ሕይወት በውጣ ውረዶች የተሞላች ነች።አንዳንድ ጊዜም መራር ዱላዋን ታሳርፍብናለች።በዚህ ተስፋ ቆርጠን ከተቀመጥን አንድ ስንዝር እንኳን ለመራመድ አዳጋች ይሆንብናል።ነገር ግን ፈተናው የአንድ ጊዜ ክስተት ብቻ ስላልሆነ ትናንትን ረስቶ ነገን ማለም የብልህ ሰው መንገዱ ነው።ተስፋ የምናደርገውን ነገርም ለማሳካት እንታገላለን።አንዳንዶቹም ለዚህ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው።ችግሮችን እንዴት ማለፍ እንደምንችል አስተምረውናል፤ ተስፋችንን አለምልመን ወደፊት እንዴት እንደምንጓዝም በሕይወታቸው ጭምር አሳይተውናል።ከእነዚህ መካከል ደግሞ ለዛሬ ‹‹የሕይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳ ያደረግናቸው ወይዘሮ ወሰንየለሽ እሸቱ አንዷ ናቸው።
እርሳቸው አገር ሰው በሚያስፈልጋት ጊዜ የደረሱ የቁርጥ ቀን ልጅ ናቸው።ለዚህም ማሳያ የሚሆነን በሰሜኑ ጦርነት የተፈናቀሉትን ከጎናቸው በመሆን ማገዛቸው ነው። በየጫካና ዱሩ እንዲሁም ዋሻ ውስጥ ያሉ ሰዎችን በመሰብሰብ የቤት ባለቤት አድርገዋል።የሚበሉትን ላጡም መጋቢ ሆነዋል።በተለይም ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ምግብ ብቻ ሳይሆን ሰውን የተራቡ ሰዎችን አለሁላችሁ በማለት በዓላትን ጭምር ከእነርሱ ጋር በማሳለፍ ሥነልቦናቸውን ያከሙ ናቸው። ጦርነቱ በተበራከተበትና አይደለም ሴት ልጅ ወንዶች እንኳን በማይደፍሩት አካባቢ ሳይቀር ተዘዋውረው የሕዝብን ችግር ማየታቸው እጅግ የሚያስገርመው ተግባራቸው ነበር።
ደግነትን ከልጅነት
የወሎ ልጅ ናቸው።በደሴ ከተማ ቦርቀው ልጅነታቸውን በደስታ አሳልፈዋል።ለቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ ሲሆኑ፤ የፈለጉት ነገር እየተደረገላቸው አድገዋል።የኋላ ኋላ ነገሮች ቢቀየሩባቸውም።በቤቱ ውስጥ ከእርሳቸው ውጪ ብዙ ቤተሰቦች ይኖሩ ነበር።ምክንያቱም እናት አባታቸው ዘመድ አዝማድ ሰብሳቢና የተቸገረ አጉራሽ ናቸው።ይህ ደግሞ ባለ ብዙ ዘመድና አገር ወዳድ አድርጓቸዋል።በተለይም መስጠትን ከልጅነታቸው ጀምሮ እንዲማሩት አድርጓቸዋል።
ቤታቸው እንግዳ የሚበዛበት በመሆኑ የሚበሉትን ምግብ ማካፈልና የሚተኙበትን አልጋ ጭምር መልቀቅም ይጠበቅባቸው ነበር።ይህ ግን አንድም ቀን አበሳጭቷቸው አያውቅም።በተቃራኒው ታላቅን ማክበር ነው ብለው ይወስዱታል።እንደ መማርያቸውም ያደርጉታል።የደግነታቸውን ጅማሮ ያጠነከረው ሌላው ተግባራቸው ለጎረቤት መላላክ መውደዳቸው ነው።አለፍ ሲሉም የአረጋውያንና የአቅመ ደካሞችን ቤት በመጥረግና በመለቅለቅ እንዲሁም የቤት ሥራዎቻቸውን በማገዝ ማገልገላቸው ለሰው ስሱ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ልብስ ወንዝ ወርደው ሲያጥቡ እንኳን የእነዚህ አቅመ ደካሞችና ዝቅተኛ ኑሮ የሚኖሩ ሰዎች ልብስን ከማጠብ ወደኋላ የማይሉ ነበሩና ደግነት የበዛላቸው እንዲሆኑም አግዟቸዋል።ከሁሉም በላይ የሚደንቀውና ለዛሬ መሰረት ጣለልኝ የሚሉት ነገር ደግሞ ከአባታቸው የሚሰጣቸውን ገንዘብ ጭምር በማጠራቀም መለገስ መጣጣራቸው ነው።አባታቸውም ቢሆኑ ሲሰጡ እርሳቸውን በማስቀደም በተግባር እያስተማሯቸው ኖረዋልና ይህንን ተግባር አሳድገውት ዛሬ ድረስ እንዲዘልቁበት ሆነዋል።
እንግዳችን በቤት ውስጥም ቤተሰብ ማገዙ ምንም እንኳን ቢያደክማቸውም ደስተኛ የሚያደርጋቸው ተግባር እንደነበር አይረሱትም።ቤታቸው ባህላዊ የሆኑ መጠጦችና ምግቦች የሚዘጋጅበት በመሆኑም ባህል ወዳድ ያደረጋቸው የልጅነት ስንቃቸው መሆኑንም ያነሳሉ።
በባህሪያቸው ሳቂታና ተጫዋች ናቸው።ይሁን እንጂ ይህ ባህሪያቸው በቤተሰባቸው አልተወደደም።በተለይም በእናታቸው ዘንድ በብዙ መልኩ ተቀባይነት አላገኘም።ምክንያቱም በእርሳቸው እምነት ሴት ልጅ ኮስታራ ስትሆን ነው የምትፈለገው።እናም ትዳር ለማግኘት ጨዋ የሚሉትን ባህሪ እንዲይዙላቸውም የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። ሆኖም እንግዳችን ግን ከመጫወት ራሳቸውን ገድበው አያውቁም።እንደውም ብዙዎቹ ጓደኞቻቸው ወንዶች እንደነበሩ ያስታውሳሉ።
ትምህርትና ፈተናው
አባታቸው ለትምህርት ያላቸው ዋጋ እጅግ ከፍ ያለ ነው።በዚህም በአካባቢው ሴት ልጅ እንድትማር ብዙም ባልተፈቀደበት ሁኔታ እርሳቸው ልጃቸውን አስመዝግበው በሕይወት እስከነበሩበት ዓመት ድረስ አስተምረዋቸዋል።የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በዚያው በትውልድ ቀያቸው ንጉሥ ሚካኤል ትምህርትቤት አስጀምረዋቸዋልም።እስከ ስድስተኛ ክፍል በዚያ ትምህርታቸውን ከተከታተሉ በኋላ ደግሞ ሚኒስትሪን ባለማለፋቸው ቤት እንዳይቀመጡ በማለት በግል እየከፈሉ በካቶሊክ ትምህር ቤት አስተምረዋቸዋል።ይህን ሲያጠናቅቁም ዳግመኛ ወደ መንግሥት ትምህርት ቤት ተመልሰው በሆጤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲማሩ አበረታተዋቸዋል።የዘጠነኛ ክፍልና የአስረኛ ክፍል ትምህርት ጅማሮ የቀጠሉትም በአባታቸው ጉትጎታና እገዛ እንደነበር አይረሱትም።
አስረኛ ክፍል ሲደርሱ ግን ሁሉ ነገር ተደበላለቀባቸው። ያሰቡት ሩቅ ቢሆንም በቅርቡ ተቀጨ። ምክንያቱም የሚንሰፈሰፉላቸውንና በትምህ ርታቸው ስኬታማ እንዲሆኑ የሚያግዟቸውን አባታቸው በሞት ተነጠቁ። በዚያ ላይ የቤተሰባቸው የመጀመሪያ ልጅ በመሆናቸው ቤቱን የማስተዳደር ኃላፊነት በእርሳቸው ላይ ወደቀ። እናም ቤተሰባቸውን ለማገዝ ትምህርታቸውን አቁመው ሥራ ተቀጠሩ።
ከትምህርት ጋር ዳግመኛ የተገናኙት ከፍ ማለት በእውቀት ነው ብለው ያምናሉና ተረጋግተው የሚማሩበትን ካመቻቹ በኋላ ነው። ደሴ ወደ ቤተሰባቸው ጠጋ ብለው ትምህርታቸውን በማታው ክፍለጊዜ በወይዘሮ ስሂን ትምህርትቤት አጠናቀዋልም።ከዚያ በኋላ ግን አልቀጠሉም።ምክንያቱም የ12ኛ ክፍል ውጤታቸው የፈለጉትን ያህል አልሆነላቸውም።በዚያ ላይ ኑሮ መስርተው ቤተሰብ አስተዳዳሪ ሆነዋልና መቀጠሉ ለእርሳቸው ብዙም አልነበረም።እናም ትምህርቱን እዚህ ላይ አቁሞ፤ ዋና ተግባራቸው ሥራ ሆነ።
የልጅ ዋልታነት
ኢትዮጵያ አሁን የሆነችውን የሆነችው እኛ ልትሆንልን በፈለግነው ልክ ማራመድ ባለመቻላችን ነው የሚል እምነት ያላቸው ባለታሪካችን፤ በመራራ ውስጥ ጣፋጭን ማግኘት ይቻላል ባይም ናቸው።በመጥፎ ሁኔታም ውስጥ መልካም ሰዎችን ማግኘትም ይቻላል ይላሉ።ለዚህም በአብነት የሚያነሱት ጦርነትና አጋዦቻቸውን ነው።ችግር የደረሰባቸውን ሰዎች ቀና ለማድረግ የሚሯሯጡ ሰዎች ምስጉኖች እንደሆኑ ያነሳሉ። ምክንያቱም እነርሱን ማገዝ አገርን ማሳደግና መደገፍ ነው ብለው ያስባሉ።
አባታቸው የቤቱ ባላ ነበሩ።የመንግሥት ሰራተኛ በመሆናቸው ቤተሰቡን በሚያገኙት ገቢ ያስተዳድራሉ። እናት ግን ውጪውን እንኳን አያውቁትም። የቤት እመቤት በመሆናቸው በቤት ውስጥ የሚከናወነውን ሥራ ብቻ ይተገብራሉ እንጂ ገቢ ማግኛ ዘዴን እንኳን አለመዱትም። በዚህም ከአባት ህልፈት በኋላ የሚያደርጉት ነገር ጠፍቷቸው ነበር። የገቢ ምንጭ ለማግኘት ለመሞከርም ምኑን አውቀው ያድርጉት።ስለዚህም ኃላፊነቱን ለእንግዳችን ሰጧቸው።የቤቱ ምሰሶ መሆን አለብሽ የተባሉት እንግዳችንም ኃላፊነቱን ተቀብለው እድሜያቸው 17 ቢሆንም ሁለት ዓመት በመጨመር ተመዝግበው ወደ ሥራ ተሰማሩ።
ቤተሰቡን የማስተዳደር ጫናው ያረፈባቸው ባለታሪካችን፤ አንድም ቀን አልችለውም የሚል ነገር ተሰምቷቸው አያውቅም።ይህንን ቤተሰብ በቻሉት ሁሉ ማገዝ እንደሚችሉም ያውቃሉ። በዚህም የአክስታቸው ልጅ ጋር አሳይታ በመሄድ ሥራውን አሀዱ ብለው ነበርና ሰርተው ያገኙትን ገንዘብ በመላክ እናትና እህታቸውን አኑረዋል። በእርግጥ የዚህን ጊዜ አንድ ነገር ቀሎላቸዋል። ይህም እንደበፊቱ ከገጠር የሚመጣው ሰው አልነበረም። ስለዚህም የሚፈልጉትን ነገር በሙሉ ለማድረግ አስችሏቸዋልም።
ወይዘሮ ወሰንየለሽ ሥራቸውን የጀመሩት ግብርና ሚኒስቴር ውስጥ የወረዳ ጸሃፊ ሆነው ሲሆን፤ ቦታው አውሳ አውራጃ ኤሊዳ ወረዳ አፋር ክልል ውስጥም ነው።በአሰብና በጂቡቲ ጠረፍ መካከልም ይገኛል።በወቅቱ የኢሃፓ እንቅስቃሴ የበዛበት በመሆኑ ግርግሮች በስፋት ይታዩ ነበር።ነገር ግን ምንም ቢመጣ እርሳቸውን ከመሥራት የሚያግዳቸው አልሆነምና ፈተናውን ተፋልመው ዓመታትን ሰርተዋል።
አውሳ ላይ ሲሄዱ ከቤተሰብ ወደ ቤተሰብ የሄዱ አይነት ስሜት እንደተሰማቸው ያጫወቱን ወይዘሮ ወሰን የለሽ፤ ለዚህ መሰረቱ አባታቸው እንደነበሩ ይናገራሉ። ምክንያቱም አባታቸው ከአፋሮች ጋር ጥብቅ ቅርርብ ያላቸው ናቸው።እናም መጀመሪያ ቤታቸው በመጋበዝ ከዚያም ደግሞ እነርሱ ያሉበት አካባቢ እንግዳችንን ይዝዋቸው በመሄድ ባህልና አኗኗራቸውን እንዲያውቁ አድርገዋቸዋል።ይህ ደግሞ ምንም እንኳን ልጅ ቢሆኑም የማያውቁትን ማህበረሰብ ስላልተቀላቀሉ ደስተኛ ሆነው እንዲያሳልፉ አግዟቸዋል። አገልግሎታቸውንም በፍቅርና በእውቀት እንዲሰጡ አስችሏቸዋል።በአባታቸው ስም የሚጠሩ የአክስትና የአጎት ልጆች በቦታው ቅርብ ርቀት ላይ መኖራቸው ደግሞ ነገሮችን አቅልሎላቸዋል።ከብቸኝነት ኑሮ ተገላግለውም ባቲ ላይ በመመላለስ ለሶስት አመታት ያህል ሰርተዋል፡፡
በቦታው ሲቆዩ አንዳንድ ፈተናዎች ገጥመዋቸው እንደነበር የሚያወሱት ወይዘሮ ወሰንየለሽ፤ የመጀመሪያው ሙቀቱ ሲሆን፤ ሰውነታቸው ለመልመድ ተቸግሮ እንዳሳለፉበት አይረሱትም። ከዚያ የሚብሰው ግን አንድ ነገር እንደነበርም ይናገራሉ። ይህም በሙቀቱ ምክንያት ምግብ ማብሰል አለመቻላቸው ነው።የበሰለውም ቢሆን ቶሎ ስለሚበላሽ ይደፋል።እንጀራ መጋገርማ ጭራሽ የማይሆን ጉዳይ ነው።እናም ጎረቤት አስቸግረው ነበር የሚያስጋግሩት።ያም ቢሆን በራቸው ክፍቱን ስለሚያድርና ስለሚውል ፍየሎች ገብተው ይደፉባቸዋል።በዚህም ጦማቸውን የሚያድሩበት አጋጣሚ እንደነበረም ያስታውሳሉ። ሌላው ፈተናቸው የጽህፈት ቤታቸው አዲስ መሆን ነው።የሚፈልጉትን ለማግኘት ይቸገሩም ነበር። በቦታው ትምህርትቤት ባለመኖሩና ሕይወታቸውን መለወጥ አለመቻላቸውም ፈተና እንደነበር ያነሳሉ።ከዚህ ውጪ አፋር ቤት እንጂ ውጪ አይደለችም ይላሉ፡፡
ቁልፍ የሚባል ነገር ሳይኖር የሚኖርባት ምድር፤ ማሕበረሰቡ ሰውንም ንብረትንም ጠብቆ በነጻነት የሚንቀሳቀሱባት ክልል ማንንም አላየሁም የሚሉት ባለታሪካችን፤ ይህንን ባህል በተለይም ዛሬ ላይ ያለው ትውልድ ቢያውቀውና ቢኖርበት ምን ያህል እንደሚለውጠን መገመት አያዳግትም ባይ ናቸው። ቀጣዩ የሥራ ቦታቸው በዝውውር ያገኙት የተወለዱባት ከተማ ደሴ ስትሆን፤ የወሎ ክፍለ አገር ግብርና ሚኒስቴር ጸሐፊ ሆነውም ገብተዋል።በዚያ ብዙ ነገራቸውን አስተካክለዋል።የመጀመሪያው ቤተሰባቸውን በቅርብ ሆነው ማገዝ ሲሆን፤ ሁለተኛው ትምህርትታቸው መቀጠል ነው።በመቀጠል ደግሞ ሁሉ ነገር ሲመቻችላቸው ትዳር መስርተው ልጆቻቸውን ወደማሳደጉ ተግባር ገቡ።
ሥራ ወዳዷ እንግዳችን ወደ አገረ አሜሪካ ከሄዱም በኋላ መቀመጥ አልቻሉም።የጤና እንክብካቤ ትምህርት በመማር በግል ለመሥራት በሳንሳይድ ኤጀንሲ አማካኝነት ተቀጠሩ።አዛውንቶችን በመንከባከብም ለዓመታት በኒዎርክ ሰሩ።በዚያ አገር ባህል የሥራ ቦታውን እንደ አገር ቤት ሰው ጠቁሞ አለያም ይዞ ሄዶ አያሳውቅም።በስልክ ሙሉ መረጃው ይሰጥና በቦታው መገኘት ብቻ ነው የሚቻለው።ስለዚህም ቦታውን በቀላሉ መልመድ አልቻሉምና ባለቤታቸው እያደረሳቸው ሲሰሩ ቆይተዋል።በቋንቋም ቢሆን በቀላሉ መግባባት ባለመቻላቸው ልጃቸው ነበረች ብዙ ነገሮችን የምትፈታላቸው። በእርግጥ ይህ የሆነው ለወራት ያህል ነው።ከከለመዱት በኋላ ምንም ሳይቸገሩ 18 ዓመታትን በዚያ ሥራ ላይ አሳልፈዋል።
ሌላው በአሜሪካ አገር ይሰሩት የነበረው ተግባር ቤተክርስቲያን አካባቢ የሚዘጋጁ ዝግጅቶችን መሸፈን ነው።ምግብ አቅራቢም ናቸው።ሥራው ቅዳሜና እሁድን የተንተራሰ በመሆኑ ከሰኞ እስከአርብ ሌላ ተግባራትን ያከናውናሉ።ይህም አዛውንቶችን መንከባከቡ ነው።ልጆቻቸው ኮሌጅ ከገቡላቸው በኋላ አዳር ጭምር ከሰኞ እስከአርብ በቦታው ላይ ይሰራሉ።ቅዳሜና እሁድን ደግሞ እንቅልፍ ሳያምራቸው ለልጆቻቸውም ሆነ ለባለቤታቸው እንዲሁም ለእርሳቸውና ለቤተክርስቲያን
ዝግጅት የሚሆነውን ያዘጋጃሉ።በተለይም ልዩ በዓላት ላይ የተሻለ ገቢ የሚያገኙበት ስለሚሆን ቤተሰቡን ጭምር በማሳተፍ ነው ሲሰሩ የሚያድሩት።በዚህም ደስተኛ ኑሮን እንዲገፉ ሆነዋል።ለዚህ ደግሞ ባለቤታቸውን እጅግ አድርገው ያመሰግኑታል።
ኑሮ በአሜሪካ
እርሳቸው ደሴ በነበሩበት ወቅት አብዛኛው የደሴ ልጅ ውጭ አገር ብሎ የሚያስበውና መሄድ የሚፈልገው ጅቡቲ ነው።በጊዜው አረብ አገር እንኳን አይታሰብም። ምክንያቱም ያ አይታወቅም። እናም እርሳቸውም እንደሌላው ልጅ ጅቡቲን አስበው ነበር።ይሁንና በቅርብ ርቀት ላይ ሆነው ስላዩዋትና ከዚያ የሚመጡ ሰዎችን ስለሚያውቁ በኑሮ አገርን የመሰለ ነገር እንደሌለ እንዲረዱ አድርጓቸዋል።እናም ሁልጊዜ አገሬ እያሉ ነው የኖሩት።አንድም ቀን ውጭ አገር እሄዳለሁ ብለውም አያስቡም።ከዚህ ጋር ተያይዞም ባለቤታቸው በዲቪ አሜሪካ ገብቶ እንኳን ቶሎ ለመሄድ አልፈለጉም።ረጅሙን ጊዜ አገራቸው ላይ ከልጆቻቸው ጋር ነው ያሳለፉት።ሆኖም ተነጣጥሎ መኖር ተገቢነት እንደሌለው በቤተሰቦቻቸውና በሌሎች ሲገፋፉ ደሴን ለቀው አሜሪካ እንዲገቡ ሆኑ።
እንግዳችን ልጆቻቸውን በኢትዮጵያ ወግና ባህል አሳድገዋል።ይህንን በሚያደርጉበት ጊዜ ግን በጣም ተፈትነዋል። ምክንያቱም በሁለቱ አገራት መካከል የባህል ልዩነት አለ። በተለይ አንዳንዶቹ ልጆቻቸው የዚያን አካባቢ ባህል በመልመዳቸው ሊቆጧቸው እንኳን አይችሉም።ለፖሊስ እንደውላለን ብዙ ጊዜ መፈክራቸው እንደሚሆንባቸውም ያወሳሉ። ነገር ግን እርሳቸው አይሰሟቸውምና ኢትዮጵያዊነትን በሚገባ እንዲኖሩት አስተምረዋቸዋል።በዚህ ደግሞ ልጆቻቸውም ሆኑ እርሳቸው ደስተኞች ናቸው።
በኢትዮጵያ ሰባት ልጆችን ወልደዋል፤ አሳድገዋልም። ይሁን እንጂ በአገራቸው እያሉ ለልጆቻቸው የሆነው ነገር በዚያ አልሆነም።ምክንያቱም በአሜሪካ ጎረቤትና የአካባቢ ሰው ልጅን ያሳድጋል ተብሎ አይታሰብም።ሁሉም የሥራ ጫና በቤተሰብ ላይ ነው የሚያርፈው።የቤት ሥራውም ሆነ የልጆች ቁጥጥሩ የእርሳቸው ኋላፊነት ብቻ ነው።ከጠዋት እስከ ማታ ያለው ሩጫ ምንም ፋታ አይሰጥምም።እንደልብ ጎረቤት ጋር ላስቀምጥም የለም። ስለዚህም በዚያ ያለ የልጅ አስተዳደግ ‹‹አገሬ ማረኝ›› ያሰኛል።ኢትዮጵያ ውስጥ ነብስ አውቀው ባይሄዱ ኖሮ እጅግ ከባድ የኑሮ ውጣውረድን እንደሚያሳልፉ ይናገራሉ።
ሌላው አሜሪካ ላይ የሚከብደው ደግሞ ማሕበራዊ ሕይወት እንደሆነ የሚያነሱት እንግዳችን፤ በአገረ አሜሪካ ብቸኝነት እንጂ ሕብረት አይታወቅም። ሲበላ እንኳን ቤተሰቤ፣ ጎረቤቴ ይጠራ የማይባልበት ነው። በዚህም አብሮ መብላትንና አብሮ ኀዘንን መካፈል ለለመደ ኢትዮጵያዊ ሰማዩ የተደፋበት ያህል ነው የሚሰማው።ምክንያቱም ይህን አኗኗር አያውቀውም። እናም እርሳቸውም ይህንን ለመሆን በብዙ መንገድ አልቻሉበትም። እንደውም ቤተክርስቲያን አካባቢ ተጠግተው መሥራት ባይጀምሩና ነገሮች ባይቀየሩላቸው ኖሮ በዚያ መቆየትን አያስቡትም ነበር።ሆኖም እድለኛ ሆኑና ኢትዮጵያዊነት በቤተክርስቲያኑ አካባቢ ተከሰተላቸው።
ቤት ውስጥ መዋልና ካለመዱት ጋር በሥራም ቢሆን ማሳለፍ እጅግ ያሳምማል። በዚያ ላይ እንደኢትዮጵያውያን ቡና መጠጣጣትና መረዳዳት የለም።ስለዚህም የአዕምሮ በሽተኛ ጭምር ያደርጋል።ግን በቤተክርስቲያን እንዲህ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል።በተለይም ማሕበራዊ መስተጋ ብሮቹ በደስታም በኀዘንም የጠነከሩ በመሆናቸው አሜሪካ ሳይሆን ኢትዮጵያ እንደሚኖሩ ከማስቻሉም በላይ ሳምንቱን በናፍቆት እየጠበቁ ሥራቸውን እንዲሰሩም አግዟቸዋል። ከዚያ አልፎ ቤታቸው ጠባብ ስለሆነ በዚያ ብዙ ነገራቸውን እንዲሸፍኑ እድል ሰጥቷቸዋልም።ማሕበር መስርተው ጭምር ለአገራቸው የሚደርሱበትን መርሃግብር እንዲዘረጉም እድል ፈጥሮላቸዋል።
የአገሬ ችግር የኔም ነው
ወደአገራቸው የተመለሱትና ለአገራቸው ድጋፍን ለማድረግ የመጡት ከ20 ዓመት ቆይታ በኋላ ነው።በአሜሪካ አገር ተስፋ ለኢትዮጵያ ድርጅት ውስጥ በመግባት በጸሀፊነት በማገልገላቸውም አገሪቱ እያጋጠማት ያለውን ችግር በዓይናቸው አይተው የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ አነሳስቷቸዋል።በእርግጥ እገዛውን በድርጅቱ ድጋፍ ብቻ አልነበረም ያደረጉት።ገንዘብ በማሰባሰብና (ፈንድ ራይዚንግ) በማዘጋጀትና ቤተሰቦቻቸውን በማስቸገር ጭምር ነው።
አገራቸውን ማገዝ የጀመሩት ኮሮና ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ነው።በፈንድራይዚንግ 40 ሺህ ዶላር አግኝተው ለአገራቸው ችግር መፍቻ አበርክተዋል።ጦርነቱ ጠንከር ሲል ደግሞ ፊታቸውን ወደዚያ አዙረው ድጋፍ የሚያደርጉበትን መንገድ ዘረጉ። የመጀመሪያው ድጋፍ ያደረጉት ድርጅታቸው ሲሆን፤ ቀጣዩ ደግሞ ጓደኞቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ናቸው።
የጦርነትን አስከፊነት ከእርሳቸው በላይ የሚረዳው ማንም የለም።ምክንያቱም እናታቸውን ያጡት በዚህ ጦርነት ምክንያት ነው። ኢህአዴግ ሲገባ ተሸሽገው ካሉበት ተባራሪ ጥይት መትቷቸው አጧቸው። መርዶ ሲመጣላቸውም በወቅቱ የሚያደርጉትን ሁሉ አጥተው ነበር። እናም ጦርነት እነርሱን እናታቸውን ወስዶ እናትም አባትም የሌለው ልጅ አድርጓቸዋል። በዚህም ‹‹በእኔ የደረሰ በሌላውም አይድረስ›› ለማለት 20 ዓመታትን ከቆዩበት አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ አድርጓቸዋል።
ወጪያቸውንና አንዳንድ ለጊዜው ያስፈልጋሉ የተባሉ ነገሮችን ልጆቻቸው ሸፍነውላቸውም የዶክተር ዐቢይ ጥሪን ተቀብለው ነበር ኢትዮጵያንና ወገናቸውን ለማየት የመጡት። በዚህም አንድም ቀን ለቤተሰባቸው ጊዜ ሳይሰጡ በቀጥታ በጦርነቱ የተጎዱትን ለመጠየቅ ተጓዙ።አመጣጣቸው ለሳምንት በሚል ቢሆንም ሁኔታ ከባድና አሳሳቢ ስለነበር አልሄዱም።እንደውም የመሄጃ ቀናቸውን እያራዘሙ ስድስት ወር ያህል ቆይተዋል። በነበራቸው ጊዜ በዱር በገደሉ ከመከላከያ፣ ከተፈናቃዩ ሕዝብ ጋር ሲገናኙም ነው ያሳለፉት።የሚበሉትንና የሚጠጡትን ጭምር እየተመገቡ ቆይተዋልም።
በአሜሪካ የነበረው ድርጅታቸው በርካታ ነገሮችን አድርጓል። የመጀመሪያው 40 ሺህ ዶላር የሚያወጣ ድጋፎችን ለሁለቱ ክልሎች አበርክቷል።ደሴ የመጀመሪያ የድጋፍ ቦታው ሲሆን፤ በጦርነቱ በጣም ስለተጎዳች ለደሴ ሆስፒታል 10 ሺህ ዶላር ፍሪጅና የሕክምና መሳሪያዎች እንዲገዛበት ተደርጓል።እንዲሁም ይዘውት የመጡት አራት ሻንጣ ልብስንም አበርክተዋል።ከዚያም ወደ አፋር በመጓዝ ዳሳርጊታ ድረስ በመሄድ አሁንም በ10 ሺህ ዶላር ወጪ የምግብ ግብዓቶችን በመግዛት ድጋፉ እንዲከናወን ተደርጓል።ሌላው በደብረብረሃን ሆስፒታል ይታከሙ ለነበሩ የመከላከያ አባላት የተደረገ ድጋፍ ሲሆን፤ 10 ሺህ ዶላር ወጥቶበታል። በተመሳሳይ ባህርዳር ላይም እንዲሁ 10 ሺህ ዶላር ወጥቶ ለቁስለኞች ድጋፍ እንዲሰጥ ሆኗል።
በድርጅታቸው ወጪ ብቻ ድጋፉን ለማድረግ ያልወደዱት እንግዳችን፤ የራሳቸውን ዘዴ በመዘየድም አሜሪካ ከሚኖረው ኢትዮጵያዊ በርካታ ገንዘብ ይዘው በመምጣት ድጋፍን አድርገዋል።አንዱ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ በመስራትና ከጓደኞቿ በመሰብሰብ ልጃቸው አንድ ሺህ ዶላር ሰብስባ የሰጠቻቸው ሲሆን፤ ‹‹አይዞን ኢትዮጵያ›› የሚል በጊዜው ተከፍቶ ነበርና ለዚያ ገቢ እንዲሆን ተደርጓል።እርሳቸውም ያንኑ ስልት በመጠቀም በአሜሪካ ላሉ ኢትዮጵያውያን በመሸጥ በጦርነቱ በጣም ለተጎዱ ወገኖች ደጉመውታል። አንዱ በእርሳቸው ጭምር ድጋፍ ያገኘው አፋር ላይ በዳሳርጊታ ወረዳ አርዳኢራ ቀበሌ ገበሬ ማሕበር በመገናኘት ብዙ ችግር ያለባቸውን ለይተው በአካል በመገኘት ያደረጉት ድጋፍ ነው።ቦታው ላይ ያዩት ችግር ያላቸውንም ገንዘብ ጭምር አራግፈው እንዲሄዱ ያደረጋቸው እንደነበር ያወሳሉ።
በዳሳርጊታ ወንዶቹ ጦርነት በመሄዳቸው ብዙኃኑ ሴቶች ነበሩ።እናም ማንም ሰው አላያቸውም።ስለዚህም ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተመካክረው ዳግመኛ በመሄድ ለ200 አባዎራዎች የምግብ አቅርቦቱን ሕጻናቱን ጭምር በአማከለ መልኩ አቅርበዋል።በ241 ሺህ ብር ወጪ እንደተደረገበትም አጫውተውናል።ከሁሉም በላይ የሚገርመው ደግሞ ብር ሲተርፋቸው ያደረጉት ነገር ነው።ይዘውት ከመመለስ ይልቅ ባይወስዱትም በአደራ መልክ ይቀመጥልኝ ብለው የራሳቸውን ገቢ እንዲያገኙ ለማስቻል ለአንድ ሰው 14ሺህ ሰባት መቶ 28 ብር ከብት የሚገዙበት በመስጠትም በቀጣይ ኑሯቸውን እንዲደጉሙ አድርገዋል።ለ25 አባወራ ይህንን አድርገዋል።
አፋርን ከጨረሱ በኋላ ወደ ቤተሰቦቻቸው አልሄዱም። አሁንም ጓደኞቻቸውን ወደማስቸገሩ ነው የገቡት። ምክንያቱም ከወለጋ የተፈናቀሉ ብዙ ሰዎች እንዳሉ ሰምተዋል። ስለዚህም አንድ ሰው ብቻ የላከላቸውን 500 ዶላርና ከልጆቻቸውና ሌሎች ቤተሰቦቻቸው ያገኙትን ተጨማሪ ዶላር በመያዝ ወደእነርሱ አመሩ። 155 ቤተሰቦችም ነበሩ።እናም መጀመሪያ ዱቄትና መሰል የምግብ እህሎችን ገዝተው ቦታው ድረስ በመሄድ ደገፏቸው።ነገር ግን ችግራቸው ከአሰቡት በላይ እንደሆነ ያዩት ነገር አረጋገጠላቸው።ሰዎቹ ከቦታ ቦታ ስለሚንቀሳቀሱ ፍራሽና ብርድልብሳቸው ጭምር ተወስዶባቸዋል።ሲሚንቶ ላይም ይተኙ ነበር።
ይህንን እያዩ ዝም ማለት ያልቻሉት ባለታሪካችን፤ ሌላ ድጋፍ እንዲያገኙ ለማስቻል ድርጅታቸው ገንዘብ እንደሌለው ቢያውቁም ለድርጅታቸው ሊቀመንበር ግን ከማማከር አልተቆጠቡም።በዚህም እርሱ የግሉ ማህበር ነበረውና ከእነርሱ ጋር ተወያይቶ ስድስት ሺህ ዶላር ላከላቸው።ይህንንም አንድም ሳያስቀሩ ፍራሽና ብርድልብስ ገዝተው በማስረከብ ደስታቸውን አብረዋቸው አሳልፈው እንዲመለሱ ሆነዋል።
እንግዳችን ለአገራቸው መሥራትን ጨርሰው ሊመለሱ ሲሉ እኛ በረከቱ ሳይደርሰን የሚሉ ጓደኞቻቸው ሲደውሉላቸውም ጭምር መሄዳቸውን የሰረዙ ናቸው።ችግር አለ የሚባልበትን ቦታ እያንኳኩ ታች ድረስ በመሄድም በተላከላቸው ገንዘብ አስፈላጊውን ነገር አድርገዋል። በደሴ ሆስፒታል ለሚገኙ ቁስለኞች ያደረጉት እገዛም የዚሁ አካል ነው፡፡
‹‹የግፍ ሰቆቃ›› የሚል አማራ ሚዲያ የዘገበውን ሲያዩ ደግሞ የባሰ ልባቸው ደማ። በዚህም መሄዳቸውን ትተው ወራትን እንዲያራዝሙም አድርጓቸዋል።ቤተሰቦቻቸውን አስቸግረው አንድ ሺህ ዶላር እንዳገኙም ወዲያውኑ ጊዜ ሳይፈጁ በዋሻ ውስጥ አሉ የተባሉትን ሰዎች ለማየት አቀኑ።ሊንኩን የላከላቸው የደሴ ከንቲባ ሳሙኤል የሚባለው ሰው ደግሞ ቦታው ላይ እንዲደርሱ ብዙ አግዟቸዋል። መጀመሪያ ግን ድጋፍ ያደረጉት በኮን ወረዳ ያለ ሆስፒታልን ሲሆን፤ አገልግሎት መስጠት በማቆሙ 40 ሺህ ብር በመመደብ ሥራ እንዲጀምር ማድረግ ነው።ከዚያ ወደ ጋሸና አቀኑ።
በጋሸና አርቢት ቀበሌ ገበሬ ማሕበር በመገኘትም በዋሻ የሚኖሩ ሰዎችን ለመታደግ 10 ሺህ የኢትዮጵያ ብር በመመደብ ቡናና ዱቄት ገዝተው ጠየቋቸውም። የተጋገረላቸውን ቂጣ ሳይቀር አብረው ቆርሰው ስለሆነባቸው ነገር አብረው አለቀሱ። ተመልሰው ከድርጅታቸው እስከነቤተሰባቸው አስቸግረው 30 ቤቶችን በመስራት ከእነ ቤት እቃው አስረከቧቸው። ይህም የሆነው ባለሥልጣን መርጦ በሰጣቸው ሳይሆን በዋሻ ውስጥ የሚኖሩት እርስ በእርስ ተመራርጠው እንዲያደርጉት በመፍቀድ ነው። በእርግጥ የቤት እቃውንና አልባሳቱን የሰጧቸው እህታቸው ሳትቀር አዲስ አበባ ላይ ከጓደኞቿ ሰብስባ እንደነበር ያስታውሳሉ።ግንቦት ልደታንም ከእነርሱ ጋር እንዳሳለፉ ይናገራሉ። ተግባራቸው አሁንም ቢሆን እንደማያበቃ ያስረዳሉ።እንደውም ‹‹አሜሪካ ብኖርም ከዚህ በኋላ የእኔ ሕይወት የሚሆነው ወገኖቼን ማገዝ ነው›› ብለውናል።
መልዕክት
ኢትዮጵያዊነት ትልቅ ትርጉም ያለው ነው። በየሄድንበት የማይረሳ ትዝታ የሚሰጥ።በተለይም መረዳዳት ላይ ማንም ጋር የሌለ ሀብት እንዳለን የምናይበት ነው። አሁን ግን አንተ ውጣልኝ ፤አትድረስብኝ የሚሉ አስተሳሰቦች እንደመጡ በብዙ መልኩ አይቻለሁ። ይህ ደግሞ ጠላቶቻችን የእኛን ለማስለቀቅና የራሳቸውን ለመዝራት የሚጠቀሙበት ነው። ሴራቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ይገለገሉበታልም። እናም ነቅተን ካልተዋጋናቸውና ካልጠበቅን አደጋው የከፋ ነው። የእኛ ሀብት አንድነታችን ፤ መረዳዳታችን ብቻ እንደሆነ ከምንም በላይ አሁን ላይ መገንዘብ አለብን የመጀመሪያው ምክራቸው ነው።
አሁን እየሆነ ያለውን ነገር ለማጥፋት ወጣቱ ቆም ብሎ ማሰብ፤ አዛውንቱ መምከርን፤ ፖለቲከኛው ደግሞ ማስተዋልን መላበስ አለበት።በዚህ ደግሞ መጀመሪያ ራሳችንን ከዚያም አገራችንን እናተርፋለን ይላሉ።
ሌላው ያነሱት ነገር ማንኛውም አገር በመስራት እንጂ በማውራት አልተለወጠም የሚለውን ነው።ሥራችን ሰውን ማዕከል ያደረገ መሆን አለበት ባይ ናቸው።መገፋፋትን ከስሩ መንግለን እናውጣው።የአስተሳሰብ ለውጥ ላይ አብሮ መሥራትም ያስፈልጋል።ብቸኛውንና ቀና የሚያደርገንን ባህላችንን ለጠላት አሳልፈን ልንሰጠው እንደማይገባም ይመክራሉ።
ዛሬ እንደ አገር የሚያስፈልገን አንድነት ነው።ወጣቱን በአገር ወዳድነት ዙሪያ ማስተማርና ለዚያ ዝግጁ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል። ሶርያዎች አገር አጥተው ኢትዮጵያ ውስጥ ሲጠለሉ አጋዢያቸው ብዙ ነው።ምክንያቱም ኢትዮጵያዊነት መስጠት ነው።ኢትዮጵያውያን ከአገር ከተሰደዱ ግን በምንም መልኩ የሚኖሩበት ምድር አይኖራቸውም። እናም ያንን አስበን አሁን ላይ ስለ አንድነታችንና መተሳሰባችን መሥራት ይጠበቅብናል ሲሉ መልእክታቸውን ያስተላልፋሉ።
በመጨረሻም ለሚዲያው አደራ የተሸከመውን መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ።ይህም ኢትዮጵያዊነት ላይ መስራት ይኖርበታል የሚለው ነው። በተለይም ሰዓታቸውን በአውሬ ፊልምና በማይረባ ትርኪሚርኪ ከማሳለፍ እኛነታችንን የሚገነባ ነገር ላይ ቢረባረቡ ልጆቻችን ብቻ ሳይሆኑ የተሳሳተ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ጭምር ይማራሉ። የተሻለ ትውልድ ለመፍጠርም ሁነኛ መፍትሄን ይሰጣሉ።ስለሆነም ያስቡበት ይላሉ። እኛም ምክራቸውና የሕይወት ተሞክሯቸው ብዙዎቻችንን የሚያበረታ ነውና እንጠቀምበት በማለት ሃሳባችንን ቋጨን።ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 24 ቀን 2014 ዓ.ም