ሰላም ልጆች እንደምን ሰነበታችሁ! በዚህ ትምህርት ቤት በተዘጋበት ወቅት ብዙ ልጆች በየቤታችሁ ቁጭ ብላችሁ እረፍታችሁን እያጣጣማችሁ ነው አይደል?
ልጆች! ዛሬ እረፍታቸውን እንዴት እያሳለፉ ስላሉ ሁለት ወንድምና እህት ታዳጊ ልጆች እንነግራችኋለን። ባህራን አምደሚካኤል እና አብሳላት አምደሚካኤል ይባላሉ። ባህራን የአብሳላት ታላቅ ወንድም ሲሆን ስምንት ዓመቱ ነው።አብሳላት ደግሞ የባህራን ታናሽ እህት ስትሆን አምስት ዓመቷ ነው። ሁለቱም በወላጆቻቸውም፤ በትምህርት ቤታቸው የተሸለሙ ጎበዝ ተማሪዎች ናቸው።
አብሳላት ትምህርት ቤት ከመዘጋቱ በፊት ከኬጂ አንድ ወደ ኪጂ ሁለት አልፋለች። ወንድሟ ባህራን ደግሞ ዘንድሮ ወደ ሦስተኛ ክፍል ተዛውሯል።ልጆች ባህራንና አብሳላት እንደነገሩን በአሁኑ ሰዓት ትምህርት ቤት ስለተዘጋ በአብዛኛው እቤት ውስጥ ነው የእረፍት ጊዜያቸውን እያሳለፉ የሚገኙት።
በቤታቸው ውስጥ ሆነው የተለያዩ ጨዋታዎችን ይጫወታሉ። የሚያዝናኑና የሚያስቁ እንዲሁም አስተማሪ የሆኑ የህጻናት ፊልሞች ያያሉ። ሲደክማቸው በተለይም ደግሞ ዝናብ ሲሆን መኝታቤታቸው ገብተው ይተኛሉ። ልጆች ዝናብ ሲሆን መተኛት ደስ ይላል አይደል? አያታቸው ወደነሱ ቤት ሲመጡ ወይም ወላጆቻቸውን አያታቸው ቤት እንዲወስዷቸው በመጠየቅ የተለያዩ ተረቶችን እንዲያወሩላቸው ይጠይቃሉ። ልጆች የአብሳላት ወንድም ባህራን እንደነገረን አምና ትምህርት ቤት በተዘጋበት ወቅት ወደ ትምህርት ቤት እየሄደ ትምህርት ቤት ሲከፈት ጎበዝ የሚያደርገው የማጠናከሪያ ትምህርት ይማር ነበር። ዘንድሮ ግን በቤት ውስጥ የተለያዩ አጋዥ መጽሐፍትን እያነበበ እንደሚያሳልፍ ነው የነገረን።
ትንሽም ብትሆን አብሳላትም ለበጋው የሚያግዛትን ትምህርት እያስተማሯት እንደሚገኙ ነግራናለች። በዝግ ወቅት በቤት ውስጥ መማራችን ትምህርት ቤት በሚከፈትበት ጊዜ ጎበዝ እንድሆን ያስችለናል ብለዋል።
ነገር ግን ልጆች የክረምት የእረፍት ጊዜ በጣም ረጅም ነው አይደል? ሁልጊዜ እቤት መዋልና መጫወት ይሰለቻል። ደስም አይልም። ስለዚህ ወላጆቻቸው ባህራንን እና አብሳላትን ቅዳሜና እሁድ አንዳንዴም ከሥራ ሲመለሱ የተለያዩ ቦታዎች በመውሰድ ያስጎበኟቸዋል። እኛም እነ ባህራንን ያገኘናቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ቅርስ መዘክርን ሲያስጎበኟቸው ነው።
‹‹የእንስሳት ሙዚየም መጎብኘት በጣም እወዳለሁ። እህቴም ትወዳለች›› ያለን ባህራን በቅርስ መዘክሩ ውስጥ ምን ምን ነገሮችን እንደጎበኙም ነግሮናል። ከጎበኟቸው ውስጥ የተለያዩ የወፍ ፤የእንስሳት ባለቁንጮ የምትባለውን ትልቅ ዓይጥ ጨምሮ የተለያዩ የዓይጥ፤የዝንጀሮና የጦጣ ፤የእባብ የዘንዶ፤እንቁራሪት፤ እንዲሁም ኢንሴክት (ነፍሳት) ተብለው በትምህርት ቤት የተማሯቸው ጢንዚዛ፤ቢራቢሮ ዝርያዎች ይገኙበታል። አንበሳ፤ ዝሆን፤ ነብር፤ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኘው ዋልያ፤አነር ፤አቦ ሸማኔ፤ጅብ፤ጉማሬ፤ተኩላ፤ ሚዳቋ፤ የሜዳ ፍየል ፤የሶልት ኢንሹ የተለያዩ ቀበሮዎች የጀርባ አጥንት ያላቸውና የሌላቸው እንዲሁም አጥቢ የሆኑና ያልሆኑ በርካታ እንስሳትን ማየት ችለዋል። ወፎቹ ትላልቅ ከሚባሉት እንደሚመደቡና ዳክዬን ጨምሮ በውሃ ውስጥና በውሃ አካባቢ የሚኖሩ እንደሆኑ፤ ነብርና አነር ከድመት ዝርያ፤እባብና ዘንዶ ከተሳቢና አጥቢ ካልሆኑ እንስሳት እንደሚመደቡ አስጎብኛቸው ነግራቸዋለች። ልጆች! ባህራንና አብሳላት ይሄን ሁሉ ማወቃቸው ደስ ይላል አይደል።
ይሄን ብቻ ሳይሆን ስለ ተኩላ፤ ቀበሮና ጦጣ ብልጠት ስለዝንጀሮም ኃይለኝነት አያታቸው በተረት የነገሯቸውን አስጎብኛቸውም እንደነገረቻቸው ከእህቱ ጋር እየተሳሳቁ ባህራን ገልጾልናል።ተኩላ ዝርያው ከውሻ ሲመደብ የሚያድነው በሕብረት ነው። አንዱ ተኩላ አድኖ ከያዘ ብዙ ሆነውና ተረባርበው ይገሉና አንድ ላይ ይበላሉ።ሶስቱንም ዓይነት የዝንጀሮ ዝርያዎችም አይተዋል።ቆላማ ቦታዎች የሚገኘው ጭላዳ ዝንጀሮ እንደዋልያ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኝ እንደሆነም አስጎብኛቸው ነግራቸዋለች። ሁሉም ዝንጀሮች በጣም ትላልቅና ፊታቸውም ረጃጅም የሚያስፈራ አፍንጫቸውም ወደ ውጪ የወጣ ነው። ነጭ ዝንጀሮ ኃይለኛ ተደባዳቢና ተጋራፊ ነው። የሚገርፈውና የሚደበድበው ዝንጀሮዎችን ብቻ ሳይሆን ሰዎችንም መሆኑ አስፈርቷቸዋል። ግን ደግሞ የሚኖረው እሩቅ ስለሆነ እነሱን ስለማያገኛቸው ደስ እንዳላቸው ነግሮናል።ጦጣዎች ግን ትንንሾች ናቸው።ፊታቸውም ትንንሽና ክብ ስለሆነ ደስ ይላሉ።አስጎብኛቸው ስለ እንስሳቱና አስገራሚ ሁኔታቸው ነግራቸዋለች።ቀይዋ የባሌ ጦጣ ብርቅዬና ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው የምትገኘው።የሶልት ኢንሹ ሣርና ቅጠላ ቅጠል ከሚመገቡ እንስሳዎች በመጠን የመጨረሻዋ ትንሽና መቼም የማታድግ ናት።ግን ልጅ ትወልዳለች። የምትገኘው አዋሽ አርባ ምንጭ አካባቢ ሲሆን በሕይወት የምትኖርበት ረጅሙ ዕድሜዋ 10 ዓመት ብቻ ነው። ልጆች ባህራን አስጎብኝው ነግራው እንደነገረን የሶልት ኢንሹን በአብዛኛው አንበሳ ባይሆንም የዳልጋ አንበሳ የሚባለው እንስሳ ይበላታል። እንስሳው ሥጋ በል ሲሆን የሶልት ኢንሹን ብቻ ሳይሆን ትናንሽ እንስሳትን ሁሉ ወፎችንም በተወሰነ ርቀት ዘሎ ይይዝና ይበላል። በምድራችን ላይ ካሉት እንስሳቶች ትልቁ ዝሆን ነው። ትልቁ እስከ 6ሺ ኪሎ ግራም ድረስ ይመዝናል። እንዳዩዋቸው ሁለቱ ጥርሶቹ እጅግ ረጃጅም ናቸው። ሰዎች የሚያድኑት ለነዚህ ጥርሶቹ ሲሆን ለጌጣጌጥ መሥሪያ ስለሚያገለግሉ ዋጋቸው በጣም ውድ ነውም ብላቸዋለች አስጎብኛቸው።
ልጆች ቁጥሮችን በቀላሉ በመያዝና ሂሳብ ትምህርትን በመውደዷ ቤተሰቦቿ እንደሸለሟት የምትናገረው አብሳላት አቦ ሸማኔ ምድር ላይ ካሉት አጥቢ እንስሳት በሰዓት እስከ 120 ኪሎ ሜትር የሚሮጥ ፈጣን መሆኑን አስጎብኛችን ነግራናለች ብላናለች።ከጎበኘቻቸው ውስጥ ቢራቢሮዎቹና ወፎቹ ደስ እንዳሏትና እባብ፤ዘንዶና ጅብን ግን በሙዚየም ውስጥ ስታያቸው ፈርታ ሮጣ ልትወጣ እንደነበርና አስጎብኛችን እንደማይባሉ ስለነገረችኝ ሳልፈራ ሁሉንም አየኋቸው ብላናለች። ልጆች ባህራንና አብሳላት በእረፍት ጊዚያቸው ይሄን ሙዚየም ጨምሮ አንበሳ ጊቢን፤አንድነትና እንጦጦ ፓርክን ጎብኝተዋል። እናንተስ?
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 17 ቀን 2014 ዓ.ም