግድግዳው ብሎኬት» ሆኖ የጸሐፊነት ስማቸውን ካ’ናት ያሰፈሩ ጸሐፊዎች ከስማቸው ቀጥሎ አስፍረውት ማንበብ ለማንም አዲስ አይደለም። ኤሌክትሮኒክሱ ሚዲያም ተቀብሎ ሂድ ሲለው መስማትም እንደዛው።
የሰው ልጅ በቡድን መኖር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የነበረ መሆኑ የሚነገርለት ሥነቃል (ቃላዊ ትውፊት)፤ «ከዕለታት አንድ ቀን …» በሚል መሠረት ላይ በመቆም ረጅም ዕድሜን ማስቆጠሩ፣ የፈጣን አእምሮ ፈጠራ ውጤትና ሲበዛም አመራማሪ መሆኑ የተረጋገጠለት ሥነቃል፤ በሚያገለግለው ማህበረሰብ ታሪክ ላይ የተመሠረተ (የሚመሠረት) መሆኑ የሚታወቅለት ሥነቃል፤ የአንድ ማህበረሰብ ፍልስፍናው መገለጫ እንደሆነ የታመነው ሥነቃል፤ ከዛሬው ዘመናዊ ተብዬ ዘመናይ የፍትህ ሥርዓት ሥራ ላይ ከመዋሉ አስቀድሞ የፍትህና ርትእ ምንጭ ሆኖ ሲያገለግል የኖረው ሥነቃል (ስለሺ ለማን «በላ ልበልሃ …» ያስታውሷል)፤ የአንድን ማህበረሰብ ወግ፣ ልማድ፣ እንዲሁም ታሪክ ማስተላለፊያና ልዩ ልዩ ክስተቶችን እና የሕይወት መልኮችን መግለጫ ጥበብ (ፍልስፍና) የሆነው ስነቃል፤ «በመነገር፣ በመተረት ወይም በመዜም በተወሰኑ ማህበራዊ አጋጣሚዎች ላይ የሚከወን ቃላዊ ፈጠራ» ስለመሆኑ የሚወሳለት ሥነቃል … እንዴት ሆኖ ለእንደዚህ ዓይነቱ የከፋ አደጋ ሊጋለጥ ይገባል የሚል ጥያቄ በቀጥታ፣ በዚህ መልክም ባይሆን በየራሱ መንገድ ሲቀርብ ቆይቷል።
ከዚህ በመለስ በማይባሉ የዘርፉ ጥናቶች ማህበረሰቦች በረጅም ዘመን ታሪካቸው ያጠራቀሙትና የሚያጠራቅሙት ቅርስ ከመሆኑ፤ ለህልውናቸው ሲሉ በሚያደርጓቸውና ከተፈጥሮ ጋር ካላቸው መስተጋብርና ትግል የሚፈጠር የአያሌ ገጠመኞች ጥርቅምና የገጠመኞችም ማንፀባረቂያ መሆኑ፤ ቃላዊ ጥበብ በተለይ ፊደል ቀርፀው በጽሑፍ በማይገለገሉ ማህበረሰቦች ዘንድ ማንነትና ምንነትን፣ እምነትን የኑሮ ዘይቤንና ፍልስፍናን ባጠቃላይ የዓለም አመለካከትን ቀርፆ ለተተኪው ትውልድ በማስተላለፍ ረገድ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ … ወዘተርፈ የታወቀው ሥነቃል እንዴት እንዴት የባህል አፍራሾች፣ ማንነት ናጆች፣ ታሪክ አፋላሾች … ሰለባ ይሁን? የሚለው የወግ ጠባቂዎችና ተቆርቋሪዎች ድምፅ መሰማት ከጀመረ ዘመኑ ዛሬ እንዳልሆነ ድርሳናትን የፈተሸ ሁሉ በሚገባ ያውቀዋል።
ማጠቃለያ
ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ቋንቋዎች ያሏት ትልቅ አገር መሆኗ ይታወቃል። ይህ ማለት ደግሞ ኢትዮጵያ የቱባ ባህል ባለቤት ነች ማለት ነው። በሁሉም አገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ቋንቋዎች አማካኝነት የካበተ የሥነቃል ሀብት ያላት አገር ነች ማለት ነው። ይህ ከሆነ የአገሪቱም ሆነ ሕዝቧ ልዩ ልዩ ፍልስፍናዎች (የአኗኗር፣ አስተሳሰብ፣ አሠራር …) ሁሉ የሚገለፁትም ሆነ የሚቀዱት ከዚሁ ነው ማለት ነው (እስቲ «በሕግ አምላክ» የሚለውን ብቻ እንኳን እንመርምረው፤ ሁለት የገዘፉ ቃላት በአንድ አብረው ለአንድ ጽንሰ ሀሳብ አድረው እናገኛቸዋለን። ከዚህ አኳያ ሥነቃሎቻችን ተደፈሩ ማለት ፍልስፍናችን ተናደ ማለት ይሆናል። ሥነቃሎቻችን ተነኩ ማለት ማንነታችን ተነካ፤ አገር በቀል እውቀታችን ተበረዘ፣ ተከለሰ … ማለት ይሆናል። ሥነቃሎቻችን ማላገጫ ሆኑ ማለት በማንነታችን ተላገጠ ማለት ይሆናል። ሥነቃሎቻችን በነጭ ተሰረዙ ማለት ማንነታችን በነጭ ተሰረዘ ማለት እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም። ሥነቃሎቻችን ተደነቆሉ ማለት አጠቃላይ ሥነጽሑፋችን አይኑ ጠፋ ማለት ነው። ወዘተርፈ ….። ሌሎች አገራት በየአመቱ፣ በተቋም ደረጃ በትላልቅ ቅፆች እየሰበሰቡና እየሰነዱ ማቆየታቸው ለጌጥ ሳይሆን ማንነታቸው በነጭ እንዳይሰረዝ በማሰብ ነው። በመሆኑም፣ እኛም የእኛዎቹን ልናለማቸው፣ ልንጠብቃቸው፤ ጠብቀንም ከ’ነወግ ማእረጋቸው ለትውልድ ልናስተላልፋቸው ይገባል። ግዴታ ያለበት ኃላፊነትም ነው። (ለዚህ ደግሞ ከመቼውም በላይ ዛሬ ምቹ ሁኔታ አለ፤ በሁሉም ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች አሉ።) በኢትዮጵያ ታሪክና ፍልስፍና ላይ እድሜያቸውን የፈጁት ፕሮፌሰሮች (ክላውድ ሰምነር፣ ሪቻርድ ፓንክረስት … እና የመነሳሰሉት) የሚሉት ይህንኑ ነው።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 29 ቀን 2014 ዓ.ም