
– ከውጭ ሀገር ሽያጭ 95 ነጥብ 4 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢም አስገኝቷል
አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ኮርፖሬት በ2014 በጀት ዓመት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገራት 12 ሺህ 30 ጊጋ ዋት ኃይል ማቅረቡን አስታወቀ።ለውጪ ሀገራት በተሸጠ የኤሌክትሪክ ሀይል 95 ነጥብ 4 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱንም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ኮርፖሬት ኮምኒኬሽን ዳሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በተጠናቀቀው የ2014 በጀት ዓመትም ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ለከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች፣ እንዲሁም ለሱዳንና ጂቡቲ የኃይል ሽያጭ በማቅረብ ገቢ መሰብሰብ እንደቻለ ተናግረዋል።
በዚህም ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት 9 ሺህ 472 ጊጋ ዋት ማቅረቡን ገልፀው፣ ለከፍተኛ ኃይል
ተጠቃሚ ደንበኞች የእቅዱን 90 በመቶ እንዲሁም ለኢትዮ ጂቡቲ ምድር ባቡር የእቅዱን 116 በመቶ ኃይል ማቅረብ መቻሉን አስረድተዋል።
ተቋሙ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለጂቡቲ 527 ጊጋ ዋት ኃይል ለማቅረብ አቅዶ 611 ጊጋ ዋት ማቅረብ መቻሉን እና ለሱዳን ደግሞ 1 ሺህ 93 ጊጋ ዋት ማቅረቡን ገልጸዋል።
ተቋሙ ለጂቡቲና ሱዳን ካቀረበው የኃይል ሽያጭ 95 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማግኘቱን እንዲሁም ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ካቀረበው ኃይል 11 ቢሊየን ብር እንደተሰበሰበም ተናግረዋል።
ያም ሆኖ ግን የበጀት አመቱ የሀይል ምርት 2013 ዓመተ ምህረት ከነበረው ሲነጻፀር የ1 ነጥብ 9 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን አስታውቀዋል።
በ2013ዓ.ም 15ሺ 7መቶ 87 ጊጋዋት ሰዓት የሀይል ምርት ማመንጨት የቻልን ሲሆን በ2014 አመተ ምህረት ግን 15ሺ 4መቶ 87 ጊጋዋት ሰዓት ነው ማምረት የቻልነው። የዚህ ምክንያት ደግሞ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የነበረው ጦርነት ነው ብለዋል።
ከሐምሌ 2013 እስከ ታህሳስ አጋማሽ ድረስ የአማራና አፋር ክልል ጦርነት ይካሄድበት የነበረ አካባቢ እንደመሆኑ መጠን የአካባቢው ነዋሪዎች እስከ ስድስት ወር ድረስ ኤሌክትሪክ ያላገኙበት ሁኔታ እንደነበር የጠቆሙት አቶ ሞገስ፤ በመሰረተ ልማቱ ላይ ውድመት በመድረሱ የኤሌክትሪክ ሀይል ተጠቃሚው ህብረተሰብ ቁጥር ቀንሶ ነበር ብለዋል።
የሀይል ማስተላለፊያ መሰረተ ልማቱ ውድመት ካጋጠመው የምታመነጨው የኤሌክትሪክ ሀይል እንደሚቀንስ ይታሰባል፤ስለዚህ የዘንድሮው የሀይል ምርት ከአምናው የማመንጨት አቅም በ1 ነጥብ 9 በመቶ ቅናሽ ማሳየት ችሏል ብለዋል።
እንደ አቶ ሞገስ ገለጻ፤ በበጀት አመቱ ከፕሮጀክት ግንባታ ጋር ተያይዞ ወደ ባህር ዳር፣ ወልድያና ኮምቦልቻ የሚገኝ የ4መቶ ኪሎ ቮልት ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ አለ። ይህ የማስተላለፊያ መስመር ግንባታ በሰሜኑ በነበረው ጦርነት ምክንያት ፕሮጀክቱን ለመስራት የሚያስችሉ ብረታ ብረቶች፣ የማስተላለፊያ መስመር እና የተለያዩ እቃዎች ሙሉ በሙሉ ተዘርፈው ተወስደዋል። በዚህም የተነሳ በፀጥታ ችግር ምክንያት ፕሮጀክቱ ላይ ችግር ደርሷል።
ሌላው ከመቀሌ ዳሉል የተዘረጋ መስመር ላይ የፖታሽ ምርት ለሚያመርቱ ፋብሪካዎች ሀይል አቅርቦት ይሆናል ተብሎ የተገነባ የነበረ የማከፋፈያ ጣቢያና የማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ነበር ያሉት ኃላፊው፤ እሱም በጦርነቱ ምክንያት ትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙት አሸጎዳና ተከዜ የሀይል ማመንጫዎች ከግሪድ ጋር ማገናኘት ባለመቻሉ አሁን ላይ ተቋራጮቹ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት እየሰጡ አይደለም ብለዋል። ይህም የፀጥታ ችግር ለሀይል ምርታችን አለመጠናቀቅ ምክንያት ቢሆንም ከጦርነቱ በኋላም የወደሙትን በፍጥነት በመጠገን አገልግሎት እንዲጀምሩ ማድረግ ተችሏል ሲሉም ጠቁመዋል።
በዚህም በ2014 ዓመተ ምህረት እናሳካለን ተብሎ ከታቀደው 86.3 በመቶ የሚሆነውን ማሳካት ተችሏል። ከዚህም በመቀጠል የሀይል ማመንጫ መሳሪያዎችን ደህንነት የመከታተልና የመጠገን ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።
ዳይሬክተሩ አቶ ሞገስ አክለውም በ2015 ዓመተ ምህረት ምናልባት የተጀመረው የሰላም ውይይት በስምምነት የሚጠናቀቅ ከሆነ ወደ ትግራይም በመሄድ የተቋረጡ መስመሮች የሚጠገኑበትና በድጋሚ አገልግሎት የሚሰጡበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል ብለዋል።
የበጀት አመቱ የተሻለ የኔትወርክ ቁጥጥር የተደረገበትና የወደሙ የኤሌክትሪክ መሰረት ልማቶችን መልሶ የመጠገን ስራ ተሰርቷል። ይሄን የመጠገን ስራ የተሰራው በዋናነት በዘጠኙም ክልሎች በሚገኙ የጥገና ሰራተኞቻችን ነው። በስራው ላይ ወደ 370 በላይ ሰራተኞች ተሳትፈዋል።
በየቀኑ ባንድ ሳይት ላይ የቀን ጉልበት ሰራተኞችን ጨምሮ ከ2 መቶ ሰራተኞች በላይ የሚሳተፉበት ጊዜ ነበር ያሉት አቶ ሞገስ፤ የጥገና ጊዜው ፈታኝ እንደነበርም ጠቁመዋል። ጦርነቱ ወዲያው እንደቆመ ወዲያውኑ የኛው ባለሙያዎች ገብተው ይሰሩ ነበር ብለዋል።
ይሄንንም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ኮርፖሬት በተለያዩ ጊዜያት መረጃዎቹን ሲያደርስ መቆየቱን አስታውሰው፣ በወቅቱም የተሰራው ስራ ውጤታማ ነው ብለዋል። ተቋሙም የህብረተሰቡን ጥያቄ ለመፍታት ምን ያህል እየሄደ መሆኑን በአግባቡ ያሳየ ስራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በአንዳንድ ቦታዎች የተኩስ ልውውጥ በነበረበት ወቅት የጥገና ባለሙያዎቻችን ገብተው የጥገና ስራ ሲያከናውኑ ነበር ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ውጤቱም በአጭር ጊዜ ውስጥ አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል የኤሌክትሪክ ሀይል እንዲያገኝ አስችሏል ብለዋል።
ነገር ግን እንደ ሰቆጣና ወልቃይት ያሉ ወረዳዎች የኤሌክትሪክ ሀይል ማግኘት አልቻሉም። ምክንያቱም ሁለቱ አካባቢዎች ኤሌክትሪክ ያገኙ የነበሩት ከትግራይ በሚወጡ መስመሮች ነው። ለምሳሌ የወልቃይቱ በሽሬ በኩል ከሚመጣው መስመር ነው ሃይል የሚያገኘው ሲሉም ጠቁመዋል።
በሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ሀምሌ 25 ቀን 2014