ዛሬ በምጣኔ ሀብታቸውና በፖለቲካ ተፅዕኗቸው የዓለም ኃያላን የሆኑት አገራት የአገር ውስጥ ባለሀብቶቻቸውን በመደገፍ ረገድ ትልቅ ተሞክሮ አላቸው፡፡ እንዲያውም ለአሁኑ የምጣኔ ሀብት ኃያልነታቸው መሠረት የሆናቸው ከውጭ ጥገኛነት ያላቀቃቸው የአምራችነት አቅማቸው ማደግ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ኢትዮጵያውያን የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላቸው ተሳትፎና ድርሻ በየጊዜው እየተሻሻለ እንደመጣ ባይካድም በቂ የሚባል ግን አይደለም፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ተሳትፎና ድርሻ እንዲሁም ተወ ዳዳሪነት ላቅ ያለ እንዳይሆን የሚጠቀሱት ምክንያቶች ዓይነተ ብዙ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ባዘጋጀው የድሬዳዋው፣ ሁለተኛው፣ ‹‹ስለኢትዮጵያ›› የውይይት መርሃ ግብር ላይ የግሉ ባለሀብት በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ስላለው ተሳትፎ፣ ስላበረከተው አስተዋፅዖ እና ስላሉበት ችግሮች ገለፃ ያቀረቡት የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አህመድ፣ ለአንድ አገር ዘላቂ እድገት የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ያላቸው ሚና የማይተካ እንደሆነ ጠቅሰው፤ የውጭ ባለሀብቶች ለውድድር እና ተሞክሮዎች እጅግ አስፈላጊ ቢሆኑም ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባም አብራርተዋል።
ዋና ሥራ አስፈፃሚው መንግሥት ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች የሚያደርገውን ድጋፍ ማሳደግ እንዳለበት ጠቁመው፤ ‹‹የአገር ውስጥ አምራቹ ከውጭ አገራት ግብይት ከሚያገኘው የንግድ ሥራ ያገኛትን የውጭ ምንዛሪ ለተጨማሪ ኢንቨስትመንት የማዋል ፍላጎት አለው፡፡ ችግሮች በአንድ ጊዜ አይፈቱም፤ ቢሆንም ግን ለውጭ አገር ባለሀብቶች የሚሰጠውን ያህል ትኩረት ሊሠጠን ይገባል›› ብለዋል። የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የአጠቃቀም ፍትሃዊነት መጓደል፣ የሥራ ባህል ደካማነት እንዲሁም ዘርፉን ለማበረታታት የሚወጡ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች በአግባቡ አለመተግበር የዘርፉ ባለሀብቶች ዋና ዋና ችግሮች መሆናቸውን አቶ ጀማል አስረድተዋል። አምራች ኢንዱስትሪው ለዘላቂ ልማት ዋነኛ ሞተር በመሆኑ በዘርፉ ያለውን እምቅ ሀብት ለመጠቀም የባለሀብቱ ችግሮች ተለይተው ሊታወቁና መፍትሄ ሊፈለግላቸው እንደሚገባም አሳስበዋል።
‹‹ሁሉም ችግሮቻችን በአንድ ጊዜ ይፈቱልን አንልም፤ አንጠብቅምም›› ያሉት አቶ ጀማል፤ መንግሥት ከባለሀብቱ ጋር ተቀራርቦ በመሥራት ችግሮቹን መፍታት እንደሚገባውም ተናግረዋል። መንግሥት የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ለመደገፍ የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ ቢሆንም በውጭ ምንዛሬ ጉዳይ ላይ ያለውን ችግር የአቅርቦትና የፍትሐዊነት ችግር ማስተካከል ይገባል›› ብለዋል፡፡
አቶ ጀማል መንግሥት የአገር ውስጥ አምራቾች እንዲበረታቱ ለዓመታት ያከናወነው ሥራ በተለያዩ ዘርፎች የግል ባለሀብቱ እንዲጠናከር አቅም መፍጠሩን ተናግረው፣ በሕዝቡም ሆነ በመንግሥት በኩል የአገር ውስጥ ምርት በመጠቀም ረገድ ያሉ ክፍተቶችን ማስተካከል እንደሚገባ ገልጸዋል። ለዚህም ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› የተሰኘው ንቅናቄ ትኩረት ተሰጥቶት በትክክል ከተተገበረ ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡
የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን የመደገፍ ጥረት በብዙ መልኮች ሊገለፅ ይችላል፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን የሚያበረታቱ ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲዎችን በመቅረፅ፣ ፋይናንስን ጨምሮ ግብዓቶችን በማቅረብ፣ የመሠረተ ልማት አቅርቦትን በማሟላት እንዲሁም ቢሮክራሲያዊ የአሠራር ውጣ ውረዶችን በማቃለል ለባለሀብቶቹ ድጋፍ ማድረግ ይቻላል፡፡
በጂግጂጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር እና የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ጥናትና ምርምር ዘርፍ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ ግርማ፣ ኢኮኖሚያዊ የሆኑትን አብዛኞቹን አስፈላጊ የኢንቨስትመንት ግብዓቶች ባለሀብቶቹ በራሳቸው ለማሟላት ጥረት እንደሚያደርጉ አመልክተው፣ መንግሥት ቢሮክራሲያዊ የአሠራር ውጣ ውረዶችን በማቃለል ረገድ ትልቅ ሚና ሊኖረው እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡ ለአብነት ያህልም መንግሥት አሰልቺ የሆኑ የአሠራር ሰንሰለቶችን በማሳጠርና አገልግሎትን በማቀላጠፍ እንዲሁም የንብረት ጥበቃ በማድረግ ለባለሀብቶቹ ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል፡፡ በተጨማሪም ባለሀብቶቹ በኢንቨስትመንት ላይ የሚኖራቸው ተሳትፎ ዘላቂ እንዲሆን መንግሥት የኃይል አቅርቦትን፣ የመንገድና የሎጂስቲክስ አገልግሎቶችን ጨምሮ ለሌሎች የመሠረተ ልማት ችግሮችም መፍትሄዎችን ማበጀት ይጠበቅበታል፡፡ የውጭ ምንዛሬን በፍትሐዊነት ማቅረብም የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡
‹‹የኢንቨስትመንት ዘርፍ የመንግሥት ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ሁሉ፣ ነፃነትም ይሻል›› የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ሐብታሙ፣ መንግሥት አላስፈላጊ የሆኑ ጣልቃ ገብነቶችን ላለማድረግ የሚያሳየው ቁርጠኝነትም እንደድጋፍ ሊቆጠር እንደሚችል ይገልፃሉ፡፡ ‹‹መንግሥት በምጣኔ ሀብት ውስጥ የሚኖረው ጣልቃ ገብነት የተጠናና በጥንቃቄ የሚመራ ሊሆን ይገባል፡፡ አላስፈላጊ የሆነ መንግሥታዊ ተፅዕኖና ጣልቃ ገብነት ባለሀብቶችንና ኩባንያዎችን የሚያዳክምና በጥቅል አገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ የተገደበ ጣልቃ ገብነት መኖር አለበት፡፡ መንግሥት ኢኮኖሚውን ነፃ አድርጎ ችግሮች ሲያጋጥሙ ድጋፍ/ድጎማ በማድረግ ባለሀብቶችን ማገዝ ይኖርበታል። የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚው ዋነኛ አንቀሳቃሽ ሞተር በመሆኑ ይህን ዘርፍ በተደራጀና ተቋማዊ በሆነ መልኩ መምራትና መደገፍ ይገባል›› ይላሉ፡፡
መንግሥት ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ከሚያደርጋቸው ድጋፎች መካከል አንዱ ባለሀብቶቹን የፋይናንስ አቅምና የሥራ ልምድ ባላቸው የውጭ ባለሀብቶች ጫና እንዳይደርስባቸው መጠበቅ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በእርግጥ ይህ እርምጃ አወንታዊ አበርክቶዎች እንዳስገኘ ባይካድም እርምጃው ከምጣኔ ሀብት መርሆችና ከነባራዊ የዜጎችና የአገር ተጠቃሚነት አንፃር ዳግም ፍተሻ እንደሚያስፈልገው ይገለፃል፡፡
በዚህ ረገድ ረዳት ፕሮፌሰር ሐብታሙ ‹‹መንግሥት የአገር ውስጥ ባለሀብቶች አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ እንዲሁም አቅም ባላቸው የውጭ ኩባንያዎችና ባለሀብቶች ጫና እንዳይደርስባቸው ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ያደረጋቸው ጥበቃዎችና የሰጣቸው ማበረታቻዎች ምን ውጤት እንዳስገኙ ማጥናትና መገምገም ያስፈልጋል፡፡ ‹‹በማበረታቻዎቹ ምክንያት አገርና ዜጎች ምን አተረፉ?›› የሚለው ጉዳይ ጥልቅ ምልከታ ይፈልጋል፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ከውጭ ኩባንያዎች ጫና ለመጠበቅ የሚደረግ ማበረታቻ ከነፃ ኢኮኖሚ የውድድር መርህ የሚገኘውን ማኅበረ-ምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳ እንዳይጎዳው ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ለባለሀብቶቹ ጥበቃ የሚደረግበት አሠራርም እስከመቼ እንደሚዘልቅ በጊዜ ገደብ ሊታሰር ይገባል፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ከውጭ ባለሀብቶች ጋር ተወዳዳሪ የሚሆኑበት አሠራር በተጨባጭ የተግባርና የጊዜ ማዕቀፍ መመዘን አለበት፡፡
በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህርና በ‹‹ፍሮንቲየርአይ (Frontieri)›› ጥናትና አማካሪ ድርጅት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሞላ አለማየሁ በበኩላቸው፤ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍ ጥያቄ ሊነሳበት የማይገባ ጉዳይ እንደሆነና ተጨማጭ ምጣኔ ሀብታዊ ለውጥ እንደሚያመጣ ይናገራሉ፡፡ ባለሀብቶቹ ምርቶችንና አገልግሎቶችን በማቅረብ ከሚኖራቸው ሚና ባሻገር ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ገቢ ምርቶችን በመተካት እና የወጪ ንግድን በመጨመር ትልቅ አስተዋፅዖ ስለሚኖራቸው ይህን ሚናቸውን የበለጠ እንዲያሳድጉ በመንግሥት ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡
እንደዶክተር ሞላ ገለፃ፣ በተለይ ኢትዮጵያ በሥራ አጥነትና በዋጋ ንረት እየተፈተነች ባለችበት በአሁኑ ወቅት የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍ እጅግ አስፈላጊ ተግባር ነው፡፡ የመንግሥት ድጋፍ ምጣኔ ሀብቱን በማነቃቃት፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ የገቢ ንግድ ዕቃዎችን በመተካት፣ የወጪ ንግድን በማሳደግ ጥቅል አገራዊ ምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴው ዘርፈ ብዙ ለውጥ እንዲኖረው ያደርጋል፡፡
የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ከሚጋጥሟቸው ችግሮች መካከል የግብዓቶች (መሠረተ ልማቶች) አለመሟላት፣ የፋይናንስ አቅርቦት ችግር እና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ዋናዎቹ እንደሆኑ ጠቁመው፤ መንግሥት የአጭር ጊዜ መፍትሄዎችን ጨምሮ የባለሀብቶቹን ችግሮች ለማቃለል የሚረዱ የፖሊሲና የመዋቅር እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚኖርበት ይመክራሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት ለባለሀብቶቹ የሚያደርገውን ድጋፍ በየጊዜው መገምገምና ማሻሻል እንዳለበትም ይገልፃሉ፡፡
የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍ አገር በራሷ አምራቾች ላይ እንድትተማመን ያስችላል። ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም ፖለቲካ ምክንያት በሚፈጠሩ ችግሮች ከሚከሰት አደጋ ለመዳንም ይረዳል፡፡ በዚህ ረገድ ዶክተር ሞላ ‹‹የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በፋይናንስና በቴክኖሎጂ አቅም ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማድረግ ምጣኔ ሀብታዊ ስብራትና ክፍተት እንዳይፈጠር ለማድረግ ያግዛል፡፡ ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉት የውጭ ኩባንያዎች በአገር ውስጥ የሚቆዩት የአገር ውስጥ ፖለቲካው እስከተመቻቸው ድረስ ነው፡፡ ፖለቲካው ሳይመቻቸው ቀርቶ ኩባንያዎቹ ከአገር ቢወጡ አገሪቱ በርካታ ዓመታት ወደኋላ እንድትመለስ የሚያደርግ አደጋ ይከሰታል። ስለሆነም ይህን ስጋት ለማስወገድ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን በመደገፍ አቅማቸውን እንዲጎለብቱ ማድረግ ያስፈልጋል›› ይላሉ፡፡
መንግሥት የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ችግሮችን ለማቃለል እየተገበራቸው ከሚገኙ የመፍትሄ እርምጃዎች መካከል የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› አገራዊ ንቅናቄ ተጠቃሽ ነው፡፡ የማምረት አቅምን ማሳደግ፣ ለዜጎች ተጨማሪ የሥራ ዕድል መፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ እና ገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሬን ማዳን ከ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› መርሃ ግብር የሚጠበቁ ውጤቶች ናቸው፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ንቅናቄው የአገር ውስጥ ባለሀብቶች የሚያጋ ጥሟቸውን ችግሮች በማቃለል ረገድ አወንታዊ ሚና እንደሚኖረው ገልፀዋል፡፡ የማምረት አቅም በማሳደግ የወጪ ንግድን ለመጨመርና ገቢ ምርቶችን ለመተካት ለሚደረገው ጥረት አወንታዊ አስተዋፅዖ እያበረከተ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ አቶ መላኩ ከንቅናቄው ምሰሶዎች መካከል አንዱ የአገር በቀል ምርቶችንና አመራረትን ማሳደግ መሆኑን ጠቅሰው፣ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ሳይደግፉ ይህን ማሳካት እንደማይቻል አስረድተዋል፡፡
‹‹መንግሥት የጀመረው ‹ኢትዮጵያ ታምርት› ንቅናቄ አገራዊ የማምረት አቅምን በማሳደግ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርቶች የመተካት ተግባርን ከማጠናከር እርምጃ ጋር ትስስር አለው›› የሚሉት ዶክተር ሞላ፣ ‹‹ለማምረት ምን ያስፈልጋል?›› ለሚለው ጉዳይ ትኩረት ከተሰጠና ንቅናቄው በተገቢው የፖሊሲ ማዕቀፍ እና በተቀናጀ ጥረት ከታገዘ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ችግሮች ለማቃለል አማራጭ መፍትሄ መሆን እንደሚችል ይጠቅሳሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢኮኖሚያቸው የበለጸጉት አገራት የአገር ውስጥ ባለሀብቶቻቸውን በመደገፍ ረገድ በርካታ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡እነዚህ አገራት ባለሀብቶቻቸውን በማገዝና በመጠበቅ የሠሩት ሥራ የአምራችነት አቅማቸውን አሳድጎ የምጣኔ ሀብት እድገታቸው ዘላቂ እንዲሆን አስችሏቸዋል፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር ሐብታሙ እነዚህ አገራት ለአገር ውስጥ አምራቾቻቸው ጥበቃ በማድረግ ትልቅ ሥራ መስራታቸውንና ድጋፋቸውም አሁንም ድረስ የዘለቀ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹አገራቱ የየአገሮቻቸው ምልክት አድርገው የሚቆጥሯቸውን ተቋሞቻቸውን የማበረታታትና የመጠበቅ ሰፊ ልምድ አላቸው፡፡ እነዚህን ተቋሞቻቸውን ደግፈውና ጠብቀው በዓለም አቀፍ ደረጃ ግዙፍና ተፅዕኖ ፈጣሪ ኩባንያዎች እንዲሆኑ አስችለዋቸዋል፤ ዓለም አቀፍ ተቋማት ከሆኑ በኋላም ይንከባከቧቸዋል›› በማለት፡፡ ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ድጋፍና ጥበቃ ማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለመደ አሠራር መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
በምጣኔ ሀብታቸው የበለፀጉት የዓለም አገራት የአገር ውስጥ ባለሀብቶቻቸውን ቀደም ባሉት ጊዜያት ብቻም ሳይሆን አሁንም ከፍተኛ ድጋፍና ጥበቃ እንደሚያደርጉላቸው የሚናገሩት ዶክተር ሞላ፣ አገራቱ በፋይናንስ አቅርቦትም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ለባለሀብቶቻቸው የተለየ የድጋፍ መርሃ ግብር እንዳላቸው ያስረዳሉ፡፡ ‹‹የበለጸጉት አገራት ለአገር ውስጥ ባለሀብቶቻቸው የሚያደርጉት ድጋፍ፣ ገና በማደግ ላይ ያሉ አገራት ከሚያደርጉት ድጋፍ ቢበልጥ እንጂ አያንስም›› ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያ ዘላቂ የምጣኔ ሀብት እንድታስመዘግብ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍና ተወዳዳሪ ማድረግ ይገባል፡፡ ‹‹የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ›› እንዲሉ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍ ዘርፍ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን የመደገፍና ተወዳዳሪ የማድረግ ጉዳይ በምጣኔ ሀብት ትብብርና በእርዳታ ስም የሚደረግን የሀብታም አገራትንና ተቋሞቻቸውን ጣልቃ ገብነት በማስቀረት ሉዓላዊነትን እስከማስከበር ድረስ የዘለቀ ትርጉምና ፋይዳ አለው፡፡
አምራችነቱን ያላሳደገ እና ፍላጎቱንና አቅርቦቱን በራሱ የማምረት አቅም ላይ ያልመሠረተ ምጣኔ ሀብት፣ ዘላቂ እድገትን ሊያስመዘግብ አይችልም። የአምራችነት አቅምን ለማሳደግና ፍላጎትን በማሟላት ከንግድ ሚዛን ጉድለትም ሆነ ጉድለቱ ከሚያስከትላቸው ምጣኔ ሀብት ጫናዎች ለመላቀቅ አገራዊ አምራችነትን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ አገራዊ የማምረት አቅምን በማሳደግ ምጣኔ ሀብታዊ እድገትን ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ ደግሞ ሁነኛው መፍትሄ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን በመደገፍ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴው ዋነኛ ተዋንያን እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 28 ቀን 2014 ዓ.ም