ያሳለፍነው ሳምንት ለኢትዮጵያ የወርቅ ሳምንት ነበር። ወርቁ ደግሞ ሰምና ወርቅ ነበረው። ሰሙ አትሌቶቻችን ያመጡት የሜዳሊያ ወርቅ ነው። ወርቁ ደግሞ እዚህም እዚያም መነቋቆር የነበረበትን አገራዊ ሁኔታ አንድ አድርጎ በአንድ ልብ እንድንግባባ ማድረጉ ነው። ‹‹በሁሉም ነገር እንዲህ ይልመድብን›› አሰኝቷል።
ታሪክን መለስ ብለን ስንዳስስ ደግሞ ይህ ሳምንት የወርቅ ሳምንት ሆኖ እናገኘዋለን።ከ42 ዓመታት በፊት አትሌት ምሩፅ ይፍጠር በድርብ ድል ለአገሩ ወርቅ ያስገኘበት ሳምንት ነው።
ሐምሌ 20 ቀን 1972 ዓ.ም የሞስኮ ኦሊምፒክ የ10 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድርን በማሸነፍ ኢትዮጵያን የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት አደረገ።በአጨራረሱ ላይ በነበረው ድንገተኛ የፍጥነት ለውጥ ምክንያት ‹‹ማርሽ ቀያሪው›› የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቶታል።
ሐምሌ 20 ቀን 1972 ዓ.ም የ10 ሺህ ሜትር ፍልሚያው ተጀመረ። ኢትዮጵያ በምሩፅ ይፍጠር፣ በቶሎሳ ቆቱ እና በመሐመድ ከድር ተወክላለች።10 ሺህ ሜትሩ ሊጠናቀቅ 300 ሜትር ሲቀረው ምሩፅ ማርሽ ቀይሮ ተፈተለከ፡፡
ምሩፅ ሙኒክ ላይ ያሸነፈውን፣ ሞንትሪያል ላይ ደግሞ እርሱ በሌለበት ባለድል የሆነውን እና ‹‹የሞስኮ አየር ጥሩ ከሆነ አሸንፋለሁ›› ብሎ ተናግሮ የነበረውን ፊንላንዳዊውን ላሲ ቪረንን በመርታት አሸነፈ።ላሲ ቪረን ‹‹የሞስኮ አየር ጥሩ ከሆነ አሸንፋለሁ›› ሲል ምሩፅ ደግሞ ‹‹ሐሩርም ይሁን ብረዶ አሸንፋለሁ›› ብሎ ነበር።
10 ሺህ ሜትሩን በ27 ደቂቃ ከ42 ሴኮንድ ከ68 ማይክሮ ሴኮንድ (27፡42፡68) በማጠናቀቅ በኦሊምፒክ ታሪክ የመጀመሪያውን የ10 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ አስገኘ። በዚሁ ውድድር ሻምበል መሐመድ ከድር ሦስተኛ፤ ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ ደግሞ አራተኛ ደረጃን በመያዝ የነሐስ ሜዳሊያና የኦሊምፒክ ዲፕሎማ አግኝተዋል።
የምሩፅ የሞስኮ ኦሊምፒክ ድል በዚህ አላበቃም።ከ10 ሺህ ሜትሩ ድል አራት ቀናት በኋላ፣ ሐምሌ 25 ቀን 1972 ዓ.ም በአምስት ሺህ ሜትር ውድድር ለመካፈል ተሰለፈ።ውድድሩ ሊጠናቀቅ 200 ሜትር ሲቀረው እንደተለመደው ማርሹን ቀይሮ በመፈትለክ ሌላ የወርቅ ሜዳሊያ አሸንፎ ድርብ የኦሊምፒክ ድል አስመዘገበ።ኢትዮጵያም የሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎች ባለቤት እንድትሆን አደረጋት።
በወቅቱ የ10 ሺህ ሜትር ውድድር አንድ፤ የአምስት ሺህ ሜትር ውድድር ደግሞ ሁለት ማጣሪያዎች ነበሯቸው።ምሩፅ በሁለት የፍፃሜ ውድድሮች አሸንፎ ድርብ ድል ያስመዘገበው ሁሉንም የማጣሪያ ውድድሮች በድል በመወጣት ነበር። በዚህም ምሩፅ በአጠቃላይ የሮጠው 35 ሺህ ሜትር ነበር ማለት ነው።
በዚህ ሳምንት የተከናወኑትን ብቻ ስለጠቀስን እንጂ አትሌት ምሩፅ ይፍጠር የበርካታ ድሎች ባለቤት ነው።ውድድር ካቆመ በኋላ እንኳን ከአትሌቲክሱ አልራቀም።እነ ቀነኒሳ በቀለን፤ ሚሊዮን ወልዴንና ገዛኸኝ አበራን የመሳሰሉ የኦሊምፒክ ጀግኖቻችንን በማሰልጠን ሌሎች ጀግኖችንም አፍርቷል።
አትሌት ምሩፅ ከአባቱ አቶ ይፍጠር ተክለሃይማኖትና ከእናቱ ወይዘሮ ለተገብርኤል ገብረአረጋዊ ጥቅምት 5 ቀን 1937 ዓ.ም ዓዲግራት ውስጥ ተወለደ።በወጣትነቱ በተለያዩ የስራ መስኮች ላይ በመሰማራት ቤተሰቦቹን ይረዳ ነበር።በ17 ዓመቱ ወደ አስመራ በመሄድ ኑሮውን በዚያው አደረገ።ጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሳትፎ አንፀባራቂ ድሎችን ማስመዝገቡን በተደጋጋሚ የሰማው ምሩፅ፤ ስለሩጫ ማሰብ ጀመረ።በአበበ ድሎች የተደነቀው ምሩፅ እርሱም እንደ አበበ መሆንን ተመኘ፤ ተመኝቶም ሆነ!
ለ20 ዓመታት ያህል አብዛኛውን መኖሪያውን በካናዳ አድርጎ የቆየው ጀግናው አትሌት ምሩፅ ይፍጠር፤ ባደረበት ጽኑ የሳምባ ሕመም ምክንያት ሕክምናውን እየተከታተለ ቆይቶ ሐሙስ ታኅሣስ 13 ቀን 2009 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
‹‹ … አገሬ ወስዳችሁ እንድትቀብሩኝ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለውለታዬ ነው›› ብሎ በተናዘዘው መሰረት አስክሬኑ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በሺዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፣ ከአገር ቤትና ከካናዳ የመጡ ቤተሰቦቹ፣ ዘመዶቹና ወዳጆቹ፣ በወቅቱ በሥልጣን ላይ ያሉና የቀድሞ መንግሥታት ሚኒስትሮችና የጦር መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ ልዑላን ቤተሰቦችና አድናቂዎቹ በተገኙበት ሥርዓተ ቀብሩ ታኅሣሥ 23 ቀን 2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ መንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል።
ሌላኛዋ የዚህ ሳምንት የወርቅ ክስተት ደግሞ ፋጡማ ሮባ ናት።ቀኑም ተከታታይ መሆኑ አስገራሚ ያደርገዋል።አትሌት ፋጡማ ሮባ በአትላንታ ኦሊምፒክ የሴቶች ማራቶን ውድድር ለኢትዮጵያ ወርቅ ያስገኘችው በዚሁ ሳምንት ሐምሌ 21 ቀን 1988 ዓ.ም ነበር።የአትሌት ፋጡማ ሮባ የወርቅ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም በሴቶች የመጀመሪያ ታሪክ ነበር።
በአንድ ወቅት ለቢቢሲ በሰጠችው ቃለ መጠይቅ ‹‹…የአትላንታ ኦሊምፒክ ለእኔ ከተሳተፍኩባቸው ሁሉ ትልቁ ውድድር ነበር..›› ያለችው ፋጡማ፤ ለውድድሩ በቂ ዝግጅት ብታደርግም ፍርሐት እንደነበራት ተናግራለች። እሷም ሆነች አሰልጣኞቿ ታሸንፋለች ብለው አልጠበቁም ነበር።ዳሩ ግን ባልተጠበቀ ሁኔታ በኦሊምፒክ ማራቶን ውድደድር ላይ በማሸነፍ የመጀመሪያዋ ሴት አፍሪካዊት ሆነች።
ከአትላንታ በኋላ በ1989 ዓ.ም፣ በ1990 ዓ.ም እና በ1991 ዓ.ም በቦስተን ማራቶን ውድድሮች በተከታትይ ለሦስት ጊዜ አሸንፋለች።ከ1990 ዓ.ም እስከ 1991 ዓ.ም የተካሄዱ የቦስተን ማራቶን ውድድሮች በተከታታይ ያሸነፈችውን ፋጡማ ‹‹የቦስተኗ ንግሥት›› የሚል ቅጽል ስም እንዲሰጣት አድርጓል።
አትሌት ፋጡማ ሮባ ታህሳስ 9 ቀን 1966 ዓ.ም በአርሲ ዞን ሌሙና ቢልቢሎ ወረዳ፣ ሁሉሌ ካራ በሚባል ስፍራ እንደተወለደች ታሪኳ ያሳያል። ገጠር ውስጥ ከአርሶ አደር ቤተሰብ ነው የወጣችው።
‹‹ኑሮዬና ትምህርቴም እንደ ማንኛውም የገጠር ልጅ ነበር።በገጠር እንዳደጉት ልጆች ከብቶችን ስጠብቅና ቤተሰብን ስረዳ ስለቆየሁ ቶሎ ትምህርት ቤት አልገባሁም። ትምህርት ቤቱም ከቤተሰቤ ርቆ ስለሚገኝ በደንብ ካደግሁ በኋላ በደርሶ መልስ 14 ኪሎ ሜትር በእግር ተጉዤ እማር ነበር›› ብላለች ለቢቢሲ በሰጠችው ቃለ መጠይቅ።እነዚህ የወርቅ ጀግኖቻችንም እነሆ ወርቃማ ታሪካቸው በደማቁ ተጽፎ ይኖራል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 24 ቀን 2014 ዓ.ም